Friday, February 1, 2013

የሽሬ እንደሥላሴ ሃገረ ስብከት የዋልድባ አበረንታንትን ሹመት አጸደቀ


“በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?” ፪ኛ ቆሮንጦስ ፲፫ ፥ ፭

·         አሥር መነኮሳት እና አሥራ አምስት ወታደሮች የመረጡት ምርጫ ተቀባይነት አግኝቷል
·         ከማይጋባ እና አዲርቃይ እቃ ቤተ ሃላፊዎች በአዲሶቹ ሹማምንቶች ተባረዋል
·         ንቡረዕድ ተስፋዬ ተወልደ የሽሬ እንደሥላሴ ሃገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ “ምርጫውን የሚቃወሙ ጸረ ልማት እና ጸረ-ሰላም ናቸው” አሉ
ባለፈው ጥር አስራ ሦስት ቀን አመሻሹ ላይ በግምት ወደ ፲፩ አካባቢ በዋልድባ አበረንታት የገዳሙን ሥርዓት እና ትውፊት ባልጠበቀ መልኩ እንዲያውም የቀበሌ ምርጫ በሚመስል መልኩ በዋልድባ አበረንታት ገዳም የወረዳ አስተዳዳሪው ባዘጋጁት መሠረት ወደ አሥር የሚጠጉ መነኮሳት ሊያውም የአንድ ብሔር ተወላጆች እንዲሁም ወደ 15 የሚጠጉ ወታደሮች በተገኙበት በቀጣይነት የዋልድባ አበረንታትን ገዳም ሊያስተዳድሩ የሚችሉ አበሜኔት እና እቃቤት ሹም ሽር ተደርጎ ነበር፤ ተዓምር ነው! በቁማችን የማናየው ጉድ የለም ዘንድሮ!


እንደ ቀደሙት የአበው ብሂል በገዳሙ ሲያስተዳድሩ የነበሩ አበሜኔት አቅማቸው ደክሞ፣ ክንዳቸው ዝሎ፣ ማስተዳደር እና መምራት ሲያቅታቸው ማኅበረ መነኮሳቱ ተሰብስቦ ሁለት ሱባኤ ተይዞ፣ ለባሕታውያኑና ለስውራኑ ጸሎት እንዲይዙ እግዚአብሔርን እንዲያመለክቱ ይጠየቃሉ፣ በመጨረሻ ከሱባኤው በኋላ እግዚአብሔርም በሚሰጣቸው ምልክት ተመርተው የገዳሙን አበሜኔት በገዳማውያኑ፥ ዋልድባን ከሌሎች ገዳማት ለየት የሚያደርገው እንደሌሎች ገዳማት ለመምረጥ የሚሰበሰቡት ገዳማውያን መናንያን ሳይሆኑ በዋልድባ ገዳም ሥምረት ያልተቀበለ ገዳማዊ መምረጥ አይችልም (ሥምረት ማለት አንድ መናኒ ወደ ገዳሙ ገብቶ የተወሰነለትን የምናኔ ጊዜ ጨርሶ ቋርፍ ጨብጦ ሥጋ ወደሙን ሲቀበል እና የገዳማውያኑን ሥርዓት ሲቀበል ማለት ነው) ዛሬ ዛሬ ያ የቀደሙት አበው ብሂል ተረስቶ እናውቅላችኋለን ባዮቻችን አረማውያን ወታደሮች ቁጭ ብለው መምረጥ ጀመሩልን እንዴት አይነት ጊዜ ላይ ደረስን? የሚመረጡትስ አባት ተብዬውች ያ የነበረው ሥርዓት ሲጠፋ እና በአንጋች ሲመረጡ እንዴትስ አዕምሮአቸው ተቀበለው? ለነገሩ ዓላማቸው አንድ ስለሆነ ችግር የለውም አባ ገብረሕይወት ተብየው የሕዋሃት ታጋይ የነበረ እንደሆነ ከአካባቢው ምንጮች ተረድተናል፥ አበሜኔት ተብለው የተሰየሙት በስመ የትግራይ ተወላጅነት እና በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት ያደሩ ለሰማያዊው መንግሥት ግድ የሌላቸው በመሆናቸው ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህ ተመራጮች ይልቁንም የእቃ ቤቱ ተመራጭ አባ ገብረ ሕይወት ተብየው የገዳሙ ንብረቶች በሆኑበት ቦታዎች ለምሳሌ በማይጋባ እንዲሁም በአዲርቃይ ያሉትን የእቃ ቤት ሃላፊዎች ከቦታቸው አንስተው በምትካቸው ለእነሱ የሚስማማቸውን ሰው አስቀምጠዋል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው አንደኛ ከዚህ በፊት የነበሩት የንብረቶቹ ጠባቂዎች አማርኛ ተናጋሪ በመሆናቸው፣ ሁለተኛ እነዚህ አባቶች ለነፍሳቸው ያደሩ እና እነዚህን ቅርሶች እንደ ህይወታቸው ጠብቀው ሲያስቀምጡ ያለምንም ጥቅም እና ድለላ ነው ለነፍሳቸው ብቻ በማሰብ ነገር ግን አሁን የሚተኩት ሰዎች ለእነ አቶ

