Wednesday, October 3, 2012

ቱባ ባለሥልጣናት ወደ ዋልድባ ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ተነገረየገዳማውያኑ የጸሎታቸው በረከት ይደርብን

·         አቶ አባይ ፀሐዬ የጀመሩትን እጅ የመጠምዘዝ ስራ እንደሚቀጥሉ ይገመታል
·         ባለፈው ከአቶ አባይ ፀሐዬ ጋር የተገናኙት መነኮሳት ተቃውሞ ገጠማቸው
·         ክንፈ ገብርኤል የተባሉት መናኝ ታስረው ወደ ማይ ጸብሪ መወሰዳቸው ተዘገበ
·         ቤተክህነቱ በዝምታው እንደቀጠለ ነው
PDF ለማንበብ ይጫኑ
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በርካታ የመንግሥት ባለ-ሥልጣናት ወደ ዋልድባ በመሄድ የሦስቱንም ማኅበራት አባቶች እንደሚያነጋግሩ ተነግሯል። የዋልድባ መነኮሳት እና ማኅበራቱ በጠቅላላው ምንም ዓይነት በገዳሙ ስም ድርድር ማድረግ እንደማይፈልጉ እና እንደማይችሉ ቢገልጹም ነገር ግን አቶ አባይ ጸሐዬ፣ አቶ በረከት ስምዖንን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት ወደ ቦታው በመሄድ ቢቻልም እጅ ጠምዝዞ ለማሳመን እና የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ በቀጣይነት ስራውን እንዲቀጥል ለማግባባት ወደ ቦታው ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያሳያል። የገዳሙ አባቶች የሰቋር ኪዳነ ምሕረት የአንድነት ገዳም፣ የዳልሻህ ኪዳነምሕረት ገዳም፣ እንዲሁም የአበረንታት ገዳም ተጠሪዎች በጉዳዩ የተነጋገሩበት ሲሆን እነሱም ውሳኔው የእነሱ ማለትም የገዳማውያኑ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች በሙሉ ውሳኔ እንደሆነ እና በእነሱ በኩል ሊመጣ የሚችለውንም ፈተና በሰማዕትነት እንደሚቀበሉት እና በዚህ ቅዱስ ቦታ ምንም ዓይነት ድርድር ሊገባም እንደማይገባ እና መነኮሳቱ ብቻቸውን ለመወሰን መብት እንደሌላቸውም ተናግረዋል።


