Wednesday, January 23, 2013

የዋልድባ ውዝግብ እንደቀጠለ ነው


ሙሉውን ቃል በ PDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
·         አማርኛ ተናጋሪ መነኮሳት ከገዳማቸው በግፍ ተባረዋል
·         መነኮሳቱ ለሁለት ቀናት ተጉዘው ጎንደር ገብተዋል
·         የትግራይ ተወላጅ አበሜኔት እና እቃ ቤት በአቶ ሲሣይ መሬሳ ተሹመዋል
·         በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው ለክልሉ ፕሬዘዳንት አቤቱታ በማሰማት ላይ ናቸው
አቶ ሲሣይ መሬሳ

ባለፈው ሳምንት እንደዘገብነው በአቶ ሲሣይ መሬሳ መሪነት ገዳማውያን መነኮሳት በግፍ አማርኛ ተናጋሪዎች ናችሁ የተባሉት ተባረዋል፣ አቅም ያላቸው በረሃ አቋርጠው ሸሽተዋል፣ ደካሞቹ አረጋውያን አባቶች እጅግ በሚያዝን ሁኔታ ጺማቸውን እየተነጩ፣ ቆባቸውን እያቀለቁ ገረፋቸው፣ ደበደቧቸው፣ ጭንቅላታቸውን በሰደፍ ደበደቧቸው . . . እውን የሰው ዘር ቀርቶ ለዚያውም ከአንድ አፈር ኢትዮጵያ ምድር የበቀለ ሰው ይፈጽመዋል ለማለት እጅግ ይከብዳል። ነገር ግን የራሳችን ሰዎች ከኢትዮጵያ አብራክ ክፋዮች ነገር ግን እራሳቸውን የአንድ ጎጥ እና ወንዝ ሰዎች ነን ብለው የለዩ፣ በዚያች ምድር ላይ ፈልገው ያልተወለዱ፣ ሰው ሊፈጽመው የማይችለውን ፍጹም ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መልኩ አረጋውያን አባቶችን ለድብደባ እና ለእስር መዳረጋቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ክርስተት ሆኗል። ለተቀሩትም የማስፈራሪያ መዓት እየደረሳችው ነው “ገዳሙን ለቃችሁ ባትሄዱ፥ ማን እንደገደላችሁ ሳይታወቅ ትሞታላችሁ” “ይሄ ምድር ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ነው፥ እናንተ ልትኖሩበት ቀርቶ ልትረግጡት አትችሉም” እና የመሳሰሉትን የማስፈራሪያ ቃላት በታጣቂዎች አማካኝነት እየተነገራቸው ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ያለ ጸሎት መጽሐፍ እና መቋሚያ የሌላቸው መነኮሳት እቤታቸውን “መሣሪያ ታጥቃችኋል” በሚል ሰበብ ዘወትር ብርበራው እና ማንገላታቱ በወጡ በገቡ ቁጥር በርግጫ እና በጡጫ መሰቃየታቸውን ቀጥለውበታል። 

በእግር ሸሽተው የወጡ መነኮሳት ለሁለት ቀናት ተጉዘው ግማሹ በደም ተነክረው፣ እራቸው ዝሎ፣ መናገር ተስኗቸው ጎንደር ከተማ ገብተዋል። ግማሹም እንዲሁ በየበረሃው የወደቁም ቀርተዋል፣ የተወሰኑትም በመንግሥት ታጣቂዎች ተይዘው ለእስር ተዳርገዋል። እነዚህ ሁሉ ገዳማውያን አባቶች ያጠፉት ጥፋት የለም፣ ገዳማችንን ተው . . የጸሎት ቦታችንን አትንኩ . . የአባቶቻችንን ድንበር አትለፉ . . . ነበር ያሉት ነገር ግን በአጸፋው ለግርፋት፣ ለድብደባ፣ ለእስር እና ለስደት ተዳረጉ። ሰሚ ያጣውስ የዋልድባ ገዳም ጉዳይ እውን ሰሚ ጆሮ ያገኝ ይሆን? እናምናለን መድኃኒዓለም ክርስቶስ ከእናቱ ጋር በኪደተ እግሩ የረገጠው እና ቃል ኪዳን የገባለትም ምድር፣ ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ምድሪቱን ወስደው በአርያም

