Tuesday, June 5, 2012

ታሪክ ራሱን ይደግማል


ያልተጻፈ የማይጻፍ ያልታየ ያልተዘገበ
          ምን አለና ነው ያልተነበበ
                   ገና ድሮ ጥንት በዘፍጥረት  በህገ ልቦናው
                   አዳም ከገነት የወጣ የተባረረው
                   የሞት ሞትን ሞቶ ከመቃብር የወረደው
                   ሄዋን ከክብር ወደ ጥልቅ የወረደችው
                   የአምላክን ትእዛዝ መርሳት መዘንጋቱዋ ነው
                   ያልተገባውን ስራ መፈጸሙዋ ነው
ታሪክ እራሱን እየደገመ ታሪክ ሆኖ ቢያልፍም
ያማይልፍ መስሎ በጊዜው ህዝብን ቢያስጨንቅም
ማለፍ ግን አይቀርም ይሄዳል
ጠባሳውን ጥሎ ባአዲስ ዘመን ይተካል
ዛሬም ታሪክ ራሱን ይደግማል


                   ጥንት ኤሳው የወደቀበትን
                   ሃብት ንብረት ተሩፋት  ያጣበትን
                   በሆዱ ተታሎ የተደለበትን
                   የእቆብ በክብር ድል የነሳበትን
                   ታግሎ ጥሎ ያገኘውን
                             የብኩርናን ክብር ሊያሳጡ
                             የበኩሮቹን በኩር ከልባችን ሊያወጡ
                             መንፈሳዊ ክብሩን አስዘንግተው
                             ንጹህ ምንጩን አደፍርሰው
                    ያንን መራራ ውሃ ሊያጠጡን
                   ውሃችንን መሪባ ውሃ ሊደርጉብን
                   ክብራችን ማንነታችንን  ሊነፍጉን
                   ተነሱ ዛሬም ሰይፋቸውን አነሱብን
                   ርስታችንን ለባእዳን አሳልፈው ሰጡብን
                   ባገራችን ስደተኛ መጻተኛ አደረጉን
           መነኮሳት ሳይታፈሩ ካህናቱ ሳይከበሩ
          ጎልማሶች አንእስት እንደሰው ሳይቆጠሩ
          ሲገፉ በአላውያን በግፍ ሲገፈተሩ
          አየናቸው ሲደግሙ ታሪክ ሲያመሰጥሩ
          የጥፋት አባቶቻቸውን ሲዘክሩ
በሄዋን ገላ የተሰወረው እባብ በክፋት                 
የህይወት በለስን ያስቀጠፋት
ዛሬም   የዘመኑ ሌጊወን
አሳድጎ አብዝቶ ልጆቹን
መጣ ለጥፋት ሊፈትነን
በልጆቹዋ ተመስሎ ገላውን አለስልሶ
አስመስሎ የበግ ለምድ ለብሶ
ልማት እያለ ፍሬ እናፍራ
እድገት ኢያለ ወሬ እያወራ
መጣ በድፍረት ሊያጠፋው
ርስታችን ያለ ዋጋ ሊያስቀረው
ዋልድባ ዋልድባ መሆኑን ዘነጋው
ያ የያዘው  ክፉ መንፈስ ልቡን ስለነሳው
ታሪክን ጠብቆ ማቆየት
ትውልድን ከትውልድ ማገናኘት

ህዝብን ከፈጣሪ ማስታረቅ
የክፉውን መንፈስማድቀቅ
                   በስነምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ
ንጹህ ዜጋን መፍጠር ማብቃት ለወግ
          ይህ ሁሉ በጎ ስራ እንደጥፋት ሆኖ  
          መልካም ማድረግ እንደወንጀል ገኖ
          ክስ ሆነባት ጥፋት
          እንደ መርገም ቆጠሩባት
የቆሙበትን ምድር እየረገሙ
ያረፉበትን መሬት እያደሙ
           ውለታዋን ዘንግተው በጎነቱዋን ረስተው
          ሊጠፉዋት መጡ ጦር ሰብቀው ዝናር ታጥቀው
          ያለፍርሃት በድፍረት ጉልበት አለን ብለው
እያወቁ እናዳላዋቂ ቢሆኑም
ታሪክን አንብበው ባይረዱትም
 ራእይ ህልማቸው ጥፋት ቢሆንም
መሽቶ ሲነጋ ግን ድል መሆን አይቀርም
ቢታመኑ በሰረገላ በጉልበታቸው     
ዘመን ተገልብጦ  ሃይል ቢሰጣቸው
          ትንቢቱ ሲፈፀም የአምላክ ቃል ኪዳኑ
          ቀኙን ሲዘረጋ ሲበራ ብርሃኑ
ይጣፋሉ እነርሱ ጉሙ ይገፈፋል
ያምላካችን ማዳን  በግልጽ ይነገራል
ዋልድባ አብረንታንት ዘላለም ይኖራል
ድንቅ ስራው ሁሉ ሲወሳ ይኖራል
እንደጥላ የሚያልፍ  ስልጣንን አለን ብለው
                    ወንበራቸው ጋሻ  ሃይል ሆኖላቸው
መንበሩን ቢነኩ በግፍ ቢደፍሩት
                              ቅዱሱን ቦታ አርሰው እሾህ ቢያበቅሉበት
                    የክፋትን ፍሬ ዘር ቢዘሩበት
                    እሾህ አሜኬላን አረም ቢያበዙበት
           የክፋትን ጥሪት ጎተራ ቢያስገቡት
 ወግማረጉን አሳጥተው ቢከትሙት
የቀደመክብሩን ቢነፍጉት
ዋልድባ ዋልድባ ነው
መሰረቱ አለት ንጹህ ደም ነው
ቀን ጊዜ ወራት ዘመን የማይሽረው
ማህተሙ በክብር የታተመው
ዋልድባ የሚለው ቃል የተፃ ፈው
በደም ቀለም ክታብ ነው
በሰማእታት ባባቶች ጸሎት ቡራኬነው
ዋልድባኮ ዋልድባ ነው ባለጊዜ የማይጥለው
ዘመን ቀናት ያልበገረው
          ጸሃይ ለባለግዜወች አድልታ
          ብርሃኑዋን ነፍጋን ተቆጥታ
          ለጥፋት  ተባባሪ ብትሆንም
          የመቅደስ መፍረስ ባይገዳትም
ዛሬ ባይሆን ነገ ሲነሳ እያሱ
በጸሎት ምህላ ሲከፈት መቅደሱ

