Thursday, June 28, 2012

የቅዳሜው በዓዲርቃይ የተካሄደው ስብሰባ ዘገባ

የዋልድባ ገዳም ህልውና ይከበር! 

 • "እርሶ እኛን አይወክሉንም እና ልንሰማዎትም ሆነ ቡራኬዎትን አንቀበልም" ከመነኩሳት ወገን ለብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ
 • "ልማቱን በግድም በውድም መቀበል ይኖርባችኋል" የመንግሥት ተወካይ
 • "በዋልድባ ገዳም ምንም ድርድር አናደርግም" የአካባቢው ነዋሪ
 • በርካታ ወጣቶችም በመንግሥት ታጣቂዎች ታፍሰው ተወስደዋል
ባለፈው ቅዳሜ በዓዲርቃይ ከተማ ላይ በዋልድባ አካባቢ ሊሰራ በታቀደው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ዙሪያ የአካቢው ነዋሪዎችን፣ የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤልሳዕ በተገኙበት፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የማኅበረ መነኩሳቱ ተወካዮች በተገኙበት እንዲሁም ከቤተክህነት ተወካዮች በተገኙበት የማስፈራራቱ እና በግድ የማሳመኑ ስራ እንደቀጠለ ነው። ሰሞኑን በደረሱን መረጃ መሰረት መንግስት ለልማቱ እፈልጋቸዋለው ከሚላቸው የዋልድባ ገዳም ክልል ውስጥ የሚፈርሱን መካናት የሚከተሉት ናቸው፡

 • ከአበረንታት
  • ማርገፅ ቅዱስ ሚካኤል  ቤተክርስቲያን
  • ድል ሰቆቃ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን
  • እጣኑ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም  ቤተክርስቲያን
  • ሙሉ ቤት ቅዱስ ሚካኤል  ቤተክርስቲያን
 • ከአባ ነፃ
  • ዲዋር ግዛ ቅዱስ ተክለሃይማኖት  ቤተክርስቲያን
  • ማይ ሸረፋ አቡነ አረጋዊ  ቤተክርስቲያን
  • አዲ ፈረጅ አብዮ እግዚ  ቤተክርስቲያን
  • ማይ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ  ቤተክርስቲያን
  • ታች እጣኖ ቅዱስተ ማርያም  ቤተክርስቲያን
  • ላይ ኩርማ አቡነ አረጋዊ  ቤተክርስቲያን
  • ጎድጓድ ቅዱስ ጊዮርጊስ  ቤተክርስቲያን
  • ቃሊማ አቡነ ሳሙኤል  ቤተክርስቲያን
  • ቃሊማ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን
  • ቃሊማ ቅድስት ሥላሴ  ቤተክርስቲያን
  • ማይ ዓርቃይ ቅዱስ ሚካኤል  ቤተክርስቲያን እና ሌሎችም ስማቸው ያልተገለጸ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚነሱ ዘገባው ደርሶናል።
ለዚህም ነው የገዳሙ መነኩሳት ይልቁንም በሰቋር ኪዳነ ምሕረት የሚገኙት መነኩሳይት (አነስት) ታላቅ ተጋድሎ እያደረጉ የሚገኙት፡፡ እንደ መነኩሳይቱ አነጋገር በመጀመሪያ እኛን ገድላችሁ መሬቱን ማረስ ትችላላችሁ አለበለዚያ ግን እኛ በሕይወት ቆመን ቅዱሳን አባቶቻችን በደማቸው እና በአጥንታቸው ያስከበሩት ገዳም በኛ በልጆቻቸው በአረማውያን ሊወሰድ አይችልም በማለት በታላቅ ተጋድሎ ላይ ይገኛሉ።  ". . .የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ. . ." መጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ ፳ ፥ ፫ የናቡቴ ቃል ዛሬም በእነዚህ መነኩሳይት አድሮ ለእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ያስተጋባል የአባቶቻችን ርስት እንሰጥ ዘንድ ከእኛ ያርቅ በማለት።

እንደመረጃ ምንጫችን ከሆነ በስብሰባው ዕለት የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በቦታው ተገኝተው ቡራኬ ለማድረግ ሲነሱ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል "እርሶ እኛን አይወክሉንም" በማለት ተሰብሰባዊ ገዳማውያኑ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ በከፍተኛ ደረጃ በቦታቸው ያልተገኙትን አረጋዊ ሊቀ ጳጳስ ኮንነዋቸዋል፣ በተያያዘ ዜና በስብሰባው እለት የቤተክህነቱም ተወካዮች በቦታው ተገኝተው ገዳማውያኑን እና የአካባቢውን ነዋሪ ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ እንደነበር እና በመጨረሻ የመንግሥት ተወካዮች ቦታው እንደውም "የአማራ ክልል አይደለም" ይህንን በቀጥታ የሚመለከተው "የክልል ትግራይ" ነዋሪ ነው በማለት የስብሰባውን መንፈስ ወደ ዘር እና ጎሳ ሲለውጡት ተመልክተዋል። እነዚሁ የመንግሥት ተወካዮችም በግድም ይሁን በውድ ልማቱን መቀበል አለባችሁ የሃገራችን የሥራ አጥ ቁጥሩን በ50000 ይቀንሳል  በማለት ዲስኩራቸውን መስማት ለሰለቸው ተሰብሳቢ ሲያሰሙ ውለዋል።

