Monday, February 11, 2013

የመፍትሔ ያለህ! . . . ይላሉ ዛሬም አባቶቻችን!


·         የሰሜን ጎንደር ገዳማት ተወካዮች የዋልድባን አባቶች እልባት ካላገኘ ሌላ ችግር ይፈጠራል
·         አዲሱ ሹም በጎንደር የሚገኘውን የገዳሙብ ባንክ ዘግተን ወደ ሽሬ እናዞረዋለን ብለዋል
·         በማይጸብሪ አቶ ሲሳይ አዲሶቹን ሹሞች እና ጥቂት አባቶችን ለስብሰባ ተጠርተዋል
·         የሰሜን ጎንደር ጸጥታ ክፍል በአዲርቃይ ስብሰባ እያዘጋጀን ነው ተብሏል
·         አራት የመነኮሳት ቡድን ወደ ባሕርዳር ለጥያቄ ተልከዋል
 ሙሉውን ቃል በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ 
ንቡረዕድ ተስፋዬ ተወልደ
የሽሬ ሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ
ባለፈው ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በዋልድባ ገዳም አካባቢ እየደረሰ ያለውን በገዳማውያኑ ላይ እየደረሰባቸው ያለውን ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ስናስነብብ ቆይተናል፣ በዚህ በገዳሙ ዙሪያ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመንግሥት ባለሥልጣናት አቤት ለማለት ወደ 40 የሚገመቱ የመነኮሳት እና መነኮሳይት ቡድን በጎንደር እንዲሁም በባሕርዳር ተገኝተው አቤቱታቸውን ማሰማታቸውንም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት መዘገባችን ይታወሳል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የአካባቢው ባለሥልጣን አቶ ሲሣይ ማስፈራራታቸውንም፣ የወጡትንም መግቢያ እንደሌላቸው ጭምር በስልክ በመደወል ብሎም በተባባሪዎቻቸው ለገዳማውያኑ መልዕክታቸውን ሲያደርሱ ቆይተዋል። በዚህ ባሳለፍናቸው ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት አስቸኳይ እልባት ለገዳማውያን አባቶች ይሰጣቸው በሚል ለሽሬው አቻቸው የተማጥኖ ደብዳቤ መላካቸውንም አስነብበን ነበር፣ የሽሬ እንደሥላሴ ሃገረ ስብከትም በብፁዕ አቡነ መቃሪዎስ የሚመራው በንቡረ ዕድ ተስፋዪ ተወልደ ሥራ አስኪያጅነት የሚመራው ደግሞ “በሥራችን ጣልቃ አትግቡብን” በማለት መመለሱን እንዲሁም በዋልድባ ገዳም የተደረገውን ኢ-ቀኖናዊ የሆነውን የገዳሙን አባቶች ሹም ሽር አስመልክቶ በንቡረ ዕድ ተስፋዬ አማካኝነት ሹመቱን መቀበላቸውን እና ከሹመኞቹም ጋር አብረው እንደሚሰሩ ነበር ያስታወቁን።


ከባዕታቸው በግፍ የተባረሩትን ገዳማውያን በመያዝ የሰሜን ጎንደር እና አካባቢው የአድባራት ተወካዮች፣ የገዳማት ተወካዮች፣ የአካባቢው ወጣቶች በመሆን ወደ ሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት በመጓዝ ጥያቄዎችን ለሃገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ለመምህር ቀለመወርቅ ባሳለፍነው ሳምንት አቅርበው ነበር። የሃገረ ስብከቱም ሥራ አስኪያጅ ጉዳዩን ከሽሬ እንደስላሴ ሃገረ ስብከት ጋር ክትትል እያደረጉ እንደሆነ፥ ከዚህም በተጨማሪ ከሰሜን ጎንደር የጸጥታ ሃላፊዎች ጋርም ግንኙነት እንዳደረጉና መፍትሄ እስከ አለፈው እሮብ ድረስ እንደሚያገኙላቸው በሃገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት ተነግሯቸው እንደነበር ለመረዳት ችለናል። ነገር ግን ረቡዕም አለፈ መፍትሄም እስከ አሁን ድረስ መገኘት አልተቻለም፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአድባራት ተወካዮቹ እና የገዳማት ተወካዮቹ ለሥራ አስኪያጁ ያስተላለፉት አስረግጠው የተናገሩት ነገር ቢኖር “የአባቶቻችንን ጉዳይ እልባት እማያገኝ ከሆነ፥ በሰሜን ጎንደር ከሚገኙ ገዳማት በሙሉ ያሉትን የትግሪኛ ተናጋሪዎች እናባርራለን” እዚህ ጋር ከመድረሳችን በፊት ጉዳዩ በአስቸኳይ እልባት እንዲያገኝ ተማጽኖም ጭምር ነበር ያስተላለፉት። ሥራ አስኪያጁም ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስም ለጉዳዩ እልባት እንዲሰጡ እንደሚያስተላልፉ እና ለመንግሥትም ባለሥልጣናት አስቸኳይ መልስ የሚሻ ችግር ብለው ተማጽኖአቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸውላቸው ነበር የተሰናበቱት።

በዋልባ ገዳም የአበረንታት መድኅኒዓለም አዲሱ የገዳሙ እቃ ቤት ሹም በሚያስገርም ፍጥነት ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል ከነዚህ ሥራዎቻቸው መካከል በጥቂቹን ለማንሳት :

፩/ በጎንደር ከተማ የነበረው የገዳሙን የባንክ ሂሳብ በአስቸኳይ ተዘግቶ በሽሬ እንደሥላሴ እንዲከፈት ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው
፪/ የገዳሙ ይዞታ በሆኑት በአዲርቃይ፣ አባነፃ፣ እና ማይገባ ላይ የነበሩትን እቃ ቤት የሚሰሩትን ሰዎች አንስተው በአስቸኳይ በራሳቸው ሰው መተካታቸው
፫/ ከገዳሙ ውስጥ ማንም ገዳማዊ ያለእነሱ ፈቃድ መውጣት እንደማይችል ውሳኔ ማስተላለፋቸው
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ውሳኔውች በአጠቃላይ የተወሰኑት ውሳኔዎች የገዳሙ ሳይሆኑ የወረዳው አስተዳዳሪ ፍላጎት እና በወረዳው አስተዳዳሪ አጀንዳ እየሰሩ እንዳሉ የሚያሳይ ውሳኔዎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎቹ ምን ያህል የገዳሙን ብሎም የሃገራችንን ብርቅዬ ቅርሶች፣ ንዋየ ቅድሳት፣ የማንነታችን መገለጫዎችን፣ የታሪካችን አሻራዎች የሆኑትን እነዚህ እድሜ ጠገብ ቅርሶቻችንን ለምዕራባውያን ለመሸጥ እና ለማሸሽ ምን ያህል እየተሽቀዳደሙ እንደሆነም ልንገነዘብ ይገባል። ዛሬ ዛሬ እነዚህን ለዓይናችን የምንሳሳላቸውን ብርቅዪ የሆኑ የቤተክርስቲያን እና የሃገር ቅርሶችን በጥቂት ለሃገር፣ ለወገን እና ለቅርስ ደንታ የለሽ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀር ባዮች ስትመዘበር፣ ለዓለም ገበያ ሲቀርቡ አቤት የሚል ሰው በመጥፋቱ የገዳማችን እንደዋዛ መፈታት ሲገርመን ቅርሶቻችን በዋጋ ሊገዙ የማይችሉት እንቁ የሆኑት ሃብቶቻችን ከዓይናችን እየተሰወሩ እና እየጠፉ ለመሆናቸው ምንም ማረጋገጫ የምንሻ አይመስለንም። ሃይማኖታችንን እንጠብቅ፣ ቅርሶቻችንን እናስከብር የእለት ተዕለት ጩኸታችን ይቀጥላል . . . ሰሚ ጆሮዎች እስከሚከፈቱ ድረስ . . .

እነዚሁ ሹማምንት ባለፈው ሳምንት በአቶ ሲሣይ መሬሳ አማካኝነት በማይጸብሪ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያካሂዱ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፣ በስብሰባውም ላይ አባ ገብረ ዋሕድ (አበሜኔት)፣ አባ ገብረ ሕይወት መስፍን (እቃ ቤት) እና ለእነሱ የሚቀርቡ ወደ ስምንት የሚጠጉ መነኮሳት ለስብሰባ ወደ ማይጸብሪ እንዲመጡ እና ከአቶ ሲሣይ ጋር እንዲሰበሰቡ አስቸኳይ እና ቀጭን ትዕዛዝ በአባ ገብረ ሕይወት አማካኝነት ተላልፏል በዚህም ጥቂቶቹ ሌሎች አባቶቻችን ለምን አልተጠሩም?፣ ከገዳሙ በግፍ የተባረሩት አባቶቻችን ይመለሱ፣ በእስር የሚገኙት አባቶቻችን ይፈቱልን፣ በማለት ቅድመ ሁኔታዎችን በማቅረብ ለስብሰባው ለመገኘት ፈቃደኞች ሳይሆኑ በመቅረታቸው በተገኙት አባቶች ስብሰባውን አቶ ሲሣይ አስተናግደው ነበር፣ በስብሰባው ለመገኘት ፈቃደኛ ያልሆኑትንም አባቶች እርምጃ እንዲወሰድባቸው ውሳኔዎች መተላለፋቸውንም ለመረዳት ችለናል። በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ከተላለፉት ውሳኔውች ውስጥ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው ቀርበዋል፡
፩/ የገዳሙ አበሜኔት በአስቸኳይ ደብዳቤዎችን ለየክልