Tuesday, July 31, 2012

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕመም የዋልድባ መነኰሳት ተጠያቂ ተደረጉ

  • READ THIS ARTICLE IN PDF.
  • ከአብረንታንት እና ማይ ለበጣ ሁለት መነኰሳት ወደ ማይ ፀብሪ ተወስደዋልበዶንዶሮቃ 50 በላይ የመነኰሳት እና መነኰሳዪያት ቤት በፖሊስ ተፈትሿል
  • ከፖሊሶቹ አንዲቱ ከጾታዋ የተነሣ ወደ ዋልድባ ለመግባት የማይፈቀድላት ሴት ናት
  • የአብረንታንቱ አባ ገብረ ሥላሴ ዋለልኝ እንደታሰሩ ናቸው
  • 49 ያላነሱ የቤተ ሚናስ መነኰሳት በፖሊስ ይፈለጋሉ
  • ‹‹እናንት ምታታሞች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመም ተጠያቂዎች ናችሁ›› /የማይ ፀብሪ ፖሊሶች/

(ደጀ ሰላም፤ ሐምሌ 23/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 30/ 2012)ምሽቱን ወደ ገዳሙ በገቡት ዐሥር ያህል የማይ ፀብሪ ፖሊሶችና ታጣቂዎች የተወሰዱት ሁለት መነኰሳት አባ ወልደ ጊዮርጊስ ከዋልድባ አብረንታንት መድኃኔዓለም፣ አባ ገብረ ማርያም ጎንዴ ከማይ ለበጣ (የማኅበረ መነኰሳቱ ሰፊው የአትክልት ቦታ) ናቸው፡፡ ሁለቱ አበው መነኰሳት በፖሊሶቹ ተይዘው ከመወሰዳቸው አስቀድሞ በኣቶቻቸው በፖሊሶቹ ፍተሻ እንደተካሄደበት ተገልጧል፡፡ ከፖሊሶቹ አንዲቱ ከጾታዋ የተነሣ ወደ ዋልድባ ለመግባት የማይፈቀድላት ሴት መኾኗ የወረዳው አስተዳደር ለገዳሙ ትውፊታዊ ሥርዐትና ክብር መጠበቅ ያለውን የወረደ ግንዛቤ የሚያሳይ ነው፡፡

Monday, July 30, 2012

ሰሚ ያጣው የዋልድባ ጉዳይ፥ እስራት፣ ድብደባ፣ እንግልት እንደቀጠለ ነው

በሰሜኑ የሃገረችን ክፍል በሚገኘው በታላቁ የዋልድባ ጉዳይ ላይ በርካታ የሆኑ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ ድርጊቶች በገዳሙ እና በገዳማውያኑ ላይ ሲደርስ ቆይቷል እንደቀጠለም ነው። እግዚአብሔር በእርግጥ በዚህ ታሪካዊና ቅዱስ ገዳም ላይ ፊቱን እንደማያዞር እምነታችን ቢሆንም ነገር ግን በገዳማውያኑ ላይ የሚደርስባቸው እንግልት በተፋጠነ ሁኔታ መቀጠሉ የችግሩን ግዝፈት ያሳየናል። ዛሬ ዛሬ ጭራሽ ሰውም በዜናው በመሰላቸት ይመስላል ዝምታው ቀጥሏል። እነዚህ ገዳማውያን ለሃገር ለወገን ለመሪዎች እንዲሁም በአጠቃላይ ለዓለም ሰላም በፀለዩ፣ እህል ስፈሩልን፣ ገንዘብ ቁጠሩልን ሳይሉ ከፈጣሪ ጋር ዕለት ተዕለት በጸሎት እና በስግደት በተገናኙ ምን በደል ኖሮባቸው ይሆን ይህ ሁሉ በደል፤ እንጀታቸው በቋርፍ ተጣብቆ የሚኖሩ አባቶቻችን ዛሬ ጀርባቸው በግርፋት፣ እጅና እግራቸው ለእግረ ሙቅ ለምን እንደተዳረጉ እንቆቅልሽ ሆኖብን ነው።

Monday, July 23, 2012

በዋልድባ መነኰሳት ላይ የሚካሄደው እስርና እንግልት ተባብሶ ቀጥሏል


  • አንድ የዋልድባ አብረንታንት ገዳም መነኰስ ወደ ማይ ፀብሪ ተወስደዋል።
  • የገዳሙ መነኰሳት የግዴታ መታወቂያ እንዲወስዱ ተደርገዋል።
  • ፓትርያርኩ ዕግድ የጣሉበት የጀርመን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሒዷል።
(ደጀ ሰላም፤ ሐምሌ 14/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 21/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ በሚያደርሰው ተጨባጭ አደጋና ታሳቢ ስጋቶች የተነሣ የፕሮጀክቱን አተገባበር በሚቃወሙ የዋልድባ ማኅበረ መነኰሳት ላይ የሚደርሰው እስር፣ እንግልትና ድብደባ ተባብሶ መቀጠሉን የሥፍራው ምንጮቸ ለደጀ ሰላም ገልጸዋል፡፡ በተለይም የፀለምት - ማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳደር በየጊዜው በመነኰሳቱ ላይ በሚወስደው የግፍ ርምጃ በሠቆቃ ውስጥ የሚገኙት ማኅበረ መነኰሳቱ ከሰኔ 21 - ኅዳር 8 ቀን የሚዘልቀው የገዳሙ የሱባኤ ወቅት እንደታወከ ተዘግቧል፡፡

