Wednesday, April 18, 2012

የዋልድባ ገዳም ህልውና "ሳይቃጠል በቅጠል"

ከዘላለም ወልደኢትዮጵያ

የዋልድባ ገዳማውያን

መቼም ልምድ ነውና ልምድ ብቻ አይደለም ባህላችንም ነውና በሰላምታ ልጀምር፡፡ውድ ኢትዮጵውያን ወገኖቼ እንደምን አላችሁ ኑሮስ አንዴት ነው? አለን መቼስ "ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል" እንደምትሉ ይገባኛል፡፡
ውድ ወገኖቼ እኔ ቃላትን ከቃላት አሳክቼ መፃፍም ሆነ ማንበብ አልችልም፤ ነገር ግን ግድ ሆነብኝና ለትምህርት የምጠቀምባትን ብዕሬን አውጥቼ ይህችን ጦማር ለመጻፍ ተዘጋጀሁ፡፡ ግን ግራ ገባኝ ለማን ነው ምፅፈው? ምን አገባኝ ልፃፈውና እንደኔ የቆረቆረው ካለ የሃሳቤ ተካፋይ ይሁን ባይሆን እንኳን ህሊናዬ ትንሽ እረፍት ያገኝ ዘንድ እንደ አንድ ዓመት ህፃን ዳዴ ማለት ጀመርሁ፡፡ነገሩ እንዲህ ነው ሰሞኑን ታላቁ የዋልድባ ገዳም ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን የግል መገናኛ ብዙሃን እያሳዩንና እያስነበቡን ይገኛሉ፡፡በእርግጥ ይህ ዜና እውነት ነው፤ ስለሆነም እንዳባቶቻችን "የሰይጣን ጀሮ አይስማው" ብለን ምናልፈው አልሆነም፡፡ይልቅስ ሰውም ሰይጣኑም ከሰማው ዋለ አደረ፡፡


ዋልድባ ገዳም በሰሜን ኢትዮጵያ በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር ወይም በአሁኑ በአማራና  በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ የሚገኝ በመጀመሪያ በኢየሱስ ክርስቶስ የስደት ዘመን በእርሱ በራሱ የተባረከና በኋላም በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእርሱ በጌታ መሥራችነት የድንጋይ ቆብ ቀርጾ ባመነኮሳቸው መነኮሳት አፅናነት የተመሰረተ ታላቅና ታሪካዌ ገዳም ነው፡፡እመቤታችን ከልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመዋዕለ ስደት ወቅት በኪደተ እግር ከረገጧቸው መካናት አንዱ ሲሆን፣ የእመቤታችን ስም የሚያመሰግኑ ቅዱሳን እንደ አሸን የሚፈሉበት ቦታ መሆኑንም ለእመቤታችን ትንቢት የተናገረው እዚሁ ገዳም ነው፡፡

ይህ ገዳም በስፋቱ፣በመነኰሳት ብዛቱ፣በፍጹማን ባሕታውያን መሸሸጊያነቱ፣ ለስዉራን ቅዱሳን መናኸርያነቱ፣ በበረሃነቱና በመሳሰሉት ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ካሉት ገዳማት ታላቁ ገዳም ሲሆን፣ በዓለም ደረጃም ሲታይ ከግብጹ አስቄጥስ ገዳም ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ የቅዱሳን በአት  ነው፡፡በአሁኑ ሰአት የተሰወሩ ቅዱሳንን ሳይጨምር ከ3000 በላይ መነኰሳት በቋሚነት ለመላው ዓለምና ለአገራቸው ቀን ከሌሊት ስብሐት ወአኮቴት ወደ አምላካቸው የሚያቀርቡበት ቦታ ነው፡፡

