Thursday, April 12, 2012

በቪኦኤ የቀረቡትን ካልጠቆማችኹ በሚል ሦስት ገዳማውያን ታስረው ተፈተዋል::

  • እስሩናአደኑየቤተሚናስመነኰሳትበተለይም1997 .ወዲህለሚደርስባቸውልዩጫናግልጽአመልካችነውተብሏል::
  • 1980 .የገዳሙንሰሜናዊክፍል (በእንስያወንዝ) የጦርካምፕለማድረግየተቃጣውሙከራበኅቡኣንአበውኵናትመወገዱተነግሯል::
  • አባ ሳሙኤል ዘ
       
(ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 29/2004 .ም፤ April 7/2012 READ THIS ARTICLE IN PDF) የመንግሥት ባለሥልጣናት በዋልድባ አብረንታንት ገዳም ዘቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳት ላይ ከሚያደርሱባቸው ወከባና ማስፈራሪያ እንዲታቀቡ እየተጠየቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሦስት የገዳሙ ማኅበር አባላት በፖሊስ ታስረው መፈታታቸው ተሰማ፡፡ መነኰሳቱ ለእስር የተዳረጉትለቪኦኤ መግለጫ የሰጡት አባት የት እንዳሉ ተናገሩከሚል የፖሊስ ጥያቄ ጋራ በተያያዘ መሆኑን ምንጮቻችን ከስፍራው ዘግበዋል፡፡ እንደ ምንጮቹ መረጃ ኮማንደር በየነ በሚባል የፀለምት ወረዳ ፖሊስ መጋቢት 23 ቀን 2004 . ከገዳሙ የተወሰዱት ሦስቱም ታሳሪዎች በገዳሙ በዲቁና የሚያገለግሉ ሲሆኑ ከሦስቱ ሁለቱ መናንያን መሆናቸው ተገልጧል፡፡

በደረሰን መረጃ መሠረት መጋቢት 23 ታስረው ከሁለት ቀናት በኋላ የተለቀቁት ገዳማውያን በስም ዝርዝራቸው ዲያቆን ገብረ ጊዮርጊስ /መናኝ/ ዲያቆን ገብረ ትንሣኤ /መናኝ/ ዲያቆን ገብረ ሥላሴ /ረድእ/ እንደሆኑ ተረድተናል፡፡ ይህም ሆኖ በማኅበረ መነኰሳቱ ተወክለው ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የዐማርኛው አገልግሎት ጋራ ስለ ወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት አሉታዊ ተጽዕኖ ቃለ ምልልስ ያደረጉት አባት (ስማቸውን ለጊዜው በይፋ መግለፁን አልፈለግንም) እስከ አሁን የት እንደሚገኙ አለመታወቁ ተመልክቷል፡፡
እኒህ አባት ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ቃለ ምልልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን በማኅበረ መነኰሳቱ ሙሉ ስምምነት ከፕሮጀክቱ የተነሣ ገዳማውያኑ ያደረባቸውን ሐዘንና ጭንቀት የሚገልጽና ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአድራሻ የተጻፈውን ደብዳቤ እንዲያደርሱ ወደ አዲስ አበባ ከተላኩት መነኰሳት አንዱ ናቸው፡፡ ፖሊስ እርሳቸውን ለመያዝ የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ እንደ ቀጠለ እየተነገረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት መነኰሱ በገዳሙ እንደማይገኙ ተዘግቧል፡፡
በምዕራብ ትግራይ ዞን የማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ መረሳ በቅርቡ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሁለቱም ቤቶች ተወክለው ወደ አዲስ አበባ የተላኩት መነኰስ በብዙኀን መገናኛ ቀርበው ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን፣ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ስጋቶች ሊነሡ እንደሚችሉና ለምን ተነሡ እንደማይባል ነገር ግን አጀንዳውየምቀኝነትና ኾን ተብሎ ሕዝብን ለማነሣሣትእንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡ ገዳማዊው