Wednesday, May 30, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን የዋልድባ ገዳም ሪፖርት ላይ የ "አንድ አድርገን" እይታ


ባሳለፍነው ሳምንት ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ ገዳም ህልውናን ያናጋል የተባለው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ላይ በላካቸው ልኡካን ቡድኖች አማካኝነት ያዩትንና የተመለከቱትን ፤ የእነርሱን እይታ ጨምረው የ9 ገጽ ሪፖርት ማቅረባቸው ይታወቃል ፤  በመጀመሪያ በዚህ ጊዜ ከቤተ ክርስትያኗ ጎን በመቆም የነበረውን ብዥታ ለማጥራት ጊዜ በመውሰድ በዋልድባ አካባቢ ያለውን እውነታ ለማቀመጥ ለደከሙ ወንድሞች አድናቆቴን ማቅረብ እወዳለሁ ፤ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መናገርም ሆነ አለመናገር የሚያስጠይቅበት ወቅት ላይ አቅም በፈቀደ መጠን ሪፖርቱ የሚያመጣውን የወደፊት ተግዳሮት ግምት ውስጥ በማገባት ይህን ስራ መስራት መቻል ከኃላፊነትም በላይ መሆኑን ላስገነዝብ እወዳለሁ ፤ ቤተክህነቱ ምዕመኑን አንገት ያስደፋ ሪፖርት ስሙኝ በማለት የኢቲቪ ጋዜጠኞችን ጠርቶ ቢያቀርብም እንኳን አሁን ደግሞ ግልጽ ያለ ነገር ምዕመኑ ማወቅ ችሏል ፤ ይህን ሪፖርት ያስቀመጣቸውን ጥሬ ሀቆች ፤ አጠይሞ ያስቀመጠውን እና የጥናቱን ውስንነት ለመዳሰስ እንወዳለን፡፡

1.      ጥናቱ ያስገኛቸው ጥሬ ሀቆች(Real Facts)

·        መንግስት በአደባባይ የዋሻቸውን ነገሮች እውነታውን ማሳየት ችሏል ፤ ለምሳሌ 16.6 ሔክታር ቦታ ከገዳሙ እንደሚነካ በማያሻማ መልኩ አስቀምጧል፡፡

·        አጽመ ቅዱሳን መነሳቱን መናገር ችሏል

·        500 ሜትር ያህል መንገድ መቀደዱ፡- የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ከስኳር ሚኒስትሩ ጋር በመሆን ለውሸት የተፈበረኩ እስኪመስል ድረስ የአየር ሰዓት ይዘው ሲዋሹ ምንም አይመስላቸውም ፤ ‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› እንደሚባለው ፤ እውነታን እያዛቡ ማቅረብ ስራቸው አድርገውት ሰንብተዋል ፤ ማህበረ ቅዱሳን ያወጣው ሪፖርት መንግስት በኢቲቪ አማካኝነት የገዳሙን ቦታ አላረስኩም ሲል የገዳሙ መነኮሳት ደግሞ ታርሷል እያሉ የተወዛገቡበትን ቦታ ሪፖርቱ መታረሱን አስረግጦ በአይን እማኞች አረጋግጦልናል ፤ በጊዜው መንግስት የገዳሙን አባቶች አንድ ቦታ ላይ ስብሰባ ጠርቷቸው ነበር ፤ የገዳሙ አባቶች ግን የታረሰው ቦታ ላይ ካልሆነ አንሰበሰብም ማለታቸው ይታወቃል ፤

·        ሶስት አብያተክርስትያናት ይፈርሳሉ፡- ማይ ሐርገፅ ጊዮርጊስ ፤ ዕጣኖ ማርያም እና ማይጋባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያናትን ይፈርሳሉ ብሎናል ፡፡ ከተለያየ ሚዲያ የሰማነው የሚፈርሱት የቤተክርስትያን ቁጥሮች ቢለያዩም ማህበረ ቅዱሳን የሰራው ሪፖርት ግን ሶስት አብያተክርስትያናት በትክክል እንደሚፈርሱ አስረግጦ ነግሮናል፡፡

o   እንደሚታወቀው ዋልድባ ላይ ከቋርፍ ውጪ የሚመገቡት ምግብ የለም ፤ እነዚህ ይፈርሳሉ የተባሉት ቤተክርስትያናት በዓመት ሁለት ጊዜ የዋልድባ አባቶች በዓላቸውን የሚያከብሩበት ከቋርፍ ውጪ ምግብ የሚበሉባቸው ቦታዎች ናቸው

o   መነኮሳቱ የራሳቸውን እና የገዳሙን ፍጆታ የሚውል ሰሊጥ ፤ ኑግና የመሳሰሉት የቅባት እህል የሚመረትባቸው አብያተክርስትያናት ናቸው፡፡

o    ገዳማውያኑ ሲታመሙ ፤ በእድሜ የገፉ አረጋውያን አባቶችና ጤናቸው የታወኩ መነኮሳት  የሚያርፉበትና ድጋፍ የሚደረግላቸው ቦታዎች ናቸው ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነገሮችን የማህበሩ ሪፖርት እውነታውን ፍንትው አድርጎ ያስቀመጠ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

