Wednesday, May 30, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን የዋልድባ ገዳም ሪፖርት ላይ የ "አንድ አድርገን" እይታ


ባሳለፍነው ሳምንት ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ ገዳም ህልውናን ያናጋል የተባለው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ላይ በላካቸው ልኡካን ቡድኖች አማካኝነት ያዩትንና የተመለከቱትን ፤ የእነርሱን እይታ ጨምረው የ9 ገጽ ሪፖርት ማቅረባቸው ይታወቃል ፤  በመጀመሪያ በዚህ ጊዜ ከቤተ ክርስትያኗ ጎን በመቆም የነበረውን ብዥታ ለማጥራት ጊዜ በመውሰድ በዋልድባ አካባቢ ያለውን እውነታ ለማቀመጥ ለደከሙ ወንድሞች አድናቆቴን ማቅረብ እወዳለሁ ፤ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መናገርም ሆነ አለመናገር የሚያስጠይቅበት ወቅት ላይ አቅም በፈቀደ መጠን ሪፖርቱ የሚያመጣውን የወደፊት ተግዳሮት ግምት ውስጥ በማገባት ይህን ስራ መስራት መቻል ከኃላፊነትም በላይ መሆኑን ላስገነዝብ እወዳለሁ ፤ ቤተክህነቱ ምዕመኑን አንገት ያስደፋ ሪፖርት ስሙኝ በማለት የኢቲቪ ጋዜጠኞችን ጠርቶ ቢያቀርብም እንኳን አሁን ደግሞ ግልጽ ያለ ነገር ምዕመኑ ማወቅ ችሏል ፤ ይህን ሪፖርት ያስቀመጣቸውን ጥሬ ሀቆች ፤ አጠይሞ ያስቀመጠውን እና የጥናቱን ውስንነት ለመዳሰስ እንወዳለን፡፡


Tuesday, May 29, 2012

አባቶች ስለ ዋልድባ ዝምታን ለምን መረጡ ?(አንድ አድርገን ግንቦት 21 2004 ዓ.ም)፡- ከቀናት በፊት ተጀምሮ ፍጻሜውን በአስር ነጥብ የአቋም መግለጫ የተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በርካታ መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ለህዝበ ክርስትያን እና ለቤተክርስትያኒቱ በሚጠቅሙ አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሮ መጠናቀቁ ይታወቃል ፤ ስብሰባው ሲጀመር የቅዱስ ሲኖዶስ 20 አጀንዳዎችን ከተቀረጹ በኋላ የዋልድባ ጉዳይ እንደ አጀንዳ አለመያዙን እያነጋገረ መሆኑን ገልጸን ጽፈን ነበር ፤ እኛ እንዳልነው ስብሰባው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በዋልድባ ጉዳይ ላይ ምንም የተባለ ነገር አለመኖሩ ምዕመኑን አስደምሞታል ፤ ለምን አባቶች አቋማቸውን መግለጽ አልፈለጉም ? ከዚህ በላይ ችግርስ አሁን በቤተክርስትያኒቱ ላይ አለን ? ምዕመኑ የተቃወመውን ያህል አባቶች ምን እንደሚሉ መስማት የብዙዎች ፍላጎት ነበር ፤ ነገር ግን ይህ ሲሆን መመልከት አልቻልንም ፤

Monday, May 28, 2012

ለገዳማት የመብዐና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ


(ማኅበረ ቅዱሳን)፡-በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል በየወሩ እየተዘጋጀ የሚቀርበው የዜና ገዳማት መርሐ ግብር ግንቦት 7 ቀንYemeba Serchet to Monks 2004 ዓ.ም. ተካሔደ፡፡ በዋነኛነት ከየካቲት 24 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ በቆየው የመብዐ ሳምንት በሚል በችግር ላይ ለሚገኙ 400 አድባራትና ገዳማትን ለመርዳት ከምእመናን የተሰበሰበን መብዐ እና አልባሳት /ልብሰ ተክህኖ/ ስርጭት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ 800 ሺህ ብር ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን እስከ 750 ምእመናን ተሳትፎ አድርገዋል በማለት የገለጹት የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ናቸው፡፡ በተገኘው ገቢ መሠረት ስርጭቱን በ4 ዙር ለማከናወን የታቀደ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር በትግራይ 7 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለሚገኙ 50 አድባራትና ገዳማት እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት ለአንድ ዓመት የሚሆን የመብዐ ስጦታ ተሰጥቷል፡፡


ጉድ ሳይሰማ!


ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም፤

ዛሬም ጉድ ተሰማ ከዋልድባ ገዳም፤

ካባቶቼ ሃገር አበረንታንት ገዳም ።

ዛሬም ጉድ ተሰማ ከሰሜን ተራራ፤

ወልቃይት ጠገዴ ከቅዱሳን ጎራ፤

ጸለምት ማይ ፀብሪ በተራ በተራ።

በጌታ ቡራኬ በቅዱሳን ጸሎት፤

በርስት ያገኘነው ካበው ከቀደሙት፤

ላይጠፋ ዘላለም የገደሙት ገዳም፤

የህይወት ምንጭ ሆኖ የቆየው ለዓለም፤

Wednesday, May 23, 2012

ወቅታዊ ግጥም


ተነስ!
ተነስ ከተኛህበት ንቃ
እምነታችን እንድትኖር ተጠብቃ
ያንቀላፋህ ቶሎ ንቃ
እምነትህ ላይ ፈተናዎች ተደቅነው
አህዛቡ ገዳማቱን ሲያቃጥለው
ዋልድባንም መንግስታችን ገብቶ ሲያርሰው
እስከመቼ ነው ዝም የምንለው?
በቃ! እንበል ዋልድባችን አይታረስ
ገዳማችንንም አታፍርስ!
ተነሳሁኝ አንተም ተነስ
እንባባል በአንድ መንፈስ።
ከአብነት ለወየሁ (ግንቦት 2004 ዓ.ም)

Monday, May 21, 2012

የውይይት መድረኮች እንደቀጠሉ ነው

የታላቁ ገዳማችን ዋልድባን በኢትዮጵያ መንግሥት መደፈር ያስቆጣቸው ክርስቲያኖች በተለያዩ የአሜሪካን ግዛቶች ውይይት እያደረጉ እንደሆነ ከተለያዩ ከተሞች የደረሰን ሪፓርት ይገልጻል። በሳንዲያጎ ካሊሮርኒያ፣ በሚኒያ ፖሊስ ሚኖሶታ፣ በሻርለት ኖርዝ ካሮላይና፣ በቶሮንቶ ካናዳ ታላላቅ ሕዝባዊ ውይይቶች ተደረገው እንደነበረ መረጃዎች ደርሰውናል። በነዚህ በተለያዩ ከተሞች የተነሱት ውይይቶች ላይ እንደተረዳነው
፩ኛ/ አጠቃላይ ስለ ዋልድባ ገዳም ጂኦግራፊካል ገለጻ
፪ኛ/ ስለ ገዳሙ ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻዎች
፫ኛ/ መንግሥት በሰጣቸው መግለጫዎች ላይ በመነሳት የባለሙያዎች ገለጻ
፬ኛ/ ክርስቲያኖች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብን እና
፭ኛ/ በመጪው June 4, 2012 ወይም ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ስለተጠራው ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ

የተለያዩ አስተያየቶች፣ መግለጫዎች እና በቀጣይነት ምን መሠራት እንዳለበት ከስብሰባው ተሰብሳቢዎች እና ከውይይት አስተባባሪ ኮሚቴዎች መሰጠቱን ለመረዳት ችለናል።
በቀጣይነት እስከ June 4, 2012 ድረስ በተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ ስብሰባዎች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስብሰባዎች፣ የስልክ ኖንፈረንሶች በተለያዩ ከተሞች እንደሚደረጉ ለመገንዘብ ችለናል፥ በዚህም መሰረት በመጪው ጥቂት ቀናት ውስጥ