አባት በበኩላቸው ስለተላኩበት ጉዳይ ለሚዲያ መግለጫ መስጠታቸውን በተመለከተ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱለሚዲያ የተናገርኹት ሃይማኖቴ ስላስገደደኝ ነውማለታቸው ይታወሳል፡፡ እርሳቸው ለቪኦኤ ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎና አሁን በፖሊስ ከሚደረግባቸው ክትትል ቀደም ብሎእውነተኛ የገዳሙ መነኵሴ አይደሉም፤ በገዳሙም አይኖሩምበሚል ስለተነዛባቸው ስም ማጥፋትምያመነኰሱኝ አባት በገዳሙ ይገኛሉ፤ የኔ ቆብ ከመርካቶ የተሸመተ አይደለም፤ብለው መመለሳቸው አይዘነጋም፡፡ በዕርግና ምክንያት ከአበምኔት ሓላፊነታቸው የተገለሉት መምህር አባ ገብረ ክርስቶስ የተባሉ አባትም ይህንኑ ቃላቸውን ለሬዲዮ ጣቢያው ማረጋገጣቸው ተዘግቧል፡፡
1997 . ምርጫ ውዝግብ ወዲህ ክልላዊ የአስተዳደር አካላት በተለይም የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳትንበሽሬ፣ ወልቃይትና ፀገዴ ለተቃዋሚዎች ቀስቅሳችኋልበሚል የሚያደርጉባቸው ተጽዕኖ የተለያዩ ሰበቦችን ሽፋን በማድረግ ከመቀጠሉም በላይ እያደር እየተጠናከረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በሌላ በኩል ለመነኰሳቱ ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወገኖች ገዳማውያኑን በመጥቀስ እንደሚናገሩት÷ እነአባአቤቱታቸውን ለክልልና የዞን አስተዳደር ቢሮዎች፤ ለአህጉረ ስብከትና የወረዳ ቤተ ክህነት /ቤቶች በግልባጭ÷ ለፌዴራል መንግሥቱ ርእሰ መስተዳድር አቶ መለስ ዜናዊ በአድራሻ ለማድረስ አነሳስቷቸዋል ብለው ከሚያምኗቸው የማይዘነጉ አጋጣሚዎች መካከል ሁለት ታሪካዊ ክዋኔዎችን ይጠቅሳሉ፡፡
አንዱ ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግል በሚያካሂድበት 1980 ግድም የሆነ ነው፡፡ የመረጃው ምንጮች ቁጥራቸውከአንድ ሺሕ አያንሱምበሚል የሚገምቷቸው የኢሕአዴግ ታጋዮች የእንስያን ወንዝ ድልድይ ተሻግረው ወደ ገዳሙ ገብተው ሰፈሩ፤ ገዳሙ አምሳለ ጦር ሰፈር /ካምፕ/ ሆነ፡፡ በዚህም ገዳማውያኑ በእጅጉ ቢያዝኑ ከታጋዮቹ 80 ያህሉ ሞተው ይገኛሉ፡፡ ከእኒህም ጥቂቶቹ ለቅዱሱ ቦታ የማይገባ ተራክቦ ሲፈጽሙ የዞረባቸው ዘንዶ ትንፋሽ ያልፈሰፈሳቸው ሲሆኑ የተቀሩትም ቦታው አይረክስም የሚሉ ኅቡኣን ኵናት የቀሠፋቸው ናቸው፡፡ መነኰሳቱ የገዳሙ ክብር የተገለጠበትን ይህን ፍትሐ እግዚአብሔር (ተግሣጽ) ለህወሓት/ኢሕአዴግ ሊቀ መንበር በማለበም፣ የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ዐቃጅና ተግባሪም ፌዴራል መንግሥቱ በመሆኑ የፕሮጀክቱ አግባብነት እንዲፈተሽ ማሳሰብ በሚል ቀናነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ/ በአድራሻ ለመጻፍ እንደቆረጡ ምንጮቹ ይናገራሉ፡፡
ለቤተ ክህነቱ አካላት በግልባጭ ብቻ ከማሳወቅ በቀር በአካል ያልሄዱበት ምክንያት ደግሞ ገዳማውያኑ ቢያንስ 16 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲያመለክቱበት ለነበረው ችግራቸው ተቋሙ መፍትሔ ሊሰጣቸው አለመቻሉ ነው፡፡ ይኸውም በሁለት ክልላዊ መስተዳድሮች የባለቤትነት ውዝግብ መካከል የቆየው የዋልድባ ገዳምለጸጥታ አጠባበቅ እንዲያመችበሚል እስከ ዳልሽሓ እና ሰቋር ድረስ ያለው ወደ አማራ ክልል ከማኅደሮ ወዲያ ያለው የገዳሙ ክፍል ደግሞ ወደ ክልል ትግራይ እንዲሆን 2000/01 . መወሰኑን ምንጮቻችን ያስረዳሉ፡፡
