Monday, January 28, 2013

አቶ ሲሣይ ለአቤቱታ በወጡት አባቶች ላይ ማስፈራራቱን ቀጥሏል

የገዳማውያኑ በረከት ይደርብን


·         ዋልድባ ከምትመለሱ እናታችሁ ሆድ ብትገቡ ይቀላችኋል (አቶ ሲሣይ መሬሳ)
·         የሽሬ እና እንደስላሴ ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የአቶ ሲሣይን አካሄድ መቃወም አለባቸው
·         የባሕር ዳር ሕዝበ ክርስቲያን እና የጎንደር ሕዝበ ክርስቲያን ሊመሰገኑ ይገባል
በፒዲፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ      

ባለፈው ሳምንት ከ30 - 40 የሚጠጉ መነኮሳት እና መነኮሳይት ከዋልድባ ገዳም በረሃ አቋርጠው ለሚመለከተው ክፍል አቤት ለማለት፣ በእነ አቶ ሲሣይ እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ ለማሳወቅ፣ ቤተክርስቲያናችንን ይተውልን በማለት አቤት ለማለት ወደ ጎንደር ከዛም ወደ ባሕር ዳር የተጓዘው የመነኮሳቱ እና የመነኮሳይቱ ቡድን አቤቱታቸውን ለሚመለከተው የመንግሥት አካላት እንዲሁም ለቤተክርስቲያኒቱ ለቀረቡት ሁሉ ብሶታቸውን ገዳማቸው (ገዳማችን) በጥቂት ጽንፈኞች በግፍ መነጠቁን ሲያሳውቁ ቆይተዋል፤ አሁንም በዚው ሥራቸው ላይ እንደሚገኙ ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

አቶ ሲሣይ መሬሳ የጸለምት ወረዳ አስተዳዳሪ ዓላማቸው በትክክል ምን እንደሆነ የማይታወቀው አስተዳዳሪ ለእርሳቸው የሚመች ከዓላማቸው ጋር የሚስማማ አበሜኔት እና እቃ ቤት ከመሾማቸውም ባሻገር የእነሱን ዘረኛ አካሄድ ተቃውመው ለሚመከተው የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ለአቤቱታ የሄዱትን አባቶች በስልክ በመደወል ማስፈራሪያ እና ወደ ገዳማቸው ከሚመለሱ እዛው እንደወጡ ቢቀሩ እንደሚሻላቸው እና ቢመለሱም ደማቸው ደበከልብ ሆኖ እንደሚቀር እያስፈራሩ ይገኛሉ፤ አቶ ሲሣይ በትላንትናው ዕለት ስልክ ደውለው ያናገሯቸው አባት እንደተናገሩት “ወደ ዋልድባ ከምትመለሱ፥ ወደ እናታችሁ ሆድ ብትመለሱ ይቀላችኋል” በማለት ማስፈራራቱን ቀጥለዋል። ይሄም የሚያሳየን የሰውየውን ጽንፈኝነት እና ለቤተክርስቲያኒቱ ወይንም ለገዳሙ ደንታ ሳይኖረው እርሱ በሚያስበው የፖለቲካ መስመር የማይሄዱትን አባቶች በማንገላታት፣ በማሰር፣ በማስፈራራት ህልሙን እውን ለማድረግ የሚሯሯጥ ሰው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

የመነኮሳቱ እና የመነኮሳይቱ ቡድን የመንግሥት የተለያዩ በለሥልጣናትን ያነገረሩ ሲሆን ከነዚህም መካከል አቶ አያሌው ጎበዜ በአማራ ክልል መስተዳደር የክልሉ ፕሬዘዳንት፣ አቶ ሙሉጌታ የአማራ ክልል መስተዳደር የፖሊስ ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ እና በርካታ በመስተዳደሩ ጽ/ቤት ውስጥ የሚሰሩ የበታች ሹማምንት የመነኮሳቱን ቡድን ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል፤ በቅርብ ቀናት ውስጥም መልስ እንደሚያገኙላቸው ቃል ገብተውላቸው አሰናብተዋቸዋል። በመቀጠል ከባሕርዳር ወደ ጎንደር በማቅናት የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕን አነጋግረዋል፥ በዚህም የደረሰባቸውን እንግልት እና በደል በእንባ ጭምር ያስረዱት የመነኮሳቱ ቡድን ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በዋልድባ የተደረገውንም የእነ አቶ ሲሣይን ሹመት ጨምረው አስረድተዋል። እርሳቸውም በትግራይ ክልል የሽሬ እና እንደሥላሴ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወደ ሆኑት ብፁዕ አቡነ መቃሪዎስ አስቸኳይ መልዕክት በመላክ ጉዳዩ አስቸኳይ ትኩረት እንደሚያሻውም በመልዕክታቸው ገልጸዋል። የሽሬ እና እንደሥላሌ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልዕክቱን ተቀብለው ከክልሉ መስተዳደር ጋር ተነጋግረው በጸለምት ወረዳ እየተደረገ ያለውን ለመናገር አቅሙም ብቃቱም እንዳላቸው ይጠበቃል፤ በውጤቱም የወረዳውን አስተዳዳሪ የራሱን ሥራ እንዲሰራ እና ከገዳማውያኑ ላይ እና በገዳሙ አስተዳደር እየገባ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ እንዲያቆም እና በገዳሙ ላይ የሾማቸውን ካድሬውች በአቸኳይ እንዲያነሳ ጥያቄው ቀርቧል የማስፈጸሙ ሥራ የሽሬ እና እንደሥላሴ ሃገረ ስብከት ቢሆንም እኛም የልጅነታችንን በጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥበት የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን።

