Monday, May 28, 2012

ጉድ ሳይሰማ!


ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም፤

ዛሬም ጉድ ተሰማ ከዋልድባ ገዳም፤

ካባቶቼ ሃገር አበረንታንት ገዳም ።

ዛሬም ጉድ ተሰማ ከሰሜን ተራራ፤

ወልቃይት ጠገዴ ከቅዱሳን ጎራ፤

ጸለምት ማይ ፀብሪ በተራ በተራ።

በጌታ ቡራኬ በቅዱሳን ጸሎት፤

በርስት ያገኘነው ካበው ከቀደሙት፤

ላይጠፋ ዘላለም የገደሙት ገዳም፤

የህይወት ምንጭ ሆኖ የቆየው ለዓለም፤ምን ተገኘ ዛሬ ከዋልድባ ገዳም፤

ማረስ ያስፈለገ መንገዱን ማጣመም።

የገዳማት በኩር የቅዱሳን ዋሻ፤

ምንድነው ዝምታህ ስትታጭ ለርሻ።

አንተ ቅዱስ ስፍራ ጌታ የመረጠህ፤

ከምድራዊው ገነት ተራራው ስር ያለህ።

እህል አይግባብህ ሃጢያት አይሻገር፤

ብሎ ሲገዝትህ አምላክህ ሲናገር።

አልሰማህውም ወይ ዝምታህ በረታ፤

ሰንጥቀው ሲወስዱ ካለህበት ቦታ።

አይደል ለኢትዮጵያ ለመላው ዓለም፤

ጸሎትህ የበጀው ዋልድባ ገዳም።

እልፍ መነኮሳትን ጠልለህ ያስቀመጥክ፤

ህዝቡን እያማለድክ ለጌታ ያቀረብክ ።

ምነው ዝም አልክ ዛሬ ለሸንኮራ ሲያጩህ፤

በዋጋ ሊሸጡ ፊትህ ሲስማሙብህ።

ከማር የሚጣፍጥ ቃል አለቀብህ ወይ፤

ሊቃውንት ሰባኪ ልጅስ የለህም ወይ፤

ሸንኮራ ሊያበቅሉ የመጡብህ ከላይ።

ውለታህን ቆጥሮ አንትን የሚታደግ፤

ታሪክ አመስጥሮ ስላንተ የሚነድ፤

እንደሻማ ቀልጦ ብርሃኑን የሚሰጥ፤

ጠላት አሳፍሮ ምርኮ ሚገለብጥ።

አሳየኝ ልጅህን ዋልድባ ንገረኝ፤

አበረንታንት ጀምር ተስፋ አታስቆርጠኝ።

የቀደመው ታሪክ ሁሉም ተዘንግቶ፤

እልፍ መነኮሳት ያኖረው አስማማምቶ፤

ያ የገነንክበት ታሪክ ዳብዛው ጠፍቶ፤

ለሸንኮራ ሲያጩህ ልጅህ አንገት ደፍቶ።

ዝምታን መረጠ በአርምሞ ከተተ፤

እስኪመስል ድረስ ባንት የተገዘተ።

ዝቋላ ሲያለቅስ ሲውል እርቃኑን፤

አሰቦት ሲቃጠል ሊያስተዛዝን አንተን።

ማቃቸውን ለብሰው ሙሾ ሲወርዱልህ፤

የገዳማት በኩር ብለው ሲያዜሙልህ።

ልጅህ ግን ዝም አለ በአርምሞ ከተተ፤

እስኪመስል ድረስ ጥንት የተገዘተ።

የጣና ገዳማት ዝምታን መረጡ፤

አክሱም ጽዮን ማርያም ሃዘንም አልወጡ።

ታች ደብረሊባኖስ በዝምታ አለፈው፤

ቅዱስ ላሊበላም ነገሩን ረሳው።

አሁን ማነው ላንተ ዋስና ጠበቃህ፤

ንገረኝ ልንገረው እንዲሟገትልህ።

ሸንኮራ ሳይዘሩት አጽሙን ሳያፈልሱት፤

ዳብዛህን ሰውረው ወዝህን ሳያጠፉት፤

ደርሶ ቢታደግህ ከዚህ ሁሉ ጥፋት።

ንገረኝ ልንገረው እንዲሟገትልህ፤

ተጠብቆ እንዲኖር ርስትና ጉልትህ።

አንተዝም ብትል አርምሞን ብትመርጥም፤

ስላንተ ተሟጋች ቃል ባትናገርም።

