Wednesday, January 23, 2013

የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ቤተ-ሚናስ ማኅበረ መነኮሳት አቤቱታቸውን ለክልሉ መንግሥት አቀረቡ


·       የትግራይ ክልል ተወላጅ ካልሆናችሁ በዚህ ገዳም መኖር አትችሉም” ተብለናል፤
·       ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋልድባ የሚለውን ስም መጥራት ሁሉ የተለየ ይዘት እየተሰጠው” ነው፤
  •       መነኮሳት ይታሰራሉ፤ ይደበደባሉ፤
  • ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጋር ተነጋግረዋል ተብሏል።
(ደጀ ሰላም፤ ጥር 12/2005 ዓ.ም፤ ጃኑዋሪ 20/2013/ PDF)፦ የዋልድባ የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ቤተ-ሚናስ ማኅበረ መነኮሳት አቤቱታቸውን ለአማራ ብሐየራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት እና ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አቀረቡ። በመነኮሳት ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የዘረዘረው ደብዳቤው የክልሉ መንግሥት በሰላማውያን መነኮሳት ላይ የሚደርሰውን እንግልት እንዲያስቆም ጠይቀዋል። የታሰሩ፣ የተንገላቱ፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን መነኮሳትም ዝርዝር አቅርበዋል። ሙሉ የደብዳቤው ሐሳብ ቀጥሎ ሰፍሯል።
የክልሉ መንግሥት የመናንያኑን አቤቱታ ይቀበል ይሆን? የምናየው ይሆናል።
ቸር ወሬ ያሰማን አሜን

ቀን፡ ጥር 16 2005 ዓ.ም.
ለአ/ብ/ክ/መ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት
እና ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባህርዳር ቅርንጫፍ

ጉዳዩ፡ የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ቤተ-ሚናስ ማኅበረ መነኮሳት መብታችን እየተጣሰ ስለሆነ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድልን ስለመጠየቅ
ዋልድባ አብረንታንት ገዳም ሀገራችን ኢትዮጵያ ካሏት መንፈሳዊ ቅርሶች ውስጥ በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መምህራንን፣ ጳጳሳትን፣ መነኮሳትን በማፍራት፣ በመንፈሳዊ ትህርምትና ተጋድሎ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን በመፀለይ የእግዚአብሔርን  በረከት ለመቀበል በርካታ መናንያን በቦታው ይኖራሉ፡፡ መንግት የዋልድባን ቅዱስ መካንና ሌሎች የሀገሪቱን ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶችና ሀብቶች የመጠበቅ ኃላፊነትና የዝብ አደራ እንዳለበት እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም የደረሱብንን የመብት ጥሰቶች በሙሉ ዘርዝረን ማቅረብ ባንችልም የሚመለከተው የመንግሥት አካል መፍት እንዲሰጠን ዋና ዋና የሆኑ ችግሮቻችንን ጠቅሰን አቅርበናል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋልድባ የሚለውን ስም መጥራት ሁሉ የተለየ ይዘት እየተሰጠው ሁሉም ነገር አዲስ እየተገነባ ካለው የስኳር ፋብሪካ ጋር እየተያያዘ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በዚህ ማመልከቻ እየጠየቅን ያለነው ጥያቄ ከፋብሪካው ጋር የተገናኘ ሳይሆን በራሱ ለረዥም ጊዜያት የቆየ አሁን ግን ችግሩ ከመጠን አልፎ አብዛኞቹን ማኅበረ መነኮሳት ያሰደደ፣ ገዳም እንዲቀይሩ ያደረገ፣ ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ያጋለጠ እንጅ ከግድቡ ግንባታ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ አለመሆኑን እንድትገነዘቡልን እንፈልጋለን፡፡