2. ጠይመው የተቀመጡ
የማህበሩ አጥኚ ቡድን የአባቶችን ፍራቻ ካስቀመጠ በኋላ በስተመጨረሻ ‹‹በዚህ ፕሮጀክት ትግበራ ላይም በተጓዳኝ የታዩ ስህተቶች ወይም ጉድለቶች ናቸው›› ብሎ ሁለት ነጥቦችን አስቀጧል ፤ ሁለተኛው ነጥብ ጠይሟል ፤ እንዲህ ይላል ‹‹ችግሩን ለመፍታት የተከሄደበት መንገድ አግባብነት ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ ይጠቀሳሉ››፡፡ መንግስት ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ ፍጹም ስህተት መሆኑን ከመግለጽ በመቆጠብ ለስለስ ብላ ፈዘዝ ያለ ቀለም የተቀባጭ ሀሳብ ሪፖርቱ ላይ እናገኛለን፡፡

እኛ ግን እስኪ መንግስት ይህን ችግር ለመፍታ የሄደበትን የስህተት ጎዳና እንጠቁማችሁ ፡፡ ሲጀመር ይህ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ይዘው የመጡትን አባቶች በስድብ መቀበል እና በማስደንበር ስህተቱ መንግስት ይጀምራል ፤ ‹‹እናንተ ደፋሮች የአንድን ሀገር መሪ ለማናገር መጣችሁ›› በማለት የስልክ መልስ ተሰቷቸዋል ፤ መነኮሳቱ ግን የመጡበትን አላማ ሳናሳካ አንመለስም በማለት ፓትርያርክ ጽ/ቤት ግልባጭ በማስገባት ዋናውን መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በአስቸኳይ መልእክት መላካቸው ይታወቃል ፤ ይህን አድርገው ሲያበቁ በተወካያቸው መነኩሴ አማካኝነት በኩል ከቪኦኤ ጋር ቃለ መጠይቅ በማድረግ ጉዳዩን የአደባባይ ሚስጥር እንዲሆን አደረጉ ፤ ይህን ጊዜ ነበር መንግስት የተሰማውን ወሬ ውሽት ነው በማለት የስኳር ሚኒስትር ሀላፊውን አቶ አቦይ ጸሀዬን ይዞ የኢቲቪ የ2 ሰዓት ፕሮግራም ላይ አቅርቦ በዚህ እድሜያቸው እንዲዋሹ ያደረገው ፤ ቃለ መጠይቅ ያደረጉትንም አባት የት እንደሚገኙ የገዳሙ አባቶች እንዲጠቁሙ ቁም ስቅላቸውን ሲያሳያቸው የከረመው፡፡ ይህ የስህተት መንገድ በማይረቡት የቤተክህነት ሰዎች አማካኝነት እንዲረጋገጥለት በመፈለግ ቤተክህነቷ ሰዎችን ልካ የግድቡ ግንባታ ምንም ችግር እንደሌለው እንድትመሰክር የማድረግ ስራ አሰርቷል ፤ ጨምረውም እነዚህ የተላኩ ሰዎች በሪፖርታቸው ‹‹መነኮሳቱ ግድቡ ካለቀ አሳ ማጥመድ ይችላሉ›› በማለት መንግስትን ደስ የሚያሰኝ ሪፖርት አቅርበዋል ፤ ይህም ሌላኛው ችግሩን ለመፍታት የተሄደበት የስህተት መንገድ ነው ፤ ቀጥሎም የቤተክህነት ሰዎች እና ጥቂት ለስጋቸው የቆሙ መነኮሳትን ከየት እንዳመጣቸው የማይታወቁ ፤ ለጊዜው በጉዳዩ ላይ የማይመለከታቸውን የእስልምና እምነት አባቶችን አንድ ላይ ሰብስቦ ‹‹ግድቡ ገዳሙ ላይ የሚያመጣው ችግር የለም›› ብሎ ቃለ ጉባኤ በመጻፍ እና በማስፈረም ፤ ባለ ስድስት ነጥብ አቋም በማውጣት የምንጊዜም ምርጥ የኢቲቪን ድራማ ዋልድባ ድረስ ሄደው ሰርተው ለተከታታይ 3 ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ በ3 ቀን 6 ጊዜ አቅርበውት መፍትሄ ለመሻት ሞክረው ነበር ፤ ይህም ግን የተሳካ አካሄድ አልነበረም ፤ ይህም አልበቃ ሲላቸው በትግረኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ፕሮግራም ሰርተውለት የሚሰራውን ስራ ህዝቡ እንዲያውቅ የማድረግ ስራ ሰርተዋል ፤ 

