Thursday, May 3, 2012

የአለኝታ ድምፅ ለታላቁ የዋልድባ ገዳም ከሳንሆዜ ምእመናን


የአለኝታ ድምፅ ለታላቁ የዋልድባ ገዳም ከሳንሆዜ ምእመናን
የሳንሆዜ ኢትዮጵያውያን ውይይት አደረጉ
ሚያዚያ 21 ቀን 2004 ዓ.ም በሳንሆዜ ካሊፎርኒያ ከተማ የምንገኝ የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ምእመናን በወቅቱ የታላቁ፣ የቅዱሳን አበውና  ሊቃውንት መፍለቂያ በሆነው ገዳማችን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት አድርገናል። በውይይቱም ላይ በከተማችን ከሚገኙ  አብያተ ክርስትያናት  በርካታ ቁጥር ያላቸው ምእመናን ተሳትፈዋል።
በውይይቱም ወቅት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ተግባራት ተከናውነዋል።
1.      ቅድስት ቤተክርስትያናችን ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ የገጠሟትንና እየገጠሟት ያሉትን ፈተናዎች የዳሰሱ ሪፖርት ቀርቧል።
2.     የታላቁን ገዳማችንን ታሪክና የቅዱሳን አባቶቻችንን ህይወትና ስራዎች የሚያሳይ ታሪካዊ ፊልም ታይቷል።
3.     በመንግስትና በቤተክህነት የወልቃይቱ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክትን በሚመለከት በመገናኛ ብዙሃን የተላለፉ መልእክቶችንና ከገዳሙ አባቶች የተሰጡትን መረጃዎች የሚተነትን ሪፖርት ቀርቧል።
4.     የቤተክርስትያናችንን ፈተናዎችና ሀይማኖታዊ ቅርሶች የሚዳስስ እጅግ አስተማሪ የሆኑ መነባንቦች ቀርበዋል።
5.      የዋልድባን ገዳም በአካል የሚያውቁና በቦታው ተገኝተው በረከት ለማግኘት የታደሉ ወንድሞች ስለቦታው ታላቅነት ምስክርነት ሰጥተዋል።
6.      ቅድስት ቤተክርስትያናችን ለአገራችን ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ያበረከተችውንና እያበረከተች ያለውን አስተዋጽዖ የሚዳስስ አጭር መልእክት ተላልፏል።
ከነዚህ መርሃ ግብራት በሁዋላ በጨዋነትና በጽሞና የተላለፉትን መልእክታት ሲከታተል የቆየው ምእመን  ውይይት አድርጓል። 

በውይይቱም ወቅት የወልቃይት የስኳር ፋብሪካ አካል የሆኑትን የግድብ ስራ፣ የሸንኮራ አገዳ ተክል እርሻ፣ የመስኖ ቦይ ስራ፣ የፋብሪካ ግንባታ፣ የመንገድ ስራ፣ የከተማ ምስረታ፣የፓርክ ግንባታ፣ የዘመናዊ እርሻ መሳሪያዎች መገጣጠሚያና ወዘተ ሁሉ በተናጠልም ይሁን በወል በገዳሙ ላይ የሚያደርሱትንና ሊቀለበሱ ወይንም ሊታረሙ የማይችሉ አደጋዎች ላይ ተወያይቷል። የእነዚህ ተቋማት ግንባታ የገዳሙን ድንበር እንደሚደፍርና ህልውናውንም አደጋ ላይ እንደሚጥል ተረድተናል። ከገዳሙ በተጨማሪ በገዳሙ አካባቢ ያሉ አብያተክርስትያናትም  ዝቅተኛ ትኩረት የሚሰጣቸውና ተራ-አብያተ ክርስትያናት ተብለው ሊጠሩ እንደማይገባና አብያተክርስትያናት በሙሉ የተቀደሱ ቦታዎች በመሆናቸው ፈጽሞ ሊፈርሱ እንደማይገባቸው ተገልጿል።
ስለዚህ የልማት ስራዎች  ሃይማኖታዊ ሉአላዊነታችንን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ መሆን እንደሌለባቸው አስረግጠው ገልጸዋል።
እንዲሁም ሁሉም ምእመናን ለዚህ ታላቅ ገዳም ህልውናና ክብር በአንድነት እንደሚቆሙ ገልጸዋል። ምእመናኑም የዋልድባ  ገዳም በምንም መልኩ ለድርድር የማይቀርብ  የህልውናችን መገለጫ መሆኑን አሳስበዋል። ስለሆነም መንግስት የጀመረውን የግንባታ ስራ በአስቸኳይ አቁሞ የልማት ስራውን ወደሌላ ቦታ እንዲያዘዋውረው  ጠይቀዋል።
በመጨረሻም የውይይቱን መንፈስና መልእክት የያዘ የአቋም መግለጫ ተዘጋጅቶ በንባብ ተሰምቷል። ይህም መግለጫ ለመንግስት እንዲላክ ተወስኗል። እንዲሁም በግልባጭ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በስደት ለሚገኙ አባቶች በሙሉ መልእክቱ እንዲተላለፍ ተወስኗል። በተጨማሪም በተለያዩ ቦታዎች ለሚገኙ የቅድስት ቤተክርስትያን ልጆች ለዚህ ታላቅ የሀይማኖታችን ሀብት፣ የቅዱሳን አበውና ሊቃውንት መፍለቂያ ለሆነው ገዳማችን ህልውናና ክብር መጠበቅ ድምጻቸውን በአንድነት ቆመው እንዲያሰሙ ጥሪ አድርገዋል። የገዳሙ ህልውና መከበሩን እርግጠኛ እስኪሆኑ ድረስ የሚደርገውን ጥረት እንደሚቀጥሉና ወደፊትም በአንድነት ድምጻቸውን ለመንግስትና ለአለም ለማሰማት በታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በንቃት ለመሳተፍና ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
                  የአባቶቻችን  አምላክ  የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር  ገዳማችንን ፣ አገራችንንና  ህዝቧን ይጠብቅልን። አሜን።

                                       አስተያየቶችን ከዚህ በታች በታየው የኢ-ሜይል አድራሻ ቢልኩልን ይደርሰናል።

                                                           Bayarea4waldba@gmail.com

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