መንፈሳዊ ቦታ በማንም ላይ የዘር መድሎ ሳይደረግበት የሚገለገልበት መሆን እንዳለበት ግልፅ ነው፡፡ በቤተክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻህፍት የተፃፉትን ለጊዜው ትተን የሀራችን ገ-መንግሥትና ሌሎች የመንግሥት ሕግጋት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት የሀገሪቱ አካባቢ የመኖርና መብቱ እንዲጠበቅለት የመጠየቅ ሰብዓዊ መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ ይሁንና የፀለምት ወረዳ አስተዳደርን የተቆጣጠሩ ግለሰቦች ለዘመናት አንድነቱ ተከብሮና የዘር መድልዎ ሳይደረግበት ማንኛውም መናኝ በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ብቻ ተመርምሮ ይኖርበት በነበረው ቦታ ግልጽ በሆነ መልኩ የትግራይ ክልል ተወላጅ ካልሆናችሁ በዚህ ገዳም መኖር አትችሉም በማለት በልዩ ልዩ መልክ ማኅበረ-መነኮሳቱን በመከፋፈል፣ ለዚህ ዓላማም በጣት የሚቆጠሩ መነኮሳትን፣ የአካባቢውን ታጣቂና የሚሊሻ ኃይል በመጠቀም ማኅበረ-መነኮሳቱን ለከባድ እንግልትና የመብት ጥሰት እየዳረጉን ይገኛሉ፡፡ ከመብት ጥሰቶቹም የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
·                     የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ መረሳ የመንግሥትን ኃላፊነት ከተቀበሉበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ መግባት የለበትም የሚለውን መርህ በመጣስ ማኅበረ-መነኮሳቱን በዘር በመከፋፈልና የራሳቸውን የፖሊስ ታጣቂና የሚልሻ ኃይል በመጠቀም እያሰሩ በተደጋጋሚ በማስደብደብ፣ ለዚህም የማናውቀውን ፖለቲካ እንደ ሽፋን ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡
·                     ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በወረዳው ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ታጣቂዎችንና ሚሊሻዎችን በዛቻና በፍጥጫ አልፎ አልፎም በድብደባ በማስገደድ መነኮሳቱን ምግብ እንዲያቀርቡላቸው ማስገደዳቸው፣
·                     ለጸሎት ከምንገለገልባቸው ቅዱሳት መጻህፍት ውጭ ምንም የሌለንን መናንያን መነኮሳት በምንናገረው ቋንቋ ምክንያት አድልኦ በማድረግ ድብቅ የጦር መሳሪያ ይዛችኋል እያሉ ማስፈራራትና ብርበራ ማካሄድ፣

