- “ከምንም ጊዜ በላይ ታጥቀን ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠል እና ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሕይወት ዋስትና መረጋገጥ በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ ነው፡፡”
***
በየዓመቱ ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የሚካሔደው፣ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ 39ኛ ዓመታዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባውን ዛሬ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋድ ማካሔድ ጀምሯል፡፡
ዐዲስ በተገነባው እና “ጽርሐ ተዋሕዶ” ተብሎ በተሰየመው አዳራሽ በጸሎተ ወንጌል በተጀመረው በዚኹ ዓመታዊ አጠቃላይ ጉባኤ መክፈቻ ላይ፣ “ወይኩን ቅኑተ ሐቈክሙ ወኅትወ መኃትዊክሙ፤ ወገባችኹ የታጠቀ፣ መብራታችኹም የበራ ይኹን፤”(ሉቃ. 12፥35)በሚል ርእስ መልእክት ያስተላለፉት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፥ ቤተ ክርስቲያንን ከገጸ ምድር ለማጥፋት በየአቅጣጫው የተነሡ ኃይሎች በተበራከቱበት እና የሚፈጽሙባትም ግፍ እየተባባሰ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ፣ ጥቃቱን ለመመከት እና መከራውን ለመግታት፣ መላውን አገልጋዮች እና ምእመናን አስተባብሮ እና አደራጅቶ ራስን ወደ መጠበቅ አማራጭ መሸጋገር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፤ ጉባኤውም ተገቢውን መፍትሔ እንዲያስቀምጥ ኣሳስበዋል፡፡