ይህም ኹኔታ በቀድሞው መንግሥታት ወቅት ልዩ ሥራ እንዳይሠራበት በዐዋጅ ተከብሮ የቆየው የገዳሙ ክልል ከብቶች እንዲሰማሩበት፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዕጣን መቃሪዎች (ለቃሚዎች) እና ወርቅ ጫሪዎች (ቆፋሪዎች) በተለይ በማይ ሰሪ ወንዝ በኩል ያለከልካይ አልፈው ጎጆ ቀልሰው እንዲሰፍሩ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ በዚህም በበጋ ወቅት መንሥኤው በማይታወቅ ቃጠሎ በየጊዜው የሚጠፋው ደን ሳያንስ በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው ዕፀዋት ፈልሰዋል፤ የማር አዝመራ የሚቆረጥባቸው ዕፀዋት ሳይቀሩ እረኛው በልምላሜ እየቆረጣቸው በቁማቸው ደርቀው ቀርተዋል፤ የግሑሳን መሳፈርያ የነበሩ የዱር እንስሳት ተሰደዋል፤ መንፈሳዊ ተጋድሎና ቅድስና ሽተው ዓለሙን ንቀው የመጡ አባቶችም ተረብሸዋል፡፡
ማኅበረ መነኰሳቱ ይህንኑ ችግራቸውን መጋቢት 27 ቀን 1989 . በገዳሙ ለተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ በወቅቱ አበምኔት መምህር አባ ተጠምቀ ገብረ ኢየሱስ በኩል አቅርበውላቸው ነበር፡፡ ሚያዝያ 30 ቀን 1989 . ታትሞ የወጣው ልሳነ ተዋሕዶ ዘኦርቶዶክስ መጽሔትከአምስቱ ፓትርያሪኮች ዋልድባን ለመጎብኘት የመጀመርያው ናቸውበተባሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተገኙበት በአበምኔቱ የተሰጠውን መግለጫ እንደሚከተለው አቅርቦት ነበር፡-
“. . .
ወኵሉ ፍጥረት ተፈሥሓ በምጽአትከ ባለው መሠረት በቅዱስነትዎ መምጣት ከፍ ያለ ደስታ ተሰምቶናል፤ ደስታውም የእኛ ብቻ ሳይሆን የዓለሙ ሁሉ ደስታ ነው፡፡ በዚህ ገዳም ያለፉት ቅዱሳን አባቶቻችን በመንፈስ እየተደሰቱ ነው፡፡ አባትዎ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስመጥቼ አየዋለኹበማለት ተስፋ ሰጥተውን ነበር፤ ነገር ግን እንዘ ወልድየ አንተ ኮንከኒ አበ እንደተባለው እርሳቸው በመንፈስ እርስዎ በአካል በመምጣትዎ ተድስተናል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፡- ከዚህ ቅዱስ ስፍራ ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መጥተው ከስውራኖች[ኅቡአን] ጋራ የተነጋገሩት ከዚህ ገዳም ነው፤ ቀጥሎም አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ 70 ዓመት ተቀምጠው ዐርፈውበታል፤ እንዲሁም በእርሳቸው እግር የተተኩ ብዙ ቅዱሳን ፈልሰውበታል፡፡
ይህ ገዳም በኢትዮጵያ ካሉት ገዳማት ቀዳሚነት ያለውና ተወዳዳሪ የሌለው ገዳም ነው፡፡ በዚህ ቅዱስ ቦታም ብዙ የበርሓ አራዊት ይገኙበታል፡፡ እንደ ድሮው አንበሳ እንኳ ባይገኝ እንደ ነብር፣ አጋዘን፣ ወደንቢ፣ ድኵላ. . .በብዛት ይገኙበታል፡፡ አሁን ግን ችግሩ ይህ የቅዱሳኖች ዋሻና የአራዊት ደን ቦታችን የከብቶች ማሰማሪያ በመኾኑ ቅዱሳኖች በመረበሽ አራዊቱም በመሰደድ ላይ መኾናቸው እንዲታወቅልን እንወዳለን፡፡. . .ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፡- . . . በየቦታው ርዳታ ማድረግና የልማት ዘርፎችን መዘርጋት ልማዱ የኾነው ቅዱስነትዎ ረድኤትና ጸሎት በማንኛውም ወቅት ከገዳማችን እንዳይለይብን እንጸልያለን በማለት አሳስበዋል፡፡
እንደ መጽሔቱ ዘገባ ፓትርያሪኩ በወቅቱ ለገዳሙ መናንያንና አገልጋዮች መነኰሳት የኀምሳ ሺሕ ብር የገንዘብ ርዳታ፣ መስቀሎችን፣ ጃንጥላዎችን፣ መጎናጸፊያዎችንና ምንጣፎችን የመሳሰሉ የንዋየ ቅድሳት ስጦታ፤ በራሳቸው የሚገለገሉባቸውን የራስ አክሊል፣ የደረት አይከን፣ የእጅ አርዌ ብርትና ሙሉ አልባሳት ለገዳሙ መገልገያ ይኾን ዘንድ ጨምረው አበርክተዋል፡፡