እንደሚታወቀው መንግሥት ይልቁንም የሱር ኮንስትራክሽን ሥራውን ለቆ ከወጣ በኃላ የቻይናው ካምፖኒ በመጣ ጊዜ የተለያየ መላምቶችን በመስጠት እና ገዳማውያኑን ለማሳመን በቻይና ዲንጓንግ ፕሮቪንስ የተፈጠረውን ምሳሌ ለኛ ገዳማውያን ለማሳየት የሚሞክሩበት ሁኔታ እንዳለ ይገመታል። ነገሩ እንዲህ ነው በቻይና ደቡባዊ ከተማ በሆነችው ዲንጓንግ ፕሮቢንስ ውስጥ የነበረ ታላቅ የቡድሃ ገዳም ነበረ፣ የቻይና መንግሥት ቦታውን ለስኳር ፋብሪካ በፈለገው ጊዜ ገዳማውያኑን አነጋግረው በምትኩ ሌላ ቦታ ተሰጣቸው ጣዖታቸውን ከቦታው አንስተው ወደተሰጣቸው ቦታ ወሰዱት ሰላም ወረደ። የእኛው ገዳምን በእኛው መንግሥት ተመሳሳይ ሁኔታ ይደረጋል ብሎ ማሰብ በጣም የተሳሳተ ነው ምክንያቱም የዋልድባ ገዳም ቦታው ነው ቅዱስ በራሱ በመድኅኒዓለም ክርስቶስ የተቀደሰ ቦታ ነው እመቤታችንም በስደቷ በኪደተ እግሯ ከረገጠቻቸው መካናት አንዱ እንደሆነ የገዳሙ ረጅም የሆነ ታሪኩ ያሳያል። በቻይና የተከሰተው ቦታውን መንግሥታቸው ሲፈልገው ቦታው ቅዱስና ስለሌለው ጣዖቱን ሲወስዱት የሚሄድበት ቦታ ጣዖታቸውን ተከትሎ ቅድስናውን ይዘውት መሄድ ይችላሉ ነገር ግን የእኛው ገዳም ቅድስናው የቦታው እንጂ በውስጡ የሚኖሩት ገዳማውያን ለቅድስናው ተጨማሪ ቅድስና ይሰጡታል እንጂ እንደቻይናው አንስተን የምንወስደው እንዳልሆነ መንግሥታችን ሊረዳው ይገባል። በ13ኛው ክፍለ ዘመን የተነሱት ታላቁ አባት አባ ሳሙኤል ምድሪቱን አንስተው እንዳስባረኩትም ገድላቸው ያስረዳናል ስለሆነም በቻይና የሆነውን ለእኛ ሀገር ለማድረግ መሞከት ሞኝነት ነው ይልቁንም ቅስፈት ሊያመጣ ስለሚችል ከፈጣሪ ጋር ተግዳሮቱን ቆጠብ ማድረግ ሳይሻል እንደማይቀር እንገምታለን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው በአባ ወልደ ማርያም አገናኝነት ከአቶ አባይ ጸሐዬ ጋር የተገናኙት መነኮሳት ትልቅ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተነገረ። አራት የመነኮሳት ቡድን የብጹዕ አቡነ ጳውሎስን እረፍት እንደተሰማ ለቀብሩ በሦስቱም ማኅበራት ተወክለው ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት የመነኮሳቱ ቡድን የቅዱስ ፖትርያሪኩን ሥርዓተ ቀብር አስፈጽመው ወደ ገዳሙ እንደሚመለሱ ነበር የተገመተው፥ ነገር ግን በአባ ወልደ ማርያም አግባቢነት ገዳምውያኑን አግባብቶ ከአቶ አባይ ጸሐዬ ጋር ተገናኝተው እንደነበር በገዳሙ በተነገረ ጊዜ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር፣ ገዳምውያኑም ወደ ባዕታቸው በተመለሱበት ወቅት እናንተን ማን ወክሏችሁ ነው ስለ ዋልድባ ገዳም ከመንግሥት ባለ-ሥልጣናት ጋር ድርድር የጀመራችሁት፣ ተልካችሁ የሄዳችሁበትን ሥርዓተ ቀብር አስፈጽማችሁ መመለስ ሲገባችሁ ለምን እንዲህ ዓይነት ድርድር አደረጋችሁ በማለት በገዳሙ አካባቢ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። ምናልባትም የአሁኑ ዙር ትልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ ገዳሙ ለመምጣት የወሰኑት እና ለመነጋገር እንመጣለን ማለታቸው ከበፊተኛው ንግግር ተከታይ ክፍል ነው በማለት ሥጋታቸውን ይገልጻሉ። አራቱም የገዳሙ ልዑካን በተፈጠረው ችግር ማዘናቸውን እና አባ ወልደ ማርያም የተባሉት ሰው ትልቅ ስህተት ውስጥ እንዳስገቧቸውም በጸጸት ይናገራሉ።

