Wednesday, February 13, 2013

ዛሬ መምህር ገ/ክርስቶስ፣ መምህር ወልደ ልዑል እና 6 መነኮሳት ለእስራት ተዳርገዋል“ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።” የያዕቆብ መልዕክት ፩ ፥ ፲፪

·         በጎንደር ከተማ የነበሩትን ገዳማውያን አስገድደው ወደ አዲርቃይ ለስብሰባ በሚል ተወስደዋል
·         መምህር ገብረ ክርስቶስን እና መምህር ወልደ ልዑልን ጨምሮ 6 መነኮሳት ለእስር ተዳርገዋል
·         ገዳማውያኑ የድረሱልን ጥሪያቸውን ዛሬም እያስተላለፉ ነው
 ሙሉውን በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ 
አባ ገብረክርስቶስ ከዋልድባ መከኖሳት ጋር
ባለፍት ጥቂት ሳምንታት በዋልድባ ገዳም አካባቢ እየደረሰ ያለውን ፈተና እና ተያይዞም የክልሉ ባለሥልጣናት እያደረሱ ያለውን ኢ-ቀኖናዊ የሆነ ሥራ ለአንባቢያን ማድረሳችን ይታወሳል። ገዳማውያኑም ተባረው ገዳሙን ጥለው ለእርዳታ ጥየቃ ብሎም ለሚመለተው አካል አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ጎንደር ብሎም ባሕር ዳር በመሄድ ለአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ችግራቸውን፣ መገፋታቸውን፣ ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ የሚደርስባቸውን ሰቆቃ በሰው ሰውኛ ለማስረዳት ሞክረዋል፥ በምላሹም ችግሮቹ ይስተካከላሉ፣ ከክልሉ አቻቸው አቶ ተወልደ የትግራይ ክልል ፕሬዘደንት ጋር ተነጋግረው መፍትሄ እንደሚሰጧቸው ተነግሯቸው ነበር፥ ሁኔታቹንም በቅርቡ እንደሚያሳውቋቸው ነግረዋቸው በጎንደር እንዲጠብቁ ነበር የተሰጣቸው መልስ፣ በጎንደርም በተመሳሳይ መልኩ ለሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ለሰሜን ጎንደር የጸጥታ ክፍል ሃላፊዎች ስለጉዳዩ ያለማሰለስ ለማስረዳት ሞክረዋል፣ አቤቱታቸውንም የአካባቢው ወጣቶች እና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በየአካባቢያቸው የተቻላቸውን እያደረጉ እነኝህን በስደት ከባዕታቸው በግፍ የተባረሩትን አባቶች በረከታችሁ ይደርብን በማለት ሲንከባከቧቸው ቆይተው ነበር።

ከትላንት በስቲያ የሰሜን ጎንደር የጸጥታው ክፍል ሃላፊዎች በአቶ ወርቁ የሚመራ፣ ከክልል ጽ/ቤት አቶ ተስፋዬ በሚባሉ እንዲሁ ከሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት በመምህር ቀለመወርቅ አሻግሬ አማካኝነት አዲርቃይ ላይ ስብሰባ ይደረጋል በስብሰባው ላይ የሚገኙት ተብሎ ከተነገራቸው መካከል
፩ኛ/ የጸለምት ወረዳ መስተዳደር ተወካዮች
፪ኛ/ ከዋልድባ አረጋውያን አባቶች
፫ኛ/ ከሰሜን ጎንደር የጸጥታው ክፍል ሃላፊዎች
፬ኛ/ ከአማራ ክልል ተወካዮች
፭ኛ/ ከሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ተወካዮች
፮ኛ/ ከሽሬእንደሥላሴ ሃገረ ስብከት ተወካዮች

በሚገኙበት በአዲርቃይ በየካቲት ፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ስብሰባ ለማድረግ  በሚል ተነግሯቸው፣ መነኮሳቱ የተለያየ ማጣሪያ በሚያደርጉበት ጊዜ ከላይ የተጠቀሱት አካላት በሙሉ ስለስብሰባው እንደማያውቁ ቢናገሩም ዛሬ እረፋዱ ላይ መሄድ አለባችሁ፣ ሰላም እንዲመጣ ንግግሩን መጀመር ይኖርብናል በሚል ከጎንደር ዩኒቨርስቲ በተገኙ መኪናዎች ተጭነው ወደ

