Friday, January 11, 2013

በዋልድባ ዛሬም እስራቱና እንግልቱ እንደቀጠለ ነው

ዘረኛው አቶ ሲሣይ መሪሳ

በትላንትናው እለት እንደዘገብነው በማይጸብሪና ጸለምት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሲሣይ መሪሳ ትእዛዝ ሰጪነት ሦስት የአካባቢው ነዋሪዎች በገዳሙ ክልል ውስጥ በመግባት በእስራት ወደ ማይጸብሪ ከተማ በመውሰት እዚያው በእስራት መቆየታቸውን እና በርካታዎች ሸሽተው ማምለጣቸውን ዘግበን ነበር። አሁንም ጽንፈኛው የአውራጃው አስተዳዳሪ ታጣቂዎቻቸውን በመላክ ወደ ገዳሙ ክልል ውስጥ በመግባት መነኮሳቱን ሲያንገላቱ፣ ሲያዳፉ፣ ሲደበድቡ ቆይተው በትላንት ምሽት ላይ ሁለት መነኮሳትን ማይለበጣ ላይ አንስተው እየደበደቡ እና እያሰቃቁ ወደ እስራት ወስደዋቸዋል፣ በመቀጠል በዛሬው ረፋዱ ላይ እነዚሁ ታጣቂዎች ተመልሰው በመምጣት ዶንዶሮቃ ላይ ሁለት ተጨማሪ መነኮሳትን እየደበደቡ ለእውራት እና ለእንግልት መዳረጋቸውን ከአካባቢው የደረሱን ምንጮች ገልጸውልናል።


በዚህ ዙር ዘመቻቸው መነኮሳቱን በግልጽ አነጋገር “ልማት የማትደግፉ ከሆነ ገዳሙን ለቃችሁ ውጡልን” በማለት አቶ ሲሣይ ለመነኮሳቱ መልዕክት ማስተላለፋቸውን እና ከዚህ በተጨማሪ በወሩ መጨረሻ ላይ በሚደረገው ስብሰባ፥ ቀደም ብሎ ለጥር ፬ የተጠራው ስብሰባ ተራዝሞ ለጥር ፴ በመቀጠሩ በዚህ ቀጠሮ ላይ የቤተ-ሚናስ አባቶች ውሳኔያቸውን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል ካሳውን ተቀብለው አካባቢውን ለቀው ወደ አማራ ክልል በሚገኙ ገዳም እንዲሄዱ ጥብቅ ትእዛዝ ተላልፏል እስከ አሁንም ድረስ ልናስቀምጣችሁ መቻላቻን እኛ ሆነን ነው፥ ልማትን እና ሰላምን እማትፈልጉ ከሆናችሁ በእኛ ክልል የመኖር መብት የላችሁም በማለት አቶ ሲሣይ ሲናገሩ መሰማታቸውን የአካባቢው ምንጮቻችን በሀዜኔታ ገልጸዋል። በገዳሙ የሚኖሩ አባቶች ላለፉት 1600 ዓመታት እንዲህ አይነት ፈተና ገጥሟቸው እንደማያውቅ እና የመጣውንም ፈተና በጸጋ እንደሚቀበሉት የሚናገሩት የገዳሙ አባቶች በተለያየ ሁኔታ በሰዎች ይልቁንም በቤተክህቱ ተስፋቸውን አጥተዋል
፩ኛ/ የገዳሙ አባቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ ተመልካች በማጣታቸው
፪ኛ/ ቤተ-ክህነቱ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ ሃላፊዎች እንደመሆናቸው መጠን ምንም አለማለታቸው እና ገዳሙን ከጥፋት ለመታደግ ጥረት ማድረግ አለመቻላቸው
፫ኛ/ በዓለም ዙሪያ ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ድምጻቸውን አጥፍተው ተመልካች ብቻ መሆናቸው
፬ኛ/ ጳጳሳት፣ ካህናት አባቶች፣ መምህራን፣ ዘማሪያን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ታሪካዊውን እና ጥንታዊውን ገዳም ለመታደግ አለማቻላቸው
፭ኛ/ በውጪም ሆነ በሃገር ውስጥ ያሉት ጳጳሳት እንደማይመለከታቸው ሁሉ በዝምታ ይልቁንም ለምርጫ መሯሯጣቸው

