Wednesday, December 5, 2012

“ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን - ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ”።

አባቶች በጋራ ከጉባኤው በፊት በተገናኙበት ወቅት

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ካህናት አባቶች፣ ዲያቆናት፣ ምዕመናን እና ምዕመናት በጉጉት ሲጠብቁት የነበሩት የቅድስት ቤተክርስቲያን አባቶች የእርቀ ሰላም ጉባኤ ዛሬ ረፋዱ ላይ በዳላስ ቴክሳስ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በጸሎት ተጀምሮ በመቀጠል በአካባቢው በሚገኘው ሆቴል የድርድሩ እና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሰላምን ለማምጣት በአባቶቻችን እና በምዕመናን ጸሎት እና ልመና የተሳካ እንደሚሆን የሁሉም ወገኖች እምነት ነው።
ላለፉት ሦስት ጊዜዎች በተለያየ ጊዜ የቤተክርስቲያኒቱን ሰላም ለማምጣት የተደረጉት ሙከራዎች ያለውጤት ቢጠናቀቁም፣ መድኅኒተዓለም ክርስቶስ ባወቀው እራሱ በፈቀደው ጊዜና ሰዓት ተጨማሪ ግልጽ መንገዶችንም በማመቻቸት ለእርቀ ሰላሙ መሳካት አይነተኛ ውጤት እንዲመጣ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። አሁንም የተደራዳሪዎቹ ግልጽነት እና ለቤተክርስቲያን ሰላም ለማምጣት እና የምዕመናኑንም መከፋፈል ለማስቆም ይህንን የመሰለ እድል እንደማይኖር እና ወደፊትም ሊመጣ እንደማይችል በመገንዘብ የመጣውን እድል ተጠቅመው ላለፉት ፳፩ ዓመታት ተለያይቶ የቆየውን ምዕመን እና ቤተክርስቲያን አንድ የማድረግ እና የምዕመናኑንም እንባ የማበስ ታሪካዊ ሃላፊነት እንዳለባቸው እንገነዘባለን። ለዚህም ጉባኤ ከኢትዮጵያ የመጡትን ብጹዓን አባቶቻችንን፣ በውጪም ያሉትን ብጹዓን አባቶቻችንን ብሎም ለዚህ ጉባኤ መሳካት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ቀን ከሌሊት ለደከሙት አባቶቻችን እና ወንድሞቻችን በሙሉ አምላከ ቅዱሳን ብድር ውለታቸውን እንዲያስብ እና ተራዳዒ መላዕክቱንም ልኮ የናፈቅነውን ሰላም እንደሚያመጣልን ልባዊ ምኞቻችን ነው።

ከኢትዮጵያ የመጣውን ልዑክ በመምራት ትላንት ኅዳር ፳፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ዳላስ ቴክሳስ የገቡት ልዑካን ቡድን
፩ኛ/ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የልዑካኑ መሪ፣
፪ኛ/ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አባል፣
፫ኛ/ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ አባል
፬ኛ/ ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በጸሐፊነት

በውጪ የሚገኙትን ብጹዓን አባቶች በመምራት ለጉባኤው በዳላት የገቡት የልዑካን ቡድን
፩ኛ/ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የልዑካኑ መሪ፣
፪ኛ/ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ አባል፣
፫ኛ/ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አባል
፬ኛ/ ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ በጸሐፊነት

ላለፉት አራት ዓመታት ደከመን፣ ሰለቸን ሳይሉ ቀን ከሌሊት በመድከም ይልቁንም የግል ገንዘባቸውን እና ሰዓታቸውን ሰውተው ለቤተክርስቲያን ሰላም ለምዕመናን አንድነት ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት የእርቀ ሰላሙ ኮሜቴ አባላት ከሰሜን አሜሪካ ከተለያዩ ከተሞች።
፩ኛ/ መላከ መንክራት ቀሲስ አንዱዓለም ይርዳው በአስታራቂ ጉባዔው ሰብሳቢ፣
፪ኛ/ ሊቀ ማዕምራን ዶ/ር አማረ ካሳዪ
፫ኛ/ ሊቀካህናት ኃይለሥላሴ ዓለማየሁ
፬ኛ/ ቀሲስ መኮነን ኃይለጊዮርጊስ
፭ኛ/ መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ፋሲል አስረስ 
፮ኛ/ ቆሞስ አባ ጽጌ ደገፋው፣
፯ኛ/ መ/ር ልዑለቃል አካሉ
፰ኛ/ ዲ/ን አንዱዓለም ዳግማዊ

