Wednesday, October 24, 2012

ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ኮሚቴ እርቀ ሰላሙ እንዲቀጥል ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ደብዳቤ ላከ


ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ጊዜያዊ ኮሚቴ የቤተክርስቲያን አንድነት እንዲመጣ፣ የአባቶች አንድነት እና የሕዝበ ክርስቲያኑ በአንድነት መቆምን በመማፀን በሀገራችን ኢትዮጵያ ለሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲሁም በውጪው ዓለም ለሚኖሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፬ኛ ፖትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አበው የተማጽኖ ደብዳቤዎችን ከጥቂት ቀናት በፊት ልኳል፡፡


 በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።
ለኢትዮጵያ ኦርቶኦክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ጉዳዩ፤ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችንና የአባቶቻችንን አንድነት ይመለከታል


የተከበራችሁ አባቶቻችን ብፁዕ አቡነ ናትናኤልና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆናችሁ በሙሉ ቡራኬያችሁና በረከታችሁ በያለንበት ይድረሰን። የናፍቆትና የአክብሮት ሰላምታችንን በፍጹም መንፈሳዊ ትህትና ስናቀርብ ከልብ በመነጨ የልጅነት አክብሮት ነው።
እኛ ከቅድስት እናት ሃገራችን ከኢትዮጵያ ውጪ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች ስለ አንዲቷና ሐዋሪያዊት ቤተ ክርስቲያን ማሰብ ያቆምንበት ጊዜ የለም። ከእናንተ የመንፈስ አባቶቻችን እንደተማርነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ጥባቆትና በአባቶች ፍጹም የመንፈስ ተጋድሎ ብዙ ፈተናዎችን አልፋ ከእኛ ትውልድ እንደደረሰች የሚታወቅ ሲሆን፥ ክርስቲያናዊ ጉዞ ረድኤተ እግዚአብሔርን፣ የእመቤታችን እንዲሁም የቅዱሳን እና የሰማዕታት ምልጃ ጋሻ አድርጎ በብዙ ፈተናዎች እና ተጋድሎ እየታለፉ የሚኖርበት የእውነት ሕይወት እንደሆነ እናንተ አባቶቻችን አስተምራችሁናል።
ክርስቲያናዊ ሕይወት በሌላ በኩል ደግሞ ዘላለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔር መንግስት ለመውረስ የምንጓዝበት ጠባብ መንገድ በፈተናና በወጀብ ቢታጀብም ዘወትር ግን ደስታንና የአእምሮ እረፍትን የሚሰጥ ነው። በአጠቃላይ የማይቻሉ የሚመስሉ የሚቻሉበት፣ የተናቁ የሚያሸንፉበት፣ የማይነቃነቁ የሚመስሉት ደግሞ እንደ ጠዋት ጤዛ አልፈው የሚታዩበትና ዕፁብ የአምላክ ሥራ የሚታይበት እና የሚነገርበት ብቸኛው የሕይወት መንገድ ነው።
እኛ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በአርባና በሰማኒያ ቀናችን በእናንተ በአባቶቻችን እጅ ከመንፈስ ቅዱስ ከተቀበልናት ተዋህዷዊ ሀይማኖታችን በላይ የምንመካበት፣ የምንደሰትበትና እለት እለት የሚያሳስበን ጉዳይ የለም።እኔም እልሀለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁ የገሃነም ደጆች አይችሏትም። የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሀለሁ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል።ማቴ ፲፮፥፲፰-፲፱
የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው። ደግሞ ሁለተኛ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሶስተኛ ጊዜ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን? አለው። ሶስተኛ ትወደኛለህ ስላለው ጴጥሮስ አዘነና ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም በጎቼን አሰማራ አለው።ዮሐ ፳፩፥፲፮-፲፯
የሚሉትንና ሌሎች ቅዱስ የመለኮት ቃሎች መሰረት በማድረግ ዓይናችን ዘወትር ወደናንተ አባቶቻችን ይመለከታሉ። እንዳንወድቅ በአባታዊ ምክራችሁ የምታፅናኑንና ስንወድቅ አይዟችሁ ብላችሁ የምታነሱን እናንተ ስለሆናችሁ ከእናንተ ከአባቶቻችን ጋር ያለን የልጅነት ህይወትና ግንኙነት ዘወትር ይገደናል። እኛ በጠቅላላ የማኅበረ ምዕማናን እናንተ አባቶቻችን አንድ ሆናችሁና በመንፈስ ቅዱስ እየተቃኛችሁ ልታስተምሩንና ልትጠብቁን ከመድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበላችሁት
አባታዊ አደራ ስላለባችሁ ዘወትር ወደናንተ እንመለከታለን። ድምፃችሁን ለመስማትና አንድነታችሁን ለማየት ዘወትር እንናፍቃለን፤ አባታዊ ስማችሁ በከንቱ ቦታ ስለ ከንቱ ነገር ሲነሳ መስማት እና ማየት ለእኛ የሞት ያህል ይከብደናል። ይህን ፅሁፍ ለእናንተ ለአባቶቻችን ለመጻፍ ያነሳሳን ባለፉት ዓመታት ጠላት ዲያብሎስ በቤተ ክርስቲያናንችን ዙሪያ የዘራው የመለያየትና የመከፋፈል በሽታን በእጅጉ ስላሳሰበን ነው። ይልቁንም ቤተክርስቲያናችንን ወዳልተፈለገ የመከፋፈልና የመለያየት መንገድ እየወሰደን እና በምዕመናን መካከልም እነዚህ ልዩነቶች እየጎሉ በመምጣታቸው ምክንያት፥ ከዚህም መለያየት ጋር ተያይዘው የመጡ ናቸው የምንላቸውን የጠላት ዲያብሎስ ውጥኖች በሚቀጥለው መንገድ እንገልጻቸዋለን።
1. ቅድስት ቤተክርስትያን በአንድ ጊዜ ሁለት ፓትርያርክ እንዲኖራት ተደርጐ የነበረ መሆኑ
2. የአባቶች መለያየትና በሁለቱም ወገኖች የተላለፈው ውግዘት
3. የአገር ቤትና የውጭ ሲኖዶስ በሚል አባቶችን ከማኅበረ ምዕመናን እንዲለያዩ በመደረጉ
4. የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስሟ እንዲጎድፍ መደረጉ
5. የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እየተዳከመ መምጣቱ
6. ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተክርስትያንም ሆነ በአገር ደረጃ ተሰሚነቱ እየቀነሰ መምጣቱ
7. በአባቶችና በምእመናን መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እንዲለያዩ መደረጉ
8. የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት መደብደብና ጠያቂም ሆነ ተጠያቂ አካል አለመኖሩ
9. በቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚደርስ ጥቃት ተናጋሪ መጥፋቱ
10. የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮት እየተቦረቦረ መሄድና በውስጧ ተሸሽገው የሚቦረቡሯት አካላት እየፈረጠሙ መሄድ
11. በተለይ በውጭው ዓለም ቅድስት ቤተ ክርስትያን የአገር ቤት፣ ስደተኛ፣ ገለልተኛና ሌላም ሌላም ተብላ እንድትከፋፈል መደረጉ
12. የቤተ ክርስትያን መዋቅር በመድከሙና የአባቶቻችን መለያየት ምክንያት ምዕመናን ተመልካች አጥተው የመለያየትና የግጭት ተምሳሌቶች መሆናችው