በዋሽንግተን ዲሲ የስልክ ኖንፈረንስ
በሚኒያፖሊስ ሜኖሶታ የውይይት መድረክ
በአትላንታ የውይይት መድረክ በዘጋጀቱን ለመረዳት ችለናል፥ ሙሉ መረጃዎቹ እንደደረሱን ለአንባቢያን እንገልጻለን።
እስከዚያው
ቸር ይግጠመን

Sunday, May 20, 2012

በብዙ ጫና ውስጥ ያለው ማ/ቅዱሳን መንግሥት በዋልድባ አካባቢ ስለሚገነባቸው ፕሮጄክቶች ሪፖርቱን አቀረበ  •    ሪፖርቱ የጠ/ቤተ ክህነት ሓላፊዎች “አቀረብን” ካሉት በይዘትም በተአማኒነትም የተሻለ ነው።
(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 10/2004 ዓ.ም፤ May 18/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ማ/ቅዱሳን መንግሥት በዋልድባ አካባቢው ሊሠራው ስላቀደው ግዙፍ ሮጄክት “አጠናሁት” ያለውን ሪፖርት አቀረበ፤ ከመንግሥት ጋር መነጋገሩንም ገለጸ። ዛሬ ይፋ የተደገው የማኅበሩ ሪፖርት የቤተ ክህነቱ አዳዲስ ተሿሚዎች ማኅበሩን በዋልድባ ጉዳይ በከሰሱ ማግስት የቀረበ ሲሆን ለእነርሱ ክስ የተሰጠ አፋጣኝ ምላሽ ይሁን አይሁን ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

Saturday, May 19, 2012

የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ!


የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ!

Thursday, May 17, 2012

የጸሎት እና የምስጋና ጥሪ በመላው ኢትዮጵያ ለምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን በሙሉ!እንደሚታወቀው በመጪው ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተዘጋጅቷል፥ ሰልፉም የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል በሚገኘው ታላቁ የዋልድባ ገዳም አካባቢ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ፣ የፓርክ ይዞታ፣ እንዲሁም የመንገድ ጥርጊያ እሰራለሁ በሚል ሰበብ የዋልድባ ገዳም ይዞታን የተለያዩ ከባድና ቀላል የእርሻ መሳሪያዎችን በመጠቀም አጽመ ቅዱሳንን በማፍለስ፣ ቦታውንም በዶዘር በማረስ መጠነ ሰፊ የሆነ የጥፋት ዘማቻ ከጀመረ ውሎ አድሯል፤ ቦታው የመድኃኒዓለም ስም የሚወደስበት የሚሰለስበት ቅዱስ ቦታ ነው ያሉ ገዳማውያኑም አቤቱታቸውን ከማይፀብሪ አውራጃ እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ብሎም በመንበረ ፖትሪያሪኩ ጽ/ቤት ድረስ አቅርበው ነበር ነገር ግን ሰሚ ሊያገኙ አልቻሉም። ለዚህም ነው ድምጻቸው ድምጻችን ነው፣ አቤቱታቸው አቤቱታችን ነው፣ መገፋታቸው መገፋታችን ነው ያልን በተለያዩ ዓለማት የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆንን በሃገር ውስጥ የገዳማውያኑን አቤቱታ ሊሰማ የፈቀደ ከመንግሥትም ከቤተክህነቱም ስለሌለ እኛ ልጆቻቸው አቤቱታቸውን ለዓለም ሕብረተሰብ ማሰማት ይኖርብናል በሚል ቅን ሀሳብ በመጪው ግንቦት ፳፯ የመድኅኒዓለም እለት በተለያዩ የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለማሳወቅ የምንወጣው፥ 
በኢትዮጵያ ሀገራችን የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ከገዳማውያኑ ጋር የዓላማ አንድነታችንን ለማሳየት፣ ይልቁንም እንደሻማ ቀልጠው ብርሃን ለሆኑት ለክርስቶስ ፍቅር ብለው በረሃ ለበረሃ ለተቅበዘበዙት አባቶቻችን መነኩሳት በዚሁ እለት የመድኅኒዓለም እለት የመድኀኒዓለም ታቦት ባለበት ቦታ ሁሉ አባቶች፣ እናቶች፣ እህቶች፣ ወንድሞች በአንድነት በፍቅር ሆነን እነዚህን ሦስት መዝሙራት እየዘመርን የአላማ አንድነታችንን እንድናሳውቅ መልክታችንን በመላው የኢትዮጵያ ለሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ ያስተላልፉን።
በአዲስ አበባ (ቦሌ መድኅኒዓለም)፣ በመቌሌ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ በደሴ፣ በሸዋ፣ በደብረዘይት፣ በናዝሬት፣ በነቀምት፣ በአርዚ፣ በሐዋሳ፣ በዲላ፣ በይርጋለም፣ በኢሉባቡር፣ በጅማ፣ በሐረር፣ በድሬደዋ፣ በይርጋለም፣ በሻሸመኔ፣ በአባ ምንጭ፣ እና በደብረብርሃን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከተሞች በሙሉ በሚገኙ የመድኀኒዓለም ደብር በሙሉ በግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. 


