Tuesday, October 23, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጀመረ


 • የሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው የቀብር ሥነ ሥርዐት ተፈጸመ:: 

(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 12/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 22/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ የ2005 ዓ.ም ጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ጸሎት ትናንት ተሲዓት በኋላ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተከናውኗል፡፡ በፍትሕ መንፈሳዊ አምስተኛው አንቀጽ ቁጥር 164 በታዘዘው መሠረት በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባውን የሚያካሂደው ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም የሚጀምረው ምልአተ ጉባኤው ከአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈተ ሕይወት በኋላ የመጀመሪያው ነው፡፡ ምልአተ ጉባኤው በሥራ ላይ በሚቆይባቸው ቀናት የዕርቀ ሰላሙ ሂደት አስቸኳይ ፍጻሜ ስለሚያገኝበት ኹኔታ፣ በፓትርያርክ አመራረጥ ሕግ ረቂቅ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሁም ካለፈው ምልአተ ጉባኤ በተላለፉ አጀንዳዎች አፈጻጸም ላይ በመወያየት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ 31ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለስድስት ቀናት በቆየበትና በአጠቃላይ ጉባኤው ታሪክ የተለየ ገጽታ በታየበት የስብሰባ ዝግጅት የተመከረባቸው የመዋቅር፣ የአደረጃጀት እና አሠራር ለውጥ ውሳኔ ሐሳቦች ላይም እንደሚመክር ተመልክቷል፡፡ ምልአተ ጉባኤ እንዲያጸድቀውና የሥራ መመሪያ አድርጎ እንዲያስተላልፈው አጠቃላይ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳቡንና የአቋም መግለጫውን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ያቀረበበት ቃለ ጉባኤ 33 ነጥቦችን እንደያዘ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአጠቃላይ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብና የአቋም መግለጫ ትኩረት የሰጣቸው ነጥቦች፦
 • የውጭ ሀገር ሐዋርያዊ ተልእኮ ትልቁ የቤተ ክርስቲያኗ ወቅታዊ ጉዳይ ከመኾኑ አንጻር በተለይ በሰሜን አሜሪካ በሦስት ቡድን ቤተ ክርስቲያኗን የከፈሉ ወገኖች ወደ አንድ ጎራ ይመጡ ዘንድ ስለ ሰላሙ ኹኔታ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥበት ጉባኤው አደራውን ሰጥቷል፡፡
 • በዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዐት የበጀት ማእከላዊነት በባለሙያ ተጠንቶ ተግባራዊ ስለሚኾንበት፣
 • መልካም አስተዳደርን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስለማስፈን፣
 • ለጥንታውያን አብነት ት/ቤቶች መምህራንና ደቀ መዛሙርት ቅድሚያ በመስጠት ቋሚ በጀት የሚተከልበት እና ተጓዳኝ ሥልጠናዎች የሚያገኙበት፤
 • አብነት ትምህርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚለካበት፣ በዓለም አቀፍ የቴዎሎጂ ጥናት ተቋማት ዕውቅና የሚያገኝበት፣ ቋንቋንና ማኅበራዊ አካባቢን ማእከል ያደረገ ወጥ ሥርዐተ ትምህርት የሚዘጋጅበት፤
 • ለሰንበት ት/ቤቶች ወጥ ሥርዐተ ትምህርት እንዲዘጋጅላቸው፤ መምህራን፣ አሳራጊዎችና ጠባቂዎች ካህናት እንዲኖራቸው፣ ማደራጃ መምሪያውም ይህን ለማስፈጸም በሚያስችል አደረጃጀት በባለሙያ እንዲጠናከር፤
 • መረን የለቀቀው የመነኰሳት ነን ባዮች እንቅስቃሴ የሚገታበት የገዳማት አስተዳደር እና የመረጃ ልውውጥ ሥርዐት እንዲዘረጋ፤ መነኰሳት ገዳማዊ ሕጋቸውን እንዲያከብሩ፤
 • ቅርሶች ለሁሉ በታወቀ የመለያ ቁጥር የሚመዘገቡበት፤ በሙዝየሞች ግንባታ፣ በዘመኑ የዲጅታይዜሽንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጥበብ የሚጠበቁበት አሠራር እንዲጠናከር፤ ቤተ ክርስቲያናችንም በገዛ ሀብቷ ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ የምትኾንበት መንገድ በቅርስ ጥበቃ መምሪያ አማካይነት እንዲመቻች፤
 • የስብከተ ወንጌል አገልግሎታችን ፈቃድ ከሌላቸው ሕገ ወጦችና መናፍቃን ሥምሪት ተጠብቆ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ድረስ አቅሙና ፍላጎቱ ባላቸው መምህራን የሚፈጸምበት የተጠናከረ መዋቅር፣ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ደንብ የሚመራበትን፤
 • የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በጎሳ ላይ ያተኰረ የቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር አፈጻጸም፣ የሰበካ ጉባኤያት በቃለ ዐዋዲው መሠረት አለመደራጀት፣ የአባላት በትክክል አስተዋፅኦ አለመክፈል፣ የሒሳብ ምርመራን በጊዜውና በትክክል አለማድረግ፣ የፐርሰንት ገቢውም በየደረጃው በቅጽ ተሞልቶ በጊዜው አለመቅረብ፣ ምንኵስናቸው እንኳ በሚገባ ላልተረጋገጠ ያለበቂ ዕውቀት በልብስ ብቻ ቅድሚያ እየተሰጠ ቅጥርና ሹመት የሚፈጸም በመኾኑ ለመነኮሳቱ ወደ አዲስ አበባ በብዛት መፍለስ እና ለገዳማት መዘጋት ምክንያት መኾኑ፣ ትክክለኛው የሀ/ስብከቱ የዘመኑ ገቢ ብር 30‚948‚367.00 ኾኖ ሳለ በሰበካ ጉባኤ ማ/መመሪያ በተመዘገበው የሀ/ስብከቱ ሪፖርት ግን ብር 37‚702‚084.25 እንደ ኾነ በመገለጹ በልዩነት የሚታየው ብር 6‚753‚717.25 ገቢ አለመደረጉና የመሳሰሉት የሙስናና የሥራ አለመቀላጠፍ ችግሮች በቋሚነት የሚፈቱበትና የማያዳግም ሥር ነቀል ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚሉ ናቸው፡፡