አዲርቃይ ለስብሰባው ለመሄድ ተገደዋል፣ ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀደም ብለው የስብሰባው ዜና እንደሰሙ ወደ ባሕርዳር 4 መነኮሳትን ቢልኩም እንሱ እስኪመለሱ እንኳን መጠበቅ እንደማይችሉ ነው የተነገራቸው። ዛሬ ቀን ላይ አዲርቃይ የገቡት መነኮሳት በመጨረሻ ስብሰባው አዲርቃይ ሳይሆን ማይጸብሪ እንዲሆን ተወስኗል በሚል መነኮሳቱን በኃይል ወደ ማይጸብሪ ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። መነኮሳቱም በአስጋዲት ማርያም በምትባል ደብር ተጠልለው ከዚህ ተነስተን የምንሄድበት ነገር የለም ሰላም ከሆነ ባለንበት አነጋግሩን በማለት በአዲርቃይ አስጋዲት ማርያም ተጠግተው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። በአሁን ሰዓት ምን ሊመጣባቸው እንደሚችል በእርግጠኛነት መናገር ከባድ ስለሆነ፤ የመነኮሳቱ ቡድን ያሉበትን እየተከታተልን ስለሆነ ሊመጣ የሚችውን ሁኔታ እናሳውቃለን።

በዚሁ በተመሳሳይ ቀን ከዋልድባ ገዳም መምህር ገብረ ክርስቶስ (የቀድሞው አበሜኔት)፣ መምህር ወልደ ልዑል፣ እና ሌሎች አራት መነኮሳትን ጨምረው ለተባለው ስብሰባ ወደ አዲርቃይ ተጠርታችኃል በሚል አንድ መኪና ኮድ 3 የሆነ ተሽከርካሪ ተልኳላቸው የተባሉት 6 አባቶች ለስሰባው በመንገድ ላይ እያሉ የጸለምት ወረዳ ሚሊሻዎች አድፍጠው በመጠበቅ ከመንገድ ላይ ስድስቱን የመነኮሳት ቡድን እና 1 ሹፌር፣ 1 ረዳት በጠቅላላው 8 ሰዎችን ወስደው በማይጸብሪ እስር ቤት እንዳስገቧቸው መረጃዎች ደርሰውናል፤ እነ አቶ ሲሣይ እንዲህ አካባቢውን ሲያውኩ፣ ያለከልካይ የፈለጉትን ሲያስሩ እና ሲፈቱ፣ በማናለብኝነት የዚህን ታላቅ ገዳም አበሜኔት እና እቃቤት እራሳቸው ሲመርጡ፣ ገዳማውያኑን አማርኛ ተናጋሪዎች ናችሁ እና ገዳሙን ትላችሁ ጥፉ እና የመሳሰሉትን ሲሰሩ መንግሥትም የዜጎችን መብት ማስጠበቅ ሲገባው በዝምታ ተቀምጧል፤ ቤተክህነቱም በካድሬ እና በአድርባይ ስለተሞላ እኛን አይመለከተንም በሚል ለሥልጣን ይሮጣሉ እንጂ ስለ እዚህ ገዳም ደህንነት እና በውስጡም ስላሉት ገዳማውያን አባቶች እና ገዳማዊት እናቶች ማንም ጆሮ ሊሰጥ አለመቻሉ ይመስላል እነ አቶ ሲሢሳይ እና ግብረአበሮቻቸው እንደፈለጉት የሚያደርጉት። የፈጣሪ ያለህ ስለ እውነት እነዚህ አረጋውያን አባቶች መምህር ገብረክርስቶስ እና መምህር ወልደ ልዑል እስር ይገባቸው ነበር? ለእነሱስ ትንሽ ሰብዓዊነት አልፈጠረባቸውም? ወይንስ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያውያን አይደሉም እንዴ?? ልብ ያለው ልብ ይበል . . .