፩ኛ/ "ማርያም ሐዘነ ልቦና ታቀላለች"
፪ኛ/ "መድኀኒዓለም አዳነን በማይሻር ቃሉ"
፫ኛ/ "ኀይል የእግዚአብሔር ነው"


ማሳሰቢያ: ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፍፁም ሰላማዊ ናትና መርኃ ግብሩሰላማይሆን ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ገዳማቶቿን በቸርነቱ ይጠብቅልን !!!

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ጊዚያዊ 

ኮሚቴ
ሰሜን አሜሪካ

Monday, May 14, 2012

ለአሜሪካን ነዋሪዎች የሰላማዊ ሰልፍ ቦታዎች
በJune 4, 2012 ለተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ከተለያዩ የአሜሪካን ከተሞች ለምትመጡ የሰላማዊ ሰልፉ እድምተኞች በተጠቀሱት የስቴት መሰረት የትራቭል አሬንጅመቶችን ከአሁኑ እንድታደርጉ በቅድሚያ እናስገነዝባለን። የስቴት ተወካዮችም ዝግጅታችሁን በዚሁ መሰረት እንድታደርጉ በቅድሚያ ለማስገንዘብ እንወዳለን።
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያ ሃገራችንን እና ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን በረደኤት ይጠብቅልን አሜን።

Sunday, May 13, 2012

ስለታላቁ ዋልድባ ገዳም የውይይት መድረክ በሳንዲያጎ ካሊፎርኒያ


በሳንዲያጎ ካሊፎርኒያ የሚገኘው ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ጊዚያዊ የሳንዲያጎ ንዑስ ኮሚቴ ስለ ታላቁ ገዳም ዋልድባ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ስለ ቀጣዩ June 4, 2012 ሰላማዊ ሰልፍ ለመወያየት በMay 16, 2012 ታላቅ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል። የሳንዲያጎ እና አካባቢው ነዋሪዎች በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ ተገኝተው የዚህ ታሪካዊ ገዳም ለመታደግ የበኩልዎን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ በትህትና እንጠይቃለን።


አድራሻው 
Christ Methodist Church 
3295 Meade Ave.
San Diego, CA 92104


ቀን: ግንቦት ፰ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. (May 16, 2012)
ሰዓት: ከ4:45pm. ጀምሮ

