Tuesday, April 10, 2012

በዋልድባ ጉዳይ ብአዴን/ኢሕአዴግ የጠራው ስብሰባ ምጥን ዘገባ (ክፍል አንድ)


·         ስብሰባ የጎንደርን ካህናትና ምእመናን እንደማይወክል ተገለጸ
“ዋልድባ ቅዱስ ገዳማችን ነው፤ እንዲነካ አንፈልግም፤ እኛም እንደ ክልል እነ ኣባይ ፀሃዬ ጉዳዩን የት እንዳደረሱት እንከታተላለን፤ ሁላችሁም ሄዳችኹ አይታችኹ እውነታውን ማረጋገጥ ትችላላችኹ” (አቶ አያሌው ጎበዜ፤ የክልሉ ፕሬዚደንት)።
 (ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 20/2004 ዓ.ም፤ ማርች 29/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ “የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት” በዋልድባ ገዳም ህልውና እና ክብር ላይ የጋረጠውን አደጋ በተመለከተ “የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ካህናትና ምእመናን የሚያነሡትን ሐሳብ ለመስማት” የሚል ስብሰባ ትንት መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ዐምባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
የስብሰባው አዘጋጅ የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሲሆን ለተመረጡ ሰዎች በየስማቸው የተሰራጨው የጥሪ ካርድ ደግሞ በጎንደር ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ሓላፊ የተፈረመበት እና እንደ ሰርግ ካርድ “የጥሪው ካርድ እንዳይለይዎ” የሚል ማሳሰቢያም የሰፈረበት ነው፡፡
ጥሪው በአንድ በኩል የሀገረ ስብከቱን የአድባራት አስተዳዳሪዎችን፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትን፣ የጉባኤ መመህራንና ሰባክያነ ወንጌልን አለማካተቱ በአንጻሩም በቤተ ክርስቲያን ላይ ያላቸው አቋም አጠራጣሪ የሆኑ ግለሰቦች ከየቀበሌው የተጠሩበት መሆኑ የስብሰባው ዓላማ ከጅምሩ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡

ስብሰባው የተመራው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ነው፡፡ ከእርሳቸውም ጋራ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ግዛት ዐብዩ በመድረኩ የተገኙ ሲሆን ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት ዋነኛው ተናጋሪ ደግሞ የስኳር ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኣባይ ፀሃዬ ናቸው፡፡

ከጠዋቱ በ2፡30 እንደሚጀመር ቀጠሮ የተያዘለት ስብሰባ ከረፋዱ 4፡15 የተጀመረ ሲሆን እስከ ቀኑ 8፡00 ድረስ ከዘለቀ በኋላ እንዲህ ባሉት ስብሰባዎች ድራማዊ በሆነ መልክ የሚዘጋጁ “የጋራ አቋም መግለጫዎች” ሳይነበቡበት ተጠናቋል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ከቤቱ የሚቀርቡ አብዛኞቹ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረክ ከሚሰጡት ምላሾች ጋራ አለመጣጣማቸው የተሳታፊዎችን ስሜት እያካረረው በመሄዱ እንደሆነ ተገልጧል፡፡

የስብሰባውን ሂደት የታዘቡ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት በገለጻ ረጅም ጊዜ የወሰዱት አቶ ኣባይ በአብዛኛው ያተኰሩት በመነኰሳቱም ይሁን በምእመኑ ባልተነሡና ደካማ በሆኑ ነጥቦች ላይ ነው - “ገዳሙ በውኃ አይጥለቀለቅም፤ ሸንኮራ አገዳ አይተከልበትም፤ ሕዝብ አይሰፍርበትም” በሚሉ ጉዳዮች፡፡ በመሆኑም ተሳታፊዎቹ አቶ ኣባይ ጥያቄያቸውን እየመለሱ እንዳልሆነ በማስገንዘብ “የገዳሙ መሬት በመንገድ ሥራ ይሁን በእርሻ ተነክቷል ወይስ አልተነካም፤ የቅዱሳን ዐፅም ተቆፍሮ ወጥቷል ወይስ አልወጣም፤ የሚፈርሱ አብያተ ክርስቲያን አሉ ወይስ የሉም?” ለሚሉት ሦስት ዐበይት ጥያቄዎች ቀጥተኛ ምላሽ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋቸዋል፡፡ ሚኒስትሩ ግን አለባብሰው ከማለፍ ውጭ የሰጡት ቀጥተኛ ምላሽ አልነበረም፡፡

ከአቶ ኣባይ ቀደም ሲል የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት ጨምሮ ከደባርቅ፣ ወገራ፣ ጃናሞራ እና ከመሳሰሉት አጎራባች ወረዳዎች የተውጣጣ ልኡካን ቡድን ወደ ፕሮጀክቱ ስፍራ በመሄድ ያደረገውን ቆይታ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ ታይቷል፡፡ የልኡካን ቡድኑ አባላት ከተሳታፊዎች ለተነሡ ጥያቄዎችም ምላሽ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