ያስባረኩት ምድር በመሆኑ ምንም ግፉ እና እንግልቱ በገዳማውያኑ ላይ ቢበረታም እናምናለን የእነሱ አይደለም እና የዋልድባን ገዳም እንኳንስ ፋብሪካ ሊሰሩበት ቀርቶ በቅጡ ተረጋግተው መቀመጥ አይችሉም የእኛ አምላክ እንደ ሰዎች ስላልሆነ እድሜ ለንሰሐ ይሰጣል፣ ይታገሳል ነገር ግን አልሰማ ብለው ስሙ ጠዋት ማታ የሚሰለስበትንና የሚወደስበትን ቦታ ለሌላ እነሱ ላሰቡት ሥራ ሊውል እንደማይችል ተግዳሮታቸውንም ካላቆሙ እራሳቸውንም እንደሚያጠፋ የታመነ አምላክ ነው። በዘጸአት ፲፬ ፥ ፰ የተጠቀሰው ቃል እንዲህ ይላል “እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ።” እንግዲህ በቃሉ የታመነ አምላካችን አሁንም የግብጹን ፈርዖን ልብ እንዲጸና ያደረገ ዛሬም የኛው ወገኖች ልባቸው ደንድኖ በወገኖቻቸው ላይ ይልቁንም በባሕታውያን ላይ ችግር እና መከራ ቢያጸኑባቸውም። ስሙ ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁንን እነዚህን ባሕታውያን ያጸናቸዋል እነርሱም ለአሳዶጆቻቸው ይጸልዩላቸዋል የቀናውን መንገድ እንዲያሳያቸው። 

ባለፈው ሳምንት በዘገብነው መሰረት ከትላንት በስቲያ የእነ አቶ ሲሣይ መሬሳ ዘረኛ እና ከፋፋይ ታጣዊዎች እና ሚሊሻዎች የገዳሙን ክልል አጥረው ወደ ገዳሙም ሆነ ከገዳሙ ውጪ መውጣት አትችሉም በማለት ገዳማውያኑን እስከ ዛሬ የነበሩትን የገዳሙን አበሜኔት እና እቃ ቤት ለእነ አቶ ሲሣይ መሰሪ ተግባር ተባባሪ ባለመሆናቸው እንዲሁም በትውልዳቸው ከትግራይ ክልል ውጪ በመሆናቸው የእነሱን መስመር የሚከተል ቆብ ያጠለቀ ካድሬ ሾመዋል። እንደ ገዳሙ ሥርዓት የገዳሙ አበሜኔት በእድሜ አለያም በጤና ምክንያት መሥራት እስካልቻሉ ድረስ እንደዚህ እንደ አሁኑ ለዚያውም በአንድ ተራ የወረዳ አስተዳዳሪ ጡጫ እና ግልምጫ እንዲህ አይነት ሥራ ተሰርቶ አይታወቅም። እስከ ዛሬ ድረስ ገዳሙን ሲያስተዳድሩ የቆዩት
፩ኛ/ መምህር ገብረ ጊዮርጊስ አበሜኔት ትውልዳቸው ከትግራይ ቢሆንም በምንም መልኩ ገዳማውያኑን አሳልፌ አልሰጥም ለእናንተም አልተባበርም በማለታቸው ተባረዋል
፪ኛ/ አባ ወልደ ሥላሴ እቃ ቤት ሆነው ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል አሁን በእነ አቶ ሲሣይ አማካኝነት በግፍ ተባረው በምትካቸው የመንግሥት እንባ ጠባቂ፣ የእነ አቶ ሲሣይ ተላላኪ የሆኑ ሰዎች በወረዳ አስተዳዳሪው መልካም ፈቃድ ተቀምጠዋል እንሱም
፩ኛ/ አባ ገብረ ዋሕድ አበሜኔት
፪ኛ/ አባ ገብረ ሕይወት መስፍን (የሕወሃት አባል) እቃ ቤት ተብለው በወረዳው አስተዳዳሪ ተሾመዋል
ከአካባቢው ምንጮች ለመረዳት እንደቻልነው  አብዛኛው ገዳማውያን ተቃውመው ብዙ እንግልት ቢደርስባቸውም ነገር ግን ጥቂቶች የመንግሥት ካድሬዎች፣ የገዳሙን መጥፋት የሚመኙ ደግፈው ይሁን ይመረጥ በማለት አይሆንም ያሉትን እየጠቆሙ ያስረፉ፣ ያስደበደቡ፣ ያስፈነከቱ ልቦና ይስጣቸው እንላለን። በተጨማሪ በዚህ የዘረኛ ሥራዎችን እነ አቶ ሲሣይ እና ግብረአበሮቻቸው ብቻ እንጂ በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችም ጭምር በመቃወማቸው እናንተ “አማራ አምላኪዎች” በመባል ይበልጥ ድብደባ እና እንግልት የደረሰባቸው በርካቶች እንደሆኑ ለመረዳት ችለናል እንደውም እስከ ዛሬ ድረስ አበሜኔት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት መምህር ገብረ ክርስቶስ የትግራይ ተወላጅ ቢሆኑም ለነ አቶ ሲሣይ የዘረኛ እና ከፋፋይ ሥራ ተባባሪ አልሆንም በማለታቸው የዚህ የዘረኞች እና ግፈኞች ድብደባ ሰለባ መሆናቸውን የታመኑት ምንጮቻችን ገልጸውልናል። የሆነ ሆኖ ገዳማውያኑ ከጥቂት የመንግሥት ካድሬዎች በስተቀር በአንድ ወንድማማችነታቸው በመጽናት ወንድሞቻችንን የተቀበሉትን ሰማዕትነት እኛም እንቀበል በማለት ለወንድሞቻቸው እና ለእናቶቻቸው ሲሉ ሲገረፉ፣ ሰደበደቡ እና ሲንገላቱ የሰነበሩ በርካቶች እንደነበሩ አረጋግጠናል።


