 |
እንኳን ለፆመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ |
“እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አርጋለች ወደ ገነት እመቤቴ ማርያም ሆይ፤ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል ።መልክአ ማርያም
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመሞቷ በፊት በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበር። መንፈስ ቅዱስም ለእመቤታችን ከዚህ ዓለም እንደምትለይ ነገራት። ጌታችንም በደብረ ዘይት ላሉ ደናግላን ነግሯቸዋልና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጥነት መጡ። እርሷን መንፈስ ቅዱስ የነገራትን ነገረቻቸው። እነሱም እንደመጡ ባየች ጊዜ እንዲህ ብላ ጸለየች። ልጄ ውዳጄ፤ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናየን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚህች ሰዓት አምጣው፤ እንዲሁም በሕይወት ያሉትንና በሕይወት የተለዩንን ቅዱሳን በሙሉ ወደ እኔም አምጣቸው። አንተ የሕያዋን አምላክ ነህና፤ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን አለች። በዚያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ቅዱስ ዮሐንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደረሰችው። ቅዱስ ዮሐንስም እንደደረሰ ሰገደላትናበፊቷ ቆሞ እንዲህ አላት፤ ሰላምታ ይገባሻል ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልደሽልናልና፤ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። አንቺ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ትሄጃለሽና። እመቤታችንም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እንዲህ ብላ አምላኳንም አመሰገነችው። ጌታዬ አምላኬ ፈጣሪዬ ሆይ፤ ላንተ ክብር ምስጋና ይገባል። የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና። አሁንም ነብሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊይሳርጓት ከሚመጡ መላእክቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ። በዚህን ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ድምጽ መጣ፤ እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ። ቅዱሳን ሐዋርያትም ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ይደርሳሉ።