በመጨረሻ ለመረዳት እንደቻልነው አቶ ሲሣይ በቅርብ የሰያማቸውን የገዳሙን አበሜኔት እና እቃቤት ሥራ ሰጥቶ እንዲተግብሩ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ከጥቂት ቀናት በፊት መዘገባችን ይታወሳል። በዚህም መሰረት ዛሬ በአባ ገብረሕይወት መስፍን የሚመራ ሦስት ሰዎች በመሆን ጎንደር ከተማ ገብተዋል፤ በዚህም ሊሰሯቸው ከመጡት ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ
·         በጎንደር ከተማ ያለውን የገዳሙን የባንክ አካውንት ዘግቶ ወደ ሽሬ ማዘዋወር
·         በሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ለሚገኙ አካላት ደብዳቤዎችን ይዘው በመምጣት ችግር እንደሌለ ለማስረዳት
·         በሰሜን ጎንደር የጸጥታው ክፍል በመቅረብ በገዳሙ ውስጥ ችግር እንደሌለ እና ሰላም እንደሆነ ለማስረዳት
·         በአማራ ክልል ጽ/ቤት በመሄድ ስለ ገዳሙ ለማስረዳት፣ ከገዳሙ የወጡትም ችግር ያለባቸው ለመሆናቸው ለማስረዳት የመሳሰሉትን ለመስራት መምጣታቸው ታውቋል በዚህም መሰረት ዛሬ በጎንደር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሄደው ባንኩን ለመዝጋት ሲሞክሩ ከፍርድ ቤት ማዘዣ ካላመጣችሁ እናንተን አናውቃችሁም በማለት የባንኩ ተወካዮች እንዳባረሯቸውም ለመረዳት ችለናል።
እንደሚታወቀው አባ ገብረሕውወት መስፍን እና አባ ገብረዋሕድ የተባሉት ባለፈው ጥር ፲፫ ቀን በጸለምት ወረዳ አስተዳዳሪ የተሾሙ የገዳሙ ተወካዮች ነን ባዮች ሲሆኑ አብዛኛው ገዳማውያን የተደረገው ሥራ ትክክል እንዳልሆነ ተቃውሞአቸውን ቢያሰሙም ሰሚ ሳያገኙ በእናውቅላችኃለን ባዮች በማናለብኝነት የተቀመጡ መኮሳት ናቸው፥ በተለይ አባ ገብረሕይወት

መስፍት በተለያየ ጊዜ በገዳሙ ላይ በሚያደርሱት በደል እና እያደረጉ ባሉት ድርጊት ከጸለምት ወረዳ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደተጻፈላቸው የሚያስረዳ ደብዳቤ ከዚህ ጋር አቅርበናል (ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ) በድጋሚ የጸለምት ወረዳ ቤተክህነት የጻፈውን ደብዳቤ የማስተካከያ ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ 

ድሮ ድሮ በገዳመ ዋልድባ ወይንም በሌሎች የኢትዮጵያ ገዳማት ሥርዓት እንደ ቀደሙት የአበው ብሂል በገዳሙ ሲያስተዳድሩ የነበሩ አበሜኔት አቅማቸው ደክሞ፣ ክንዳቸው ዝሎ፣ ማስተዳደር እና መምራት ሲያቅታቸው ማኅበረ መነኮሳቱ ተሰብስቦ ሁለት ሱባኤ ተይዞ፣ ለባሕታውያኑና ለስውራኑ ጸሎት እንዲይዙ እግዚአብሔርን እንዲያመለክቱ ይጠየቃሉ፣ በመጨረሻ ከሱባኤው በኋላ እግዚአብሔርም በሚሰጣቸው ምልክት ተመርተው የገዳሙን አበሜኔት በገዳማውያኑ ልመናና ጸሎት አበሜኔት የሚመርጡበት ሁኔታ ነው እስከ አሁን ያለው፥ ነገር ግን የአሁኑ ለየት ያደረገው በወረዳ አስተዳዳሪ ፈቃድ እና ፍላጎት ለዚያውም አረማዊ (እምነት የሌለው) በሚፈልገው መልኩ በወታደር አስከብቦ ነበር ምርጫው የተካሄደው፥ ዋልድባን ከሌሎች ገዳማት ለየት የሚያደርገው እንደሌሎች ገዳማት ለመምረጥ የሚሰበሰቡት ገዳማውያንና መናንያን ሳይሆኑ በዋልድባ ገዳም ሥምረት ያልተቀበለ ገዳማዊ መምረጥ አይችልም (ሥምረት ማለት አንድ መናኝ ወደ ገዳሙ ገብቶ የተወሰነለትን የምናኔ ጊዜ ጨርሶ ቋርፍ ጨብጦ ሥጋ ወደሙን ሲቀበል እና የገዳማውያኑን ሥርዓት ሲቀበል ማለት ነው) ዛሬ ዛሬ ያ የቀደሙት አበው ብሂል ተረስቶ እናውቅላችኋለን ባዮቻችን አረማውያን ወታደሮች ቁጭ ብለው መምረጥ ጀመሩልን እንዴት አይነት ጊዜ ላይ ደረስን? የሚመረጡትስ አባት ተብዬውች ያ የነበረው ሥርዓት ሲጠፋ እና በአንጋች ሲመረጡ እንዴትስ አዕምሮአቸው ተቀበለው?

