Thursday, April 12, 2012

ዋልድባ


መናኒያን በዋልድባ ገዳም

የዋልድባ ገዳም የሚገኘው በሰሜን ተራራዎች እግር ስር ነው፣ የዋልድባ ገዳም የተመሠረተው በ፬ኛው ምዕተ ዓመን እንደነበር ሲያያዝ የመጣው ትውፊታዊ ታሪክ ያስረዳል። የዋልድባን ገዳም ያደራጁና የተባሕትዎን ኑሮ ያጠናከሩ ቅዱስ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ናቸው።እርሳቸውም በ14ኛው ማለቂያና በ15ኛው መጀመሪያ በአፄ ዳዊት ከ1365 - 1395 ዓ.ም. በዋልድባ ኑረዋል። አንድ የመነኩሳት ቡድን ከደብረሊባኖስ ተንቀሳቅሶ ዋልድባ ደርሷል፥ የቡድኑም አባላት አባ ሙሴ፣ አባ አናንያ፣ አባ እስጢፋኖስ፣ አባ ገብረ መስቀል፣ አባ ገብረ ክርስቶስ ነበሩ። እነዚህ አባቶች የገዳሙን ኑሮ መልክ በመስጠት ቋሚና ዘላቂ ሥራ ሠርተዋል።

