Wednesday, May 23, 2012

ወቅታዊ ግጥም


ተነስ!
ተነስ ከተኛህበት ንቃ
እምነታችን እንድትኖር ተጠብቃ
ያንቀላፋህ ቶሎ ንቃ
እምነትህ ላይ ፈተናዎች ተደቅነው
አህዛቡ ገዳማቱን ሲያቃጥለው
ዋልድባንም መንግስታችን ገብቶ ሲያርሰው
እስከመቼ ነው ዝም የምንለው?
በቃ! እንበል ዋልድባችን አይታረስ
ገዳማችንንም አታፍርስ!
ተነሳሁኝ አንተም ተነስ
እንባባል በአንድ መንፈስ።
ከአብነት ለወየሁ (ግንቦት 2004 ዓ.ም)



ለምን ይሆን ዝምታሁ?

ጥቁሩን ቆብ የደፋችሁ
የመከራውን መገለጫ ጥቁር ቀሚስ ለብሳችሁ
የማይገኘውን ክብር አግኝታችሁ
በመድረክ ላይ ሰብካችሁ
የጌታን ፍቅር መስክራችሁ
የሰማዕታትን ታሪክ ተናግራችሁ
ሰማዕት ሁኑ እያላችሁ
እንናንተ እንዳትሆኑ ምን ያዛችሁ?
ስታስተምሩ ስንሰማችሁ
መነኮሰ ሞተ ካላችሁ
እኮ የታል መሞታችሁ?
ወይስ እንደ ባሕርዛፍ መልሳችሁ አበባችሁ
የዚህች አለም ውጥንቅጧ እንቅ አድርጎ ያዛችሁ
አሁን ይብቃ አይታሰር ምላሳችሁ
ለስጋዊው ሞት አትፍሩ እንዳላችሁ
እኛም አትፍሩ ብለናል ልጆቻችሁ
በሉ እዘዙን እንስማችሁ
የገደማችሁባት ገዳም ተምር ያያችሁባት ቦታ
እንዴት በእናንተ ዝምታ ገዳማችን ይፈታ
በሉ እንጂ ተናገሩ ዝምታውን ስበሩት
አርምሞአችሁን አይተው ገዳማችንን ደፈሩት
በታሪክ ተወቃሽ ናችሁ በእኛ ዘመን ያላችሁ
ጥቁሩን ቀሚስ ለብሳችሁ ቃል ያልተናገራችሁ
መቼም ከእናንተ ነውና ቃሉን ከልቤ የሰማሁት
ያዕቆብ የኤሳውን ድርሻ ወስዶ በረከት እንዳገኘበት
እናንተም አፍ ላለው ሽጡት እምነቱን ይናገርበት።
ከአብነት ለወየሁ (ግንቦት 2004 ዓ.ም)

የግጥሙን ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