Tuesday, April 10, 2012

በዋልድባ ጉዳይ ብአዴን/ኢሕአዴግ ስብሰባ ጠራ


አርእስተ ጉዳዮች፡-
(ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 19/2004 ዓ.ም፤ ማርች 28/2012 READ THIS ARTICLE IN PDF)፦
·         ከሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ከዋልድባ ገዳም ተወክለዋል የተባሉ መነኰሳት፣ ከጎንደር ከተማ የተመረጡ ምእመናንና በማኅበረ ቅዱሳን የጎንደር ማእከል ሥራ አስፈጻሚ አባላት ነገ፣ መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም፣ የመንግሥት ‹‹የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት›› በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ ስለ ደቀነው ስጋት፣ በተጨባጭም ስለታየው መጋፋት ውይይት እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡ ስብሰባውን የጠራውን ብአዴን/ኢሕአዴግ ሲሆን የሚካሄደውም በጎንደር ከተማ መሆኑ ተመልክቷል፡፡


በስብሰባው ላይ የፕሮጀክቱ ስፍራ ድረስ በመሄድ የግድቡን ግንባታ ከሚያካሂደው ተቋራጭ (ሱር ኮንስትራክሽን) ባለሞያና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ የቀጥታ ውይይት አካሂደዋል የተባሉ ግለሰቦች በስብሰባው ላይ ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ እኒህ ግለሰቦች ከትላንት በስቲያ የኢትዮጵያ ቴሊቪዥን ዘገባ ላይ የግድቡ ግንባታ፣ የሸንኮራ ልማቱንና ስኳር ፋብሪካው ከገዳሙ ክልል ጋራ ግንኙነት እንደሌለው፣ ይልቁንም ልማቱ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ እንደሚደግፉት ሲገልጹ የተሰሙት ናቸው፡፡

የዜናው ምንጮች እንደሚገልጹት በኢ.ቴቪ ዜና ዘገባ ላይ ቀርበው እንዲህ ዐይነቱን አስተያየት የሰጡት ወገኖች ተጨማሪ ሹመት ሽልማት የሚፈልጉ፣ ሁሉንም የገዳሙን ማኅበር አባላት የማይወክሉ፣ ለድርጅቱ እንደ ካድሬ ሆነው የሚያገለግሉ በመሆኑ ሪፖርታቸው ተቀባይነት እንደማይኖረው ተነግሯል፡፡

በሌላ በኩል፡-
·         የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የገዳመ ዋልድባ ችግር ከተሰማበት ዕለት አንሥቶ ጸሎተ እንዲያዝ ዐውጀው እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ይኹንና ‹‹እንዴት ጸሎት ያውጃሉ፤ ዐመፅ ለመቀስቀስ ነው ወይ?›› በሚል በአንድ የዞኑ ባለሥልጣን በተጠየቁበት ወቅት ‹‹ጸሎት እንዳላውጅ ማን ይከለክለኛል?›› ብለው መልሰዋል፡፡ የዞኑ ሓላፊም ማንኛውም ሰው ወደ ፕሮጀክቱ አካባቢ ሄዶ ግድቡ ለገዳሙ ጉዳት እንደሌለው ማረጋገጥ እንደሚችል በገለጸው መሠረት ሰዎች ተመርጠው ወደ ፕሮጀክቱ አካባቢ ለመሄድ ሲዘጋጁ ግን እንዳይሄዱ ተከልክለዋል፡፡


በምትኩ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ልኡካን በጎን ተልከው ባወጡት መግለጫ ምእመኑ ክፉኛ ማዘኑ ተመልክቷል፡፡ የግድቡ ውኃ የሚሸፍናቸው በገዳሙ ክልል የሚገኙ አራት አብያተ ክርስቲያን እንደሚፈርሱ ግልጽ ሆኖ እያለ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መግለጫና በኢ.ቴቪ ዘገባ የገዳሙ ድንበር እንዳልተደፈረ የተላለፈው ዘገባ ከእውነቱ የራቀ መሆኑም ተገልጧል፡፡ ይኸው ዘገባ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት የገዳሙን ህልውና እና ክብር ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢያሳርፍም ‹‹የኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀብት የሆነው ገዳመ ዋልድባ ዕድል በቀላጤ/ቅጥረኛ ሓላፊዎች መግለጫ ሊወሰን አይችልም፤›› ተብሏል፡፡

·         አባ ነፃ በተባለው የብዙ ቅዱሳን ዐፅም በክብር የፈለሰበትና፣ የሙዝ ቋርፍ የሚዘጋጅበት የገዳሙ የአትክልት ቦታ የታረሰ በመሆኑ ‹‹ለቋርፍ ተለዋጭ መሬትና በጠፋውም የቋርፍ ተክል ምትክ በስድስት ወር የሚደርስ የሙዝ ዘር እንሰጣችኋለን፤›› ቢባልም ማኅበረ መነኰሳቱ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተዘግቧል፡፡ የሙታን ዐፅም ከተቀበረበት መፍለሱን ያመኑት የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ‹‹የፈለሰው ግን የቅዱሳን ዐፅም አይደለም›› ለማለት መሞከራቸው ባልተጣቸው ሥልጣን መግባታቸውን ያሳያል፡፡
·         ከአራቱ የገዳሙ አብያተ ክርስቲያን መነሣት ውጭ የቀሪዎቹ 14 የገጠር አብያተ ክርስቲያን መነሣት በተመለከተ ከጥቂት ጊዜያት በፊት በጎንደር ከተማ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋራ በተፈጠረ አለመግባባት ሙስሊሞቹ ከቦታው ሲነሡ መስጊዱ ግን እስከ አሁን ተጠብቆ የቆየበት ሁኔታ በምሳሌነት ቀርቧል፡፡ ከዚህ አኳያ ሕዝቡ ሲነሣ ማኅበራዊ ተቋሞቹ አብረው ይነሣሉ በሚል 14 አብያተ ክርስቲያን እንደሚፈርሱ መገለጹ ፍትሐዊ ባለመሆኑ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
ይህ በዝምታ ከታለፈ ነገ በከተማ ያሉ አብያተ ክርስቲያን ሳይቀሩ በስመ ልማት ይፍረሱ የሚባሉበት ጊዜ ሩቅ ባለመሆኑ መንግሥት የክርስቲያኑን ጩኸትና አቤቱታ አድምጦ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ጸንቶ መታገል እንደሚያስፈልግ የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል በዓዲ አርቃይ፣ በማይ ፀብሪ እና በሽሬ ተመሳሳይ ውይይት ስለመካሄዱ በመንግሥት ባለሥልጣናትና ብዙኀን መገናኛዎች መገለጹ ይታወሳል፡፡
 አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