ሲሣይ እና አባ ገብረሕይወት እነዚህን ብርቅዪ የሀገር የወገን ሃብቶች ንዋየ ቅዱሳት፣ በተለያዩ ጊዚያት በተለያዩ ነገሥታት እንደ ገጸ በረከት ለገዳሙ የተበረከቱ የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ መስቀሎች፣ ድባቦች፣ በወርቅ የተለበጡ መጻሕፍት፣ የኢትዮጵያዊውን ኢትዮጵያዊነት ሊመሠክሩ እና ሊናገሩ የሚችሉ የታሪክ አሻራዎች፣ እድሜ ጠገብ የብራና መጻሕፍት እስከ አሁን በዓለም ዙሪያ ያልተገኙ በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተካተቱ ድንቅ መጽሐፍት ብዙ ብዙ የሀገር እና የወገን ንብረት እና ቅርስ በእነዚህ ሰዎች ወደቀ ማለት ነገ እነዚህን የወገን መኩሪያ ሃብቶቻችንን ለምዕራባውያን እየወጡ እንደሚቸበችቡት ምንም ጥርጥር የለንም ለዚህም ነው መነኮሳቱ ከዚህ በፊት የአካባቢውን ምዕመናን ኑና ቅርሶቻችሁን ተረከቡን፣ የእኛ ሃላፊነት እስከዚህ ድረስ ብቻ ነው ዛሬ እናንተ ተንከባክባችሁ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ካልቻላችሁ የማንነታችን መገለጫዎቻችን ሁሉ ይጠፋሉ በባለጊዜዎች ይመዘበራል ተረከቡን . . . በማለት ድምጻቸውን ሲያሰሙ የነበሩት ትውልዱም ዝም አለ ባለጊዜዎችም ከምዕራባውያን ጋር እየተደራደሩ ይገኛሉ ኸረ ለማን አቤት ይባል . . .

በጣም ከሁሉ የሚደንቀው ደግሞ ዛሬ ለሃይማኖታቸው ሳይሆን ዘራቸውን እና ጎጣቸውን ተመክተው ጸረ-ሰላም ኃይሎች ወይም ጸረ-ልማት ኃይሎች ናቸው በማለት እያደናገሩ ለሃይማኖታቸው እና ለቤተክርስቲያናቸው ግድ የሌላቸው የቤተክርስቲያናቱ ሰዎችም ይስተዋላሉ ከነዚህም መካከል በትግራይ ሽሬ እንደሥላሴ ሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ንቡረዕድ ተስፋዬ ተወልደ ትላንት በዋልድባ የገደረገውን በአንጋቾች የተደረገውን ምርጫ ተቀብለነዋል አጽድቀነዋል። በማለት ሲናገሩ ሲሰሙ እውነት ለካ ቆቡን የደፋ ሁሉ ለቤተክርስቲያን የቆመ አይደለም ለካስ ከቤተክርስቲያን በላይ ዘር እና ጎጥ በልጦባቸዋል ማለት ነው እንድንል አድርጎናል። ከዚህ በተጨማሪ ለአቤቱታ የወጡት መነኮሳት በጎንደር አቤቱታቸውን ቢያሰሙም፣ የሀገረ ስብከቱ ተወካዮች እንዴት እንዲህ አይነት ውንብድና በገዳማችን ላይ ይሰራል በማለት በቁጭት ወደ ሽሬ ቢያመለክቱም የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ደግሞ በሽሬ እንደሥላሴ ሃገረ ስብከት ምን አገባው! በማለት “ስለ እራሳችሁ ሃገረ ስብከት አስቡ፥ በእኛ ሃገረ ስብከት ሥራ ጣልቃ አትግቡብን” በማለት ነበር የመለሱት ንቡረዕዱ፥ ከዚህም በላይ ለአቤቱታ የወጡትንም አባቶች እነሱንም ድሮም እናውቃቸዋለን “ገዳሙን ለመበተን ሲሰሩ የነበሩ፥ ከጸረ - ልማት ኃይሎች ጋር ተባባሪዎች” ናቸው ነበር ያሉት፤ እውን ገዳማችንን አታፍርሱ፣ በዘር በጎጥ አትከፋፍሉን፣ የገዳማችንን ሥርዓት አታፍርሱ፣ ጠብ መንጃ ይዛችሁ ቤተ እግዚአብሔር አትግቡብን፣ አባቶቻችንን አትደብድቡብን፣ ማለት ጸረ-ሰላም እና ጸረ-ልማት ኃይል ያስብላል? ኸረ የወገን ያለህ. . . ኸረ የቤተክርስቲያን አምላክ ወደኛ ተመልከት . . .

