Monday, September 10, 2012

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ የኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክየአዲስ ዓመት መልእክት አስተላለፉ(ደጀ ሰላም፤ ጳጉሜን 4/2004 ዓ.ም፤ September 9/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ አዲሱ የቤተ ክርስቲያናችን አቃቤ መንበር እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል አዲሱን ዓመት አስመልክተው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ሰፍሯል። ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
Ø    በሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
Ø    የሀገርን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
Ø    በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራባ ተይዛችሁ በየሆስፒታሉ የምትገኙ፣
Ø    የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በማረሚአ ቤት ያላችሁ፣
Ø    በተለያየ ምክንያት ከሀገራችሁ ከኢትዮጵያ ወጥታችሁ በዓለሙ ሁሉ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤


የዘመናት ጌታ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎች 2005 ዓ.ም በሰለማም አደረሳችሁ፤ ለሚቀጥለውም ዘመን በቸርነቱ ጠብቆ በሰላምና በጤና እንዲያደርሳችሁ ቤተ ክርስቲአናችን ዘወትር ጸሎቷን ወደ ፈጣሪ ታቀርባለች።

“ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር ስብሐተ ሐዲሰ”. “እግዚአብሔርን በአዲስ ምስጋና አመስግኑት” ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት (መዝ. 149 ቁ. 1)

ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ባለፈው ዓመት ስለተደረገልን መልካም ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ማመስገን፣ በአዲሱ ዓመትም በአዲስመንፈስ አዲስ ሥራን ለመሥራት እንዲረዳን የልመና ጸሎት ማቅረብ ይገባናል።

የሰው ልጅ በዘመን ተወስኖ የሚኖር ሲሆን፣ እግዚአብሔር አምላካችን በዘመን፣ በዘመናት ሳይወሰን የነበረ፣ ያለና የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ ነው፤ ዘመናትን መቁጠር የተጀመረውም እግዚአብሔር የሥነ ፍጥረታትን ሥራ ከጀመረበት አንሥቶ መሆኑን የሥነ ፍጥረት ታሪክ ያረጋግጣል። በስድስተኛውም ቀን የተፈጠረው ሰው ወደ ሥራ የገባው ከተፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ መሆኑ ግልፅ ነው።

በመሆኑም የሰው ልጅ የኖረበት ዘመን ሁሉ የሥራና የታሪክ መን ሁኖ ይታያል። ከዚህ አንፃር ሁሉም ኅብረተ ሰብ መልካም ታሪክን ለማስመዝገብ በተሠለፈበት ዓላማ የሚጠበቅበትን ድርሻ ማበርከት ይኖርበታል።
በአዲስ ዓመት፣ በአዲስ ዕለት እግዚአብሔርን ለማመስገን አዲስ ምክንያትን ይሰጠናል፤ እግዚአብሔር በየቀኑ ለእኛ አዲስ ነገርን እያደረገልን ነው፤ ምሕረቱና ቸርነቱ በየማለዳው አዲስ ነው፤ እኛም ስለ ምሕሩ ቸርነቱ ምስጋናን ማቅረብ እንደሚገባን “እግዚአብሔርን በአዲስ ምስጋና አመስግኑት” ተብሎ ተጽፏል።

ሁል ጊዜ አዲስ ዓመት፣ አዲስ ዕለት ማለት የተለመደ ነው፤ ነገር ግን አዲስ ዓመትና አዲስ ዕለት ማለት የዓመቱ መለወጥ ሳይሆን ከላይ እንደተጠቀሰው አዲስ ዕቅድ በማውጣት አዲስ ሥራን መ ራት ሲቻል ነው፤ ማለትም በአምልኮተ እግዚአብሔር የጸና፣ በፍቅር በሰላም የተመሠረተ፣ ሁሉንም ያካተተ የመኖር እንቅስቃሴ ሲኖር ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ለለአሐዱ ዘዘዚአሁ ጸጋሁ፤ የእያንዳንዱ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው፣ መንፈስ ግን አንድ ነው፣ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው፣ ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፤ በሁሉ ላይ አድሮ ሁሉን የሚያደርግ አንድ እግዚአብሔር ነው” ብሎ ተናግሮአል (1ቆሮ. 12፡4-5)።

በዚሁ መሠረት እያንዳንዳችን የምንሠራው ሥራ ሁሉ በታደልነው ጸጋ እግዚአብሔር መሠረት ነው። ባለፈው ዘመን ልንሠራው የሚገባንን ሠርተን ከሆነበአዲሱም ዘመን የበለጠ መልካም ሥራን መሥራት እንችላለን። ልንሠራው የሚገባንን ሳንሠራ እንዲሁ ጊዜውን በቸልተኛነት አሳልፈነው ከሆነ ደግሞ የዘመኑ መለወጥ ብቻ ፋይዳ የለውም።
ለሀገር ልማት፣ ለወገን ዕድገት የሚሆን ሥራን ሠርቶ በታሪክ አስመዝግቦ ማለፉ ለትውልደ ትውልድ የማይረሳ ታሪክ ሁኖ ይኖራል።