በተያያዘ ዜና ባለው በዋልድባ ገዳም አካባቢ የተሰሩት ግድብ እና ድልድይ በአምላክ ተኣምራት ተጠራርገው ሲሄዱ ክንፈ ገብርኤል የተሰኙ መናኝ ገዳማዊ “በዋልድባ ላይ የተነሳ የሰራው ሳይሆን እራሱ ይፈርሳል” በማለት በሃይለ ቃል በመናገራቸው በአካባቢው የነበሩ ታጣቂዎች ከፍተኛ ድብደባ አድርሰውባቸው እንደነበርና ወደ ማይ ገባ አካባቢ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ገብተው በህክምና ሲረዱ መቆየታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፣ አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት እኝሁ ገዳማዊ መናኝ በመንግሥት ታጣቂዎች ከጤና ጣቢያው ተወስደው በማይጸብሪ በእስር ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ችለናል ወደ አካባቢው ተደጋጋሚ ሙከራን ብናደርግም ክንፈ ገብርኤል የተባሉት መናኝ ያሉበትን የጤና ሁኔታ ለመረዳት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፤ በአካባቢው በደረሰን ዜና መሰረት እንደ ገዳማዊው ክንፈ ገብርኤል አይነት በተለያየ ጊዜ ታጣቂዎቹ በምሽት በመምጣት ገዳማውያኑን ወደ እስር በመውሰድ ከፍተኛ ድብደባ እና እንግልት እያደረሱባቸው እንደሚገኙም ለመረዳት ችለናል።

በዋልድባ ገዳም ላይ እና በገዳማውያኑ ላይ እንዲህ ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጸም፣ መንግሥት የገዳማውያኑን እጅ በመጠምዘዝ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ሲሞክሩ፣ ገዳማውያኑ ሲሰደዱ፣ በርካታ ችግሮች ሲያጋጥማቸው እና የሰው ያለህ በሚሉበት ወቅት ቤተክህነቱ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠቱ ይበልጡኑ ብዙዎችን ኦርቶዶክሳዊያን አሳዝኗል። እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት በቦታው ሄደን ገዳሙን ምንም እንዳልነካው ወይንም እንደማይነካው አረጋግጠናል ብለው በሕዝብ ፊት የዋሹት የእነ አቶ ተስፋዬ ቡድን በቤተክህነቱ ላይ ሰፍሮ ያለውን የነቀዘ የዘረኝነት እና የአድር ባይነት ጸባይ በእጅጉ ጎልቶ ያሳየ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፥ ነገር ግን በአሁን ሰዓት ችግሩን ነጻ በሆነ አካል ለማጣራት ብሎም ገዳማውያኑን በቦታው ሄደው ከቦታው በረከት እንደማግኘት እንደዚህ በዝምታ ተሸብቦ መመልከት ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማያድን ለማስገንዘብ እንወዳለን።
የገዳማውያኑ የጸሎታቸው በረከት ይደርብን
ቸር ይግጠመን 

4 comments:

  1. Why don't you organize tel conferencing in Ethiopia. We Christians in Ethiopia can't participate because to call on us cell phone is expensive.

    ReplyDelete
  2. ቤቴ የፀሎት ቤት እንጂ.... የሚለውን አስተውለው እንዲመለሱ እግዚአብሔር ይርዳቸው!!!

    ReplyDelete
  3. “እግዝአብሔር ታላቅና ሐያል ዓምላክ ነው” አቶ አባይ ፀሐዩን እባካችሁ ይሄዱ ወደ ዋልድባ ተዋቸው:: ተወደደም ተጠላ የዘንድሮው ተረኛ እሳቸው ናቸው:: የሜያሳዝነው ልባቸው ሳያምንበት ለመኖር ብለው አብረው የሜሮጡት ያለ እንደነ በረከት ስምዖን አይነቱ ነው:: አንድ ነገር ልናገር ይህ የዋልድባ መናንያን ስቃይና ግፍ የህዝበ ክርስትያን ሃጥያት ያመጣው መዘዝ ሰለሆነ ግድ ይላል :: እኛ መእመን በቀን ሶስት ግዜ አገርንና በተክርስትያንን በተመለከተ እጃችንን በአንድ ልብ ብናነሳና ብንፀልይ ፀጥ ረጭ ማድረግ የሜያውቀው አምላክ በፊታችን ይቆማል:: እባካችሁ ህልናችሁን ሰብሰብ አርጋችሁ ልትሰሙኝ ሞክሩ:: አሜን

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