በመጨረሻ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ለሆንን ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መምህራን፣ ዘማሪያን እና ምዕመናን ሁላችን እስቲ ልብ እንበል ትላንት የአሰቦት ገዳም ተቃጠለ ተባልን፣ የዝቋላ አቦ ገዳም በአራት መዕዘን በእሳት ተቃጠለ፣ በጅማ ሻሾ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ካህናት እና ምዕመናን እቤተክርስቲያን ውስጥ እያሉ በእሳት ተበሉ አንገታቸው በካራ ተቀላ፣ በጉራጌና ሃድያ ዞን የጻድቋ እናታችን ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን በጠራራ ጸሐይ ተቃጠለች፣ በጎንደር እድሜ ጠገብ የሆነው የብሉያት እና የሐዲሳት መማሪያ እና ቤተመጻሕፍት የነበረው የአብነት ት/ቤት ከነ ሙሉ ንብረቱ ተቃጠለ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላለፉት ስድሳ ዓመታት ሊቃውንትን ሲያስመርቅ የነበረው የአብነት ት/ቤት በበጀት እጥረት ተዘጋ፣ የጻድቁ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልትም ይፈርሳል ተባልን፣ ዛሬ የገዳማት ማማ ዋልድባ ገዳም እንደዋዛ እየጠፋ እና እየተፈታ ነው ገዳማውያኑን በማሰደድ፣ በልማት ሰበብ ይዞታዎችን በመውሰድ ገዳማውያኑ ተሰደው ካለቁ እንደምንፈልገው እናደርጋለን ብለው ያሰቡ ባለጊዜዎች ቀስ በቀስ እየገዘገዙን ማንነታችንን ሲያጠፉ፣ ሃይማኖታችንን ለማጥፋት ከምዕራባውያን ጋር ተባብረው ቅርሶቻችንን በመሸጥ እና በማውደም ቤተክርስቲያናችን እየጠፋች ነው፤ ከእንግዲህ ምን ይዘን ነው ኦርቶዶክሳውያን ነን ለማለት የምንችለው? እንደ እውነቱ ከሆነ ዛሬ ኦርቶዶክሳዊነታችን የሚፈተንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ቤተክርስቲያኒቱን ባለቤት እንደሌላት ሌሎች ለዚያውም አረማውያን እንደሚፈልጉት ሲያደርጓት ዝም ብለን መመልከት ወይስ ለሃይማኖታችን እና ለቤተክርስቲያናችን ክብር በመቆም እውነትን በመናገር ከታሪክ ተጠያቂነት ለማምለጥ የበኩላችንን ማድረግ? መልሱን እራሳችን እንመልስ ሕሊና የየራሳችን ዳኛ ነው እውነት ሰርተን እና ተናግረን ከሆነ ከሕሊና ዳኝነት ከትውልድም ተጠያቂነት እንድናለን አለበለዚያ ግን . . .
ቸር ይግጠመን 
 የቤተሚናስ አባቶች ለመላው ዓለም ያስተላለፉትን አቤቱታ እዚህ ጋር ደብዳቤውን አያይዘነዋል ይመልከቱት በተጨማሪ፣ ከደብዳቤው ጋር ተያይዞ ያለውን የአባቶች እና እናቶች ስም ሰርዘነዋል ለአባቶቹ ደህነት በማሰብ ስለሆነ ይቅርታ እንጠይቃለን
 ቸር ይግጠመን


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

4 comments:

 1. አኹን እኔ ክርስቲያን ነኝ?
  አኹን እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ?
  ይኽንን እየሰማኍ እንቅልፍ የሚወስደኝ!