ይህም አመርቂ ስላልሆነ ጎንደር ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ስብሰባ አካሂደው ያለ መፍትሄ መበተኑ ሌላኛው መንገድ ነው ፤ እዚህ ስብሰባ ላይ አንድ የቤተክህነቱ ተወካይ አቶ ተስፋዬ በፊት የኢህአዴግ ሰላይ ሰው ለጎንደር ህዝብ ስለ ዋድባ ማስረዳት ሞክሮ ነበር ፤ በስተመጨረሻ የጎንደር ህዝብ ‹‹ዝም በል አንተ ነህ ስለ ዋልድባ ለጎንደር ህዝብ ማስረዳት የምትሞክረው? ›› ተብሎ የሚናገረውን ህዝብ እንዲያውቅ በስብሰባ ላይ ተነግሮታል ፤ ይህ ሰው በዚህ የስብሰባ አዳራሽ ላይ ‹‹ስኳር ተወዷል ፤ ህዝቡ እየተቸገረ ነው ፤ ምን ችግር አለ ፕሮጀክቱ ቢሰራ? ››  ማለቱም የወራት ትውስታችን ነው ፤ በስተመጨረሻ መንግስት ግራ ሲገባው የደርግ ርዝራዥ ወታደሮች ናቸው በማለት ገዳማውያኑን ከፖለቲካ ጋር የማያያዝ እና ማህበረሰቡ እንክ እንትፍ ብሎ እንዲተፋቸው የማድረግ ስራ ሰርቷል ነገር ግን አልተሳካም ፤ ይህን ሁሉ ሲያደርግ ምዕመኑ ውስጥ ውስጡን መረጃው እየደረሰው እና እየተደረገ ያለው ነገር እየገባው መጣ፡፡ ከዚያ ነገሮች እየከረሩ ሲመጡ የተቃወሙትን ሰዎች ‹‹አሸባሪ›› ከማለት ይልቅ ብሎ በማሰብ ‹‹ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አቋማቸውን ለማራመድ የሚፈልጉ ሰዎች ›› በማለት ስም የመለጠፍ ስራ በመስራት የእሱን እውነተኝነት የማረጋገጥ ስራ አከናወነ ይህም አልተሳካም ፤ በስተመጨረሻ ግራ ሲገባው እንደ ሌባ በለሊት የራሱን ሰዎች በማሰማራት መረጃ ፍለጋ የገዳሙን 65 ሺህ አካባቢ የሚገመት ገንዘብ ዘረፈ እጅጉንም አባቶች አቋማቸውን እንዲለውጡ የማስፈራራት ስራ አካሄደ ፤ አሁንም የተገኝ ውጤት የለም  ፡፡

በስተመጨረሻ ከጎንደርና ከአካባቢው በሺህ የሚቆጠር ምዕመን ወደ ወልቃይት የስኳር ፕሮጀክት ስፍራ  አካፋ ፤ ዶማ ፤ ጦር ይዞ ሲነጉድ የዛኔ ‹‹ቆይ ረጋ በሉ በጠረጴዛ ዙሪያ እንነጋገር ፤ መፍትሄ ይኖረዋል›› በማለት እየሄደ ያለው መንገድ ወዴት እንደሚወስደው ተመልክቶ ያበጠ ልቡ ትንሽ ተንፈስ አለለት ፤ ይህን መንገድ ነው የማህበረ ቅዱሳን አጥኚ ቡድን ‹‹ችግሩን ለመፍታት የተሄደበት መንገድ የአግባብነት ጥያቄ የሚያስነሳ ›› በማለት የጠየመ ጽሁፍ በሪፖርቱ ላይ ያካተተው፡፡  ይህን መናገር ወይም አለመናገር ተገቢ ነበር ፤

3.     የጥናቱ ውስንነት

1.      ሪፖርቱ ሲጀምር ‹‹ካለፉት ከሁለትና ከሶስት ወራት በፊት ከዋድባ ገዳም ጋር በተያያዘ መንግስትና በገዳሙ መካከል አለመግባባት ተከስቷል›› በማለት ይጀምራል ፡፡ ከመጋቢት 25-30 2004 ዓ.ም ድረስ 5 የሚያህሉ የማህበረ ቅዱሳን አባላትን እውነታውን ለማጣራት የልኡካን ቡድን አባላቱን ወደ ቦታው እንደላከ ያስረዳል ፤ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ ቢኖር የጥናት ቡድኑ የምን አይነት ሙያ ባለቤት እንደሆኑ የተገለጸ ነገር አለመኖሩ ነው  ፤ ቡድኑ ይህን የሚያህል ትልቅ የስኳር ፕሮጀክት ገዳሙ ላይ የሚያሳድረውን ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ጉዳቶችን የማውጣት ብቃቱ ምን ያህል ነው ? ፤ ይህ የጥናት ቡድን የሙያ ስብጥራቸው ምን ይመስላል ? እንደእኛ ሀሳብ በተለይ የዚህ ቡድን አባላት  በምህንድስና ትምህርት የተማሩ በሙያውም የረዥም ጊዜ ልምድ ከሌላቸው መንግስት የሚሰራውን ስራ እና ፕሮጀክቱን የመገምገም ብቃታቸው ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ይመስለናል፡፡ የሚያቀርቡትንም ሪፖርት ለመቀበል አዳጋች ይሆንብናል ፡፡ ለዚህ እንደ ማሳያ ለማንሳት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ለምትሰራው ግድብ ሱዳንና ግብጽ የሚሰራውን ፕሮጀክቱ ሀገራቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽህኖ ለመገምገም  በዓለም አቀፍ ደረጃ በሙያው ላይ በርካታ ዓመታትን ያሳለፉና የመመዘን ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች  በማካተት የሚገኝውን ጥቅምና የሚያመጣው ጉዳት  የማጥናት ስራ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ እነርሱ በሀገራቸው በቂ  በምህንድስና የተማረ ሰው አጥተው ሳይሆን የተሻለ ውጤት ያለው የጥናት ውጤት ማግኝት በመፈለጋቸው ነው ይህን ሊያደርጉ የቻሉት ፡፡ አሁንም ማህበረ ቅዱሳን መጀመሪያ ልኡካን ቡድኑን ከመላኩ በፊት  ይህን ማየት መቻል ያለበት ከመሆኑም በተጨማሪ የሰዎቹን የትምህርትም ሆነ የስራ ሙያ ብቃታቸውን ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ መቻል አለበት ብለን እናምናለን ፤ የማህበሩ አባላት ሆነው ይህን ስራ መስራት የሚችሉ ባለሙያዎች ካሉ መልካም ፤ ካልሆነ ሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያሉ ባለሙያዎችን በማማከር ጊዜ ወስዶ ጥናቱን ቢያሰራ መልካ ነበር የሚል አስተያየት አለን፡፡ የ8 ቢሊየን ብር ፕሮጀክትን ገምግሞ ሪፖርት ማቅረብ  ከተለያዩ ባለሙያዎች ስብጥር ካልሆነ ከበድ የሚል ይመስለናል፡፡ የተላኩት ሰዎች ያላቸው የትምህርት ደረጃ ምንድነው? ሪፖርቱ የልኡካኑን ማንነት ባይገልጽ እንኳን የትምህርት ደረጃቸውንና ከዚህ በፊት ስለሰሩት ስራ ጥቂት ማለት ነበረበት ፤ ይህንንም ፕሮጀክት የመገምገም ብቃታቸውን ሲጀምር ማስቀመጥ ነበረበት ብለን እናምናለን፡፡ ፕሮጀክት በባለሙያዎች ቢጠና ሪፖርቱ በመንግስት ዘንድ ተዓማኒነቱ የጎላ ይሆናል ፡፡