ድብደባና የመብት ጥሰት ከደረሰባቸው ገዳማውያን መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
v    አባ ገብረ ስላሴ ዋለልኝን ሐምሌ 13, 2004 ዓ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት ከገዳሙ በሚሊሻና በሁለት ፖሊሶች አስወጥተው እንኮይላህም ድረስ ከወሰዷቸው በኋላ ተከትለው የሄዱ ሌሎች መነኮሳትን ስንቅ ማቀበል እንደማይችሉ ገልጸው ማይጸብሪ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ወስደዋቸዋል፣ በጊዜውም ደብድበዋቸዋል፡፡
v     አባ ወልደጊዮርጊስ ኃይለ ማርያም እና አባ ገ/ማርያም ገ/ዮሐንስን ሐምሌ 21 ቀን 2004 ዓ.ም በገዳሙ ስርዓት መውጣት በማይቻልበት የህርመት ሰዓት ከሱባኤ አስወጥተው የጦር መሳሪያ አላችሁ በማለት ቤታቸው ከተበረበረ በኋላ ምንም አለመገኘቱ እየታወቀ ከመነኮሳቱ ለይተው ወደ ማይጸብሪ ወስደዋቸዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ሳይሆን የጸጥታ ፖሊስ ቢሮ እያሳደሩ ሌሊት ሌሊት በሽፍን መኪና እየወሰዱ የምንኩስና ቆባቸውንና ቀሚሳቸውን በማስወለቅ ሰረንቲያ በተባለ ወንዝ በሽቦ በተደጋጋሚ ደብድበዋቸዋል፡፡ ዋልድባ መኖር አትችሉም ብሎ አስተዳዳሪው ከለከላቸው፡፡ አክሱም ጸሎት እያደረግን እንኑር ሲሉ አስተዳዳሪው "አክሱምስ ቢሆን የማን ግዛት ነው?" በማለት ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ካልወጣችሁ ትገደላላችሁ፣ ገዳያችሁም አይታወቅም ብሏቸዋል፡፡ አሁን የት እንዳሉ አናውቅም፣ ከደረሰባቸው ግፍ አንጻርም ሁሉን ሰው ስለሚጠራጠሩ በስልክ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡
v    መናኝ ክንፈገብርኤል ወልደሳሙኤል ነሐሴ 2004 ዓ.ም. ከአባ ነፃ አካባቢ ለገዳም ተልዕኮ ሲንቀሳቀስ ተይዞ ማይገባ አስገብተው ወልቃይት ወረዳ ላይ ለሳምንት አስረው ከደበደቧቸው በኋላ ማይጸብሪ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ለአራት ወራት ፍርድቤት ሳይቀርብ ታስሮ ለበዓለ ልደት ተለቋል፡፡
v    አባ ገ/ስላሴ ገ/እግዚአብሔር ነሐሴ 20 2004 ያለምንም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና አቡነ ጳውሎስ በመሞታቸው ደስ ብሎሃል ብለው  ከገዳሙ አስወጥተው ፖሊሶች ወልቃይት ወረዳ ማይገባ አስረውኝ ከ9 ቀን በኋላ ፍ/ቤት በዋስ ተለቀዋል፡፡
v    መናኝ ወልደሩፋኤል ወልደሳሙኤል ከገዳሙ ውስጥ ለተልዕኮ ሲንቀሳቀስ ነሐሴ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ላይ ፌዴራል ፖሊሶችና የአካባቢ ሚሊሻዎች አገርህ የት ነው ብለው ከጠየቋቸው በኋላ ደበደቧቸው፣ ደብዳቢው መዝን የተባለ ታጣቂ ነው፡፡ ከደበደቡት በኋላ ሌሎች ማኅበረ-መነኮሳት ወዳሉበት ማይለበጣ አምጥተውት ብዙዎቻችን እየሰማን "ዱላው ተስማማህ ወይ?" እያሉ ተዘባበቱበት፡፡ በድብደባውም እጃቸው ተሰብሯል፡፡ ከዋልድባ ውስጥ በድብደባው ምክንያት አብረንታንትን ለቀው ዋልድባ ዳልሻ ከተባለው ቦታ ይገኛሉ፡፡
v    ቤተ-ሚናስ ውስጥ በመነኮሳት መካከል የጠፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የአካባቢው ነዋሪዎች ለማስታረቅ ማህበረ መነኮሳቱን ፈቃድ ጠይቀው ማህበረ መነኮሳቱም ስለተስማማ ለሽምግልና 40 የሐገር ሽማግሌ ተመርጠው በገዳሙ ማኅተም ጥሪ ተደርጎላቸው ነበር፡፡ ለህጋዊነትም መንግሥት እንዲያውቀው የወረዳውን አስተዳደር ጠይቁ ብሎ ማኅበረ መነኮሳቱ ስለጠየቁ የማይፀብሪ አስተዳደር መነኮሳቱን የምታስታርቁ ከሆነ እርምጃ እወስድባቸዋለሁ አላቸው፡፡ ይህን ማስጠንቀቂያ የሰሙት ሽማግሌዎች ሲቀሩ  ከሽማግሌዎቹ መካከል አራቱ ማለትም አቶ አለምሸት ሙሉ፣ አቶ ተክሌ ገ/ኪዳን፣ አቶ አምባቸው ጥላሁንና አለቃ መሀቤ ገ/መስቀል ይህን ስላልሰሙ ወደ ገዳሙ ለማስታረቅ ስለመጡ ሀሙስ ዕለት ጥር 2፣ 2005 ዓ.ም የማይጸብሪ ወረዳ ጸጥታ ሰራተኛ ነኝ ያለ አቶ ረዘነ የተባለ ሰው አስሮ ይዟቸው ሄዶ ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋቸው ለቀዋቸዋል፡፡ ከሽማግሌዎቹ አንዱን አቶ አለምሸትን የትግራይ ተወላጅ ስላልሆንክ ወደ ሀገርህ ወደ ክልል ሦስት ለቀህ ሂድ በማለት አዘውታል፡፡
v    ጥር 2 2005 ዓ.ም. አባ ወ/ገብርኤል ገ/ስላሴና አባ ገ/ህይወት ተ/ማርያምን ማይለበጣ ገዳሙ ውስጥ እያለን የማይጸብሪ ፖሊሶች በዓታችን ውስጥ እያለን ከጓደኞቻችን ለይተው ካስወጡን በኋላ ትፈለጋላችሁ ብለው ከባላገር ቤት ለየብቻ አሳደሩን፡፡ ለሽንት እንኳ እንውጣ ብለን ስንጠይቅ በጥፊ እየደበደቡ አሳደሩን፡፡ ጠዋትም እንደናንተ ያለ ሽፍታ መነኩሴ አግኝተናል ብለው ለጸሎት ደንደረቋ ከተባለ ቤ/ክን ስመለስ አባ ኃ/ማርያም ገ/ስላሴን እና መናኝ ታዲዮስ ገ/መድህንን ጨምረው ማይጸብሪ ወስደው አሰሩን፡፡ ለአራት ቀን ካቆዩን በኋላ ነጻ ናችሁ ተብለን ተለቀቅን፡፡ በግምት 10 ኪ.ሜ ያህል ወደ ገዳሙ መመለስ ከጀመርን በኋላ እንደገና በሽፍን መኪና ተከታትለው እናንተ ሽፍቶች ቁሙ ብለው መልሰው እያዳፉ እስር ቤት መለሱን፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ ከእስር ቤት አስጠርቶ ቢሮው ከወሰደን በኋላ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ሆኖ "እናንተ ተመልሳችሁ ወደ ገዳም መግባት አትችሉም፣ የወጡትም አይመለሱም፣ በገዳሙ የቀሩትንም እየመነጠርን እናወጣቸዋለን፤ እንገባለን ካላችሁ ገዳያችሁን ሳታውቁ ትገደላላችሁ ብሎናል፡፡ የጎጃም፣ የጎንደርና የሸዋ ሌባ ተሰብስባችሁ ከገዳሙ ልትቀመጡ አትችሉም ብሎናል፡፡ በተደጋጋሚ ባደረገው ንግግር ከማሰርና ከመደብደብ አልፎ አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወደ ዋልድባ ገዳም መግባት አትችሉም፣ ከውስጥ ያሉትንም ጠራርጌ አወጣቸዋለሁ በማለት፣ ይህን ባታደርጉ ግን ገዳያችሁ ማን እንደሆነ ሳይታወቅ ትገደላላችሁ ስለተባልን አቅም ያለን መነኮሳት ወጥተናል፡፡