እነርሱም እስከሄዱበት ጊዜ ድረስ የዋልድባ መነኩሳት እህል እየተመገቡ ይኖሩ ነበር፥ አባ ሙሴ ሌሎቹን መነኩሳት ቢያናግሩ ብዙዎቹ በጉዳዩ ስለተስማሙበት የመነኩሳቱ ምግብ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቋርፍ እና ሙዝ በጨው ተቀቅሎ እንዲሆን ወሰኑ፣ ውሳኔያቸውንም ማኅበራቱ ተቀበላቸው፤ ከዓለም ሰዎች ጋርም ያለውን ግንኙነት በተቻለ መጠን ያነሰ እንዲሆን  ተወስኗል። መሠረታዊ ተፈላጊ እቃዎችን እንደልብስ እና ጨው የመሳሰሉትን ለማግኘት አንድ የገዳሙ መነኩስ ከገዳሙ ወጥቶ ወደ ዓለም ሰዎች ሄዶ ለመሰንበት የሚፈቀድለት 15 ቀን ብቻ ነበር፥ ነገር ግን ይህን ቢያሳልፍ የ30 ቀን ቅጣት ይሰጠዋል። በዚህም ወቅት የሚሰጠው ድርጎ ጨው የሌለው ቋርፍ ሲሆን በጣም ከቆየ ደግሞ ከገዳሙ ይባረር ነበር። ሆኖም በዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ እህል እንዲበላ ተፈቅዷል ይኽውም በልደት፣ በትንሳኤ፣ እና በካሕናተ ሰማይ በዓል ነው፤ የካሕናተ ሰማይ በዓል ሕዳር 24 ቀን ነው፥ መነኩሳት በሚያረጁበት ወቅት አንድ አንድ ረድ ይሰጣቸዋል የረዱ ተግባር ያረጀውን መጦር ሲኖን፣ ሽማግሌውም ለረዱ የሚያስፈልገውን መሳሪያ ማቅረብ ግዴታ አለበት። አንድ ረድ ከመነኩሳቱ ጋር ሳይስማማ ቢቀር ጥል እንዳይፈጠር ሌሎች አበው መቀበል የለባቸውም፥ ረድ ተበደልኩ ቢል ለማኅበሩ ሊከስ ይችላል።
ምንም ዋልድባ የመናኒያን ቦታ ቢሆንም አንዳንድ አበሜኔቶች ወደነገሥታቱ እየሄዱ ርስትና ጉልት ማውጣትን አልተዉም የመጀመሪያው አበሜኔት አባ በኪሞስ የሚባሉ ነበሩ እርሳቸውም ወደ አፄ ዳዊት ሄደው 80 ጉልት አውጥተው ተመልስዋል፥ ይኽንኑም ማኅበሩን ሰብስበው ቢነግሯቸው ከፍተኛ ተቃውሞ አድርሰውባቸዋል ምክንያቱም እነርሱ ወደዚያ የገቡት ለሃብትና ለንብረት ሳይሆን የጽድቅ ስለሆነ አሻፈረን ብለው ጉልቱን ሳይቀበሉ ቀርተዋል ስለዚህ ያንን ጉልት የአባ ሳሙኤል አጽም ላለረፈበት ደብረ አባይ ገዳም ሰጥተው በወንጌል ዘወርቅ አጽፈውታል። በአፄ ዘርአያቆብ ከ1426 - 1460 ዓ.ም. የዋልድባ ገዳም ከአራቱ ጅረት መለስ እንዲሆን ተከልሎ ገዢ እንዳይገባ፣ አራሽም እንዳይሰማራ ተከልክሏል፤ የአፄ ዘርአያቆብ ልጅ አፄ በዕደማርያም ከ1460 - 1470 ዓ.ም. የበአቱን ደንብ በማጠናከር ገዢዎች የገዳሙን ቦታ እንዳይደፍሩ ደንብ ሰርተዋል።
ግራኝ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ በዋልድባ ገዳም ከሁለት በኩል አደጋ አድርሶበታል፥ በአንድ በኩል የግራኝ ወታደሮች ሲያጠቁ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጠረፍ ነዋሪዎች አደገ ጥለዋል ያን ጊዜ የገዳሙ አበሜኔት አባ ዘወልደ ማርያም ይባሉ ነበር እርሳቸው ከአደጋው የተረፉትን ጥቂት መነኩሳት ይዘው ተሰደዱ፤ ገዳሙ ግን ተመዘበረ፣ ተቃጠለ። አፄ ንብለድንግል በስደት ላይ እንዳሉ ወደ ገዳሙ መልክተኛ ልከው  ስለመንግሥታቸው የወደፊት እድል ጠይቀው ነበር እርሳቸው መንግሥታቸው እንደገና እንደሚቆምና ልጃቸው እንደሚነግስ እርሳቸው ግን የሞታቸውን ጊዜ ስለተቃረበ ወደ ደብረ ዳሞ ሄደው እዚያ እንደሚያርፉ ተነግሯቸው ነበር ይባላል፤ እንደተባለውም  አፄ ንብለድንግል በ1543 ዓ.ም. በደብረ ዳሞ ላይ አርፈው እዚያው ተቀበሩ ልጃቸው አፄ ገላውዴዎስ ነገሱ፥ የአባ ተስፋሐዋሪያት ትንቢት ንግስት ሰብለወንጌል የአጼ ንብለድንግል ባለቤት ያውቁ ስለነበር ነገሩን ለልጃቸው አጫውተው አባ ተስፋሐዋሪያትን እንዲጠይቁ መልእክተኞችን ወደ ዋልድባ ላኩ ነገር ግን አባ ተስፋሐዋሪያት ሞተው ስለነበር መልእክተኞቹ ከአባ ተስፋሐዋሪያት ደቀመዝሙር ጥቂቶቹን ይዘው ተመለሱ፣ መነኩሳቱም ለገዳሙ መርጃ የሚሆን የ15 አገር ጉልት ተቀብው ወደ ገዳማቸው ተመለሱ፥ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም መናኒያኑ በሙሉ ከነጋሲ የተቀበልነውን ጉልት አንቀበልም አሉ እንደውም ጉልቱን የተቀበሉትን መነኩሳት ወደ ገዳሙም አናስገባም ብለው ነበር በኃላ ግን በገላጋይ ወደገዳሙ ሊገቡ ችለዋል።
አበሜኔቱ አባ ወልደማርያም ከስደት ተመልሰው ለጥቂት ዓመታት ካስተዳደሩ በኃላ አረፉ እሳቸውም ከሞቱ በኃላ አባ ሚናስ ተተኩ፣ ከአባ ሚናስ በኃላ፣ አባ ጰራቅሊጦስ አበሜኔት ሆነው ተሹመው ነበር እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከዚህ በፊት እንዳየነው የመነኩሳቱ ምግብ ቋርፍ ነበር፣ በአባ ጰራቅሊጦስ ዘመን ብዙ ሙዝ ተተክሎ ያፈራው እየተቀቀለ መበላት ተጀመረ ይህም ልማድ እስከአሁን ድረስ እንደቀጠለ ነው ከዚህ በኃላ አባዲር የሚባሉ መነኩስ አቤሜኔት ሆነዋል በዚህ ጊዜ ሳይሆን አልቀረም ገዳሙ ዳግመኛ የጠፋው የዚህ መነሻው በትክክል ተለይቶ አይታወቅም መነኩሳቱ በሙሉ ተግድለዋል ወይንም ተሰደዋል ታቦት አጣኝ አንድ መነኩሴ እንኳል አልቀረም ነበር ይህንንም ተከትሎ ቦታው ምድረ በዳ ሆኖ ለሰባት ዓመታት ቆየ፥ ከዚህ በኃላ አባ ወልደማርያም የሚባሉ መነኩሴ ከደብረ ሊባኖስ ሄደው ታቦቱን እያጠኑ ተቀመጡ እየቆየም ሌሎች መናኒያን መሰባሰብ ጀመሩ ገዳሙም የቀድሞ መልኩን እያገኘ ሄደ አባ ወልደ ማርያምም አቤሜኔት ሆነው ያስተዳድሩ ጀመር። በአሁኑ ወቅት ዋልድባ አያሌ መነኩሳት የሚኖሩበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ገዳም ነው ከዚህ ገዳም ብዙሐን የቤተክርስቲያን መሪዎች ተገኝተዋል ገዳሙ ጥንታዊ እና ታሪካዊ በመሆኑ ብዙ ሰዎች በየቀኑ ይጎበኙታል ይግ ገዳም ሊጠበቅና ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ ነው እንላለን።
የጸሎት ቦታችን፣ ታሪካችን፣ ሃይማኖታችን ይጠበቅልን!

በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ መንግስት የስኳር ፋብሪካ እና የፖርክ ክልል እንከልላለን በማለት በ48 ሄክታር መሬት ላይ ሥራውን ከተጀመረ በርከት ያሉ ወራቶችን ማስቆጠሩ አይዘነጋም፥ እላይ እንደተመለከትነው ይህ ታሪካዊና ታላቅ ገዳም ለሃገር፣ ለወገን፣ እንዲሁም ለዓለም የሚጸልዩ ገዳማዊያን ያሉበት እለት ተእለት ከዓለም ሰዎች ይሄንን ስጡን ሳይሉ ዘወትር ምስጋና በአርያም ለመዳኀኒተ ክርስቶስ እያሉ በአርምሞ የሚኖሩበት ቦታ ሆኖ ሳለ መንግሥት ለምን ይህንን ቦታ ለዚህ ልማት እንደመረጠው በትክክል የእምነቱን ተከታዮች ያላነጋገረበት፣ የአካባቢውን ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብት ያላገናዘቡ ሥራዎች ናቸው እና ሥራዎቹን በአስቸኳይ አቁሞ ለዜጎች ያለውን ከበሬታ ይልቁንም ላለፉት 3000 ዘመናት ተከብራ የኖረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሀይማኖት የቀደመ ክብሯን እንዲመልስና በሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላትን ሕጋዊ መብቶች ሁሉ እንዲያስከብር እንጠይቃልን።
የጻድቁ አባት አቡነ ሳሙኤል ረደኤት በረከት በሁላችንም ይደርብን አሜን

 

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