በበለጠ ለመረዳት: 
619-792-2048
619-817-1378
619-829-6199 
savewaldba@gmail.com 


Friday, May 11, 2012

የዋልድባ እንታደግ ዓለም አቀፍ ንዑስ ኮሚቴ የሳን ሆዜ ብራንች ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደብዳቤ ላከዋልድባን ለመታደግ ከተቋቋመው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ የሳን ሆዜ ንዕስ ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ የአቋም መግለጫ ፳፩ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ልከዋል። የሳንሆዜ ንዕስ ኮሚቴ በዚሁ በተጠቀሰው ቀን በሳንሆዜ እና ኦክላንድ ተዋሪዎችን ስብሰባ ጠርቶ መጠነ ሰፊ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብር ማዘጋጀቱ ይታወሳል በዚሁ ዕለትም ለበርካታ የሁለቱ ከተማ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥት በልማት ሰበብ እያደረሰ ያለውን የሃይማኖት ማጥፋት እና የድንበር መጋፋት በሃይማኖታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ እና ክብር ያለው የዋልድባ ገዳም መነካቱ (መደፈሩ) በእጅጉ የከተማውን ነዋሪዎች እንዳስቆጣና ለዚህም ደግሞ መንግሥት ከሃላፊነት እንደማያመልጥ ጠቁመዋል። የሁለቱ ከተማ ነዋሪች እየተሰራ ያለውን የስኳር ልማት ፕሮጀክት በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቀዋል።


የደብዳቤውን ሙሉ ቃል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Tuesday, May 8, 2012

ስለታላቁ ዋልድባ ጉዳይ ደብዳቤዎች ለቅ/ሲኖዶስ እና ለጠ/ሚኒስትሩ ተላኩለአቶ መለስ ዜናዊ
ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ

ጉዳዩ  ፦  ታሪካዊ  የዋልድባ ገዳማችን ይዞታና  የመነኮሳት ሰብዓዊ መብት  እንዲከበርልን  ስለመጠየቅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ለኢትዮጵያ ታሪክ ማኅበራዊና ሥነ- ጥበብ እድገት ያበረከተችው  አስተዋጽዖ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም የሚታወቅ አውነታ ነው ። ቤተ ክርስቲያናችን ባላት  ታሪክና መንፈሳዊ  ሀብት ለበርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትልቁን ድርሻ የምትይዝ ሲሆን  በዚህም መንግሥትንና የተለያዩ ተቋማትን ተጠቃሚ እያደረገች ስትገኝ ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶችም በዋነኛነት የቤተ ክርስቲያናችንን  ጥንታዊያን ገዳማት አድባራት እና እንደ ጥምቀት መስቀል/ደመራ/ እና ልደት የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት መንፈሳዊ  አከባበርን ለመመልከት እንደሚመጡ   ዘወትር የሚመሰክሩት ነው ።  በአጠቃላይ  ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ  ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ጥበብ እድገት ያበረከተችውን አስተዋጽዖ በየትኛውም ዘመን የነበረ እና ወደፊትም የሚኖር  በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ይዘነጋዋል ብለን አንጠብቅም። በተለይም አሁን አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው መንግሥት  የባህልና ቱሪዝም ኮሚሽንን የበለጠ አጠናክሬ እሰራለሁ ብሎ በተነሳበት ፤ በዚህ ሰዓት  የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሆነባትን ቤተ ክርስቲያን ገዳማቷ እና  አድባራቷ እንዲጠበቁ ማድረግ  መንግሥታዊ  የአስተዳደር ኃላፊነቱ ነው ።

Sunday, May 6, 2012

ማስታወቂያ ክተት ወደ ዋልድባ!