  ReplyDelete
 2. ወንድሞች የዚህ ብሎግ ሀላፊዎች ፀሀፊዎች ሁልግዜ ስስማም ሳነብም ዋልድባ ገዳም ትልቅ ችግር እየደረሰበት ያለ ገዳም ነው ነገር ግን እኛ ማረግ ያለብን ማሳሰብም ያለባሁችሁ ምዕመኑ እኛም ቢሆን እንደየአቅማችን የቻለ ሱባዬ ይዞ ያልቻለ ምህላ እያደረሰ ጸሎት እንዲያረግ ማሳሰብ አለባችሁ እንጂ ቀን በቀን የዋልድባን ችግር ብትነግሩን ብትጽፉልን ምንም የምንፈይደው ነገር የለም ወደ አምላካችን ስቃያቸውን እንዲያቀልልላቸው ካለምንን መንገስት እንደሆነ ጆሮዳባ ልበስ ብሏል እና ወንድሞች የዚ ብሎግ ሀላፊዎች ፀሀፊዎች በ ቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እልምናችኋለሁ ህዝበ ክርስቲያኑን ወደፀሎት ወደ እግዚአብሄር እንዲያመለክት ንገሩት ንገሩን እንጂ ህዝቡን አትውቀሱት ምንም ማረግ አይችልም እባካችሁ አሁንም እደግመዋለሁኝ ህዝበ ክርስቲያኑን ወደ እግዚአብሄር እንዲያመለክት ንገሩት ንገሩን እግዚአብሄር ይስጥልኝ