ከእነርሱም መካከል የጩጌ ማርያም ገዳም አበምኔት አባ ወልደ ገብርኤል እና የኮሶዬ /ወገራ/ በኣታ ለማርያሙ ካህን የሰጡት ምስክርነት ከሌሎቹ ለየት ያለ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ የኮሶዬ /ወገራ/ በኣታ ለማርያሙ ካህንምቤተ ክርስቲያን እንደሚፈርስ ተነግሮናል፤ በሚፈርሱት አብያተ ክርስቲያን ቁጥር ለእያንዳንዳቸው አንድ ሚልዮን ብር ካሳ እንሰጣችኋለን ሲሉ ሰምቻለሁ” ማለታቸው ተዘግቧል። ከሁለቱ የልኡካን ቡድኑ አባላት በተፃራሪ የጎንደር በኣታ እና የአዘዞ ሚካኤል አስተዳዳሪው አባ ብርሃነ መስቀል በዘጋቢ ፊልሙ ላይ የእሳት ጎረቤት እንጂ የውኃ ጎረቤት አይጎዳችሁም እያሉ መነኰሳቱን ሲያግባቡ ታይተዋል፡፡ ለዚህ አነጋገራቸው ከቤቱ ጃፓንን የጎዳት የውኃ ሱናሚ አይደለም ወይ? እንዴት የውኃ ጎረቤት አይጎዳም ትላለህ? የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ 
አርእስተ ጉዳይ፡-
 • በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረበው ‹የሀገረ ስብከቱ ልኡካን ቡድን› ዘገባ ከእውነታው ፈጽሞ የተለየ ስለ መሆኑ በስብሰባው ላይ ተጋልጧል፡፡ የልኡካን ቡድኑ አባል የነበሩ አንድ አባት በተለያዩ አካባቢዎች ከ500 ሜትር እስከ ሦስት ሰዓት መንገድ የሚሆን የገዳሙ መሬት ታርሶ መመልከታቸውን መስክረዋል፡፡
 • የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከቀድሞ የተለየና ያልተጠበቀ አቋም ማሳየታቸው ብዙዎችን አስከፍቷልከቤተ ክህነቱና ከመንግሥት ሓላፊዎች በተደረገባቸው ጫና ሳይደረግባቸው አልቀረም ተብሏል።
 • የመንግሥት ባለሥልጣናት በማይ ፀብሪ፣ በማይ ገባ፣ በዓዲ አርቃይ የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ዘቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳት ላይ የሚፈጽሙትን ልዩ ጫናና ማስፈራሪያ እንዲያቆሙ ተጠይቋል፡፡
 • የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳቱ በልማቱ ላይ እንደተወያዩ በኢ.ቴቪ የተላለፈውን ዘገባ ተቃውመዋል፤ ወደ ቦታው ሄጃለሁ፤ አይቻለሁ፤ ያየሁትን እናገራለሁ፤ ፊልሙ ተቆራርጦ ነው የቀረበው፡፡ ገዳማችንን ደፍራችሁታል፡፡ እዚያ መነኰሳቱን ስንጠይቃቸው ለእኛ የነገሩንገዳማችንን ደፍራችሁታል፤ ምነው በእኛ ዘመን ይህን አመጣብን ብለን እያዘንን፤ እየጸለይን፤ እያለቀስን ነው ያለነው፡፡ ጥያቄያችንን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ልከን መልስ እየጠበቅን ነው፡፡
 • ልማቱን ስለመደገፍ ሲጠየቁም እኛ የልማት ፀሮች አይደለንም ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን በዓዲ አርቃይ፣ በማይ ፀብሪ፣ በማይ ገባ የቤተ ሚናስ መነኮሳትን ስታስጨንቋቸው፣ ስታስፈሯሯቸው፣ ስትጫኗቸው አይቻለሁ፡፡ የቴሌቪዥኑ ጋዜጠኛ ከቆመበት በላይ ወደ ገዳሙ እስከ 500 ሜትር ታርሶ አይቻለሁ፡፡ አባ ነፃ በሚባለው የአትክልት (ሙዝ) ስፍራ እስከ ሦስት ሰዓት የእግር መንገድ የሚሰድ ርቀት ታርሶ አይአለሁ፡፡
 • “በአባቶቻችን አፍረናል” በማለት የተናገሩ የስብሰባው ተሳታፊዎች የቡድኑን አባላት እነርሱ እንዳልመረጧቸው፣ ሊወክሏቸውም እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
