Monday, July 30, 2012

ሰሚ ያጣው የዋልድባ ጉዳይ፥ እስራት፣ ድብደባ፣ እንግልት እንደቀጠለ ነው

በሰሜኑ የሃገረችን ክፍል በሚገኘው በታላቁ የዋልድባ ጉዳይ ላይ በርካታ የሆኑ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ ድርጊቶች በገዳሙ እና በገዳማውያኑ ላይ ሲደርስ ቆይቷል እንደቀጠለም ነው። እግዚአብሔር በእርግጥ በዚህ ታሪካዊና ቅዱስ ገዳም ላይ ፊቱን እንደማያዞር እምነታችን ቢሆንም ነገር ግን በገዳማውያኑ ላይ የሚደርስባቸው እንግልት በተፋጠነ ሁኔታ መቀጠሉ የችግሩን ግዝፈት ያሳየናል። ዛሬ ዛሬ ጭራሽ ሰውም በዜናው በመሰላቸት ይመስላል ዝምታው ቀጥሏል። እነዚህ ገዳማውያን ለሃገር ለወገን ለመሪዎች እንዲሁም በአጠቃላይ ለዓለም ሰላም በፀለዩ፣ እህል ስፈሩልን፣ ገንዘብ ቁጠሩልን ሳይሉ ከፈጣሪ ጋር ዕለት ተዕለት በጸሎት እና በስግደት በተገናኙ ምን በደል ኖሮባቸው ይሆን ይህ ሁሉ በደል፤ እንጀታቸው በቋርፍ ተጣብቆ የሚኖሩ አባቶቻችን ዛሬ ጀርባቸው በግርፋት፣ እጅና እግራቸው ለእግረ ሙቅ ለምን እንደተዳረጉ እንቆቅልሽ ሆኖብን ነው።


ዛሬ ለምን ይህን አላችሁ እንደምትሉን እርግጠኞች ነን፥ በትላንትናው ዕለት በዚሁ በታላቁ ገዳም አበረንታት ገዳም አካባቢ የመንግሥት ታጣቂዎች በመግባት መነኩሳቱን ለእስር እና ለግርፋት መዳረጋቸውን ከአካባቢው ባሉን ምንጮች ደርሶናል በዚህ በትላንቱ የመንግሥት ታጣቂዎች በርካቶች ሲታሰሩ ይልቁንም የእቃ ቤቱ ሃላፊ አባ ገብረ ማርያም እና ሌሎች መነኩሳት ታስረስ ወደ ማይ ጸብሪ ወረዳ ለእስር ተወሥደዋል፤ በዚህም የተነሳ ይመስላል ወደ 49 የሚደርሱ መነኩሳት ሱባኤ አቋርጨው ወደ ማይ ጸብሪ ወረዳ አቤቱታቸውን ለማቅረብ ሄደዋል። ልክ ከዚህ በፊቱ እንደሆነው እነኝህ ታጣቂዎች መነኩሳቱን ለእስር ሲወስዷቸው በድብደባ እና በማንገላታት ነው ይህንን ለተመለከተ ህግ እና ፍትህ በሃገራችን ላይ እንደጠፋ ለማንም ግልጽ ነው። ገዳማውያኑ የአንድ ዜጋ መብት እንኳን መብት ሳይጠበቅላቸው እንደ ወንጀለኛ እየተገረፉ እና የተሰደቡ መወሰዳቸው የማንንም ንጹህ ህሊና ያለውን ሰው አእምሮ እንደሚያሳምም ግልጽ ነው።


እነዚህ የመንግሥት ታጣቂዎች ወደ ገዳሙ ክልል በመግባት የመነኩሳቱን መኖሪያ ሲፈትሹ፣ ሲሳደቡ፣ የቤተክርስቲያኑ ክልል ሳይቀር ሲመዝብሩ መቆየታቸውን እነዚህ ምንጮች ገልጸውልናል፤ እነዚሁ ታጣቂዎች 28 የሚሆኑ መነኩሳትን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል እነዚህ የሚፈለጉት መነኩሳት በተለያየ ጊዜ ተቃውሞአቸውን ያሰሙ፣ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብ በዋልድባ ገዳም እየደረሰ ያለውን ለመገናኛ ብዙሃን በመግለጻቸው (በመናገራቸው) ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም በደል አልተገኘባቸውም፤ በእርግጥ እነዚህን አባቶቻችንን እንዲህ እንደ አውሬ ማሳደድ፣ ማንገላታት፣ ማሰር፣ መደብደብ የመሳሰሉት የተለያዩ በደሎችን ቢያደርሱም ገዳማውያኑ አላማቸው ጥያቄያቸው ሁሉ "ገዳማችንን አትንኩብን" የሚል ጥያቄ ሆኖ እናገኘዋለን በእውነት ባልጠፋ ቦታ እነዚህን ገዳማውያን በርግጥ ማሳደድ ሃሳባቸውን ለማስቀየር ይሆን ወይስ ሌላ ምን አላማ ይኖረው ይሆን? ለሃገር ለወገን ለቅርስ እና ለታሪክ የሚጨነቅ እና የሚያስብ መንግሥት በሃገራችን ላይ ባለመኖሩ 1600 ዓመት የቆየውን ይህንን ገዳም ለማጥፋት፣ ገዳማውያኑን ማሳደድ አላማው ምን ይሆን? እውን ይሄ ሁሉ ለልማት ሥራ ነው ወይስ ሌላ ድብቅ ዓላማ ይኖራቸው ይሆን? እነዚህን ሁሉ ነገሮች በቀጣይነት በጊዜ ሊፈቱ ወይም ልንደርስባቸው የሚችሉ ሁኔታዎች ናቸው።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያ ሃገራችንን ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ጽላቶቻችንን እና ገዳማቶቻችንን በረደኤት ይጠብቅልን
አሜን

1 comment:

  1. Amen, Let God save and bless our Gedam Abatochachinin, and Gedam churches where ever they are.
    If they kill our Christians they will get their punishments from him "Jesus Christ" as the Holy Bible states!!
    Egziabher Yitebiken, Ke Fetenawim Yawtan, this is a time for all of us to repent, fast, and pray a lot.

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