2.     ሪፖርቱን ያቀረቡት ሰዎች ስራውን ሲጀምሩ ከመንግስት አካላትና የተሰጣቸውን መረጃ መቶ በመቶ በማመን ነው የጥናቱን ስራ መስራት የጀመሩት ፤ አምኖ መጀመር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ፤ የተሰጣቸው መረጃ ትክክለኛነቱን በምን ማረጋገጥ ቻሉ ?

3.     የልኡኩ አላማ የሚታዩ ችግሮችን ብቻ ለመመስከር የሄደ ነው የሚመስለው ፡- ይህ ደግሞ ፕሮጀክቱ እየተሰራ ሳለ ይሁን ተሰርቶ ሲያልቅ የሚመጣውን ለውጥ ግምት ውስጥ ያስገባ ስራ መስራት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡

4.    የጥናት ቡድኑ ፕሮጀክቱ ከተሰራ በኋላ የሚያመጣውን ተጽህኖ (Project Overall impact) ማሳየት አልቻሉም

a.   About   Urbanization ?

b.    መንፈሳዊ ህይወት ላይ የሚያመጣውን ችግር

c.     ስነ ምህዳር ተጽህኖ ፡- ይህ ፕሮጀክት ተሰርቶ ቢያልቅ አሁን የምናውቀው ክብረ ገዳማት ዋልድባ ስነ-ምህዳሩ ሳይቀየር  ይኖራል ?

d.     ፕሮጀክቱ ብህውትናው ህይወት ላይ የሚያመጣውን ችግር

e.     የአባቶቻችን የተመስጦ ህይወት ምን ሊመስል ይችላል ? የሚሉትን ጉዳዮች መመልት አልቻለም

5.     የተነሱበት የጥናት ወሰን (scope) በጣም ጠባብ በመሆኑ በፕሮጀክቱ ላይ አስፍቶ ያለመመልከት ችግር ይታያል ፤

6.    የመጀመሪያው ገጽ ላይ ጥናቱን ሲያካሂዱ የገዳሙን አባቶች ፤ የፕሮጀክቱን ኃላፊዎች እና የተለያዩ የማህበረሰቡን ክፍሎች ሀሳብ እንደያዘ ያስረዳል ፤ እዚህ ላይ ግን እነዚህ አካላት ብቻ መሰረት አድርጎ ጥናት ማካሄድ ጥናቱን ሙሉ ያደርገዋል የሚል እምነት የለንም ፤ ቢያንስ በየስልጣን ተዋረዱ የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣኖችን ታሳቢ ማድረግ ይገባዋል ብለን እናምናለን፡፡ ፕሮጀክቱን ካዘጋጀው አካል ጀምሮ ፕሮጀክቱን በኃላፊነት ወስዶ እስከሚያስፈጽመው አካል ድረስ ፤

7.     መንግስት ስራውን ከጀመረ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የሰራውን ስራ አይገልጽም ፤ እስከ አሁን ምዕመኑም ሆነ የገዳሙ አባቶች ያሳለፉትን ውጣ ውረድ አይዳስስም ፤ መንግስት በመገናኛ ብዙሀን የተናገራቸውን ነገሮች የአጥኚ ቡድኑ በአካል ሄዶ የተመለከተውን ነገር በንጽጽር ለማቅረብ አይሞክርም ፤ መንግስት እያካሄደ ያለውን ተግባር ገዳሙ ውስጥ የሚገኙት አባቶች ምን ያህል ጉዳት ይድረስባቸው ፤ አይድረስባቸው ለመናገር አይደፍርም ፡፡

