Sunday, May 20, 2012

በብዙ ጫና ውስጥ ያለው ማ/ቅዱሳን መንግሥት በዋልድባ አካባቢ ስለሚገነባቸው ፕሮጄክቶች ሪፖርቱን አቀረበ  •    ሪፖርቱ የጠ/ቤተ ክህነት ሓላፊዎች “አቀረብን” ካሉት በይዘትም በተአማኒነትም የተሻለ ነው።
(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 10/2004 ዓ.ም፤ May 18/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ማ/ቅዱሳን መንግሥት በዋልድባ አካባቢው ሊሠራው ስላቀደው ግዙፍ ሮጄክት “አጠናሁት” ያለውን ሪፖርት አቀረበ፤ ከመንግሥት ጋር መነጋገሩንም ገለጸ። ዛሬ ይፋ የተደገው የማኅበሩ ሪፖርት የቤተ ክህነቱ አዳዲስ ተሿሚዎች ማኅበሩን በዋልድባ ጉዳይ በከሰሱ ማግስት የቀረበ ሲሆን ለእነርሱ ክስ የተሰጠ አፋጣኝ ምላሽ ይሁን አይሁን ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

አዲስ የተሾሙት የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ኃላፊ መምህር ዕንቁ ባሕርይ ተከስተ “በዋልድባ አካባቢ መንግሥት ሊሠራ ያቀደውን ግዙፍ የስኳር ፋብሪካን በማስመልከት በዋልድባ ይዞታ ላይ ያደረሰው ተጽእኖ መኖር አለመኖሩን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ተፈላጊውን የማጣራት ሥራ አከናውኖ” ከተመለሰ በኋላ “ጋዜጣዊ መግለጫ መሰጠቱና … የማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጠኞች መከታተላቸው መሣተፋቸውና የሚፈልጉትን ጥያቄ በይፋ አቅርበው ምላሽ መሰጠቱ”ን ጠቅሰው “ማንኛውም ጋዜጠኛ በተለይም ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሣን የሆነው የማኅበሩ ጋዜጣና መጽሔት መረጃ ከወሰደ በኋላ መግለጫውን አለማውጣቱ አግባብነት የሌለው ከመሆኑም በላይ የሚዲያ ሥነ ምግባርንም ያልተከተለ ስለሆነ” ጽሑፉ ያልወጣበትን ምክንያት ማኅበሩ በጽሑፍ ይገልጽ ዘንድ ከሕዝብ ግንኙነት መምሪያ መታዘዛቸውን እንዳብራሩ መዘገባችን ይታወሳል።
የመምሪያው ደብዳቤ “ጋዜጣዊ መግለጫውን በሚዲያ ለማውጣት ተስማምታችሁ ሪፖርት እንድታደርጉ ከወሰናችሁ በኋላ ዘገባው የቀረበት ምክንያት በጽሑፍ ለማደራጃ መምሪያው” እንዲመለስ እንደሚጠብቅ በመግለጽ “ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎትና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን” ግልባጭ ተደርጓል። ደጀ ሰላምም “የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እና ሕግ አገልግሎት መምሪያ የቤተ ክርስቲያናችን አካላት ስለሆነ በቀጥታም ባይሆን ጉዳዩ ሊያገባቸው ይችላል። ከላይ ስማቸው የተዘረዘሩት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በምን አግባብ ነው ስለ አንድ ማኅበር፣ ያውም በአንድ መምሪያ ሥር ስላለ አካል ግልባጭ የሚደረግላቸው? መንግስታዊ መሥሪያ ቤቶቹ ከሚዲያ ጋር የተገናኙ እንኳን ቢሆኑ በግድምድሞሽ “ግንኙነት አላቸው” ይባል ይሆናል። ፌዴራል ጉዳዮች፣ ደኅንነት፣ ፖሊስ … መጠቀሳቸው ለምን ያስፈልጋል? እሰሩልን፣ ግደሉልን፣ ቀፍዱድልን ለማለት