13. የቤተክርስትያን ሊቃውንትና መምህራን ከቤተክህነት እንዲገለሉ ወይንም ጉልህ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳይኖራቸው መደረጉና በተቃራኒው ደግሞ ቤተክርስትያን ለጥቅም፣ለዘርና ለፖለቲካ ተገዥነት ባላቸው ጥቂት ግለሰቦች ተፅእኖ ውስጥ እንድትወድቅ መደረጉ
14. የማንነታችን መለያ የሆኑት ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማቶቻችን መፍረስና መደፈር፤ በተለይ ደግሞ የቅዱሳን አበውና ሊቃውንት መፍለቂያ የሆነው የታላቁ የዋልድባ ገዳም መደፈርና ለዚህም ቤተክርስትያን እንደተባባሪ ተደርጋ በአንዳንድ የቤተክርስትያን አካላት መገለፁ የችግሩን ስር መስደድ አመልክቷል። እስከአሁንም ድረስ ይህ ለ1,600 ዓመታት ተጠብቆ የቆየ ታላቅ ገዳም አንድ ጊዜ ከጠፋ ወይንም ለዘገምተኛ ጥፋት ከተጋለጠ በኋላ ለማረም እጅግ አዳጋች እንደሚሆን እየታወቀ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ
15. ከላይ የተጠቀሱት ክስተቶች ውጤት ምክንያት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ከህይወት መንገድ ወጥተው ከቤተክርስትያን ተለይተው እነዚህን ልዩነቶች ከምናይ በሚል ወደ ሌላ ሃይማኖት ወይም ከቤተክርስቲያን ፈጽመው መራቃቸውና መጥፋታቸው
የተከበራችሁ አባቶቻችን፤ እናንተ የመድኅኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እንደራሴ የሆናችሁ አባቶቻችን እያላችሁ ከላይ የተዘረዘሩትና ሌሎችም በቤተክርስቲያንና በምዕመናን ላይ በመድረሳቸው ሀዘናችን ወደር የለሽ ነው። ዛሬ ያለንበት የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብዙ የተደበላለቁ አስቸጋሪ ነገሮችን ይዞ የመምጣቱን ያህል የሰው ልጆች ለመልካም ምግባርና ለመቀራረብ ዓይናቸውንም የገለጡበት ዘመን ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉያ ውስጥ ያለውና የነጠረው የእግዚአብሔር ቃል አልጫው ዓለም የሚጣፍጥበት ጨው፤ የድንግዝግዙም ዓለም ብርሃን ነው። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን ትምህርቷ በጭንቀትና፣ በስስት፣ በሌሎችም አያሌ ችግሮች ለታወከው የዓለም ማህበረሰብ ፍቱን መድኃኒት እንደሆነ እሙን ነው።
አሜሌቃውያንና ፈሪሳውያን የአይሁድ መሲህ ይወለዳል ብለው የነብያቱን ትንቢት ሲማሩና ሲያስተምሩ እንዳልኖሩ ሁሉ መድኅን ዓለም ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከምስራች አብሳሪነት ወደ አሳዳጅነት ተቀየሩ። የተከበራችሁም አባቶቻችን፤ እኛ የቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ምዕመናን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት በግጭትና በፀብ አፍነን ይዘን ዳግማዊ አይሁድ እየሆንን ይሆን እንዴ? ዛሬ በአባቶች ላይ እየተሰነዘረ ያለው የድፍረት ቃላት እንዲሁም የአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች እኛ እዛኛው ደብር አንሄድም ውግዝ ስለሆነ፥ እዚህኛውም ደብር አንሄድም የዚህኛው ወገን ስለሆነ በመባባል ምዕመናን ከካህናቱ ጋር የተለያዩበት ዘመን ያንን የአይሁድ አሳዳጆች ዘመን ተመልሶ መጣ እንዴ እንድንል አድርጎናል። ለቀባሪ ማርዳት አይሁንብንና የቀደሙትን ነብያት እነ ሙሴን፣ እነ ዳዊትን፣ እነ ሶሎሞንን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ቅዱሳን አበውን ስናስብ፤ የእናንተም አባትነት እግዚአብሔር እንደልቤ ነው ከሚለው ከልበ አምላክ ዳዊት የተለየ ሃላፊነት የላችሁም፥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በሥርዓት፣ በምግባር ሕዝቦችን ሲያስተዳር እንደነበር እናንተም መንፈሳዊ አባቶቻችን የእነ ቅዱስ ዳዊት ልጆች ናችሁና በፍኖተ እግሩ የተተካችሁ ብጹዓን አባቶቻችን ዘመን የፈጠረውን ልዩነት ወደጎን ትታችሁ
ሕዝበ ክርስቲያኑን በአንድ ልብ ሆናቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት በመሪነታችሁ እንድታደርሱት እንጠይቃለን። ቤተ ክርስቲያንንና ምዕመኑን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያንና በውስጧ የበቀሉ ልጆቿን በሙሉ ደህንነትና ህልውና ይጠበቅ ዘንድ አደራና ግዴታ ከማንም በላይ ያለባችሁ እናንተ ናችሁ። ይህን ስንል ቤተ ክርስቲያንን ከመንግስት ጋር መደመራችን አይደለም። ነገር ግን መንግስትና ተቋማቱ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች አገልጋዮች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። ከመንግስቱም የገቢ ምንጮቹ፣ ፀጥታ አስከባሪዎቹና ሰራዊቱ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም። ይህን ማንሳት ያስፈለገበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ካለችበት የዝቅተኝነት ደረጃ ወጥታ በሀገር ብሎም በማህበረሰቡ ሕይወት ውስጥ የሚገባትን ስፍራ ትይዝ ዘንድ ውስጣዊ ችግሮቿን ይዋል ይደር ሳይባል ዛሬውኑ ተነጋግሮ በመፍታት የቤተ ክርስቲያንን ክብር ወደሚመጥን ላቅ ወዳለ ተግባር መግባት በእጅጉ እንደሚያስፈልግ በሁሉም ወገኖች ያታመናል።
ለፈጣሪያችን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ቤተ ክርስቲያንን ለገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ መፍትሄ እንዳላቸው እናምናለን። በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ቸርነትና በእናንተ አባታዊ አመራር ከላይ የተገለጹት ታርመው የቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ትንሣኤ ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን። የጠፉት የሚመለሱበት፣ የተዋረዱት ወደ ክብር የሚመለሱበት፣ የተሰደዱት ወደ ሃገር የሚገቡበት፣ ቤተ ክርስቲያን የዓለም ጨውና ብርሃን የምትሆንበት፣ ቤተክርስቲያን የምትዳኝ ሳይሆን የምትፈርድ የምትሆንበት፣ ተሸምጋይ ሳትሆን ሸምጋይ የምትሆንበትን ቀን የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር እንደሚያሳየን ተስፋ እናደርጋለን። “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።” ገላ ፩፥፰-፱