ስልጣኑዋ ተነፍጎ ባለችበት ስትቆም
የሃፍረትን ሸማ  በአርምሞ ስትቆም
አሁን እናያለን በርቱ ክርስቲያኖች
የኢቶጵያ አኝታ የቁርጥ ቀን ልጆች
          የክረምት ጨረቃን ተከትለው ወጥተው
          እውነት ብርሃኑዋ ያዛልቃል ብለው
          የክረምት ጨረቃ ትርጉሙ ጠፍቶዋቸው
          ማሰተዋል ጥበቡ ተሰው ሮባቸው
ሊነጋ ሲል ጨልሞ በድቅድቅ ተውጠው
ተስፋ ያደረጉዋት ጨረቃ ረስታቸው
በአውሬየተበሉ እጅግ ብዙ ናቸው 
የክረምት ጨረቃ ሳይነጋ ከድታቸው
          ላታዛልቅ ቀድማ ወጥታ
 ብርሃኑዋን አሳይታ
          አባብላ በስሜት  አስኮብልላ አስወጥታ
          ስንቱን አስቀረችው ካልሆነ ስፍራ ካልሆነ ቦታ
አሁንም ዛሬ የተከተላችሁዋት
አምናችሁ እሱዋን የወጣችሁ የምታመልኩዋት
እባካችሁ ካለፈው ተማሩ
እንደወጣችሁ እንዳትቀሩ
ዋልድባ እኮ ዋልድባ ነው
ዘመን ግዜ የማይሽረው
          ለክብር ለመብቃት ካሰባችሁ
          ሰማእትነቱን ለመቀበል ከወሰናችሁ
          ከውስጥም ከውጭም ተገፍተን ተዘልፈን  
          የክፉወችን ወሬ በፍጹም ታግሰን
          ነገሳይሆን ዛሬ መነሳት አለብን
ምንመም እንኩዋን አምላክ ዝምቢልም
ምላሹን ለመስጠት ድምጹን ባያሰማም
ቃልኪዳን ስላለን በእምነት የከበረ
ሃይማኖት ስላለን በገድል የታጠረ
የባቶች አበውን ፍኖት ተከትለን
ዛሬ ባይ ሆን ነገ መፈጸሙን አውቀን
ነገ ሳይሆን ዛሬ መነሳት አለብን
          ክፉን ለመቃወም ክፋትን ለማስቆም
          መንገዱን ክፈቱ ካህናቱ ምሩን
መለከቱ ይነፋ ይጎሰም ነጋሪት
                    አዋጁን አውጁ ህዝቡንም አበርቱት
                    ውጡ ለሰአታት ቁሙ ለማህሌት
                    አውጡት ጸናጽሉን ከበሮውን ምቱት
ምህላ ጸሎቱን ዛሬውኑ አውጁት
ዋልድባን ታደጉ ልባችሁ ይከፈት
ምሩ መንገዱን አሳዩን
          እምቢ ብትሉ ግን ዛሬ ባትነሱ
          የሃሰትን እንባ ለቅሶ ብታለቅሱ
          ቸለል ብላችሁ ዋልድባን ብትረሱ
          ታሪክ ይፈርደናል ያስተዛዝበናል
          ጸሃይ የወጣችለት ትንሳኤ ይሆናል
ባለ በገና መዝሙረኛው
ክፉ መንፈስ ቀጥቅጦ የገዛው
አጋንንትን አስሮ ገደል የጣላቸው
ሰባት ሃብታት የተቸረው
ስለ እየሩሳሌም ሲናገር ሲያመሰጥር
ስለ ህልውናዋ ሲ,መመሰክር
          ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ ነው ያለው
          ስለቅድስት ሃገሩ ግድ ቢለው


         
           

           
         


           
           


No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