እነዚህ እና ተመሳሳይ የቤተክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ እና ወቅታዊ ችግሮች ተጨማምረው የቤተክርስቲያኒቱን ይዞታ ሊያስከብር እና ሊከራከር የሚችል አካል ባለመኖሩ ታላቁን ገዳማችንን በዋዛ ፈዛዛ ልናጣው እንደምንችል ከወዲሁ መገመት አያዳግትም። በአሁኑ ሰዓት በዋልድባ በጸሎት ተወስነው፣ በአርምሞ ከእግዚአብሔር ጋር ዘወትር በመነጋገር፣ ለዓለም ሕዝቦች፣ ለሃገራችን ሕዝቦች፣ ለቤተክርስቲያን መሪዎች፣ ለሕዝበ ክርስቲያኑ፣ ለአንባብያኑ፣ እናት አባት ለሞቱባቸው ሕፃናት፣ ለአረጋውያኑ እና ለደከሙት የሚጸልዩ አባቶች እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው በማይጸብሪ ከተማ ታጣቂዎች በዱር በገደሉ፣ በረሃ ለበረሃ ተሰደው የሚንከራተቱት አባቶች ቁጥር ወደ 49 የሚጠጉ ናቸው ከአካባቢው ምንጮቻችን ለማረጋገጥ እንደቻልነው እነዚህን አባቶች ይዞ በግርፋት፣ በድብደባ ህይወታቸውን ለማሳለፍ በዚህም መንግሥት የሚፈልገውን ሥራ ለመስራት እቅዶቹን ለማስፈጸም ብቸኛው መንገድ ነው ብሎ ማመኑ የመንግሥታችንን የዋህነት እና ትግሉ እና ተግዳሮቱ ከሥጋና ከነፍስ ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር መሆኑን ሊያውቀው ይገባል።
ይባስ ብሎ ዘረኛው የአቶ ሲሣይ መሪሳ አመራር በዋልድባ ገዳም አቤሜኔት የትግራይ ተወላጅ መሆን አለበት በማለት በገዳሙ ያሉትን መነኮሳት አማራዎች የልማት ተቃዋሚዎች ናቸው፣ ትግራይ እንድልማ አይፈልጉም፣ እስከ ዛሬ ሲጨቁኑን የኖሩት በቂ ነው፣ አሁን ጊዜው የኛ ነው፥ የፈለግነውን ማድረግ ይኖርብናል በማለት በዚያው በዋልድባ ገዳም አሰሮ ምንኮስናውን ተቀብለው የመነኮሱ አባቶችን ዘረኝነት፣ ጽንፈኝነትን፣ የጎጥ እና የወንዝ አጀንዳን በማስታጠቅ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ ይልቁንም ከአካባቢው ለማሰደድ ቆርጠው መነሳታቸውን ስንሰማ በእጅጉ ልብ የሚሰብር ዜና ሆኖ አግኝተነዋል። ለነፍሳቸው ያደሩትን መነኮሳት “እናንተ የትግራይ ተወላጆች ናችሁ፣ እናንተ ደግሞ አማራዎች ናችሁ” መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማያት ሰማይ ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ቤዛ የሆነን የትግራይ አለያም አማራ ስለሆንን ሳይሆን የአዳም እና የሄዋን ዘሮች በመሆናች መሆኑን የረሱት እነ አቶ ሲሣይ፥ ዋልድባ በትግራይ ልጅ ብቻ ተመራ በማለት ዋልድባ ገዳም ይልቁንም አበረንታት በጸለምት ወረዳ ስለሚገኝ የትግራይ ክልል በመሆኑ በገዳሙ አስተዳደር (አበሜኔት)፣ እቃ ቤት፣ መጋቢው በአጠቃላይ የበላዮቹ በሙሉ የትግራይ ተወላጅ መሆን አለባቸው በሚል ስንኩል ሃሳብ የጀመሩትን የሕይወት ጉዞ፣ ፈጣሪን የማገልገል ጉዞ እነሱ የሚኖሩበት የዘረኝነት እና የጎጠኝነት ጉዞ በአባቶች ላይ በማስተላለፋቸው ይበልጡኑ ያሳዝናል ያስለቅሳል።

በነገራችን ላይ የእነ አቶ ሲሣይ አስተዳር ለምን ዓይናቸውን በገዳመ ዋልድባ ላይ ተከሉ ኢ-አማናውያን (አረማውያን) ሆነው ሳለ ስለምን ብለው ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ለመየት ፈለጉ? ምን ዓይነት ጥቅም እና ፍላጎት ኖሯቸው ነው? እነዚህን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በሚቀጥለው ዝግጅታችን ይዘን ስለምንቀርብ ተከታተሉን።
ቸር እንሰንብት፤

1 comment:

  1. አይዞቸሁ ጌታ አምላክ ታላቅ ነው ስራውን አይፈታም ።

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