በተጨማሪም ከገዳሙ ለመውጣትም ሆነ ወደ ገዳሙ ለመግባት በምንንቀሳቀስበት ጊዜም የትግራይ ክልል ነዋሪ መሆናችሁን የሚያሳይ የቀበሌ መታዎቂያ ካላመጣችሁ እያሉ ያስገድዱናል፡፡ የገዳሙ ማኅተም ያለበት መታዎቂያ ስናሳይ ተቀባይነት የለውም እየተባልን መንቀሳቀስ እንዳንችል ተደርገናል፡፡ አሁን ወደ ጎንደር ስንመጣም ያስሩናል ብለን በትክክለኛው መንገድ መውጣት አልቻልንም፡፡ ስለሆነም ተጨማሪ የሁለት ቀን የእግር መንገድ በርሃ ለበርሃ ተጉዘን ጎንደር ገባን፡፡ በዋናው መንገድ ለመምጣት የሞከሩት ታስረዋል፡፡ ማኅበረ-መነኮሳቱን በዘረኝነት ከበተኑ በኋላ 31 ያህል መነኮሳት ይህን ማመልከቻ ስናቀርብ ሌሎች ብዙዎች ገዳም ቀይረው ሄደዋል፡፡ እኛን ካስወጡ በኋላ የገዳሙን አስተዳደር ከወረዳ አስተዳደር የተላኩ ሚሊሻዎችን ይዘው መምህር፣ እቃቤትና ሌሎች ሰራተኞችን በአዲስ አዋቅረዋል፡፡ ይህም ግልጽ የሆነ ጣልቃገብነት ነው፡፡ የገዳሙንም ስርዓት ያልጠበቀ ነው፡፡