Thursday, July 12, 2012

ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ August 12, 2012


ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ
በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ለምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች በሙሉ፥ እንደሚታወቀው ቅድስት ቤተክርስቲያን በበርካታ ዘመን ወለድ ችግሮች፣ በአስተዳር፣ እና በተለያዩ ተጽዕኖዎች ውስጥ እንዳለች ይታወቃል፥ ሆኖም ችግሮቿን በግልጽ ተነጋግሮ ለችግሮቹም የመፍትሄ ሃሳብ ማምጣትም፣ መፍትሄም መሆን የሚችለው ደግሞ አማኙ እንደሆነ እሙን  በመሆኑ ፤ ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ የዋሽንግተን ዲሲ ንዑስ ክፍል በመጪው 
ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. (August 12, 2012) በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው 
Saint George Ball Room and Conference room
4335 16th Street, NW.
Washington, DC 20011 ታላቅ መንፈሳዊ ዝግጅት አዘጋጅቷል፥ በዝግጅቱም ላይ በርካታ የቤተክርስቲያኒቱ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸውን ለመወያየት እና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በቦታው ተገኝተው ሃይማኖታዊ ግዴታዎትን እንዲወጡ በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም እንጠይቃለን። 
በዚህ ጉባኤ ላይ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ መምህራን፣ ዘማሪያን እንዲሁም ምሁራን ይገኙበታል።
አስታውሱ August 12, 2012 From 4:00 pm. ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ
ለተጨማሪ መረጃ:
571-244-2869 ወይም 571-299-0975 ይደውሉ።

Friday, July 6, 2012

በዋልድባ ውጥረቱ ቀጥሏል. . . ESAT Radio Interview


በዋልድባ ገዳም ውጥረቱ እንደቀጠለ ነው፥ እስራቱ፣ እንግልቱ፣ ማሳደዱ፣ ድብደባው በፌደራል ወታደሮች እንደቀጠለ ነው ገዳማውያኑ አባቶቻችንም ጩኽታቸውን አቤቱታቸውን በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እያስተላለፉ ነው፥ ዝምታውም ቀጥሏል መንግሥትም መፍረሱን እንደቀጠለ ነው። ዝምታችን ይብቃ ገዳማውያኑን እና ታሪካዊ ገዳማችንን እንታደግ እንተባበር። 
በተለይ በአሁን ሰዓት ቤተክርስቲያን ልጆቿን የምትፈልግበት ወቅት ላይ ደርሰናል በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለቅድስት ቤተክርስቲያን ስለሃገራችን ስለገዳማውያኑ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ገዳም ውስጥ የሚገኙት ገዳማውያን ለሃገር በጸለዩ፣ ለወገን በለመኑ፣ ለመሪዎች እና ለሃገር ወደ አምላካችን በለመኑ በየገዳሙ ዛሬ እስራት፣ ግርፋት፣ እንግልት እንዲሁም ግድያ እየደረሰባቸው ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ከዚህ የከፋ በቤተክርስቲያናችን ላይ ሊመጣ አይችልም ስለዚህ እግዚአብሔር ያከበራችሁ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቆሞሳት፣ ካሕናት አባቶች መከኩሳት፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ መምሕራን፣ ዘማሪያን፣ ዲያቆናት እንዲሁም የቤተክርስቲያን ፈርጦች የሆናችኊ ምዕመናን በሙሉ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከዮዲት ጉዲት እና ከግራኝ መሀመድ በኃላ እንዲህ ዓይነት ፈተና ገጥሟት አያውቅም ስለዚህ ከሊቅ እስከ ደቂት ተባብረን ልዩነታችንን ወደ ጎን ትተን ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ልንታደግ ይገባናል እንላለን።