እስካለሁበት ቀን ካልሞትኩ በስተቀር፤

አላይም ሲያፈርሱህ ሲያመርቱብህ ስኩዋር።

ድንበርህን አፍርሰው ወንዝህን ተሻግረው፤

መካናቱ ወድቀው ከማያቸው ፈርሰው።

አሁን እሄዳለሁ ስላንተ እዘምታለሁ፤

ቃልኪዳን ገባሁኝ እስከመጨረሻው እሰዋልሃለሁ።

እናንት ገበሬዎች ስኩዋሩን አልሚዎች፤

የኢትዮጵያ ገዢ አስተዳዳሪዎች።

ዛሬ ምን አያችሁ ከዋልድባ ገዳም፤

ካባቶቼ ርስት አበረንታንት ገዳም።

መሬቱን ልታርሱ ድንበር ልታፈርሱ፤

ቅርስ መዝብራችሁ ሰው ልታስለቅሱ።

ለምን ደፈራችሁ ነገሩኝ ሚስጥሩን፤

ልቤም አይሸበር ልረዳ ነገሩን።

ታሪክ አታውቁም ወይ ነጋሪስ የለም ወይ፤

ከእግዜር ጋር መጣላት አያሳፍርም ወይ።

የቀደሙት ሁሉ ከመንገድ የወጡት፤

ከወንበራቸው ላይ የተገለበጡት፤

ከክብር ወደታች በግፍ የወረዱት።

የእግዚአብሄርን መንበር ሲገዳደሩት ነው፤

ቅዱሳን አበውን ሲያስጨንቁዋቸው ነው።

አሁንም ልምከርህ አንድም ብለህ ጀምር፤

ከቀደመው ታሪክ ጥቂት እናመስጥር።

ሰው ከሰው ጋር ታግሎ ሰውን ያሸንፋል፤

በጉልበት ሃያላን ድል ሲመቱ አይተናል፤

ዳዊት ጎልያድን በጠጠር ጥሎታል፤

በአህያ መንጋጋ ሽውን አርግፎታል።

ነገር ግን ከጌታ ከእግዚአብሄር ተጣልቶ፤

ድል የቀናው የለም ያሸነፈም ከቶ።

ማሰብም ድፍረት ነው አይደለም መታገል፤

አሁን ልብ ግዛ በጣምም ቸል አትበል።

ዋልድባን ለማየት ብሩህ አይን ከለህ፤

ውሳጣዊ አይንህን ጌታ ካበራልህ።

ሂድ ግባ ሱባኤ ትጋበት ለፀሎት፤

ሸንኮራው ይቅርብህ አለ የሚበሉት፤

አንተም ትበላለህ ከፈለግክ ድህነት።

አልቀበልም ካልክ ልብህ ከታወረ፤

ለጥፋት ዘመቻ አንገትህ ከዞረ።

አወዳደቅህን ከአሁኑ አሳምረህ፤

መንገድህን ጀምር ሂድ ብያለሁ ይቅናህ።

በታሪክ ማህደር በዚያ ክብር መዝገብ፤

በግራ ተጽፎ ለህዝቡ ሲነበብ።

የተጓዝከው ጉዞ ያደረግከው ድርጊት፤

የሰራሀው ወንጃል ያጠፋሀው ጥፋት፤

ከመሃመድ ጋራ የተባበርክበት።

ለጥፋት ዘመቻ የተዛመድክበት፤

ዮዲትንም በግብር የተመሰልክበት፤

ተጽፎ ይቀራል በታሪክ መዛግብት።

ማጥፋትህም ሁሉ ለህዝብ ይነገራል፤

አንትም ትሄዳለህ ዘመንህ ያበቃል፤

ዋልድባ አበረንታንት ዘላለም ይነግሳል፤

እስከመጨረሻው ሲዘከር ይኖራል፤

ላይጠፋ ዘላለም በአለት ላይ ታንጿል፤

ጽኑ ቃል ኪዳኑ በክብር ተጽፏል።


ፍኖተጽድቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈለገ ሃዋርያት ሰንበት ትምህርት ቤት

መጋቢት ፳፻፬ ዓ.ም.

ማናየ አለማየሁ።

ሙሉውን ግጥም ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