ካልሆነ” ማለቷ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ማኅበሩ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የዋልድባ አጥኚ ቡድን ሪፖርት እጥር ምጥን አድርጎ አቅርቧል። ከመንግሥት ከቤተ ክህነትም መልስ ለሚፈልጉ ሰዎች የየድርሻቸውን በመስጠት ከነገሩ ጦም እደሩ ለማለት ሞክሯል። ከሀ-ሠ በተዘረዘሩ ዐበይት ዐዕማድ ርዕሶች የተዘረዘረው ሪፖርቱ ከአጠቃላይ ዳራ (Background) በመጀመር በማጠቃለያ ይፈጽማል። እነዚህም ሀ “ዳራ”፣ ለ “ዋልድባ ገዳምና አካባቢ ከመንፈሳውያት ተቋማት አንጻር” ፣ ሐ “በቅዱሱ ቦታ ድንበርና አካባቢ ስለሚገነባው ፕሮጄክት አጠቃላይ ዳሰሳ”፣ መ “ፕሮጄክቱ ላይ ገዳማውያኑ ያነሡአቸው ጥያቄዎችና የልዑካኑ ዕይታ”፣ ሠ “ማጠቃለያ” ናቸው።
ማኅበሩ በመንደርደሪያው ጉዳዩ ብዙ ወገኖችን ያነጋገረ፣ ያከራከረ መሆኑን ጠቅሶ “የጉዳዩን ምንጭ እና መፍትሔ ነጣጥሎ ማየት እስከሚከብድ ድረስ በሰው ልቡና ሲመላለስ ቆይቷል” ይላል። ምንጩን እና መፍትሔውን ለምን ለያይቶ ማየት እንደሚያስፈልግ አላብራራም። መፍትሔው የሚመጣው ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ከሚደረግ ጥረት መሆኑን (የcause and effect ግንኙነት) የዘነጋው ይመስላል።
ቀጥሎም “ከመጋቢት 25-30 ቀን 2004 ዓ.ም አምስት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ወደቦታው” ተልኮ እንደነበር፤ “በቦታው በመገኘት ሁሉንም አካላት ማለትም የገዳሙን አባቶች፣ የፕሮጄክቱን ሓላፊዎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማነጋገር ያገኘውን ምላሽ ከልዑካኑ ዕይታ ጋር በመጨመር ሰፋ ያለ ሪፖርት ይዞ” መመለሱን ጠቅሶ የማኅበሩ አመራር አካልም ሪፖርቱን “ከሰማ በኋላ፣ ከልዩ ልዩ አቅጣጫዎችና ተጨማሪ መረጃዎች ጋር በመመርመር” እንዳጸደቀው ይተርካል።
የማኅበሩ አመራር የቀረበለትን መረጃ “ከልዩ ልዩ አቅጣጫዎች” ማየቱ መልካም ቢሆንም  ከጠ/ሚኒስትሩ ንግግር እስከ መምህር ዕንቁ ባሕርይ ደብዳቤ ድረስ ማኅበሩ ከባድ ጫና ውስጥ መግባቱን ለሚያውቅ ማንኛውም ወገን ማለትም በመንግሥት ዘንድ “ሞገስ ያገኙት” ተሐድሶዎች እና ብሎጎቻቸው በተደጋጋሚ ሲሉት እንደነበረው መንግሥት በዋልድባ ዙሪያ የሚያካሒደውን “ፕሮጄክት” ለመቃወም በመላው ዓለም የተነሣው እንቅስቃሴ መሪ “ማኅበረ ቅዱሳን እንደሆነ” ተደርጎ መዘገቡ፣ ከአቦይ ስብሐት ጀምሮ ሌሎች የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጣታቸውን በማኅበሩ ላይ መቀሰራቸውን ለሚገነዘብ ሁሉ ሪፖርቱ በነጻነት የተዘጋጀ ነው ለማለት ይከብዳል። ለዚህም ፍንጭ የሚሰጠው በማጠቃለያው ላይ “ማኅበሩ በወልቃይት እየተገነባ በሚገኘው የስኳር ፕሮጄክትና በግድቡ ዙሪያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አጥንቶ ያዘጋጀውን ሪፖርት ከሚመለከተው ከፍተኛ የመንግሥት አካል ጋር ውይይት አድርጎ ነበር” የሚለው ዐቢይ ዐረፍተ ነገር ነው።