ይህ ሁሉ የመብት ጥሰት የሚደርስብን ምንም ጥፋት ተገኝቶብን አይደለም፡፡ በእኛ እምነት ይቅርና የብዙ ዘመን ታሪክ ያለው ዋልድባ አብረንታንት ገዳም ማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ባለ ገዳም ውስጥ መንፈሳዊ ስርዓቱን ተከትለን የመኖር መብታችን ሊጠበቅልን ይገባል፡፡ ይሑንና በተደጋጋሚ ያለአግባብ እየታሰርን፣ እየተደበደብን፣ የመንቀሳቀስ ነፃነታችን ተገድቦ፣ የግድያ ማስፈራሪያ በመንግሥት ባለስልጣን እየደረሰን በገዳማችን ለመኖር አልቻልንም፡፡ ዋስትናም አጥተናል፡፡ የሌላ ሀገር ዜጋ የሆንን ይመስል ያለጥፋት በመንፈሳዊ በዓታችን እንዳንኖር የማናውቀውን ፖለቲካ ተገን ባደረገ ዘረኛ አስተሳሰብ በገዳማችን የመቀጠል መብታችንና የገማኅበረ-መነኮሳቱ ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ በገዳሙ መነኮሳት ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በእኛ ብቻ ሊያቆም የሚችል ሳይሆን ውሎ አድሮ መጥፎ ጠባሳ የሚተው ጉዳይ በመሆኑ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሙሉ መፍትሄ እንዲሰጠን እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን፡፡

ስለሆነም የሚመለከተው የመንግሥት አካል ወደ ገዳማችን ያለችግር መግባት እንድንችል ዋስትና እንዲሰጠን፣ መደብደብና ማስፈራራት እንዳይደርስብን፣ በነጻነት የመኖርና የመንቀሳቀስ መብታችንን እንዲያስጠብቅልን፣ መብታችንን በተደጋጋሚ የጣሱብንን የመንግሥት አካላትም ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወስድልን፣ የወረዳው የጸጥታ አካላትና አስተዳደርም ህገ-ወጥ በሆነ መልኩ በገዳሙ አስተዳደር ላይ ሹም ሽር ማስደረግን ጨምሮ የሚፈጽሙትን ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙልን እንዲደረግልን በቤተክርስቲያን አምላክ ስም እንጠይቃለን፡፡
የአመልካች ማኅበረ-መነኮሳት ስም ዝርዝርና ፊርማ
1.              አባ ገ/ዮሐንስ ወ/ሳሙኤል
2.             አባ ገ/ስላሴ ገ/እግዚአብሔር
3.             አባ ወ/ተክለሃይማኖት ዮሐንስ
4.             አባ ገ/መድህን ወ/ገብርኤል
5.             አባ ገ/ስላሴ ጥሩነህ
6.             አባ ገ/ስላሴ ወ/ሳሙኤል
7.             አባ ገ/ሚካኤል ኃ/ማርያም
8.             አባ ገ/ስላሴ ገ/መድህን
9.             አባ ገ/ስላሴ
10.           አባ ገ/ሚካኤል ወ/ሳሙኤል
11.             አባ ኃ/ማርያም ገ/ስላሴ
12.            አባ ገ/ህይወት ተክለማርያም
13.            አባ ወ/ገብርኤል ገ/ስላሴ
14.           አባ ገ/ህይወት
15.            አባ ገ/ማርያም ወ/ህይወት
16.           መናኝ ኃ/መለኮት ሐዋዝ
17.            መናኝ ታዴዎስ ገ/መድህን
18.           መናኝ ገ/ሚካኤል ሰሎሞን
19.           መናኝ ኃ/ስላሴ ዳዊት
20.          መናኝ ሠይፈስላሴ ወ/ሳሙኤል
21.            መናኝ ገ/መድህን ወ/ሳሙኤል
22.           መናኝ ገ/እግዚእ
23.           መናኝ ወ/ሩፋኤል ወ/ሳሙኤል
24.          እማሆይ ፅጌ ድንግል
25.           እማሆይ ወለተሰንበት
26.          እማሆይ ወለተስላሴ
27.           እማሆይ አመተኢየሱስ
28.          እማሆይ ወለተፃድቅ
29.          እማሆይ ወለተማርያም
30.          እማሆይ አፀደማርያም
31.            እማሆይ ሂሩተሥላሴ

ግልባጭ፡
ü    ለሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት ጽ/ቤት
ü    ለሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