ከጳጉሜ ቀን ፳፻፬ . እስከ መስከረም ቀን ፳፻፭ . ድረስ በቅድስት ቤተ ክርስትያን ታውጆ የነበረው ምህላና ፀሎት የቤተክርስቲያን የትንሣኤ ቀን ለመቃረቡ ምልክት ሆኖናል። በዚህ ተስፋ ሰጪ ጅምርም ደስ መሰኘታችንን ለመግለጽ እንወዳለን። የዚህ አይነት አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት አብረው መሰራት ያለባቸው ተዛማጅ ተግባራት እንዳሉ ይሰማናል። ምህላና ፀሎት ለምን ታወጀ? እግዚአብሔር ምን እንዲሰጠን ልንጠይቀው ይገባል? ከእግዚአብሔር መልስ ለማግኘት ምን ቀንሰን ምን እንጨምር? እነማን ይሳተፉ? አዋጁ እነማንስ ጆሮ ይድረስ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች እየተዘረዘሩና እየተብራሩ በአገር ቤትና በመላው ዓለም እንደ ጨው ተበትኖ ለሚገኝው ምዕመን ሁሉ ጆሮ እንዲደርስ መደረጉ አስፈላጊ ነው። በዚህ መሰረት ወደፊትም ቅድስት ቤተ ክርስትያን ይህን መሳይ ውሳኔ ስታሳልፍ ወደ ምዕመናን እንዴትና እነማን ያድርሱት የሚለው ጉዳይ ከተፈተሸ የእረኛውና የመንጋው ግንኙነት እየጠነከረ ይሄዳል ብለን እናምናለን። በዘላቂነት የቤተ ክርስትያን አንድነት ተጠብቆ በደሙ ከመሰረታት ከክርስቶስ የተሰጣትን ተግባር ቅድስት ቤተ ክርስትያን መወጣት እንድትችል በአስቸኳይ መከናወን ያለባቸው ተግባራት እንዳሉ እናምናለን። ቅድስት ቤተ ክርስትያናችን በሕይወት በአንድ ጊዜ ሁለት ፓትርያርኮች የነበሯት ስለነበረ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የግጭት ማዕበል ለማስታገስ እጅግ
አዳጋች ሆኖ እንደነበር መገመት አያዳግትም። ዛሬ ግን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በድንገት ወደ እግዚአብሔር መጠራት ከትላንት ይልቅ ዛሬ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የተሻለ እድል አለ ብለን እናምናለን። መፍትሄው ግን ይህ ነው ብለን በእናንት አባቶች የስራ ድርሻ ውስጥ ገብተን እንዲህ ነው ለማለት ብቃቱም ድፍረቱም የለንም። ነገር ግን ለእናንተ በአገር ቤትና ከሀገር ውጭም ባላችሁ አባቶቻችን ላይ ባለን የልጅነት መመካት የተነሳ ችግሩን ፈትታችሁ እንድታሳዩን የመጠየቅ ድፍረቱ አለን።
በዚህ መሰረት የሚከተሉትን ጥያቄዎች በአክብሮት ለእናንተ ስናቀርብ አስፍታችሁና አብዝታችሁ መፍትሄ እንደምታበጁ እምነታችን በእናንተ አባቶችን ላይ እንደሆነ ሳንገልጽ አናልፍም። የምናመልከው አምላክ ነገሮችን ሁሉ ወደነበረበት እንደሚመልስ በፍጹም እምነታችን ቢሆንም፥ ለእናንተ አባቶቻችን ደግሞ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናቀርባለን።
1. በቀድሞው ዘመን እግዚአብሔር የለም ተብሎ በሀገረ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ምድር የተነገረ በመሆኑና ዛሬም በብዙ መልኩ እንደ ባቢሎን ሕዝቦች እግዚአብሔርን እየተገዳደርነው ስለሆነ እግዚአብሔር ጨርሶ ይቅር እስኪለን ድረስ በየገዳማቱና አድባራቱ ሁሉ ያልተቋረጠ፤ ከወትሮው የተለየ ፀሎትና ምህላው እንዲቀጥል ማድረግ
2. በእናንተ በአባቶቻችን መካከል በአገር ቤትና በውጭ አሉ የሚባሉትን መከፋፈል ይዋል ይደር ሳይባል ተመካክራችሁ ችግሩን ፈትታችሁ እንድታሳዩንና ለዓለም የእርቅ ተምሳሌት እንድትሆኑ
3. እናንተ ከቀደምት አባቶች አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትሪያርክ ያላት አንዲት ዓለማቀፋዊትና ሐዋሪያዊት ቤተ ክርስቲያን ተረክባችሁ እንደነበራችሁ ሁሉ ዛሬም ለዚህ ትውልድ አንድነቷ የተጠበቀ፣ አንድ ሲኖዶስና አንድ ፓትሪያርክ ብቻ ያላት ቤተ ክርስቲያን እንድታስረክቡን፤
4. ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በተለይ ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሠራው እና በሚወስነው ውሳኔ ላይ ምንም አይነት የመንግሥትም ሆነ የሌሎች የቤተ ክርስቲያን ህልውና የማይገዳቸው አካላት ተፅዕኖ እንዳይኖርበት