ጥናቱ በገዳሙ እና በመንግሥት መካከል ያለውን አለመግባባት ተመርኩዞ የተደረገ እስከሆነ ድረስ፣ ማኅበሩም በገለልተኝነት እና በሃይማኖታዊ ተቆርቋሪነት ነጻ እና ሙያዊ ትንተና ለመስጠት የፈለገ ከመሆኑ አንጻር ሪፖርቱን ሚዛናዊና ነጻ በሆነ መልክ ይፋ ከማድረጉ በፊት ለአለመግባባቱ አንድ አካል ማለትም ለመንግሥት “ከፍተኛ አካል” ቀድሞ ካቀረበ ምኑን “ነጻ ሪፖርት” ሆነው? “ከፍተኛ አካል” የሚለው በራሱ ከፍተኛነቱ ከትከሻ እስከ ራስ ድረስ ምን ያህል ከፍ እንዳለ ግልጽ ባይሆንም ሪፖርት አቅራቢው ክፍል ይህንን ሁሉ “ከፍተኛነት” ተቋቁሞ ለማለፍ አቅሙ እስከምን እንደሆነ ለማወቅ ይቸግራል።
የከፍተኛ ባለሥልጣኖችን አስፈሪ ግርማ ተቋቁሞ እውነቱን ብቻ በመናገር በኩል የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች ተፈትነው እንደወደቁ እናውቃለን። ከፓትርያርኩ እስከ ሌሎች አባቶች ድረስ ባለሥልጣናቱን ከመላእክት ባልተናነሰ እንደሚያከብሯቸው እና እንደሚፈሯቸው እናውቃለን። የማኅበረ ቅዱሳን ሪፖርት አቅራቢዎችና አመራር አካላት ይህንን የባለሥልጣናት “ግርማ” እና ውስጠ-ዘ መመሪያ ተቋቁመው “ነጻ ሪፖርት” ለማቅረብ ችለው ይሆን? ሪፖርቱ “ሐሰት” እንደሌለበት ብናምንም “ከእውነታው ላለመቆንጸሉ” ግን እርግጠኞች አይደለንም። ስለዚህም ይህ ሪፖርት ምን አዲስ ነገር ነገረን ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። “አዲስ ነገር” ካልነገረን ደግሞ የቀረ ነገር መኖሩን እንጠረጥራለን። ያ የቀረው ነገር ምንድነው? ይዋል ይደር እንጂ መውጣቱ አይቀርም።
በጎ ጎኑን ከተመለከትን ሪፖርቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች “አቀረብን” ካሉት በይዘትም በተአማኒነትም የተሻለ ነው። ለውይይት ጥሩ መነሻ  ይሆናል። መንግሥት ያዘጋጀውን ጥናት በአጭሩ ማቅረቡም ጥሩ ነው። የገዳሙን ታሪክ እና ማን ምን እንደሆነ ማብራራቱም በዋልድባ ጉዳይ የሚኖረን ውይይታችን መሠረት ያለው እንዲሆን ይረዳል። ፎቶዎቹ፣ ካርታዎቹ እና ዳሰሳዎቹ ጥሩ “ዳራ” ይሰጣሉ። ከዚህ የሚቀረው ፈረንጆቹ (reading between the lines) እንደሚሉት ከተጻፈው የማኅበሩ ሪፖርት ላይ በመመርኮዝ ያልተጻፈውን፣ አጠይሞ ያለፈውን እና ሳይናገረው በጥቅሻ ብቻ ያለፈውን ማብራራት ነው። እንዳለመታደል ሆኖ “ነጻ አስተያየት” የሚሰጡ አካላት የሚደቆሱበት አገር ስለሆነ ከማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በላይ መጠበቅ “ግፍ” ሊሆን ይችላል። ጭራሹኑ “እሳት ውስጥ” ግቡልን እኛ ዳር ቆመን እናያለን ከማለት እንዳይቆጠርብን፣ ያንንም ለማለት “ሞራላዊ ብቃታችን” ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ በሪፖርቱ ባንረካም “መቸስ ምን ይደረግ፣ አገሩ ኢትዮጵያ ሆነ” ከማለት ውጪ።
በጠቅላላው ሪፖርቱ አዲስ የውይይት በር ከመክፈት በስተቀር የተከፈተውን የተቃውሞ እና የውይይት በር የሚዘጋ እና እልባት የሚሰጥ ሊሆን አይችልም። ተቃውሞውም ይቀጥላል፤ ውይይቱም ይቀጥላል። አጭሩ መፍትሔ መንግሥት የጀመረውን ነገር ማቆም ብቻ ነው። ይዋል ይደር እንጂ መቆሙ ግን አይቀርም። ያለ ሕዝብ ተቀባይነት የሚጀመር ነገር መረሻው ምን እንሆነ በታሪክ እናውቃለን፤ በአገራችንም አይተነዋል። ደርግ መንደር ምሥረታ አለ፣ ልማት አለ፣ ገበሬውን ሰበሰበ … ለውድቀቱ ምክንያት ሆነ፣ መንደሩም ተበተነ፣ ልማቱም እንደቆመ ቀረ። ይኼኛውስ ምን የተለየ ያደርገዋል?

READ THE REPORT IN PDF

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