8.    ይህን ጥናት ማህበረ ቅዱሳን ብቻ ባያጠናው መልካም ነበር ፤ የስኳር ልማቱ በገዳሙ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መጀመሪያ የሚመለከታት የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገዳማትና አድባራት መምሪያ ነው ፤ ነገር ግን ጉዳቱ ሳይታያቸው ቀርቶ ሳይሆን ጉዳዩን ቤተክህነታችን አይቶ ዝም ቢል ማህበረ ቅዱሳን ቦታው ድረስ ሄዶ መመልከት መቻሉ እና የአቅሙን ሪፖርት ማቅረቡ ሊያስመሰግነው ይገባል ፤ ይህ ነገር መልካም ቢሆንም የተሻለ ጥናት ለማድረግ ከመንግስት እውቅና እስከተሰጠው ድረስ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ማለትም  ፤ ከባህልና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት(የህዝብ ተመራጮች) ፤  ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፤ ከአማራ እና ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት ፤ ከከፍተኛ የሀይማኖት አባቶች ፤ ከታዋቂ ሰዎች ፤ ግድብ ስራ ከሚሰሩ ከባለሙያዎች(Engineers) ፤ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ፤ ፕሮጀክቱን ከቀረጹት ባለሙያዎች ፤ ፕሮጀክቱን ከሚያስፈጽሙት ሰዎች በተዋቀረ ኮሚቴ ጥናቱ ረዘም ያለ ጊዜ ተወስዶ ቢካሄድ የጥናቱ ተቀባይነቱ በመንግስት የጎላ ይሆናል የሚል አመለካከት አለን ፤ ያለበለዚያ ግን እንከን የማይወጣለት ንጹህ ስራ መስራት ቢቻል እንኳ ማህበረ ቅዱሳን ያቀረበውን ሪፖርት በቤተክህነቱም ሆነ በመንግሰት ዘንድ ተቀባይነቱ ላይ ጥያቄ ይጭራል፡፡

9.    አቶ አባይ ጸሀዬ ፓርላማ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት ከአካባቢው የሚነሱ ወደ 7ሺህ አባወራዎች(20 ሰዎች) እንዳሉ አስረድተዋል ፤ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ደግሞ ጠቅላላ ነዋሪዎቹ በቁጥር 20 ሺህ እንደሚደርሱ ዘግቧል ፤ የጥናት ቡድኑ እነዚህን አስመልክቶ ከኢንጅነር ይስሀቅ እንደተረዳው እነዚህ ሰዎች የት እንደሚሰፍሩ ግልጽ ሆኖ የተቀመጠ ነገር እንደሌለው በመላምት የተነገራቸውን በመላምት አስቀምጠውታል ፤ ጥናትን ለማቅረብ ደግሞ ደግሞ የሚጨበጥ ነገር መኖር አለበት ፤ ይህን የሚያህል ፕሮጀክት ላይ የእነዚህ ሰዎች ማረፊያ ታሳቢ ሳይደረግ የተሰራ ነው ለማለት ይከብዳል ፤ ሚኒስትሩም የነዋሪዎች ማረፊያ መሰረተ ልማት ችግር እንደፈጠረባቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የ9 ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ገልጸዋል ፤ እዚህ ላይ ከኢንጅነሩ ፤ ከጥናት ቡድኑ እና ፕሮጀክቱ መሀል ክፍተት ያለበት ይመስለናል፡፡ የስኳር ፕሮጀክቱ ሙሉ ጥናት የአጥኝው ልኡካን ቡድን ጋር እጁ ላይ እንደገባ እርግጠኛ ሆነን መናገር አያስችለንም  ፤ ለምን ቢባል ? መላምት የማያስፈልጋቸው ነገሮች በመላምት የተቀመጡበት ሁኔታ ሪፖርቱ ላይ ይታያል፡፡  በዚህ ምክንያት የጥናቱ ሙሉ ሰነድ እጃቸው ላይ መግባት መቻሉን ጥያቄ ይጭራል ፤ በሪፖርተር ጋዜጣ እንዳነብነው አባይ ጸሀዬ ሲናገሩ እንደሰማነው ነዋሪዎቹ ሲነሱ አብረዋቸው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፤ ጤና ተቋማት እና ቤተክርስትያኖች ይነሳሉ ፤ እነዚህ አካባቢ ደግሞ 18 ቤተክርስትያናት እንደሚኖሩ ከገዳሙ አባቶች እና ከአቦይ ጸሀዬ ለማወቅ ችለናል ፤ የማህበሩ ሪፖርት ግን 3 ብቻ ብሎ ያስቀምጣቸዋል፡፡ ውሀ የሚያጥለቀልቃቸው 3 ሊሆኑ ይችላሉ የሚነሱት ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙት ደግሞ 15 ናቸው ፤ እነዚህን የመዳሰስ ሁኔታ በሪፖርቱ ላይ አይታይም፡፡