በመጨረሻ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ተሰብሳቢው የማኅበረ መነኩሳቱ ተወካዮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ በኃላ ስብሰባ አትጥሩን አቋማችን የታወቀ እና አንድ ነው የአባቶቻችንን ርስት አትንኩብን፣ አጽመ ቅዱሳኑን አታፍልሱ፣ ካልጠፋ መሬት ለምን ወደገዳማን መጣችሁብን፣ እኛ ጉልበታችን መድኅኒዓለም ነው ያሻችሁን ማድረግ ትችላላችሁ መሬቱንም ስታርሱ እኛንም ገድላችሁ መሆን አለበት በማለት ከፍተኛ የሆነ ሁካታ ተነስቶ በስብሰባው ከተሳተፉትም አንሰበሰብም በማለት በውጭ ቁጭ ብለው ከነበሩ በተለይ ወጣቶችን የመንግሥት ታጣቂዎች በርካታዎችን ጭነው ለእስር ዳርገዋቸዋል በርካቶችም ሸሸተው ወደ ጫካ እንደገቡ ከአካባቢው ምንጮቻችን ገልጸውልናል። ማኅበረ መነኩሳቱም ምሬት በተሞላበት መልኩ ነዋሪዎችን "መጥታችሁ ቅርሶቻችሁን ተረከቡን" ሲሉ መሰማታቸውንም እነዚሁ ምንጮቻችን ገልጸውናል።

መንግሥትም በማናለብኝነት አብያተ ክርስቲያኑን እንደሚያፈርስ ሲገልጽ፣ የቤተክህነቱም ተወካዮች ተባባሪ ሆነው ለአብያተ ክርስቲያኑ መፍረስ አይነተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ በሌላ በኩል የዋልድባ ገዳም ማኅበረ መነኩሳቱ፣ የአካባዊ ነዋሪ በተለይ ደባቅ፣ ዛሬማ፣ ዓዲርቃይ፣ እና አካባቢው ላይ ያሉ የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች ከመንግሥት ሃህሎች ጋር ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት እየከፈሉ በሚገኙበት በዚህ ሰዓት እኛ እንደክርስቲያን አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል። በማንኛውም በጸሎትም በማቴሪያልም በገንዘብም በማንኛውም መንገድ ልንተባበራቸው እና ቅዱሱን ገዳማችንን የሊቃውንት መፍለቂያ እንዲሁም የበረካታ ዓይናማ መምህራንና የቤተክርስቲያን ሊቃውንት መገኛ የሆነውን ገዳም ልንታደግ ይገባል እንላለን። 

የአባቶቻችን አምላክ ድል የማትነሳዋ የተዋሕዶ እምነታችው በእኝም በልጆቻቸው ይደርብን አሜን።

4 comments:

 1. GOD give strength for our fathers,The idea of these project is not only to produce sugar but also to destroyed orthodox church.
  where they gotthe money to build these project?There are somthing at the back planning to destroyed orthodox church (our identities)
  Our power is GOD, and pray pray...............

  ReplyDelete
 2. ምንድን ነው ይሄ ነገር? እውን የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ለማድረግ እያሰበ / እየተንቀሳቀሰ ነው ??
  በጥንታዊት ኢትዮጵያ ይህ ይደረጋል ብሎ ለማመን ይከብዳል: ከሆነ ግን ......

  ReplyDelete
 3. ወቅታዊውን የዋልድባን ጉዳይ እየተከታተላችሁ ስለምታቀርቡልን እናመሰግናለን::ችግሩ የሁላችንም የተዋህዶ ልጆቸ በመሆኑ ከጸሎት ባሻገር እኛስ ምን እናድርግ? ሃይማኖት የለሹን መንግስት ትተን ቤ/ክ ዓናት ላይ የተቀመጡትም ዓላማቸው ቤ/ክ ማጥፋት ነው::ሃይማኖታችንን ሲበርዙና ሲከልሱ ዝም በመባላችው ነው ዛሬ ገድማትን ማቃጠልና ማረስ የጀመሩት::ከዚህ የባሰ ሳይመጣ ማድረግ የሚገባንን የእቅማችንን እንድናደርግ በመጀመሪያ አንገብጋቢውን የዋልድባን ገዳም ለማዳን በቀጣይ ደግሞ ቤ/ክንን ከመናፍቃን መሪዎች እጅ እንድትወጣ በተለይ እገር ውስጥ ያለነው በተግባር ልንገልጸው የምንችለውን መንፈሳዊ ግዴታችንን በግልጽ እሳውቁን ችግሩን እየሰማን ዝም ብሎ መቀመጥ ትልቅ የህሊና ወቀሳ ነውና::እምላከ ቅዱሳን ቤ/ክንን ይታደግልን::

  ReplyDelete
 4. የዋልድባ ነገር የሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ሁሉ አይን ነው እባካችሁን ያለውን ነገር ሁሉ ተከታትላችሁ አሳውቁን መቼም ካልጠፋ መሬት እንዴት ዋልድባ ለመንግስት ታየው ዓላማው ቤተክርስቲያንና ልጆቿን ለማጥፋት የታለመ መሆኑ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ወጣቱ ለሀይማኖቱ ያለውን ጥንካሬ ያሳየበት ወቅት ነው እግዚአብሔር ሁላችንንም በቸርነቱ ይጠብቀን እናንተንም ያበርታችሁ በሌሎች ሚዲያዎች ሁሉ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ያለውን ነገር በግልጽ እንዲያውቁ ብትጥሩልን አንዳንድ ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆሩ አባቶችን ብታነጋግሩና ኃሳባቸውን ብትገልፁልን ያለውን ነገር ለህዝብ ጆሮ እንዲደርስ ሊያግዝ ይችላል፡፡
  የበላይሰብ እመቤት ወላዲተአምላክ እሷ ትታደገን

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