Tuesday, May 29, 2012

አባቶች ስለ ዋልድባ ዝምታን ለምን መረጡ ?(አንድ አድርገን ግንቦት 21 2004 ዓ.ም)፡- ከቀናት በፊት ተጀምሮ ፍጻሜውን በአስር ነጥብ የአቋም መግለጫ የተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በርካታ መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ለህዝበ ክርስትያን እና ለቤተክርስትያኒቱ በሚጠቅሙ አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሮ መጠናቀቁ ይታወቃል ፤ ስብሰባው ሲጀመር የቅዱስ ሲኖዶስ 20 አጀንዳዎችን ከተቀረጹ በኋላ የዋልድባ ጉዳይ እንደ አጀንዳ አለመያዙን እያነጋገረ መሆኑን ገልጸን ጽፈን ነበር ፤ እኛ እንዳልነው ስብሰባው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በዋልድባ ጉዳይ ላይ ምንም የተባለ ነገር አለመኖሩ ምዕመኑን አስደምሞታል ፤ ለምን አባቶች አቋማቸውን መግለጽ አልፈለጉም ? ከዚህ በላይ ችግርስ አሁን በቤተክርስትያኒቱ ላይ አለን ? ምዕመኑ የተቃወመውን ያህል አባቶች ምን እንደሚሉ መስማት የብዙዎች ፍላጎት ነበር ፤ ነገር ግን ይህ ሲሆን መመልከት አልቻልንም ፤
ይህ ጉዳይ ሀገር ያወቀው ጸሀይ የሞቀውን ነገር እንደ አጀንዳ ይዘው መነጋገር አለመቻላቸው ብዙዎችን አስገርሟል ፤ እኛ ባለን አቋም ፕሮጀክቱን መቃወምም ሆነ መደገፍ ሁለቱም አቋም ነው የሚል እምነት አለ ፤ በኢሜል ከሚደርሱን በርካታ ጥያቄዎች አንዱ የዋልድባ ነገር ምን ደረጃ ደርሷል? የሚል ጥያቄ ነው፡፡  ፤ የነገሩን አካሄድ ስንመለከት ትንሽ ከመንግስት በኩል ለዘብ የማድረግ አዝማሚያ ይታያል ፤ ከገዳሙ አባቶች እና ከቤተክህነቷ ጋር ለመነጋገር ቀነ ቀጠሮ ባይቆርጥም ለመነጋር ሀሳብ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል ፤ ማህበረ ቅዱሳን ይዞት የመጣው ሪፖርት ላይም ይህን የሚደግፍ ሀሳብ እንዳለ አመላክቷል ፡፡ከሳምንታት በፊት ህዝቡ ወደ ወልቃይት ስኳር ፕሮጀክት ሲወርድ እንደነበረ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ቦታው ድረስ ሄደው ከመጡ ሰዎች መስማት ችለን ነበር ፤ መንግስትም ሚያዚያ 29/2004 ዓ.ም ህዝቡን ለማወያየት አስቦ ነበር ፤ ስብሰባው ይደረግ አይደረግ የታወቀ ነገር ባይኖርም ፤
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስታቸውን የ9 ወር የስራ ክንውን በገለጹበትና ስለ አሸባሪነት ጠለቅ ያለ መረጃ ባተላለፉበት  ጊዜ ጀምሮ መንግስት የአካሄድ ለውጥ ማድረጉን ሁኔታዎች ያመላክታሉ ፤  በዚህ ስብሰባ ላይ እየተጋጋለ የመጣውን  የሙስሊሞች ጥያቄ ፤ የዋልድባ ገዳም የስኳር ፕሮጀክት ጉዳይ እና የህዝብ ተቃውሞ መሰረት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ይሰጡባል ተብሎ ቢጠበቅም በስተመጨረሻ ባደረጉት የአቋም ለውጥ ዝምታን