በመላው ዓለም ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ!
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ሀገራችን የሚገኙት ገዳማቶቻችን በተለያየ ጊዜ የሚደርስባቸው የተለያየ እንግልት፣ ጥፋት፣ ቃጠሎ፣ ስደት
ድብደባ እንደቀጠለ ነው፥ ይልቁንም በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ መንግስት ሆን ብሎ ታሪክን እና ሃይማኖታችንን ለማጥፋት ከውጪ
ሃይሎች ጋር በመተባበር በዋልድባ ገዳም አካባቢ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ልማት፣ የፖርክ ይዞታን ለመከለል በሚል ሰበብ በዋልድባ
ገዳም ላይ ሥራውን ከጀመረ ወሎ አድሯል። በዚህ ሰበብ በገዳማውያኑም ላይ የተለያየ ድብደባ፣ ማሳደድ፣ ጥፋት፣ እንግልት፣ ማስፈራራት እያደረሰ ይገኛል። እኛም በመላው ዓለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ትተን ስለአዲት ሃገራችን
 እና ሃይማቶታችን መጥፋት ግድ የሚለን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ታላቅ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ በመጨው ግንቦት
                  ፳፯ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. (June 4,2012)
 በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሰላማዊ ትዕይንት በማድረግ መላው ሰላም ወዳዱን የዓለም
ሕዝብ በሃገራችን እና በገዳማቾቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ የማጥፋት ዘመቻ ስለምናሳውቅ፤ በመላው ዓለም የምትገኙ
ትውልደ ኢትዮጵያውያን  ለዚህ ሃገራዊና  ሃይማኖታዊ ጥሪ መልካም ምላሽ እንደምትሰጡ እምነታችን ነው።

Thursday, May 3, 2012

የአለኝታ ድምፅ ለታላቁ የዋልድባ ገዳም ከሳንሆዜ ምእመናን


የአለኝታ ድምፅ ለታላቁ የዋልድባ ገዳም ከሳንሆዜ ምእመናን
የሳንሆዜ ኢትዮጵያውያን ውይይት አደረጉ
ሚያዚያ 21 ቀን 2004 ዓ.ም በሳንሆዜ ካሊፎርኒያ ከተማ የምንገኝ የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ምእመናን በወቅቱ የታላቁ፣ የቅዱሳን አበውና  ሊቃውንት መፍለቂያ በሆነው ገዳማችን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት አድርገናል። በውይይቱም ላይ በከተማችን ከሚገኙ  አብያተ ክርስትያናት  በርካታ ቁጥር ያላቸው ምእመናን ተሳትፈዋል።
በውይይቱም ወቅት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ተግባራት ተከናውነዋል።
1.      ቅድስት ቤተክርስትያናችን ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ የገጠሟትንና እየገጠሟት ያሉትን ፈተናዎች የዳሰሱ ሪፖርት ቀርቧል።
2.     የታላቁን ገዳማችንን ታሪክና የቅዱሳን አባቶቻችንን ህይወትና ስራዎች የሚያሳይ ታሪካዊ ፊልም ታይቷል።
3.     በመንግስትና በቤተክህነት የወልቃይቱ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክትን በሚመለከት በመገናኛ ብዙሃን የተላለፉ መልእክቶችንና ከገዳሙ አባቶች የተሰጡትን መረጃዎች የሚተነትን ሪፖርት ቀርቧል።
4.     የቤተክርስትያናችንን ፈተናዎችና ሀይማኖታዊ ቅርሶች የሚዳስስ እጅግ አስተማሪ የሆኑ መነባንቦች ቀርበዋል።
5.      የዋልድባን ገዳም በአካል የሚያውቁና በቦታው ተገኝተው በረከት ለማግኘት የታደሉ ወንድሞች ስለቦታው ታላቅነት ምስክርነት ሰጥተዋል።
6.      ቅድስት ቤተክርስትያናችን ለአገራችን ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ያበረከተችውንና እያበረከተች ያለውን አስተዋጽዖ የሚዳስስ አጭር መልእክት ተላልፏል።
ከነዚህ መርሃ ግብራት በሁዋላ በጨዋነትና በጽሞና የተላለፉትን መልእክታት ሲከታተል የቆየው ምእመን  ውይይት አድርጓል። 

(ሰበር ዜና) የዋልድባ ገዳም ተመዘበረ!!