5. የእናንተ የአባቶቻችን ድምፅ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ መስማት የምንችልባቸውን የመገናኛ መስመሮች መዘርጋት
6. በሕዝብ መገናኛ መድረኮች በመቅረብ አዘውትራችሁ ምዕመናንን የሚያረጋጋና ወደ አንድነት የሚያመጡ ተስፋ ፈንጣቂ መልዕክቶች እንዲደርስ ማድረግ
7. ከጠፉ ሊተኩ የማይችሉ ገዳማት፣ አድባራት፣ መካናትና የቤተ ክርስትያን ቅርሶች ሁሉ እንዲጠበቁና ምዕመኑም የድርሻውን እንዲወጣ ማትጋት
8. በታላቁ የዋልድባ ገዳም ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋትና እንግልት ተያይዞም በቦታው ላይ እየተሰራ ያለውን የስኳር ፋብሪካም ሆነ የፖርክ ይዞታ በአስቸኳይ ማስቆም
9. በቤተክርስትያን ውስጥ ያሉ የተለያዩ የስራ ዘርፎች ሃይማኖታዊ ቅንዓትና ብቃት ባላቸው አባቶችና ሊቃውንቶች እንዲሸፈኑ ማድረግ
10. በዚህ ሁሉ መካከል እኛ ምእመናን እንድንታዘዝና የድርሻችንን እንድንወጣ እንድታስተምሩን እየጠየቅን

እኛም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ረድኤተ እግዚአብሔርን ረዳት አድርገን የናንተን የአባቶትቻንን ቡራኬ ትእዛዝ እየተቀበልን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከጠላት ፍላፃ ለመጠበቅና ብሎም ሐዋሪያዊ ግልጋሎቷ እንዲስፋፋ ያልተቆጠበ ጥረት እናደርጋለን።
የተከበራችሁ ውድ አባቶቻችን ሀሳቦቻችን አንድ ከመሆንና ልዩነትን ከመፍታት ውጪ ያሉ አማራጭ መንገዶች ሁሉ የጠላት ዲያብሎስ ምኞትና መንገድ ስለሆነ ለእኛ አይገቡንም፤ ለአፍታም አናስባቸውም። ይህን ሁሉ ማለታችን የቤተ ክርስትያን ጉዳይ ከእናንተ በላይ የሚገደን ሆነን ወይንም ደግሞ እናንተ አላሰባችሁበትም በማለት ሳይሆን የልጅነት ግዴታችንንም ለመወጣት ጭምር ነው። አሁንም በሀገር ውስጥም በውጭም ያላችሁ አባቶቻችን የፀብን፣ የልዩነትን፣ የመወጋገዝንና የሁለትነትን መንፈስ አስወግዳችሁ አንድ ላይ ቆማችሁ እንደምትባርኩን ተስፋ እናደርጋለን። በዚህም መድኅኒዓለም ክርስቶስ ሲከብር፤ ቤተ ክርስትያን ከፍ ስትል ለማየት እንናፍቃለን።
ቡራኬያችሁና፣ የጸሎታችሁ በረከት አይለይን። የአባቶቻችን አምላክ የሰራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የተመሰገነ ይሁን። ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስትያንን እመአምላክ በምልጃዋ ትጠብቅልን።
ወስብሀት ለእግዚአብሔር
ከታላቅ መንፈሳዊ አክብሮት ጋር
ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ጊዜያዊ ኮሚቴ
ግልባጭ፡-
† በብፁዕ አቡነ መርቆርዮስ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሰሜን አሜሪካ
† ለሰላምና የአንድነት የእርቅ ጉባኤ
በውጪ ዓለም ለሚገኙ አብያተ ክርስትያናት ሰበካ ጉባኤዎችና ቦርዶች አስተዳደር /ቤት


ደብዳቤዎቹ የተላኩት በቀጥታ
፩/ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ኢትዮጵያ (ለማንበብ ይጫኑ )
፪/ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፬ኛው የኢ/ኦ/ተ/ቤ ፖትሪያርክ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ኮሎምበስ ኦሃዮ  (ለማንበብ ይጫኑ )

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