መምረጣቸው ይታወቃል፡፡ ሪፖርቱ እስከሚቀርብበት ጥቂት ቀናት ድረስ ዋድባን መሰረት አድርገው ቦታው ላይ እየሆነ ያለውን እና የተደረገውን ስራ የህዝቡን ጥያቄ መሰረት በማድረግ መልስ ይሰጡበታል ፤ የመንግስታቸውን አቋም ያንጸባርቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ግን ሆኖ መመልከት አልቻልንም ፤ ይህ ጉዳይ ከሙስሊሞች ጥያቅ ያነሰ ሆኖ ሳይሆን በመንግስት በኩል የአካሄድ ለውጥ እንዳለ አመላካች ነው የሚልም አስተያየት አለ፡፡
በመሰረቱ ጉዳዩ የማያነጋግርና አቋም የማይወሰድበት ሆኖ ሳይሆን ከመንግስት የተንጸባረቀው የአቋም ለውጥ አባቶች ጉዳዩን በጉባኤው ላይ እንዳይነጋገሩበት መንገድ የከፈተ ይመስላል ፤ አባቶች “ለአሁን እንለፈው ወደፊት መንግስት ጉዳዩን ወደኛ ሲያመጣው እንነጋገርበታለን” የሚል አካሄድን የተከተሉ ይመስላሉ፡፡ ፤ በሌላ በኩል “መንግስት ላሰበው ፕሮጀክት ቤተክርስትያኒቱ በሲኖዶስ ደረጃ አቋም እንዳትይዝ ትንሽ ዘግየት እንድትል ትዕዛዝ የተላለፈ ይመስላል” የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ ፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩን እንዲለዝብ ያደረገው  አንዱ እና ዋንኛው ሆኖ የሚወሰደው በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች “ይህ ሊሆን አይደለም ሊታሰብ የማይገባው ተግባር ነው ፤ በእምነታችን ላይ የመጣ የማፈራረስ ሴራ ነው” በማለት ጦር ፤ ዶማ ፤ አካፋ ይዘው ወደ ቦታው መትመማቸው መሆኑ ይታመናል ፤ ጉዳዩም ወዴት እንደሚሄድ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን  መነሳሳት በመመልከት የያዘውን አቋም ለዘብ እንዲያደርግ ምክንያት ሆኗል ተብሎ ይታሰባል፡፡
 ጉዳዩ እንዳይነሳ ካደረጉት ነጥቦች ጥቂቶቹ
1.     ስፍር ቁጥር የሌላቸው የውስጥ ችግሮችን መፍታት አለመቻል፡- በዓመት ሁለት ጊዜ የሚደረገው የሲኖዶስ ስብሰባ ከጊዜ በኋላ በአቡነ ጳውሎስ አምባገነንነ አካሄድ ፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ ጸባይ ዘወትር ለመስማት የሚታክት  ንትርክ  መስማት ጆሯችን የለመደው ነገር ሆኗል ፤ በቤተክርስያኒቱ ውስጥ ያሉት ችግሮችን ቀድሞ አለመፍታት ይህን ጉዳይ ወደ ኋላ እንዲል አድርጎታል ፤ የተሀድሶያውያንና የመናፍቃን ፤ ለህገ ቤተክርስትያን ተገዥ አለመሆን ፤ የአቡነ ጳውሎስ ረዥም እጅ ፤ ሙስና ፤ ጎጠኝነትና  አድርባይነት  የመሳሰሉት ችግሮች ቤተክርስትያኒቷ በሁለት እግሯ ቆማ ወንጌልን ለመላው ዓለም እንዳታዳርስ ፤ ይህን የመሰለውን አንገብጋቢ ጉዳይ በጊዜው እንዳትመክርበት እንቅፋት ሆኖባት ይገኛል ፤ አብዛኛው የሲኖዶስ ስብሰባ የያዘውን አጀንዳ በአግባቡ ሳይቋጭ ለሚቀጥለው እንደሚያስተላልፍ ይታወቃል ፤ ይህ ማለት የችግሩን ብዛት እና መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መበራከት ያመጣው ችግር መሆኑ እሙን ነው ፤ ስለዚህ በርካታ የውስጥ ችግር ያለባት ቤተክርስትያን በመሆኗ መጀመሪያ የውስጡን የማጥራት ስራ ስላተሰራ ጉዳዩን ወደ ኋላ እንዲል አድርጎታል፡፡