በመጨረሻ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ለሆንን ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መምህራን፣ ዘማሪያን እና ምዕመናን ሁላችን እስቲ ልብ እንበል ትላንት የአሰቦት ገዳም ተቃጠለ ተባልን፣ የዝቋላ አቦ ገዳም በአራት መዕዘን በእሳት ተቃጠለ፣ በጅማ ሻሾ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ካህናት እና ምዕመናን እቤተክርስቲያን ውስጥ እያሉ በእሳት ተበሉ አንገታቸው በካራ ተቀላ፣ በጉራጌና ሃድያ ዞን የጻድቋ እናታችን ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን በጠራራ ጸሐይ ተቃጠለች፣ በጎንደር እድሜ ጠገብ የሆነው የብሉያት እና የሐዲሳት የሆነው የአብነት ት/ቤት ከነ ሙሉ ንብረቱ ተቃጠለ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላለፉት ስድሳ ዓመታት ሊቃውንትን ሲያስመርቅ የነበረው የአብነት ት/ቤት በበጀት እጥረት ተዘጋ፣ የጻድቁ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልትም ይፈርሳል ተባልን፣ ዛሬ የገዳማት ማማ ዋልድባ ገዳም እንደዋዛ እየጠፋ እና እየተፈታ ነው ገዳማውያኑን በማሰደድ፣ በልማት ሰበብ ይዞታዎችን በመውሰድ ገዳማውያኑ ተሰደው ካለቁ እንደምንፈልገው እናደርጋለን ብለው ያሰቡ ባለጊዜዎች ቀስ በቀስ እየገዘገዙን ማንነታችንን ሲያጠፉ፣ ሃይማኖታችንን ለማጥፋት ከምዕራባውያን ጋር ተባብረው ቅርሶቻችንን በመሸጥ እና በማውደም ቤተክርስቲያናችን እየጠፋች ነው፤ ከእንግዲህ ምን ይዘን ነው ኦርቶዶክሳውያን ነን ለማለት የምንችለው? እንደ እውነቱ ከሆነ ዛሬ ኦርቶዶክሳዊነታችን የሚፈተንበት ጊዜ ላይ

ደርሰናል ቤተክርስቲያኒቱን ባለቤት እንደሌላት ሌሎች ለዚያውም አረማውያን እንደሚፈልጉት ሲያደርጓት ዝም ብለን መመልከት ወይስ ለሃይማኖታችን እና ለቤተክርስቲያናችን ክብር በመቆም እውነትን በመናገር ከታሪክ ተጠያቂነት ለማምለጥ የበኩላችንን ማድረግ? መልሱን እራሳችን እንመልስ ሕሊና የየራሳችን ዳኛ ነው እውነት ሰርተን እና ተናግረን ከሆነ ከሕሊና ዳኝነት ከትውልድም ተጠያቂነት እንድናለን አለበለዚያ ግን . . .
ቸር ይግጠመን 
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