10.   ስለ አጽመ ቅዱሳን የቀረበው ሪፖርት ላይ ፡- የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊ አቶ አቦይ ጸሀዬ 27 የሚደርሱ አጽሞች እንዳነሱ እና 20ዎቹ ባለቤት እንደተገኝላቸው በክብር እንዳለፉ በኢቲቪ ቀርበው ሲያስረዱ ነበር ፤ ሪፖርቱ ላይ ከኦፕሬሽን ኃላፊው አቶ ጌታቸው እንዳሉት ቁጥሮቹን 20 ሆነው እናገኛቸዋልን ፤ መንግስትን ከሚወክሉ ባለሙያዎችና ባለስልጣናት በአንድ ምላስ ሁለት የሚጋጭ ነገር እየሰማን ነው ፤ አቶ አባይ ጸሀዬም ሆኑ አቶ ጌታቸው መንግስትን ወክለው የሚናገሩ ይመስለናል ፤ እዚህ ላይ ለእኚህ የኦፕሬሽን ሀላፊ የአቦይ ጸሀዬ የተናገሩትን ነገር ማንሳት አልተቻለም ነበር ወይ ? ወደ ቦታው ሲሄዱ መንግስት በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ያቀረባቸውን ዘገባዎች ጠንቅቀው ቢያውቁት እየተወራ ያለውን እና እየተሰራ ያለውን ለማነጻጸር ይረዳቸዋል የሚል አስተያየት አለ ፤  የገዳሙ አባቶች የሚሉትን ሳንጠቅስ ማለት ነው፡፡

11.     አቶ አባይ ጸሀዬ እስከ አሁን የፈረሰ አንድም ቤተክርስትያን የለም ስለሚፈርሱ ቤተክርስትያኖች ወደፊት ከእምነት አባቶች ጋር እንነጋገርበታለን ብለዋል ፤ በዚህ ላይ የተባለ ነገር የለም ፤ በዚህ ላይ እንነጋገርበታለን የተባለው ቤተክርስትያኖቹን ስለማፍረስ ሂደት ላይ ነው ወይስ ሌላ ነገር?

12.   የዚህ ፕሮጀክት ስራ ሲከናወን መንግስት የገዳሙ መነኮሳት ብሎ የሰበሰባቸው አባቶች በቴሌቪዥን ተመልክተን ነበር ፤ እነዚህ አባቶች ገዳሙን የሚወክሉ ናቸው ወይስ አይደሉም ? በሪፖርቱ ላይ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ፕሮጀክቱን የሚቀበሉ እና የማይቀበሉ መነኮሳት እንዳሉ እናውቃለን ፤

13.   የማህበሩ አስተያየቶች ፡- ይህ አስተያየት በጣም ያነሰ ሆኖ አግኝተነዋል ፤ ለ5 ቀናት ዋልድባ ድረስ በመሄድ ችግሩን በማጥናት አደጋውን ሙሉ በሙሉ በማይገልጽ መልኩ የተቀመጠ ይመስለናል ፤ አጥኝ ቡድኑ የራሱን አስተያየት ከመስጠት ይልቅ አባቶች እንዲህ አይነት ስጋት አላቸው እያለ የእነርሱ አንደበት ላይ አስታኮ ሪፖርን ያቀረበበት ሁኔታ ይታያል ፤ ከተለያዩ ሚዲያዎች የሰማነው የገዳሙ አባቶች ያስቀመጡት ፍራቻን በሪፖርቱ በጠቅላላ አልተዳሰሰም ፤ ወይ የገዳሙ አባቶች ትክክለኛ መረጃ አልተናገሩም ወይም ደግሞ አጥኚ ቡድኑ በፍራቻ ማቅረብን አልወደደም ፤ እውነታውን ብቻ ማቀመጥ መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት የለንም፡፡

14.   የሪፖርት አቀራረብ ፡- ሪፖርት አቀራረቡ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም ፤ ሪፖርቱ ማካተት ከሚገባቸው ነገሮች በቅደም ተከተል መከተል ይገባው ነበር ፤

a.     ስለ ዋልድባ ትንሽ መግቢያ፤(ለ9 ገጽ ሪፖርተ 3 ገጽ መግቢያ መቅረብ የለበትም)

b.    መንግስት ስለሰራው ስራ ፤- መንግስት እስከ አሁን በገዳሙ አካባቢ ምን አይነት ስራ አከናወነ ፤ አሁንስ ምን እየሰራ ይገኛል ፤ በቦታው ላይ ስለተሰሩት ካምፖች ፤  ……. ሌላም ነገሮችን

c.     በልኡካን ቡድን ውስጥ ስለተካተቱት ሰዎች ጠለቅ ያለ መረጃ (ማንነታቸውን ማወቅ ባንፈልግ እንኳን የትምህርት ደረጃቸው ፤ ከዚህ በፊት የሰሩትን ፕሮጀክት ፤ ያላቸውን የስራ ብቃት እና መሰል መረጃዎችን መገለጽ ነበረበት ፤ እነዚህ ነገሮች በግልጽ ካልተገጹ ሙያ የሌላት ሴት የሰራችው ወጥ እንዳይሆን )፤

d.     የጥናቱን አላማ እና ግቡንም ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ አለበት ፡- መነሻውንና መድረሻውን የሚፈለገውን ውጤት ፤ ጥናቱን የሚያካሄድበት እና ያካሄደበት መንገድ መቀመጥ መቻል አለበት..