2.    ሀገር ውስጥ የሚኖረው ምዕመን ገፍቶ መሄድ አለመቻል ፡- በመሰረቱ የዋልድባ ጉዳይ ከተሰማ ጀምሮ ሰዎች በጉዳዩ ላይ አትኩሮት ሰጥተው በየጊዜው በቪኦኤ ፤ በተለያዩ ድረ ገጾችና ጋዜጣዎች ሲከታተሉ መመልከት ችለን ነበር ፤ ነገር ግን ያሰቡትንና የተሰማቸውን ጥያቄያቸውን በአንድነት ሆነው ማቅረብ የቻሉ በጣም ጥቂቶች ናቸው ፤ “ይህ ጉዳይ የገዳሙን ህልውና የሚያናጋ እና እምነታችን ላይ የተሰነዘረ ጦር ነው” በማለት በጎንደርና አካባቢው ያሉት ነዋሪዎች መንግስት የስኳር ልማት አቋቁምበታለው ብሎ ማረስ ወደ ጀመረው ቦታ በተናጠልና አነስ ባለ አንድነት መንቀሳቀሳቸው ይታወቃል ፤ ይህም ጥያቄ እዛው መቅረቱ ጉዳዩ በአባቶች ዘንድ ውሀ ደፍቶ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንዳይሆን የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓ ፤ በመሰረቱ ይህ ጉዳይ የተሰማ አካባቢ ስድስት ኪሎ የሚገኝው የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን አንድ እሁድ የቀድሞ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን በፌስ ቡክ አማካኝነት በጉዳዩ ላይ ለመነጋር ስብሰባ መጥራት ተችሎ ነበር ፤ ነገር ግን በወቅቱ ከተባለው ሰዓት በፊት ሲቪል የለበሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ፌደራል ፖሊስ አባላት ግቢውን እንደ አንበጣ ወረውት የሚሆነውን ነገር ለመከታተል ቀድመው በቤተክርስትያኑ ተገኝተው ነበር፡፡ ህገ-መንግስቱ አንቀጽ 30 የመሰብሰብ ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ መብት ላይ ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ “ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታን የማቅረብ መብት አለው፡፡” በማለት በግልጽ ያስቀምጣል መንግስታችን ግን የህጎች ሁሉ የበላይ ላይ ይህን አስቀምጦ ሰዎች ለመሰብሰብ ሲሞክሩ ቀድሞ ከስብሰባው በፊት ቦታው ላይ በመገኝት ሰዎች በነጻነት ስብሰባ እንዳያደርጉ በማድረግ የሽፍታነት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሲፈልግ ደግሞ መሰብሰብ ትችላላችሁ ብሎ ህጋዊ ፍቃድ ይሰጥና ተሰብሳቢዎች መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳያገኙ በሮቹን ሁሉ ይቆልፋል ፤ አዳራሽ ያላቸውን ሆቴሎችንም በቀጭኗ ሽቦ ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፍ ህገ መንግስቱ የፈቀደውን መብት የመጣስ ስራ ይሰራል ፤  በዚህ አይነት ምክንያቶች ስለ ዋልድባ ጉዳይ መረጃ የደረሰው ምዕመን እንዳይሰበሰብ እና በጉዳዩ ላይ ሀሳብ እንዳያንሸራሽር መንግስት እንቅፋት በመሆኑ ስብሰባ ለማድረግ አይደለም ለማሰብ አልቻለም ፤ ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ምዕመናን ይልቅ በውጭ የሚገኙ ምዕመናን በዋልድባ ስኳር ልማት ላይ ጊዜያዊ አለማቀፋዊ ኮሚቴ አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይታወቃል ፤ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች June 4 2012 (ግንቦት 27 2004 ዓ.ም) እስከ ዛሬ ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ በአሜሪካ ፤ አውሮፓ እና በአፍሪካ በተለያዩ ሀገሮች በበርካታ ከተሞች ላይ እጅግ ብዙ ሺህ ህዝብ የሚገኝበትን የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ እንደተዘጋጁና የቤት ስራቸውን ቀድመው እንዳጠናቀቁ ለማወቅ ችለናል ፤ ይህ ጊዜያዊ ኮሚቴ ከዚህ በተጨማሪም አለማቀፋዊ ለሆኑ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት የሚሰራውን ስራ በመቃወም ደብዳቤዎችን መላክ ችሏል ፤ ሀገር ቤት የሚገኝው ምዕመን ግን ከመንግስት ሊመጣ የሚችለውን ነገር በመፍራት እንደ ባለቤት ሲንቀሳቀስና ጥያቄውን ቢያንስ እንኳን ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያቀርብ አልተመለከትንም ፤ ይህ በህዝቡ ውስጥ ያለውን ከልክ ያለፈ ፍርሀት እንደማሳያ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰዎች የማህበረ ቅዱሳንን ሪፖርት ሲጠባበቁ ነበር ፤ ማህበሩ የሚጠበቅበትን ስራ በማከናወን የአቅሙን ያህል ሪፖርት ማቅረብ ችሏል ፤ እንደ እኛ ሀሳብ ከአሁን በኋላ ያለው ስራ የእኛ የምዕመናን እንጂ የማንም አይደለም ፤ ሪፖርቱ ብቻውን መፍትሄ አይሆንም ፤ “ፈረስ ያደርሳል እንጂ…..” የሚባል ተረት አለ፡፡ እኛ ጉዳዩን ጉዳያችን በማድረግ ሁሉም ምዕመን በግልም ሆነ በህብረት  ስራ መስራት ካልቻለ ማንም መጥቶ ገዳሙን ከሸንኮራ ተክል ሊታደገው አይችልም ፤ ነገሮችን “እግዚአብሔር ያውቃል” ብለን ለአምላክ አሳልፈን መስጠት ያለብን መጀመሪያ የአቅማችንን ሙከራ አድርገን መሆን መቻል አለበት ፤   

3.    የፖለቲካ አይዲዎሎጂ፡- ይህ ፖለቲካ የሚባል ነገር በአሁኑ ሰዓት ነቀርሳ ያልሆነበት ሰውና ተቋም ለማገኝት ይቸግራል ፤ አንዱ ይህ ነገር ችግር ከሆነበት ቦታ ቤተክህነቱ ነው ፤ መንግስትን ለማስደሰት ሲሉ መደረግ የሌለበትን ነገር ሲያደርጉ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም ፤ ፖለቲከኞቹ ስለሚሰራው የስኳር ልማት ገለጻ ሳያደርጉ ልወደድ ባዮችና ክሬዲት ማግኝት የሚፈልጉ አቶ ተስፋዬን የሚመስሉ ሰዎች የሚገኙበት ነው፡፡ እምነት ደግሞ የፖለቲካ ተቃራኒ ነው ፤ ምንም አንድ የሚያደርጋቸው ነጥብ የለም ስለዚህ ፖለቲከኛ ሆኖ የቤተክርስትያኒቱን ወንበር ሳይገባቸው የያዙ ሰዎች ባላቸው የገዥው ፓርቲ ደጋፊ አቋም መሰረት ለመቃወምም ሆነ ለመደገፍ አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠሩ ይገኛሉ ፤ መንግስት የሚፈልገው የሱን ስራ እንዲደግፉለት ነው ፤ እነርሱም ለጊዜው አይናቸው ይታወርና በጭፍን መለስ ዜናዊ ስለተናገረ ብቻ ፤ አባይ ጸሀዬ ስላወሩ ብቻ በነርሱ ጎራ ሲቆሙ እየተመለከትን ነው፡፡ ‹‹ህዝቡ ስኳር እየተቸገረ ነው ›› ብለው ባለስልጣናቱ ተናግረው ሳይጨርሱ እነርሱ የገደል ማሚቱ ሆነው ድምጹን ሲያስተጋቡ እየተመለከትን ነው ፤ ፖለቲካ የዘመኑ የቤተክርስትያን ፈተና ሆኖም እየተመለከትን ነው፡፡

4.    የአባቶች በሁለት ጎራ መቆም ፡- ይህን ፕሮጀክት ላይ ጥርት ያለ አቋም ያላቸው አባቶች እንዳሉም ሌሎች አባቶች ደግሞ ፕሮጀክቱ ላይ ሀሳብ የማይሰጡም ይገኛሉ ፤ የትግራይ ክልል ሊቀ ጳጳስ ውዝግቡ ሲጀመር በጸሎት ከማስጀመር ያለፈ መናገር አለመፈለጋቸው እናውቃለን ፤ የጎንደር ሊቀ ጳጳስም መጀመሪያ ላይ የነበራቸውን አቋም እስከ መጨረሻ ማስኬድ አለመቻላቸውም የሚታወቅ ነው ፤ ታዲያ በተግባር እንዲህ ያደረጉት አባቶች ሁለት ቢሆኑ እንኳን ሌሎቹም እንዲህ አያደርጉም ማለት የሚከብድ ይመስለናል፡፡ አቡነ ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ደግፈው በእርሳቸው በኩል አቡነ ፋኑኤልን እና አቡነ ገሪማን የመሰሉ አባቶች እንደሚያሰልፉ እሙን ነው ፤ ሌሎች አባቶች ደግሞ አቋማቸው የእርሳቸው ተቃራኒ ሊሆን ይችላል ፤ ዝም ማለትም የሚፈልጉ አባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ፤ በዚህ ጊዜ የሚፈጠረው አለመግባባት ሌላ ችግር እንዳይፈጥር በመስጋት ይህ ጉዳይ ላይ ከመንግስት መጥቶ እንወያይ እስኪላቸው ድረስ ማቆየቱን የወደዱ ይመስላሉ፡፡

5.    መንግስትን መጠበቅ ፡- ጉዳዩ ላይ ለጊዜው መንግስት ዝምታን ስለመረጠ አባቶችም ይህችን ክፍተት በመጠቀም መንግስት ጉዳዩን ሲያመጣው ብቻ መነጋር የፈለጉ ይመስላል ፤ መንግስት ስራውን ባላመነበትና ዘወትር በሚዋሽበት ሁኔታ ላይ አጀንዳ አድርጎ በጉዳዩ ላይ መነጋገር ከመንግስት ሌላ ጥያቄ እንዳያስነሳም ያሰጋል ፤ “ዋልድባ ገዳም ምን ሆነና ነው በዚህ ጉዳይ ለመነጋገር አጀንዳ የያዛችሁት?” ብሎ ቢጠይቅ ለጥያቄው መልስ መስጠት የሚችሉ የአባቶቻችን ብዛት ከጣቶቻችን አይበልጡም ፤ እንደ አቡነ ፋኑኤል ያሉት አባቶች አቋማቸው ቀድሞ ይታወቃል ፤ አቡነ ፋኑኤል በግልጽ ተናገሩ እንጂ ይህ ጉዳይ ተደርጎ በአጀንዳነት ቢያዝ ኖሮ አቡነ ጳውሎስ እና ሌሎች አባቶች እንደሚከተሏቸው ይታወቃል ፤ ድምጻቸው ሚዛን ባይደፋም ፤ ጉዳዩን ሳይነጋገሩበት በስተመጨረሻ ቀን ቃለጉባኤው ላይ ሊያስፈርሟቸው የነበረውን ሀሳብ ለተመለከተ ሰው ቢወያዩበት ኖሮ ምን ይፈጠራል ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አያስቸግረውም የሚል እምነት አለን፡፡