·  የገዳሙ ዕቃ ቤት በሮች ተሰባብረው 65,000 ብር ተዘርፏል፤ ሙዳየ ምጽዋት እና የመጻሕፍት መያዣ ሣጥኖች ተገለባብጠዋል፤ አርድእቱ ተንገላተዋል
·  የማይ ፀብሪ ወረዳ ፖሊስ “እናንተው ራሳችኹ ኾነ ብላችኹ የፈጠራችኹት ችግር ቢኾንስ” በሚል መነኰሳቱን ተዳፍሯል
·      ሕዝቡ በዛሬማ አቅጣጫ ወደ ፕሮጀክቱ ቦታ መትመሙን እንደቀጠለ ተገልጧል
 (ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 25/2004 ዓ.ም፤ May 3/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ከዋልድባ ገዳም ዕቃ ቤት እና የአትክልት ቦታ ይዞታዎች አንዱ የኾነው ማይ ለበጣንት፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2004 ዓ.ም ሌሊት ማንነታቸው ባልታወቁ ኀይሎች መመዝበሩ ተገለጸ፡፡

አምላክ ሆይ ተለመነን!
የገዳሙ መነኰሳት ለዜና ሰዎች እንደተናገሩት÷ መዝባሪዎቹ ማይ ለበጣ ወደሚገኘው የገዳሙ ዕቃ ቤት የገቡት መንፈቀ ሌሊት ላይ ነው፡፡ ለሁለት ሰዓት ያህል ፍራውን ድራሽ አምላኩን እያጠፉ የቆዩት እኒህ አፍራሽ ወራሪዎች አርድእቱንና መነኰሳቱን አግተው ከዕቃ ቤቱ ስድስት በሮች ሦስቱን በመሰባበር ለኑግ መግዣ የተቀመጠውን ብር 65,000 ዘርፈዋል፤ ከቦታው ሞቃታማነት የተነሣ በሜዳው የዕንቅልፍ ዕረፍት ላይ የነበሩትን ዐሥር አርድእት ቤት ውስጥ አስገብተው ከዘጉባቸው በኋላ “የምንፈልገው ሰው አለ” በሚል ፊታቸውን በባትሪ ብርሃን እያዩ አንገላተዋቸዋል፡፡
ስለ ዘራፊዎቹ አኳኋን እንዲገልጹ የተጠየቁት አንድ አባት፣ “ቁጥራቸው ከ5 - 7 ይሆናሉ፤ በአለባበሳቸው ሚሊሻ ይመስላሉ፤ እንዳንለያቸው ፊታቸውን በጨርቅ ሸፍነውታል፤ ያልከፈቱት ሙዳየ ምጽዋትና መጻሕፍት መያዣ ሣጥን የለም” በማለት አስረድተዋል፡፡
መዝባሪዎቹ ስፍራውን ለቀው ከሄዱ በኋላ ከመነኰሳቱ ለማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳደር በስልክ በተገለጸው መሠረት ዛሬ ጠዋት ወደ ማይ ለበጣ የመጡት ሓላፊዎች “እናንተው ራሳችሁ ኾነ ብላችኹ የፈጠራችሁት ችግር ቢኾንስ” በሚል መነኰሳቱን መዳፈራቸው ተዘግቧል፡፡
ባለሥልጣናቱ ወደ ማይ ለበጣ በመጡበት መኪና ወደ ወረዳው የፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ ያመሩት ገዳማውያኑ ኹኔታውን በዝርዝር በማስረዳት ማመልከታቸውንና “ጉዳዩን እንከታተለዋለን” የሚል ምላሽ ብቻ ተሰጧቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
 

Wednesday, May 2, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ ጉዳይ ከፓትርያሪኩ እና ከመንግሥት ጋራ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።


ማኅበሩ የወልቃይት ስኳር ፕሮጀክት በዋልድባ ገዳም ላይ ስለሚያደርሰው ተጽዕኖ ያጠናቀረውን ሪፖርት አስመልክቶ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል::