ይኹንና ፓትርያሪኩ በቤተ ክርስቲያን ስም እንደሰጡት የተገለጸው የብር ርዳታ ይቅርብን ወይስ እንቀበል በሚል አነጋግሮ እንደነበረው ሁሉ በቃለ ቡራኬያቸውም ወቅት፡- “ገዳሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከመናንያኑ የቋርፍ ምግብ በስተቀር እህል ውኃ ስለማይቀመስበትና ሴቶች እስከተወሰነ ቦታ ድረስ ስለማይገቡበት መንፈሳዊውን አገልግሎት በአንድነት ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኖ የቆየ በመሆኑ ወደፊት ለሁሉም በሚያመች አማካይ ስፍራ ሁሉም በአንድነት አገልግሎት የሚያገኙበት ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራሲሉ በትግርኛም በአማርኛም የሰጡት መምሪያ በማኅበረ መነኰሳቱ ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬና ቍጣ ቀስቅሶባቸው እንደነበርም የመረጃው ምንጮች ያስታውሳሉ፡፡
አሁን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ስም መግለጫ የሚሰጡ አካላት በፕሮጀክቱ ላይ የሚቀርቡትን የመነኰሳቱን ስጋት አለመልካቸው መልክ መስጠታቸውሁሉም አገልግሎት የሚያገኙበት ቤተ ክርስቲያን ይሠራበሚል ሽፋን የገዳሙን ሥርዐት ለመከለስ የሚሹትን የአቡነ ጳውሎስን መመሪያ በስኳር ፋብሪካ ግንባታና በሸንኮራ ልማት አጋጣሚ ለማሳካት የሚደረግ መፍጨርጨር ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በገዳማውያኑ ጸሎትና ሕዝቡ በጻፈላቸው ግልጽ ደብዳቤ ተፈጻሚ ሳይሆን መቅረቱ በሚነገርለት በዚሁ የአቡነ ጳውሎስ መመሪያ አዝነውና አልቅሰው በወቅቱ ፓትርያሪኩን ፊት ለፊት የተቃወሙና ያስጠነቀቁት (ከቤተ ጣዕማም ከቤተ ሚናስም) እንደ አባ ተስፋ ሚካኤል፣ አባ ቃለ ጽድቅ እና አባ ገብረ ሥላሴ የተባሉ አበው መነኰሳት በፓትርያሪኩ ባለሟሎችእብዶችበሚል ተዘልፈው እንደነበርም ምንጮቹ አይዘነጉም፡፡
ጥቡዐኑ መነኰሳት የተቆጡትሰምተነው አናውቅምባሉት በዚሁ የፓትርያሪኩ ንግግር ብቻም አልነበረም፤ በጉብኝቱ ወቅትገዳሙን የጦር አውድማ አስመስሎት ነበርበሚል የተነቀፈው ለአቡነ ጳውሎስ የተደረገ ወታደራዊ እጀባ እና ውጠራም ጭምር እንጂ፡፡ ይኸው 1989 . ለሃይማኖት አባት ሊደረግ ከሚያስፈልገው በተጋነነ መልኩ ታይቶ የነበረው የኀይል ስምሪትና ውጠራ ፓትርያሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ገዳሙ በመጡበት 2002 . ከበፊቱ በተጠናከረ አኳኋን መደገሙ በተአምኖ እግዚአብሔር ብቻ ላይ ጸንተው የኖሩትንና የሚኖሩትን አበው ልብ በእጅጉ ያሻከረ እንደሆነ ነው ምንጮቹ ለማብራራት የሚሞክሩት፡፡
እናሳ? በአጠቃላይ በዘላቂ ሥነ ልማት አስተምህሮ አግባብ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ተጽዕኖው በሚዛን ታይቶ ቢታቀድ፣ መንግሥት እንደሚለው የአገር ውስጥ ስኳር ፍጆታን ከማሟላት አልፎ በዓለም አቀፍ ገበያ የውጭ ምንዛሪን ለማስገኘት፣ የኢንዱስትሪ ልማቱን በማስፋፋት የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥና የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ የሚጠቅመው የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ÷ የገዳሙን ህልውናና ክብር የሚፈታተን፣ ከዚህም አልፎ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አጋጣሚዎች ጋራ እየተሸመነ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መለዮ የኾኑ ገዳማትን የማጥፋት ተልእኮ ተደርጎ ባልተወሰደ ነበር !!


ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