ከጥቂት ቀናት በፊት ግፈኞችን ሸሽተው በጎንደር የገቡት ከ30 - 40 የሚጠጉ መነኮሳት በጎንደር ከተማ በሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ በምዕመናን አስተባባሪነት እርሮቻቸውን ሲያጥቡ፣ ደማቸውን ሲጠርጉ፣ የደረቀ ጉሮሮአቸውን በውሃ ሲያርሱ፣ በመንገድ የደከመ ጎናቸውን መኝታ ሰጥተው ድካማቸውን እና እንግልታቸውን የተጋሩ የጎንደር ከተማ ወጣቶች ምስጋና ይግባቸው እና እነዚህን አባቶች ለጥቂት ቀናት ሲንከባከቡ ቆይተው ትላንት ገዳማውያኑ አቤቱታቸውን ለክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ለማቅረብ እና እየደረሰባቸው ያለውን እንግልት እና ድብደባ ለመንግሥት አካላት ለማሳወቅ ወደ ባሕር ዳር ማቅናታቸውን የታመኑ ምንጮቻችን ገልጸውልናል። በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሚመራው የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት እኛን አይመለከትንም ወደ እዚህ አትድረሱብን በሚል ችግራቸውን ለመስማት እንኳን በራቸውን ለመክፈት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ለመረዳት ችለናል። ሃገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ የተቋቋመው በሃገረ ስብከቱ ሥር ያሉ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት፣ አድባራት እና ገዳማት ችግር ሲኖር፣ ችግራቸውን ለመፍታት፣ አቤቱታ ሲኖር ተቀብሎ ችግሮችን መፍታት አለያም ለበላይ የቤተክርስቲያኒቱ አካላት በመውሰድ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረግ ሲሆን፥ የሰሜን ጎንገር ሃገረ ስብከት ግን ችግሩንም ለመስማት ፈቃደኞች አለመሆናቸውን በራቸውን በመዝጋት አሳውቀዋል።