ከ25 ያላነሱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በትናንቱ የምልአተ ጉባኤው መክፈቻ ጸሎት ፍጻሜ የዕለቱን ትምህርት በጽሑፍ ያቀረቡት ብፁዕ አቡነ ገሪማ÷ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ቀኖና መሥራታቸውን መነሻ በማድረግ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬም ለቤተ ክርስቲያን ህልውና፣ ለምእመኑ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ኑሮ አስፈላጊ የኾኑ ሕጎችን እንደሚያወጣ ተናግረዋል፡፡ አገልጋዩና ምእመኑ ሀገር እንዲለማ፣ ሃይማኖት እንዲቀና፣ የተቸገረው እንዲረዳ፣ ወጣቱ ለሀገሩ ታማኝና ቅን ዜጋ እንዲኾን፣ ለታሪክ ቅርሶች ክብካቤ እንዲደረግ የሚወጣውን መምሪያና የሚተላለፈውን ውሳኔ በመጠበቅና በማስጠበቅ ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ ለሕገ ቤተ ክርስቲያን ተገዥ መኾን እንደሚገባ ብፁዕነታቸው አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ትናንት ጠዋት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቅዱሳን ፓትርያርኮችና የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የመታሰቢያ ጸሎተ ፍትሐት ተካሂዷል፡፡ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዐቱ በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አሳሳቢነትና በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ ብፁዓን ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት እና ኤጲስ ቆጶሳት ለቤተ ክርስቲያን ያስመዘገቧቸውን ሥራዎች ለማዘከር ታስቦ የሚደረግ መኾኑን ያስታወሱት የድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በንባብ ባሰሙት ትምህርት ለቅዱስ ሲኖዶሱ አንድ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ይኸውም በፍትሐ ነገሥቱ ፍትሕ መንፈሳዊ “ወሰብአ ኢትዮጵያሰ ኢይሢሙ ሊቀ እም ማእምራኒሆሙ፤ የኢትዮጵያ ሰዎች ከዐዋቂዎቻቸው ወገን ኤጲስ ቆጶስ አይሹሙ” ተብሎ በሥርዋጽ የገባውን አንቀጽ እና ሚያዝያ 10 ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር “ኢትዮጵያውያን የማይገባቸውን ኤጲስ ቆጶስነት ስለፈለጉና ስለተመኙ እግዚአብሔር ተቆጥቶ በአገራቸው ሦስት ዓመት ሙሉ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከልክሏቸው ድርቅ አመጣባቸው” የሚለውን ወበዛቲ የሚመለከት ነው፡፡

ብፁዕነታቸው እንዳስረዱት በፍትሕ መንፈሳዊ የተመለከተው አንቀጽ በኮፕቶቹና በ15ው መ.ክ.ዘ ከዐረብኛ ወደ ግእዝ በተተረጎመው በእኛው ፍትሐ ነገሥት ካልኾነ በቀር በሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያን የማይገኝ፣ በ325 ዓ.ም በኒቂያ የተሰበሰቡ 318 ሊቃውንት የወሰኑት በማስመሰል በሰባተኛው መ.ክ.ዘ በሥርዋጽ (በጣልቃ) የገባ አንቀጽ ነው፡፡ ይህንኑ አንቀጽ የሚያጠናክረው ንባብም ሚያዝያ 10 ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር በግብጻዊው ፓትርያርክ ዳግማዊ ገብርኤል ተመዝግቦ እንደሚገኝ ያመለከቱት ብፁዕነታቸው÷ “በደግነት ይኹን በየዋህነት እኛም በዕለቱ እያነበብን ተቀብለነው ኖረናል፤”በማለት ቁጭታቸውን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በ34 ዓ.ም) በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካይነት መኾኑንና የኤጲስ ቆጶስነትን ማዕርግ ደግሞ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአኵስም ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት በመመካከር ወደው ፈቅደው ወደ እስክንድርያ በላኩት በቅዱስ ፍሬምናጦስ አማካይነት ማግኘቷን ያስታወሱት ብፁዕነታቸው÷ “ኤጲስ ቆጶስነትን ከእስክንድርያ ማምጣት ክርስትናን ምማጣት አይደለም፤” ብለዋል፡፡