 • “በፕሮጀክቱ 50,000 ሰው የሥራ ዕድል ያገኛል፤ 5000 መኖርያ ቤቶች ይሠራሉ ብላችኋል፡፡ መነኰሳቱኮ ዋልድባ ድረስ የሄዱት ዓለምን ጥለው ጥሞናን ሽተው ነው፡፡ ታዲያ እናንተ የገዳሙን ክልል ከተማ ማድረጋችኹ አግባብ ነው ወይ?” /ከተነሡት ጥያቄዎች አንዱ/ ለተሳታፊዎች ጥያቄ ምላሽ ያልሰጡት አቶ ኣባይ ፀሃዬ አበው መነኰሳቱን ‹ፖሊቲከኞች› ገዳሙንም ‹የፖሊቲከኞች መሸሸጊያ› በሚል መናገራቸው በኢሕአዴግ አገዛዝ የቀጠለው ቤተ ክርስቲያንን የመናቅና መዳፈር አስተሳሰብና ተግባር አካል መሆኑ በተሰብሳቢዎቹ ተነግሯቸዋል
 • አቶ ኣባይ የዋልድባ መሬት ‹ለአፈር ምርመራ› በሚል መታረሱንና ዐፅሞችም መነሣታቸውን ያመኑ ሲሆን በገዳሙ ክልል ውስጥና ውጭ ‹ከሕዝቡ ጋራ በመነጋገር› የሚፈርሱ አብያተ ክርስቲያን እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡
 • የጠ/ቤ/ክህነቱ ም/ዋ/ሥ/አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት እና የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ ወደ አዲስ አበባ ተልከው የሄዱ መነኰሳትን “መዋቅር ያልጠበቁ ሕገ ወጦች ናቸው” በማለት ዘልፈዋቸዋል፡፡
 • አቶ ኣባይንና አወያዩን አቶ አያሌው ጎበዜን ሳይቀር ደስ ያላሰኘው የአቶ ተስፋዬ ‹ውዳሴ ኢሕአዴግ› በተሰብሳቢው ተቃውሞ ተቋርጧል፡፡
 • በዕለቱ በስብሰባ አመራራቸው የተወያዮቹ መጽናኛ የሆኑት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ “ዋልድባ ቅዱስ ገዳማችን ነው፤ እንዲነካ አንፈልግም፤ እኛም እንደ ክልል እነ ኣባይ ፀሃዬ ጉዳዩን የት እንዳደረሱት እንከታተላለን፤ ሁላችሁም ሄዳችኹ አይታችኹ እውነታውን ማረጋገጥ ትችላላችኹ፤” በማለት ተሳታፊዎች ያነሷቸው ‹ስጋቶች› በምክክር እና ውይይት መፈታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
 • ቅዱስ ሲኖዶስ የራሱን አጣሪ ቡድን ልኰ የገዳሙን ህልውና የሚያስጠብቅ አቋም እንዲወስድ፤ መንፈሳውያን ማኅበራት ትክክለኛውን መረጃ ይዘው ገዳሙን የማስጠበቅ እንቀስቃሴ እንዲያካሂዱ፣ መንግሥትም ቀስ በቀስ በይፋ እያመነ የመጣቸውን መረጃዎች በተሟላ ይዘታቸው (እውነታቸው) ለሕዝቡ ግልጽ በማድረግ ተነጋግሮ የማስማሚያ ነጥብ እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡
በተያያዘ ጉዳይ፦
 • ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ዋልድባ ገዳም አምርቶ የፕሮጀክቱን ተጽዕኖ በመገምገም ይፋዊ ሪፖርት የሚያቀርብ የባለሞያዎች ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱ እየተነገረ ነው፡፡
 • መጋቢት 27 ቀን በዋልድባ አብረንታንት መድኃኔዓለም  ክብረ በዓል (በዓለ ንግሥ) ነው፡፡ በርካታ የጎንደር ከተማ ምእመን በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከነገ መጋቢት 21 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስፍራው መጓዝ ይጀምራል -  አንድም ለአክብሮ በዓል በሌላም በኩል ለገዳሙ ያለውን አለኝታ ለመግለጽ፡፡ ጉዞው ከጎንደር እስከ ዓዲ አርቃይ በተሽከርካሪ ከዚያ በኋላ የ18 ሰዓታት የእግር መንገድ ነው፡፡
 • “ዋልድባ ዓለም አቀፍ ገዳማችን ነው፤ የትግሬው ወይም የአማራው ብቻ አይደለም !!” (ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ አንድ የዞኑ የደኅንነት መኰንን ዋልድባ በትግራይ ክልል የሚገኝ በመሆኑ በልማቱ ላይ ጥያቄ ማንሣት እንደማይችሉ ለተናገራቸው ቃል የመለሱለት)

የአርእስተ ጉዳዮቹ ዝርዝር እንደረሰልን የምናቀርብ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