በሌላ በኩል የመነኮሳቱ ቡድን በመጀመሪያ በጎንደር በገቡበት ወቅት እግራቸውን በማጠብ፣ እህል ውሃ በማድረስ፣ ማረፊያ ቦታዎችን በማዘጋጀት የተባበሩት የጎንደር ከተማ ወጣት የሰንበት ት/ቤት አባላት እና ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፥ ስላደረጉት ታላቅ ተጋድሎ በመነኮሳቱ ቡድን ስም ታላቅ ምስጋናን እና ከበሬታን ለማቅረብ እንወዳለን። በመቀጠልም በበሕር ዳር በደረሱበት ወቅት ከዚያም በአዳራቸው ሁሉ ማረፊዎችን እና እህል ውሃ በማዘጋጀት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የከፈሉት መስዋዕትነት በቃላት ብቻ ብንገልጸው ማሳነስ እንዳይሆንብን ላበረከቱት አስተዋጾዖ በሙሉ አምላከ ቅዱሳን ዘወትር ከማያልቀው  በረከቱ እንዲያድላቸው ምኞታችን ነው። በመጨረሻ መነኮሳቱ እና መነኮሳይቱ በጎንደር ከተማ በተመለሱበት ወቅት እና እስከ አሁንም ድረስ በማስተናገድ ወደ ባዕታቸው እስከሚመለሱ ድረስ የሚደረግላቸውን ትብብር ስለእውነት ቃላቶች ሊገልጹት አይችሉም እና እንደው በደፈናው በያሉበት ያሉትን ወጣቶች ስለቤተክርስቲያን፣ ስለሃይማኖታችን የሚያደርጉትን ተጋድሎ ትውልድ አይረሳውም እግዚአብሔር አምላክ ዳግም በሚመጣ ጊዜ ‘ኑ እናንተ ቡርካን’ ከሚላቸው በቀኙ ከሚቆሙት ቅዱሳን ወገን ይደምርልን፣ ጸጋውን ያብዛላችሁ እንላለን።
ቸር ይግጠመን

1 comment:

  1. የመነኮሳቱ ቡድን በመጀመሪያ በጎንደር በገቡበት ወቅት እግራቸውን በማጠብ፣ እህል ውሃ በማድረስ፣ ማረፊያ ቦታዎችን በማዘጋጀት የተባበሩት የጎንደር ከተማ ወጣት የሰንበት ት/ቤት አባላት እና ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፥ ስላደረጉት ታላቅ ተጋድሎ በመነኮሳቱ ቡድን ስም ታላቅ ምስጋናን እና ከበሬታን ለማቅረብ እንወዳለን።

    በመቀጠልም በበሕር ዳር በደረሱበት ወቅት ከዚያም በአዳራቸው ሁሉ ማረፊዎችን እና እህል ውሃ በማዘጋጀት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የከፈሉት መስዋዕትነት በቃላት ብቻ ብንገልጸው ማሳነስ እንዳይሆንብን ላበረከቱት አስተዋጾዖ በሙሉ አምላከ ቅዱሳን ዘወትር ከማያልቀው በረከቱ እንዲያድላቸው ምኞታችን ነው። በመጨረሻ መነኮሳቱ እና መነኮሳይቱ በጎንደር ከተማ በተመለሱበት ወቅት እና እስከ አሁንም ድረስ በማስተናገድ ወደ ባዕታቸው እስከሚመለሱ ድረስ የሚደረግላቸውን ትብብር ስለእውነት ቃላቶች ሊገልጹት አይችሉም እና እንደው በደፈናው በያሉበት ያሉትን ወጣቶች ስለቤተክርስቲያን፣ ስለሃይማኖታችን የሚያደርጉትን ተጋድሎ ትውልድ አይረሳውም እግዚአብሔር አምላክ ዳግም በሚመጣ ጊዜ ‘ኑ እናንተ ቡርካን’ ከሚላቸው በቀኙ ከሚቆሙት ቅዱሳን ወገን ይደምርልን፣ ጸጋውን ያብዛላችሁ እንላለን።

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