በዚህ ገዳም እልፍ አእላፍ የተሰወሩ መናንያን እንዳሉ በአንድ ወቅት የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ስለተሰወሩ መነኮሳት ተጠይቀው የሰጡትን መለስ ማንሳቱ በቂ ነው፡፡እንዲህ ነበር ያሉት፤ "ግብፅ ውስጥ የማይታወቅ (የተሰወረ) መነኩሴ በአሁኑ ጊዜ የለም፤ ኢትዮጵያ ብትሄዱ ግን ብዙ የተሰወሩ መናንያንን ታገኛላችሁ" ነበር ያሉት፡፡እነዚህ የዋልድባ መነኰሳት የሚመገቡት ጌታ የባረከላቸውን በቀን አንድ ጭብጥ ቋርፍ ሲሆን፣ የዓመት ልብሳቸውንም የሚሸፍኑት ከበጎ አድራጊ ምእመናን ከሚያገኙት ስጦታ ነው፡፡ ታዲያ በዓይን የማይታይ ምግብ ይሁን እንጂ ሰማያዊውን ምስጋና እየተመገቡ ፀባ አጋንንቱን፣ ግርማ አራዊቱን በተለይም አንድ ቀን ለመዋል እንኳ የሚከብደውን ያን ከባድ የበረሃ ዋዕይ ታግሰው ለራሳቸውና ለዓለም ድህነትን (ህ ይዋጣል) ሲለምኑ ኖረዋል ፣እየኖሩም ነው፣ይኖራሉም፡፡

የዋልድባ ገዳም እንዲህ በቀላሉ ዘርዝረን የማንጨርሰው ብዙ ታሪክና ቃልኪዳን ያለው ቦታ ነው፡፡ጌታም ዋልድባን "እህልና ኃጢያት አይሻገርብሽ"ብሎ ለመናንያን መጠጊያና የምስጋና ማቅረቢያ ቦታ እንድትሆን ምግባቸውም መራራው ጣፋጭ እንዲሆን በቦታው ተገኝቶ ባርኮላቸዋል፡፡በዚህም ምክንያት ላለፉት እስራ ምእት (2000 ዓመታት) ለገዳሙ መነኰሳት ምግብነት ከተፈቀደው የሙዝ ተክል ውጭ ምንም አይነት እህል መሬቱን ሳይደፍር ቃልኪዳኑ ተጠብቆ እስካሁን ቆይቷል፡፡

በእርግጥ በአንድ ወቅት ባማረው የዋልድባ ሜዳ ላይ እህል አበቅላለሁ ብሎ የተነሳ አንድ ገበሬ  ቃልኪዳኑን (ውግዘቱን ) በመተላለፉ ከእንስሳቱ ጋር እንደ ናቡከደነፆር ወደ ዱር አውሬነት እንደተቀየረ በገዳሙ ውስጥ ከ 20 ዓመት በላይ የቆዩ አንድ አባት ከሁለት ዓመት በፊት ነግረውኛል፡፡በእርግጥ አሁን አሁን በኃጢያታችንና በውሸታችን ብዛት ለአባቶቻችን የተሰጠ ቃልኪዳን ከእኛ እየሸሸ ቢሆንም ቅሉ ስለ ተወሰኑ ደግ አባቶች ሲል ግን እንደማይተወን አምናለሁ፡፡

እንግዲህ በዚህ ገዳም ላይ ነው መንግሥት የሰሜን ተራሮችን አቋርጦ የሚሄደውን የዛሪማን ወንዝ በመጥለፍ ለስኳር ፋብሪካ ግባት የሚሆን የሸንኮራ አገዳ ሰብል ለማልማትና የተወሰነውን ደግሞ  በፓርክነት ከልሎ ለመጠቀም ሥራውን የጀመረው፡፡ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ በግሬደር የቅዱሳን አፅም እየፈለሰ መሆኑ ነው፡፡ ለ2000 ዓመታት ተከብሮ የቆየ ገዳም ነው እንግዲህ እንዲህ አይነት አደጋ የተጋረጠበት፡፡ አባቴ ዱሮ ሲተርት " ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ "ይል ነበር፡፡