e.      ፕሮጀክቱ ለገዳማውያን መልካምም ሆነ የሚጎዳ ነገር ካለው ጥናቱ  በግልጽ  ማስቀመጥ አለበት እንጂ የገዳሙ አባቶች እንዲህ አይነት ስጋት አለባቸው ፤ እንዲህ አይነት አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል እያለ የጥናት ቡድኑ መናገር የፈለገውን ነገር በመናገር እውነታውን  በአባቶች ፍራቻ ላይ መሰረት አድርጎ ማስቀመጥ የለበትም ፤ ጥሬ እውነቱን ማስቀመጥ መቻል አለበት   ፡፡

f.      የጥናት ቡድኑ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያየውን የተመከተውን ነገር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የመፍትሄ አቅጣጫ መጠቆም መቻልም አለበት ፡- ጥናት አንዱ ጥቅሙ ችግሩን አይቶ ተገቢ መፍትሄ ለመስጠት ነው ፤ እንደ እኛ ዩኒቨርሲቲዎች የመመረቂያ ጽሁፍ መደርደሪያ ላይ የሚቀመጥ መሆን መቻል የለበትም ፤ በዚህ ጊዜ ማህበረ ቅዱሳን ዋልድባ ላይ ያንዣበበውን ችግር ጥናት አድርጎ ነበር ለማለት ሳይሆን አጥንቶ የመፍትሄ ሀሳብ አቅርቦ ነበር ቢባል መልካም ነው፡፡

g.      ጥናቱ እነዚህ ነገሮች ቢስተካከሉለት የገዳማውያኑን ስጋት ያስቀራል ብሎ አማራጭ መፍትሄዎችን ማስቀመጥ መቻል  አለበት

h.    በስተመጨረሻም የጥናት ሰነድ  ሊያሟላ የሚያስፈልጋቸውን  ነገሮች ሁሉ ማሟላት አለበት ፤

15.   በማጠቃለያው ላይ ማህበሩ ያዘጋጀው ሪፖርት መንግስት አካላት ጋር ይዞ ሄዶ እንደተወያየ ይገልጻል ፤ ‹‹ምንም እንኳን ህዝቡንና መነኮሳቱን ያሳዘነ ድርጊት ቢከሰትም የተፈጠረውን ችግር በውይይት ለመፍታት በመንግስት በኩል ዝግጁነት እንዳለ ለመረዳት ችሏል›› ይላል ፡፡ ምን አይነት ችግር ነው ህዝብና መነኮሳትን ያሳዘነው ? ሪፖርቱ ምንም ሳይናገር ለማጠቃለል እና ለመደምደም ይጥራል፡፡  በመሰረቱ ማጠቃለያ ማለት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን ሪፖርት በመጭመቅ ገላጭ በሚያስብል መልኩ ሀሳብ የሚቀርብበት አንቀጽ ነው፡፡  ነገር ግን ‹‹ህዝቡንና መነኮሳቱን ያሳዘነ ተግባር›› በግልጽ በሪፖርቱ ላይ  የቀረበበት ቦታ የለም ፤ ሪፖርቱ ላይ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ሲደረግ የነበረው እና የተደረገው ነገር ግልጽ ባለ መልኩ ሳይቀመጥ ፤ ህዝብ ያዘነበት ተግባር ፤ መነኮሳቱ የተከፉበት ምግባር ሳይጻፍ መደምደሚያው ላይ ችግሩን በውይይት ለመፍታት በመንግስት በኩል ዝግጁነት እንዳለ ይነግረናል ፤ ለምን እያንዳንዷ ነገር የመንግስት ? የህዝብ ? ወይስ የመነኮሳቱ ? ችግር እንደሆነ አልተገለጸም ፤ በስተመጨረሻ መፍትሄውን ለማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን በ3ወራት ውስጥ የተከናወኑትን እያንዳንዷን ነገር መገለጽ ነበረበት የሚል እምነት አለን ፤ የሆነውን ካልገለጹ ደግሞ የተፈጠረውን ችግር እና መናገር የፈለጉትን  የመፍትሄ ሀሳብ አንድ ላይ መዝለል ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፡፡

16.   በሌላ በኩል በማጠቃለያው ላይ ‹‹ፕሮጀክቱ በገዳሙ እና በገዳማውያኑ ላመጣው ጉዳት ተገቢውን ካሳና ተለዋጭ ቦታ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነም ተገንዝቧል ፤ ስለዚህም በቤተክርስትያኗ በኩል አስፈላጊው አካል ተመድቦ ውይይት እንዲጀምር በተደረገው ውይይት ተገልጿል›› በማለት ያስቀምጣል፡፡ይህ ነገር ሪፖርቱ ላይ ግልጽ አይደለም ፤ መንግስት ላረሰው የገዳሙ ይዞታ ነው ተለዋጭ ቦታ የሚሰጠው? ወይስ ይፈርሳሉ ተብለው ስለታሰቡት አብያተክርስትያናት ? መንግስት ለሰራው ወይም ለመስራ ላሰበው  ስራ የትኞቹ ናቸው ካሳ የሚያስፈልጋቸው ? ለፈነቀረው የቅዱሳን አጽም? ያለአግባብ የተንገላቱን መነኮሳት ? አልገባንም፡፡ ስለ ‹‹ካሳ›› ከተነሳ የመጀመሪያ ስራ የሚሆነው በቦታ እና በብር ካሳ የሚጠየቅባቸው እና የማይጠየቅባቸው ተብለው መለየት መቻል አለባቸው ፤ ለምን ቢባል ይህ የእምነት ጉዳይ ነው ፡፡