በመኾኑም ኢትዮጵያውያኑ ደገኛ ነገሥታት (ቅዱስ ሐርቤ፣ ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ) የግዛታቸውን ስፋት፣ የሕዝቡን ብዛት በማየት፣ በቋንቋም በኩል ከግብጽ እየተላኩ የሚመጡት ጳጳሳት ከካህናቱም ይኹን ከሕዝቡ ለመግባባት አለመቻላቸውን በመረዳት ኢትዮጵያውያን መነኰሳት በብዛት ኤጲስ ቆጶስነት ይሾሙ ዘንድ ሲያቀርቡ የቆዩት ጥያቄ በካይሮው ቅዱስ ሲኖዶስ ውድቅ ሲደረግ የቆየበትን የፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ የሚደግፈው የመጽሐፈ ስንክሳሩ የሚያዝያ ዐሥር ወበዛቲ እርምት ሊደረግበት እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጠቁመዋል - “ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቦበት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከመጽሐፈ ስንክሳሩ ቢያወጣው ያማረ፣ የሠመረ ታሪክ በኾነ ነበር” ለብፁዕነታቸው ጥቆማ በዐውደ ምሕረቱ የነበሩት ካህናትና ምእመናን የጭብጨባ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም ሕይወታቸው ያለፈው የሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው የቀብር ሥነ ሥርዐት ትናንት ጠዋት ለቅዱሳን ፓትርያርኮችና ለብፁዓን ጳጳሳት የመታሰቢያ ጸሎተ ፍትሐት በተካሄደበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ ሃይማኖቱንም ፖለቲካውንም በሚገባ እንደተካኑበት የሚነገርላቸው አንደበተ ርቱዑው የቅኔና የሥነ ጽሑፍ ሰው ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው በቀድሞው መንግሥት ውሳኔ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ለሰባት ዓመታት በዋና ሥራ አስኪያጅነት ከመምራታቸውም በላይ በስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊነት፣ በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ድርጅት በዳይሬክተርነት፣ በሰባኪነትና በሥነ ጽሑፍ አራሚነት ማገልገላቸውን ዜና ሕይወታቸው ያመለክታል፡፡

ሊቀ ማእምራን አበባ ይግዛው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከነበራቸው ሓላፊነት ባሻገር በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ መጻሕፍት፣ በደርግ ጽ/ቤት በፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ቡድን በትውስት፣ በጎንደር ከተማ ከንቲባነት በኋላም ለአምስት ዓመታት የክፍለ ሀገሩ ምክትል አስተዳዳሪነት፣ ለሁለት ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስና ማስታወቂያ መምሪያ ተ/ሓላፊነት፣ በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚኒስትር ካውንስለርነት፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ መንግሥትና የገዳማቱ ንብረት በጉዳይ ፈጻሚነት፣ በፕሮቶኮል እየተሾሙና እየተመደቡ ቅን አገልግሎታቸውን እንዳበረከቱ ግብአተ መሬታቸው በተፈጸመበት ወቅት የተሰራጨው መረጃ ያመለክታል፡፡

በወቅቱ የሊቀ ማእምራን አበባውን ዜና ሕይወትና ሥራዎች ከእንባ ጋራ በማዘክር ቅኔ ከሰጡት ወዳጆቻቸው አንዱ የኾኑት የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ÷ ሊቀ ማእምራን አበባው ከመናኙ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋራ ደክመው ባቋቋሙትና በ1974 ዓ.ም በአገር ዓቀፍ ደረጃ የተጀመረው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለ31 ጊዜ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ በፈጸመበት ወቅት ማረፋቸው “እግዚአብሔር የድካሙን ዋጋ እንደከፈለው ያሳያል” ብለዋል፡፡ ስማቸው አበባው መኾኑን በሞት የተጠሩበት ወቅትም ዘመነ መፀው፣ ዘመነ ጽጌ፣ የአበባ ወቅት መኾኑ፤ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነትም ያሉት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከሊቀ ማእምራን አበባው ጋራ በአገልግሎት አብረው የደከሙ መኾኑ ሌላው አስገራሚ መገጣጠም መኾኑን መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ባለትዳር፣ የሦስት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የነበሩት ሊቀ ማእምራን አበባው ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ መኖርያቸውን ከኢየሩሳሌም ወደ ታላቋ ብሪታንያ በማድረግ ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ በዚያው አሳልፈዋል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