ጎበዝ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶና ጠግቦ ነው ወይ እያደረ ያለው፡፡ኢትዮጵያዊ እኮ ሃብቱ ሳይሆን እምነቱና ባህሉ፣ የአባቶቹ ጸሎት ነው እያኖረው ያለው፡፡አመንም አላመንም የእኛ በሰላም ውሎ ማደር፣ ጤንነት ፣ኑሮ በእኛ ኃይል ብቻ የመጣ ሳይሆን እንደኛ አጥንትና ደም ሳይቆጥሩ ሌት ከቀን በሚፀልዩት አባቶቻችን ጭምር የመጣ ነው፡፡

እስቲ ጎበዝ ቆም ብለን እናስብ፤ ኢትዮጵያ ጣሊያንን ያሸነፈችው ኃይለኛ ጦር ስላላት አይደለም፤ኃይለኛውን አምላክ የሚማጸኑ ቅዱሳን ስላሏት እንጂ፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል ዓድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት እኮ ከሠራዊቱ ጋር በመሆን አብረው ሲያለቅሱ፣ሲፀልዩና ሠራዊቱን ሲናዝዙ ከነበሩት ባህታውያን መካከል አብዛኞቹ የዋልድባ ገዳም መነኰሳት መሆናቸውን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ታዲያ እነዚህን የአገራችን አንጡራ ሃብቶች መንከባከብና መደገፍ ሲገባን ነው መንጥሮ ማጥፋት እንደመፍትሔ እየተወሰደ ያለው፡፡

ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያ በእውነት ይህን ያህል አቅሙ ኖሯት ሁሉን ቦታ አዳርሳ ነው ከዚህ ለመንገድ እንኳ አስቸጋሪ የሆነ ቦታ ላይ ሄዳ የስኳር ፋብሪካ ልገንባ የምትል? ምናልባት "ጠብ ናፈቀኝ እዚያ ማዶ አድረሱኝ" ካልሆነ በቀር፡፡ መች በአገራችን ያሉ ሰፋፊ ወንዞችንና ሜዳዎችን ተጠቅመን መጨረስ ቀርቶ ጀመርናቸውና ነው ቅዱሳን እንዳሸን በፈሉበትና አፅማቸው ባረፈበት ቦታ ላይ ሸንኮራ አገዳ እናልማ የምንል? በእርግጥ ሸንኮራ አገዳው ቢዘራም አይበቅል እንጂ ቢበቅልም ስኳር መስጠቱ ቀርቶ እሬት ይሰጠን ይሆናል፡፡

አንድ መንግሥት የሚመራው ሕዝቡን ከሆነ ያውም በዲሞክራሲ፤ የሕዝቡን ባህል፣ሃይማኖት፣ትውፊት፣አኗኗር የመሳሰሉትን መለያ ባህሪዎች ማክበር አለበት፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋልድባ ገዳም ፈርሶ ስኳር ተመርቶ ሻይ ከሚጠጣ እድሜ ልኩን መራራ ሻይና ቡና ቢጠጣ ይመርጣል፡፡ምክንያቱም ሻይው ጣፍቶት ቢጠጣም ኑሮው መምረሩ አይቀርምና፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በላይ የማንነትና የህልውና ጉዳይ የለምና  ጉዳዩን በቀላል ማየት ያለብን አይመስለኝም፡፡ምናልባት እኔን ውስጤን ያንገበገበኝ ሄጀ ስላየሁት ሊሆን ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህን ነገር ከሸንኮራ አገዳና ከስኳር ባለፈ ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ ቢያየውና በጎ ምላሽ ቢሰጥ መልካም ነው፡፡ምናልባት አባቶች በታሪክ መንግሥት ሊወድቅ ሲያምረው ከታቦት ጋር ይጣላል የሚሉት እውነት እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ሰይጣን እንኳን ሊያስበው የማይገባውን ሃሳብ ከማሰብ ጀምሮ በተግባር እያደረጋችሁ ያላችሁ ሰዎች በዚያው ዋልድባ በሚገኘው በማይለበጣ ወንዝ ሄዳችሁ ተጠምቃችሁ ኃጢያታችሁን የማይለበጣ ወንዝ ይፈውሳችሁ እንደሆነ እንጂ የአሁኑ ትውልድም ይሁን የመጭው ትውልድ ይቅር የማይላችሁን ትልቅ ወንጀል እየሠራችሁ መሆኑን ልታውቁት ይገባል፡፡