4. ማጠቃለያ

በአሁኑ ሰዓት ለልማት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የከተማዋን ደረጃ ለማሻሻል ነዋሪዎችን በማማከር የሚነሱበትን እና ቦታው የተሻለ ህንጻ የሚሰራበት ሁኔታ እየተመለከትን ነው ፤ ይህ መልካም ሆኑ ሳለ መንግስት ዋልድባን የሚያህል ክብረ ገዳማትን ግሬደር አስገብቶ ሲያርስ ቤተክርስትያኒቱን የሚወክሉትን አባቶችንና የገዳሙን መነኮሳት  አለማማከሩ እጅጉን አስገርሞናል ፤ አዲስ አበባ ላይ የአንድ ሰው ቤት ለማፍረስ ከ10 ያላነሱ የቀበሌ ስብሰባዎች ቀድመው ሲደረጉ ዋልድባን የሚያህል የቤትክርስትያናችን ዓይን ገዳምን ለማረስ ለማማከር አንድ እርምጃ አለመሄዱ መንግሰት ለእኛ ያለው የንቀቱን መጠን ያመላክተናል፡፡‹‹ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ›› ይላል ያገሬ ሰው፡፡  መንግስት ለቤተክርስትያናችን ያለው እይታ ምንም ያህል የተዛባ ቢሆንም ዋናው  ‹‹እኛ ለራሳችን የምንሰጠው እይታ እርሱ ከሚሰጠን አይነስ›› ነው ቁም ነገሩ  ፤ ማንም በሸውራራ አይኑ ይመልከተን የእሱ መመልከት የእኛን እይታ ላይ የሚፈጥረው ችግር የለም፡፡

 በተጨማሪ ግድቡ በቦታው ላይ በመሰራቱ የውሀው መጥለቅለቅ ችግር ያጋጥማል ፤  መንግስት ፕሮጀክቱ ላይ እንዳሰበው ሳይሆን ዝናብ እንደዘነበ መጠን የውሀው መጠን ከፍ ሊል ይችላል ፤ በዚህ ጊዜ ማንም የማይቆጣጠረው የሩቅ ምስራቆችን አይነት ጎርፍ ይከሰታል ፤ ብዙ መቶ አመታትን በሰላም የዘለቀ ገዳም የአንድ ቀን የጎርፍ ሲሳይ እንዳይሆን ስጋት አለን ፤ ይህ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም ፤

እኛ መፍትሄ ብለን የምናስቀምጠው ነገር ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያላትን የውሀ ሀብት የተጠቀመችው ከ10 ከመቶ በታች ነው ፤ ስለዚህ ቀሪ 90 በመቶ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ላይ ወንዞች እንዳሻቸው የሚፈሱበት አካባቢዎች በርካታ ናቸው ፤ ስለዚህ የቦታም ሆነ የውሀ እጥረት የሌለባት ሀገር ስለሆነች መንግስት ፕሮጀክቱን ወደ ሌላ ቦታ ያዛውረው ዘንድ ምክራችን ነው፡፡ ይህ ጉዳይ 1000 ሺህ ጊዜ ሪፖርት ቢሰራበት አሳማኝ ነገር ለማምጣት ስለሚከብድ ፕሮጀክቱ መቆም አለበት የሚል አቋም አለን፡፡ያለበለዚያ ግን ከእግዚአብሔር ጋር እንደምትገዳደሩ እወቁት ፤

በብልሀት የተሰራው ሪፖርት ከነችግሩ ጥሩ ነው ፤ አንድ አይናማ በአፈር ስለማይጫወት ሪፖርቱ ላይ ፍርሀት ፤ ብልጠት ፤ ጥንቃቄ ፤ ከመንግስትም ሆነ ከቤተክህነቱ ጋር ላለመጋጨት የተደረገ አካሄድ  መልካም ነው፡፡

ያቀረብነውን ሀሳብ ብቻ  መሰረት አድርገው አስተያየትዎን ይጻፉልን

2 comments:

  1. ምን ታዘብኽ በሉኝ፦ ፍርሃት ተራ-በ-ተራ!

    ማበሩ መንግሥትን ሲፈራ፣ ይህ ጣፊ ደግሞ ማበሩን እንደፈራው! እኔም'ንጂ በተራየ ጣፊውን ፈርቼ በ"ስምአይጠሩ" (በአኖኒም) ማለፌ። ምን ይሻለናል እናንተው? እንዴት አድርገን ከፍርሃት እንላቀቅ?

    ReplyDelete
  2. Thank you both. There are so many things to consider as to what to say or to write. The MK report is clear to those who are aware of the issues in Waldba. Your comments are somehow good. On the other hand, as you all know this is a very sensitive issue and needs a very careful and wise approach. We can not just confront or take spontanous measures as it might aggravate the damage to either sides. It is always one step at a time, and God willing we shall see a divine intervention; we do our part and the rest is upto the Almighty God! May our good Lord bless us all!

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