
ጽጌ ጾም በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 5 ያሉ አርባ ቀናት ዘመነ ጽጌ (ወርሃ ጽጌ) እንደሚባሉ ይታወቃል። የቤተክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገስት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል ። “ጾምስ በታወቀው ዕለት ፣በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው። ይህም ኃጢአቱን ለማስተስረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ህግን ለሰራለት እየታዘዘ፤ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ፤ ሥጋም ለነባቢት ነፍሥ ትታዘዝ ዘንድ ነው” /ፍት.ነገ.ፍት.መን.አንቀጽ 15፥564/።
ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው። ለፈቃደ ሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው። ሰው ፈቃደ ሥጋን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት ስንቅ ነው። “ጾም ቁስለ ነፍስን የምፈውስ ፣ ኃይለ ፍተዎትንም የምታደክም ፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ፣ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣የጽሙዳን ክብራቸው ፣የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው ፣የጸሎት ምክንያት/እናት/ የእንባ መገኛ ምንጭ፣አርምሞን የምታስተምር፣ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ ፣ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት።/ማር ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6/