በመጨረሻም በመላው ዓለም የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች በያለንበት ቦታ ሁሉ አባቶቻችንን ውይይታቸውን ጨርሰው መልካም ዜና እስኪያሰሙን ድረስ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ ለቤተክርስቲያናችን ሰላም፣ ለምዕመናን አንድነት፣ ለሃገራችን ሰላም እና እድገት፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ሃገራችን ላሉ ገዳማት እና አድባራት ለሚደርስባቸው በደል እና እንግልት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክ መልካሙን ሁሉ እንዲያመጣልን አባቶቻችን በአንድነት ለአገልግሎት ሲፋጠኑ፣ ምዕመናኖቿ በጋራ ወደ ፈጣሪያቸው ሲጸልዩ፣ ሀገራችን የዜጎች በብቶች ተከብረው ገዳማውያኑ በገዳማቸው ጸንተው ለሃገር እና ለሕዝባቸው እየጸለዩ፣ የቤተክርስቲያናችን ርስቶቿ እና ጉልቶቿ በሕግ ተጠብቀው፣ ምዕመናን እና ምዕመናት በነጻነት ወደ እግዚአብሔር ልመናቸውን እና ጩኽታቸውን የሚያቀርቡበትን፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በጋር ያለ መንግሥት ወይም ሁለተኛ አካል ተጽዕኖ ሳይኖርባቸው የሚወስኑበትን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እና ሥርዓት አልበኞች ተለይተው፣ ሥርዓት አልበኛውም በቀኖና እና በንሰሃ ቅድስት ቤተክርስቲያቸውን የሚያገለግሉበትን ጊዜና ሰዓት በዓይናችን ለማየት ናፍቀናል፥ ዘወትር በኪዳን፣ ወትሮም በሰርክ ጸሎት የምንማጸነው የእስራኤል አምላክ የምንመኘውን ሰላም በዓይናችን እንዲያሳየን የሁላችን ልመናና ጸሎት እንዲሆን እየጠየቅን፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ቢቻል በጸሎት ቤታችን አለያም በመንገዳችን ሁሉ ለምንመኘው ሰላም እና አንድነት ሁሉ ቢያንስ አንድ “አቡነ ዘበሰማያት” እንድናደርስ በታላቅ ትህትና እናስታውሳለን።
ቅድስት ሃገራችንን ኢትዮጵያን እና ቤተክርስቲያናችንን በረደኤት ይጠብቅልን 

2 comments:

 1. ቢያንስ አንድ “አቡነ ዘበሰማያት” እንድናደርስ በታላቅ ትህትና እናስታውሳለን።
  ቅድስት ሃገራችንን ኢትዮጵያን እና ቤተክርስቲያናችንን በረደኤት ይጠብቅልን :: Amein!

  ReplyDelete
 2. ይህ እርቁን ለማደናቀፍ የተጻፈ በፍጽም አይደለም። ጉዳዩ መ/ር ልዑለቃል አካሉ ይመለከታል።

  ለምን እርሱ እንደተወከለ ሊገባኝ አልቻልም፤ ምክያቱም አቋሙ እንደቀድሞ ከወነ የፕሮቴስታቶች ሰላይ ቢሆንስ ። እንዲህ ለማለት ያስቻለኝ 1989 አ.ም በአዲስ አበባ በገዳመ ኢየሱስ ቤተክርስቲያ ከግርማ በቀለ እና ጽጌ ስጦታው ከተባሉ "ፕሮተስታንቶ" ጋር የክረምት ኮርስ ሰጥቶኝ ነበር። ኮርስ የሰጣቸው የሰንበት ተማሪዎች የፕሮተስታንትን ካንፕ እንዲቀላቀሉ ምክንያት ወኖአል።

  ከሁሉም ግን የማልረሳው ልዑለቃል አካሉ ለመዳን ምን ያስፈልጋል ብሎ ፈተና ላይ ለጠቀን ጥያቄ የሰጠውት መልስና፤ እርሱን ኤክስ አድርጎ የጻፈው መልስ እስካሁን ይገርመኛል። እኔ የመለስኩት በስላሴ ፤በክርስቶስ ኢየሱስ ስለማመን፤ ስልመጠመቅ፤ ስለቅዱስ ቁርባን፤፦ እሱ ሁሉም ላይ አንዴአስምሮ(አክስ አድርጎ) በጌታ ማመን ብሎ ጻፈበት። ኮርሱ ከተሰጠ በኃላ ከ 1-2 አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሁሉም የሰንበት ት/ቤት አባላት ማለት ይቻላል ፕሮተስታንት ቸርች ተቀላቀሉ።

  ከዚያ ድርጊቱ ከታረመ መልካም። ካልታረመ ግን በአባቶች መካከል ምን ያደርጋል?

  ኢየሱስ ክርስቶስ የጌቶ ጌታ ነው።

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