                                   
አቶ  
ዛሬ እረፋዱ ላይ በደረሰን መረጃ መሰረት ከዋልድባ አበረንታት ገዳም በግፍ አማርኛ ተናጋሪዎች ናችሁ፣ አማራ እዚህ ሊኖር አይችልም፣ ይሄ የትግራይ ምድር ነው ተብለው የተሰደዱት አባቶች እና እናቶች ባሕር ዳር ደርሰው አቶ አያሌው ጎበዜ የአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ቢሮ በመገኘት አቤቱታቸውን እንዲቀበሏቸው በተማጽኖ ላይ እንደነበሩ ምንጮቻችን ገልጸውልናል። የገዳሙ መነኮሳትም ከአቤቱታቸው ጋር ለክልሉ ፕሬዘዳንት የአቤቱታ ደብዳቤም እንደሚሰጧቸው እና ለችግሮቻቸው መፍትሄ እንዲሰጧቸው እንደሚያመለክቱ ተረድተናል። በትግራይ ክልል እየደረሰባቸው ካለው በደል እና ግፍ እንዲሁም መነኮሳቱ
·         እንደ አንድ ዜጋ እንኳን የመናገር ወይም የመጠየቅ መብታቸውን ጭምር እንደተነፈጉ፣
·         ለለፉት በርካታ ዓመታት የኖርንበትን ገዳም ቤተ እግዚአብሔር ጥለን የምንሄድበት የለንም፣ 
·         ገዳማችንን እና ቤተክርስቲያናችንን ጥለን ልንሄድ አንችልም፣
·         ያለ ጥፋታቸው እና በደላቸው በእስር የታጎሩ ወንድሞቻችን ይፈቱልን፣
·         አቶ ሲሣይ መሬሳ የሚባለውን የወረዳው አስተዳዳሪ ያስታግሱልን፤ ጨካኝ አረመኔ ሰው በመሆኑ ልንቋቋመው አልቻልንም፣
·         በሃገራችን በምድራችን ይልቁንም እግዚአብሔርን ለማገልገል በምንኖርበት ገዳማችን ለመኖር መብታችን ይጠበቅልን፣

እና ተመሳሳይ በርካታ አቤቱታዎችን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ምንጮቻችን ገልጸውልናል። የክልል መስተዳደር ጽ/ቤቱም የገዳማውያኑን አቤቱታ ተቀብሎ መልካም ምላሽ እንደሚሰጣቸው በመተማመን ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፥ ነገር ግን በተቃራኒው ለአቤቱታቸው መልካም መልስ ባያገኙ እና ይልቁንም እየደረሰ ያለውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ችግሩ ተባብሶ ከቀጠለ ገዳማውያኑ በእርግጥ ወደ የት እንደሚሄዱ ባይታወቅም እነ አቶ ሲሣይ ግን አላማቸው ሊሰምር ይችላል በማለት ከወዲሁ የቀሩትን ተከራካሪዎች አባረው እና ገፍተው አስወጥተው ዝርፊያውንም፣ እርሻውንም፣ ለመጀመር ጎምዥተው ተቀምጠዋል ነገር ግን እግዚአብሔር ዘወትር ከጸረሃ አርያም በዓይኖቹ እንቅልፍ ሳያልፍ የሚጠብቃት ቅድስት ቤተክርስቲያን እነዙ እነሚፈልጉት ፈጽሞ ሊያደርጓት፥ “የተቃጡ እጆች ይቆረጣሉ” እንዳለው እስከ አሁንም እየተቆረጡ ነው ወደፊትም በእግዚአብሔር ቤትና ሕዝቦች ላይ እጁን የሚያነሳ በጊዜው ብድራቱን ሳይውል ሳያድር ያገኛል። እኛም ለትዕቢተኞች ልቦናን፣ ለደካሞች ጽናትን፣ ከአባቶቻችን የጸሎታቸው እና ምልጃቸው በእኛም በልጆቻቸው ይደርብን እያልን በቀጣይ መነኮሳቱ ከክልሉ መስተዳደር የተሰጣቸውን መልስ ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን ይጠብቁን።
ቸር ወሬ ያሰማን

ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።
፩ኛ ተሰሎንቄ ፭ ፥ ፲፬

4 comments:

 1. ኧረ የመድሃኒያለም ያለህ!!!!!

  ReplyDelete
 2. You will see what will happen after Megabit 27,2005 E.C as the holy fathers said!

  ReplyDelete
 3. Please call strong prayer from Megabit 1-21,2005 all over the world as the holy fathers living in the monasteries said. Please be HERO!

  ReplyDelete
 4. "ስለ አንተ ሁልጊዜም ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል።አቤቱ፥ ንቃ፤ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን።ለምንስ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራችንንና ችግራችንንስ ለምን ትረሳለህ?ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቍላለችና፥ ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለችና።አቤቱ፥ ተነሥና እርዳን፥ ስለ ስምህም ተቤዠን። "

  መዝሙረ ዳዊት 44:22-26

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