- በደሉ፥ በበርካታ የምስል፣ የድምፅና የሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጧል
- በደርዘን ለሚቆጠሩ ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲላገድ ቆይቷል
- ከሐዋሳ የመጡ ልኡካን፣ በደሉንና ድፍረቱን በማስረጃ አብራርተዋል
- የይቅርታ ዕድሎች በቂ በመኾናቸው፣ ጠርቶ መጠየቁ አላስፈለገም
- ውግዘቱ የተላለፈው ልዩነት በሌለበት የምልአተ ጉባኤ ድምፅ ነው፤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በተደጋጋሚ የሰጠችውን የንስሐና የይቅርታ ዕድል ተጠቅሞ ከመታረም ይልቅ፣ ለማንነቷና ማዕከላዊ አንድነቷ ስጋት የኾነውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ማስተጋባት የመረጠውና በቅርቡም ክብሯን እያንኳሰሰ ለመገዳደር የዛተው በጋሻው ደሳለኝ፤ የማይታረም የጥፋት መሣሪያ እንደኾነ ያረጋገጠው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አውግዞ ለየው፡፡
ውግዘቱ የተላለፈው፣ የበጋሻው በደሎች በስፋትና በተደጋጋሚ በተፈጸሙበት የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ቀደም ሲል ለቋሚ ሲኖዶስ በደብዳቤ ባስታወቁት መሠረት፣ በምልአተ ጉባኤ ተ.ቁ(10) የተያዘው አጀንዳ፣ በዛሬው፣ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ የቀትር በኋላ ውሎ በታየበት ወቅት ነው፡፡
ከ1997 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ፣ ላለፉት ከደርዘን በላይ ዓመታት በጋሻው በንግግርም በድርጊትም በቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጸማቸውን በደሎች የሚያስረዱ በርካታ የድምፅ፣ የምስልና የሰነድ ማስረጃዎች እየቀረቡ ተነጻጻሪ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ከሐዋሳ የመጡ ዐሥር ያህል ልኡካን በአስረጅነት ያቀረቡና ያብራሩ ሲኾን፤ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ሥርዓተ እምነትን፣ ክርስቲያናዊ ትውፊትንና ታሪክ በንግግርም በድርጊትም በመናቅና በማቃለል የፈጸማቸውን በደሎች የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ በዘመናት ብሔራዊ አስተዋፅኦዋ የገነባችውን መልካም ስም በዐደባባይ እያንኳሰሰ “ትከሻ ለመለካካት” የዛተባቸውና የተገዳደረባቸውም ናቸው፡፡
ከተጠቀሱት ውስጥ፡- “ጋለሞታዪቱ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ክርስቶስን ሰብካ የማታውቅ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ከፖሊቲካ ጋራ የተጋባች ቤተ ክርስቲያን”፣ “ውሸት ሰብስባ ውሸት ስታስተምር የኖረች ቤተ ክርስቲያን”፣ “ምእመናኗን በትና ገንዘብ የምትሰበስብ ቤተ ክርስቲያን”፣… ወዘተ የሚሉት እንደሚገኙበትና እነኚህን የመሳሰሉ ሌሎችም በርካታ ነገሮች ከነማብራሪያቸው መቅረባቸው ተገልጿል፡፡