ሌላው በአዲሱ ኣመት ሊዘነጋ የማይገባው ዓቢይ ነገር ቢኖር ለበዓሉ ክብር ሲባል ለቤተሰባችን ከምናደርግላቸው በረከት እንዳይለዩብን ያለንን ሁሉ በማብቃቃት በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸው ሙተውባቸው ሰብሳቢ ያጡ ሕጻናትን፣ ጠዋሪ የሌላቸው ሽማግሌዎች አሮጊቶችን፣ የሰው ፊት አይተው የሚኖሩትን፣ ለችግር የተጋለጡትን፣ ለደዌ የተዳረጉትን ወገኖች በሀሉም አቅጣጫ መርዳት፣ እንደሚገባ ሃይማኖታዊም፣ ወገናዊም፣ ሰብአዊም ግዴታ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ልዩ ልዩ ባህሎች፣ ትውፊቶች እንደሚታዩባት የሚታወቅ ነው፤ አንዱ ለሌላው ባህል ያለውን አክብሮት ባለመንፈግ፣ በማክበርና በመከባብ ነቀፌታ ካለበት አመለካከትና ጠባይ በመራቅና በመቻቻል መኖር፣ አሁንም ሀገራዊ፣ ሃይማኖታዊና ሰብአዊ ግዴታ ከመሆኑ ጋር ለአንድነታችንና ለሰላማችን ታላቅ ዋስትና አለው።
“ኢይፈርሆ ለእኩይ እስመ አንተ ምስሌየ፣ አንተ ከእኔ ጋር ከሆንክ ክፉውን ሁሉ አልፈራም” ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት (መዝ. 22፤4)

የመኖር ዋስትናውን በሕገ እግዚአብሔር የሚመራ ሰው ማናቸውም ፈተና ቢያጋጥመው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለሆነ የሚደርስበትን ፈተና ሁሉ መቋቋምና መከላከል አያዳግተውም።

ስለዚህ በእምነትም ሆነ በባህል ልዩነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያት ወገኖች ሁሉ በተፈጥሮ ወገናዊነት - ሰው በመሆን ወዘተ. አንድ ሲሆኑ፣ ከመለያየት ይለቅ አንድነትን፣ ከጭካኔ ርህራሄን፣ ከመራራቅም መቀራረብን አጎልብተው ስለሀገር ሰላምና ዕድገት በአዲሱ ዓመት በአንድነት መንፈስ እንዲሠሩ በዚህ አጋጣሚ መልእክታችን በአጽንኦት ለማስተላለፍ እንወዳለን።
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ወስመ ጥምቀቱ “ገብረ ማርያም” ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያት ያግባልን፣ በዘመናቸው ተጀምሮ የነበረው የልማት፣ የዕድገት እንቅስቃሴ በተጀመረው ሁኔታ እንዲቀጥል አደራችንን ለሁሉም እናስተላልፋለን፤ በብፁዕ ወቅዱስ ዶክት አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ክርስቲያን ፓትርያርክ ተጀምሮ የነበረውም መንፈሳዊው እንቅስቃሴና ዕድገት በነበረው ሁኔታ እንዲቀጥል አደራ እንላለን፤ ነፍሳቸውን ከቅዱሳኑ ጋር ይደምርልን።

እግዚአብሔር አምላካችን አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ አንድነት ዘመን ያድርግልን፣ ሕሙማኑን ይፈውስልን፣ ሕጻናቱን ያሳድግልን፣ የታሠሩትን ያስፈታልን፣ ወገኖቻችን ኢትዮጵያውያንን፣ ኢትዮጵያውያትን ሁሉ በያሉበት በፍቅር አንድነት፣ በስምምነት አኑርልን፣ የተዘራውን፣ የተተከለውን ለበረከት ለፍሬ ያብቃልን፤ ለሀገራችንና ለመላው ዓለም ሰላሙን ይስጥልን፣ ከሀገራችን ድህነትን፣ ኋላቀርነትን ለማስወገድ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለውጤት ያብቃልን፣ ርዕሰ ዐውደ ዓመቱን በቸርነቱ ይባርክልን፣ ቸሩ እግዚአብሔር  አምላክ ሁላችንንም ይጠብቅ፣ ይቀድስ አሜን።

አባ ናትናኤል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ፣ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ጳጉሜን 5 ቀን 2004 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