6.    ከመጠን ያለፈ ፍርሀት ፡- እውነቱን ለመናገር ከአቡነ ጳውሎስ ጀምሮ ሁሉም በሚያስብል መልኩ መንግስትን እና የመንግስትን ባለስልጣናት በሚሰሩት ተገቢ ያልሆነ ስራ ስለ እውነት ብለው የሚጋፈጡ አባቶች አሉ ለማለት አያስደፍርም ፤ ከ2 ወር በፊት ጎንደር ላይ ዋልድባን በማስመልከት ‹‹ምህላ አውጃለሁ›› ያሉ አባት ከመንግስት “ምን ተፈጠረ እና ነው ምህላ የሚያውጁት?”` የሚል ጥያቄ ሲመጣ ‹‹ምህላ ማወጅ መብቴ ነው ፤ የእናንተን መልስ መጠበቅ አይጠበቅብኝም›› ብለው የመለሱት ቆራጥ አባት በተደረገባቸው ተጽህኖ አማካኝነት ‹‹ ዋልድባ ላይ ውሀ ቢፈስ ምን ችግር አለው ፤ ገነትም እኮ ውሀ ይፈስባታል›› በማለት ከአቋማቻ ሸርተት ማለታቸው ይታወቃል፡፡  ይህ ማለት ስለ እውነት ብለው ለተናገሩት ነገርና መጀመሪያ የነበራቸውን አቋም እስከመጨረሻ ይዞ አለመዝለቅ ችግር እንዳለ ያሳየናል ፤ ይህ ደግሞ ፍርሀት ብቻ ነው ሊባል የሚችለው ፤ ከጎንደርና  አካባቢው ዓመታዊ የመድሀኒአለም በዓል ለማክበር እና ዋልድባ ገዳም ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት በርካታ ወንድሞችና እህቶች ወደ ቦታው መሄዳቸው የሚታወቅ ነው ፤ ቦታው ድረስ ሂደው ተመልክተው የመጡትን ነገርና በመንግስት ወታደሮች ያለአግባብ የደረሰባቸውን ጉዳት ለአቡነ ኤልሳዕ ሊያስረዷቸው ወደ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት  በመሄድ መናገር ሲጀምሩ ከአቡነ ኤልሳዕ ያገኙት መልስ “ስለሚታረሰው አያገባችኹም፤ ስለተተኮሰባችኹና ስለተደበደባችኹት አያገባንም” የሚል  ነበር ፡፡ ለዚህ ከመጠን ያለፈ ፍርሀት እንደማሳያ ከዓመታት በፊት በተደረገው የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች አመጽ ቤተክርስትያን የገቡትን ተማሪዎች ኦራል መጥቶ አፍሶ ሲወስዳቸው ሁለት አይነት አቋም መንጸባረቅ ችሎ ነበር ፤ የፈሩት ‹‹ይውሰዷቸው ›› ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ‹‹አይሆንም›› ያሉ እንደነበሩ በጊዜው መመልከት ተችሏል ፡፡ በጊዜው የደህንነት ኋላፊው አቶ ክንፈ መጥቶ ቤተክርስትያን የገቡትን ተማሪዎች በንቀት ተመልክቶ ካበቃ በኋላ ‹‹ስንቱ ታጋይ በርሀ ላይ ወድቋል እናተም ሰው ሆናችሁ ታምጻላችሁ? ለአንድ ተማሪ አንድ ጥይት ይበቃናል…››ብሎ በተናገረ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጦር ኃይሎች መኮንንኖች አዳራሽ የድርጅት ስብሰባ አድርጎ ሲወጣ አንድ ጓደኛው በጭንቅላቱ 2 ጥይት እንደለቀቀበት የዓመታት ትውስታችን ነው፡፡ በቤታችን ውስጥ ለማድረግ የሚታሰብንና በተደረገ ነገር ላይ አቋም መያዝ አለመቻል ከፍርሀት ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? 