  ReplyDelete
  Replies
  1. ወንድማችን ወይም እህታችን "ደመ አድ" እውነት ብለዋል ምናልባት ምንም ላናደርግ እንችላለን ነገር ግን ሕዝብ የማወቅ መብቱ መጠበቅ አለበት የሚል እምነት አለን። በተለይ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ መንግሥት የሚነግራቸውን ብቻ እየሰሙ ምን እየተደረገ እንዳለ ለማያውቁ፣ አውቀምም ለተኙ መረጃው ከእውነተኛው ቦታ እንደተኘ መድረስ አለበት እኛ ሰማይና ምድርን የዘረጋው መድኃኒዓለም ያውቀዋል ምንም ዓይነት ሌላ ድብቅ አላማ የለንም፣ ነገር ግን ቤተክርስቲያናችንን አትንኩ፣ ገዳማችንን እና ታሪካችንን አታጥፉ በማለት መናገር ፖለቲካ ነው እያሉ የሚናገሩትን ሁሉ እውነታው ምን እንደሆነ ማሳወቅ አንዱ የእውነተኛ ሰዎች ምስክርነት ስለሆነ ማሳወቅ ግድ ይለናል። እርሶ እንዳሉት ወደ ጸሎት፣ ወደ እግዚአብሔር ማመልከት የዘወትር ጥያቄያችን ነው እሱንም ለማድረግ በየቦታው ያለውን ችግር እርሶም የሚረዱት ይመስለናል፣ እኛ እኮ ዋልድባ ላይ፥ ርስት የለንም፣ ቦታውንም ከነጭራሹ አናውቀውም፣ ወይንም አንዳንዶች እንደሚሉት የአካባቢው ተወላጆችም አይደለንም። እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በ40 እና በ80 የወለደችን ልጆች ነን፥ እርሷን ደግሞ መጠበቅ እና ለዚህች ርትይት ቤተክርስቲያን መስዋዕት መሆን በእኛ እንዳልተጀመረ እርሶም ጠንቅቀው የሚያውቁት ይመስለናል እድሜ ዘመናችንን ስንሰማው የነበርነው ስንክሳሩ፣ ገድላቱ እና ተዓምራቱ የቅዱሳንኑን የሰማዕታቱን ዘወትር የምንሰማው ስለሆነ እኛ ደግሞ የእነዚህ ቅዱሳን እና ሰማዕታት ልጆች ነን በግብር ልንመስላቸው ደግሞ ቅዱሳን መጻህፍት ያስተምሩናል።
   ቅዱስ ጊዮርጊስ እኮ የነገሥታት ወገን ነበረ፣ ሹመት፣ ሽልማት እና ሥልጣኑን እምቢ ያለው አምላኩን እና ዘላለማዊ ርስቱን ዛሬ ሲያልፍ የሚያልፈውን ዓለም ትቶ ለፈጣሪው ታማኝ ሆኖ ከአላውያን ነገሥታት ጋር ስለፈጣሪው ሲመሰክር ነው በመጋዝ የተሰነጠቀው፣ በመንኩራኩር የተፈጨው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪኩ ዛሬም በእኛ በምናምነው ህያው ሆኖ የሚኖረው ኦርቶዶክሳዊያን ስለሆንን ነው እና እስከ መጨረሻው እንመሰክራለን፣ እስከ ህልፈታችን እጃችሁን፣ ከቤተክርስቲያናችን ላይ አንሱ እንላለን፣ ቅዱሳን ገዳሞቻችን ለአረማውያን መከራቸውን የሚያዩበት ነገር ለእኛ ለምናምነው ርስተ መንግሥተ ሰማያትን፣ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን የምናይባቸው ቅዱሳት ቦታዎችንን አትንኩብን ማለታችንን አናቆምም እስከ መጨረሻውም እንታገላለን።
   ዛሬ ባለጊዜዎች ሃያላን ቢሆኑም ነገር ግን ዘላለማዊውን አምላክ ስለምናምን ነገ እንደሮማውያን፣ እንደአሜሌቃውያን ወይም እንደ ፈርዖን ተንኮታኩተው መውደቃቸው እውነት ነው ቤተክርስቲያናችን እና ቅርሶቻችን ግን ዘላለማዊ ምስክሮች ሆነው ይኖራሉ፣ እኛ እናልፋለን ተተኪው ትውልድ ግን ዘወትር ሲያወድሳቸው ይኖራል፣ ሲያፈርሱ፣ ሲመዘብሩ፣ ግፍ ሲውሉ ያሉትንም ዓይቶ እንዳላየ የሆነውንም ጭምር በመከሩ ወራት ፍርድ የማያጓድል አምላክ እንደየሥራችን ስለሚሰጥ እንጠባበቃለን።
   በመጨረሻ ትንሽ ምክር ለመስጠት ያህል፣ እርሶም ሆኑ ሌሎች ወገኖቻችን በያለንበት ስለቤተክርስቲያን ሰላም፣ ስለ ሃገራችን ገዳማት እና አድባራት፣ ያለበደላቸው በእስር ስለሚንገላቱት አባቶቻችን፣ ከባዕታቸው ተባረው ስለሚንከራተቱት አባቶቻችን እና እናቶቻችን በአጠቃላይ በቅድስት ቤተክርስቲያን አጸድ ያሉትን ሰውም ሆነ ነፍሳት በቸርነቱ እንዲጠብቅልን፣ ከፈተና እንዲሰውርልን፣ ጉልበተኞችን እንዲያስታግስልን በሚኖሩበት አጥቢያ ጊዜ ወስደን ስለ እነዚህ ሁሉ እንድንጸል እና እንድላቀስ እስቲ ጥረት ያድርጉ? ምናልባት እኛ እና እርሶ በተለያየ ጊዜ ለአጥቢያችን ድቃቂ ሳንቲም ስንሰጥ ቀኑን ሙሉ ስማችን በጸሎት ሲነሳ ይውላል፣ እነዚህ እንደ እሳት እራት ለእኛና ለእርሶ ሃይማኖት፣ ገዳማት ክብር በግፍ ለሚንገላቱት ማን ይጸልይላቸው ማን ወደ እግዚአብሔር ያመልክትላቸው? ማን አለን ይበልላቸው? ትላንት ሁላችንም እንደምናስታውሰው በግብጽ ቤተክርስቲያን 150 ክርስቲያኖች በአክራሪዎች ሲገደሉ በኢትዮጵያ እና በውጪ ያሉ አድባራት እና አጥቢያዎች ሁሉ ሲጸልዩላቸው ሰንብተዋል፣ ጥሩ ነው ክርስቲያን ለክርስቲያኑ ቢጸልይ ተገቢ ነው፣ ታዲያ ለራሳችን ለወገኖቻችን፣ ለሃይማኖት አባቶቻችን፣ ለገዳሞቻችን እንዴት አንድ አቡነ ዘበሰማያት ተሳነን???
   ቸር ይግጠመን እስኪ

   Delete
 3. walidba yegonder menekosat woim yetigray new way .christan gonder lay yelem yih hulu gif sifetsem.be 0912721302dewlulgn ena defar tekorkuari tewahidowochin yizhe balesltanatin eyaneku bahir ena gedel asgebachewalehu.yaletewahido menor alchilm.adera.

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