ዛሬ ቤተክርስቲያን ከእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ የመክሊቱን እንዲያበረክት ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታቀርባለች፣ ገዳማውያኑ የወገን ያለህ እያሉ ነው ስለዚህ በዚህ ታሪካዊ ጥሪ ተቀብለን የበኩላችንን ጥረት ለማድረግ አምላከ ቅዱሳን የጻድቁ አባ ሳሙኤል ዘዋልድ
ባ አምላክ እንዲረዳን ሁላችን ከሕፃን እስከ አዋቂ ወደአምላካችን ልንጸልይ ይገባናል።
ገጸ ምሕረቱን ይመልስልን ለሕዝባችን፣ ለሃገራችን፣ ለቤተክርስቲያናችን አሜን
ለማንኛውም መረጃ በሚከተሉት ሊያገኙን ይችላሉ
savewaldba@gmail.com
Save Waldba Foundation
PO Box 56145
Washington DC 20040


Thursday, July 5, 2012

የታሰሩት የዋልድባ መነኰሳት በነዋሪው ተቃውሞ ለተቃጠለው የፕሮጀክቱ ዶዘር እና ለተጎዱት ሠራተኞች ሓላፊነት እንዲወሰዱ እየተገደዱ ነው·         የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሠራተኞች በአካባቢው ሕዝብ እየተሳደዱ ነው::
·         ነዋሪው ሠራተኞቹን እስከ ማይ ገባከተማ ድረስ እንዳሳደዳቸው ተነግሯል::
·         የዓዲ አርቃይና ማይ ፀብሪ ወረዳዎች ሓላፊዎች በታሰሩት መነኰሳት እየተወዛገቡ ነው::
·         ከዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም የተወሰዱት አምስት መነኰሳት በዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰሩ ናቸው::
(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 27/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 4/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም÷ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ከዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም የተወሰዱት አምስት መነኰሳት በዓዲ አርቃይ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በአንድ ቆርቆሮ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ መኾናቸውን የስፍራው ምንጮች ለደጀ ሰላም ገለጹ፡፡

Tuesday, July 3, 2012

በዋልድባ አባቶች ላይ ፈተናው ጨምሯል ከጸሎት በመሣሪያ ወደ እስር ቤት እየተወሰዱ ነው


በዋልድባ ሰቋር ኪዳነምሕረት የሴቶች አንድነት ገዳም አባቶች እና እናቶች በሱባኤ ባሉበት ወቅት የመንግሥት ታጣቂ ወታደሮች ወደ ገዳሙ ክልል በመግባት 5 አረጋውያን መነኩሳትን ለእስር ዳርገዋቸዋል ምክንያታቸውም ሕዝቡን የምታነሳሱት እናንተ ናችሁ ለዓመጽ እና ለጦርነት አነሳሳችሁት በሚል ሰበብ ነው። እውነታው ግን እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ለሃይማኖቱ እና ለቤተክርስቲያኑ ክብር መቆም ያለበት መሆኑን ሁላችንም ጠንቅቀን እናውቃለን። እነዚህ አባቶች ለሀገር፣ ለወገን፣ ለመሪዎችን እንዲሁም ለአለም በጸለዩ የአባቶቻችንን ርስት አንሰጥም ባሉ እስር መዳረጋቸው ትልቅ ቁጣ አስተስቷል በዓለም ዙሪያ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን እባካችሁ ዝም አንበል የአባቶቻችን ደም ይጠራናል የበኩላችንን እናድርግ ስለ እመብርሃን የጭንቅ አማላጇ ብላችሁ ቤተክርስቲያንን እንጠብቅ
"እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ሁን" ራዕይ 10:3
ቸር ወሬ ያሰማን

Sunday, July 1, 2012

ሰበር ዜና - የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም በፌዴራል ፖሊስ ተከቧል


·        አራት መነኰሳት በፖሊስ ተይዘው ተወስደዋል፤ ሌሎቹ መነኰሳት እየተደበደቡ ተበታትነዋል።
·        የገዳሙ የሱባኤ ወቅት በፖሊስ የኀይል ርምጃ እየታወከ ነው።
·        በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚገነባውን የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግድብ የሚሠራው ሱር ኮንስትራክሽን  ለቆ መውጣቱ እየተነገረ ነው፤ በምትኩ የቻይና ተቋራጭ የገባ ቢኾንም በእርሱም ላይ ተቃውሞው መቀጠሉ ተሰምቷል።

(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 24/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 1/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ዓዲ አርቃይ ወረዳ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም ከማይ ፀብሪና ዓዲ አርቃይ ወረዳዎች በአምስት መኪና ተጭነው በመጡ የፌዴራል ፖሊስ ኀይሎች ሥምሪት ውስጥ እንደሚገኝ የስፍራው ምንጮች ለደጀ ሰላምገለጹ፡፡

ትናንት፣ ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ገዳሙን በተቆጣጠረው የፖሊስ ኀይል አራት የገዳሙ መነኰሳት ተይዘው ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱ ሲኾን ሌሎቹ መነኰሳት ደግሞ ለሱባኤ (ሕርመት) ከተሰበሰቡበት በቆመጥ እየተደበደቡ መበታተናቸው ተጠቁሟል፡፡