"እስከ 20 ሄ/ር የገዳሙ መሬት በግድቡ ውኃ ይሸፈናል፤ ፕሮጀክቱ የገዳሙን 40% የምርት ገቢ 60% የምእመናን ድጋፍ ያሳጣዋል" (የማኅበሩ አጥኚ ቡድን ሪፖርት)::


ማኅበሩ የፕሮጀክቱ አካባቢ ከሚለወጥበት እስከ ዲዛየን ማሻሻያ የሚደርስ የጥናት አማራጭ እንዲያቀርብ፣ ገዳማውያኑ ስለ ፕሮጀክቱ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ተጽዕኖ ያላቸው ሐሳብ የሚደመጥበት አቋማቸውንም ያለጫና የሚያሳውቁበት መድረክ እንዲያመቻች ተጠይቋል::


የስኳር ኮርፖሬሽኑ በፕሮጀክትና ፋብሪካ ማኔጅመንት የአቅም ማነስ ችግር እንዳጋጠመው አስታውቋል::


"ወደ ፕሮጀክቱ ትግበራ ከመግባታችን አስቀድሞ መነኰሳቱን እንደ መንግሥት በአለማነጋገራችን አጥፍተናል፤ እነርሱን [የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳትን] ማማከር ነበረብን፡፡" (የፕሮጀክቱ ሓላፊዎችና የወረዳው ባለሥልጣናት)::


"መንግሥት የፕሮጀክቱን የጥናት ሰነዶች ይፋ ያድርግ" (አንድ የኢንቫይሮመንታል ዲዛይን ምሁር)::

(ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 19/2004 ዓ.ም፤ April 27/2012)፦ መንግሥት በክልል ትግራይ ምዕራባዊ ዞን ወልቃይት ወረዳ በሚገኘው የዛሬማ፣ ዱቁቆ እና ተከዜ ሸለቆ በሚያካሂደው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት የተነሣ ከአገራችን ታላላቅና ቀደምት ቅዱሳት መካናት አንዱ በኾነው በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ የተጋረጠው አደጋ ለብዙኀን መገናኛ ዘገባ ከዋለ ድፍን ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡

የዋልድባ ገዳም ክብርና ህልውና ሊደፈር አይችልም!


በዋልባ ገዳም ክብር በኛ ጊዜ ሊደፈር አይችልም በሚል ከሰሜን ጎንደር ጃናሞራ፣ ጃኖራ፣ ቆላ ወገራ፣ ጠገዴ፣ አርማጮሆ፣  ካንግ፣ ሻግኔ የሚባሉ የሰሜን ጎንደር ክልል ነዋሪዎች ስንቃቸውን በአህያ በመጫን መሳሪያ ያለው መሳሪያውን፣ የሌለው ዶማ፣ አካፋ፣ መጥረቢያ፣ የመሳሰሉትን በመያዝ መንግስት ግድብ እገድባለሁ ብሎ ሥራውን በጀመረበት ቦታ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ቦታው ሊሠራ የተጀመረውን ሥራ እናፈርሳለን በማለት ወደ አካባቢው ሄዷል፣ መንግስትም የመከላከያ ሠራዊቱን ወደ ኃላ አፈግፍግ ብሏል ለጊዜው። የአካባቢው ነዋሪዎችም ሥራው ሙሉ ለሙሉ ካልቆመ ወደቤታችን አንመለስም ሥራውንም ለማቆማቸው የምናውቀስ በሥራ ላይ ያሉ ሁለት ትላልቅ ጀነሬተሮች እስካላቆሙድረስ ችግር ሊፈጠር ይችላል በማለት መንግስም ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ድርድር ለመጀመር ሥራዎችን የጀመሩ ይመስላል የደባርቅ እና የአድርቃይ እንዲሁም የማይጸብሪ አስተዳዳሪዎች ችግሮችን ለመዳኘት ሙከራ እየተደረገ ነው።
እግዚአብሔር ቸር ያሰማን
የገዳማችን ክብር እና ህልውና መደፈር የለበትም!