ስለዚህ "ሳይቃጠል በቅጠል" ነውና ሁሉም ነገር ወደነበረበት ቢመለስ መልካም ይሆናል፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ዝምታ መልስ ነው፡፡ይህ ህዝብ ምንም ሞኝ ቢመስልና ዝምታን ቢያበዛ ትናንት ለሃገራቸው ዳር ድንበር፣ታሪክ፣ቅርስና ባህል ሲሉ የዛሬቱን ኢትዮጵያ ከእነማንነቷ ለእኛ ለማውረስ ሲሉ፤ ደማቸውን ያፈሰሱት፣አጥንታቸውን የከሰከሱት የእነአፄ ቴዎድሮስ፣ የእነአፄ ዮሐንስ፣ የእነእምዬ ምኒሊክና የእነቅዱስ ጴጥሮስ ልጅ ነው፡፡ይህ ትውልድ አባቶቹ ያቆዩለትን ታሪክ፣ቅርስ፣ባህል፣ትውፊትና ሃይማኖት ሲመዘበር ዝም ብዬ ልይ ቢል እንኳ አይችልም፤ በአጥንትና በደም ማህተም ያወረሱት ቃልና አደራ አለበትና፡፡

እኔ ይህን የምለው እንደ ሃይማኖተኛ ሁኘ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ነው፡፡ በሃገራችን ለውጥ ሊመጣ የሚችለው እርስ በርስ ከመበላላት ይልቅ እርስ በርስ በወሬ ሳይሆን በተግባር ተቻችለን ያሉንን ታሪካዊ ሃብቶች ስንከባከብ ነው፤ እድገትን ከነሙሉ ታረኩ ልንጎናፀፍ የምንችለው፡፡ይህ ካልሆነ ግን ውሃ በቀጠነ አንድ ሁለት እያልን ታላቅ ታሪካዊና አገራዊ ዳራ ያላቸውን ሀብቶቻችንን ካጠፋን ማን ያውቃል ነገ የእኛ ልጆች ስለአገራቸው ታሪክ ለማወቅ ወደ ምዕራብና ሩቅ ምሥራቅ አገሮች የሚሄዱበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ "መብላት ቢያቅታት በተነችው" የሚባለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ምን አለበት የቱሪስት መስህብነታቸውን በመጠበቅ ታሪካቸውን በጠበቀ መልኩ ብናሳድጋቸው፤ ከእስራኤል ለምን አንማርም ያውም ለማታምንበት ነገር በዓመት ከቅዱሳን መካናት ምን ያህል ገቢ እንደምታገኝ፡፡ አይ ጉድ ሁሉንም ነገር ከአዲስ የመጀመርና አፍርሶ የመሥራት አባዜ ኑሮብን እንጂ ባለን ነገር እየቀጠልን ብንሠራ ኑሮ ዛሬ የት ነበርን?

ልብ ያለው ልብ ይበል ጆሮ ያለው ይስማ
ከመውደሙ በፊት የአገሪቱ ካስማ፡፡
ኦ አንትሙ ሕዝብዬ አንሥኡ እደዊክሙ እንዘ ትብሉ "ኦ እግዚኦ ፈንው እዴከ ኀበ ርስትከ ወውሉድከ" [እጃችሁን ወደ ሰማይ አንሥታችሁ “አቤቱ ወደ ርስትህና ወደ ልጆችህ እጅህን ዘርጋ፤” በሉ፡፡]

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በዚህ አድራሻ zwethiopia@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡

1 comment:

  1. አቤቱ ወደ ርስትህና ወደ ልጆችህ እጅህን ዘርጋ

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