7.    መሰልቸት ፡- በአሁን ሰዓት የሚገኙ የሲኖዶስ አባላት እጅጉን በእድሜ የገፉ መሆናቸው ይታወቃል ፤ በቀን ለ8 ሰዓታት ያህል ለ16 ቀናት ሳይሰለቹ ስለ ህዝበ ክርስትያን እና ስለ ቤተክርስትያን አንድነት ሳይታክቱ ስብሰባ መቀመጥ ቀላል የሚባል ነገር አይደለም ፤ በዚህ ስብሰባ ላይ በህመም ምክንያት አንዳንድ አባቶች ቤት ማረፍ ቢገባቸው እንኳን “ቤተክርስትያንን ለአቡነ ጳውሎስ አሳልፌ አልሰጥ” በሚል ሀሳብ ከነህመማቸው ስብሰባው ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ የስብሰባው ሂደት ላይ የነበሩ አባቶች እንዳሉ ለማወቅ ችለናል ፤ ከአጀንዳዎቹ ብዛትና ከቀኑ ብዛት የተነሳ አባቶች ቢሰለቹም አይፈረድባቸውም ፤ በተቻላቸው መጠን ያህል አጀንዳዎቹን መመልከት እና ውሳኔ ማሳለፍ ችለዋል ፤ ተፈጻሚነቱ ላይ ጥያቄ ቢኖርም ፤ ከዚህ ረዥምና አሰልቺ የስብሰባ ጊዜያት በኋላ ይህን ጉዳይ ተነጋግረው አቋም ይወስዳሉ ማለት ይከብዳል፡፡

8.    የአቡነ ጳውሎስ ተጽህኖ ፡- አቡነ ጳውሎስ የሚያሳድሩት ተጽህኖ ቀላል የሚባል አይደለም ፤ የባለፈው ሲኖዶስ ስብሰባ ጊዜ ሲኖዶሱ ይፍረስ ብሎ የወሰነውን የአቡነ ጳውሎስን ጣኦት በተጽህኖ አማካኝነት እስከ አሁን ሳይፈርስ በቦታው ተቀምጦ አለ ፤ እርሳቸው ካመኑበት ሌሎች አባቶችን ከጎን ማሰለፉን ተክነውታል ፤ ይህ የዋልድባ ገዳም ጉዳይ ላይ የሳቸው አቋም ፕሮጀክቱ ቢሰራ ችግር የለውም የሚል ነው ፤ ይህ የታወቀው አባቶች ስብሰባን ጨርሰው ቃለጉባኤ ለመጻፍ የተወከሉ አባቶች ተጽፎ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ሲነበብላቸው ‹‹በዋልድባ ገዳም ላይ የሚሰራውን የስኳር ልማት እንደግፋለን›› የሚል ሀሳብ ያለው ሲሆን ፤ ‹‹ይህን ጉዳይ ተነጋግረን አቋም ያልወሰድንበት ሳለ እንዴት እዚህ ውስጥ ሊጠቃለል ቻለ?›› የሚል ጥያቄ በመነሳቱ አባቶች  ከቃለ ጉባኤው ላይ ማሰረዝ ችለዋል፡፡ ይች አካሄድ በአንድም ሆነ በሌላ አቡነ ጳውሎስ የሚደግፏት ሀሳብ መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ ስለዚህ አቡነ ጳውሎስ ጉዳዩን ከአባቶች ጋር ባይነጋገሩበትም መስመራቸውን መመልከት ችለናል ፤ የያዙት መንገድ ያዝልቃቸው አያዝልቃቸው የምናውቀው ነገር ባይኖርም፡፡

ምንጭ: አንድ አድርገን ብሎግ

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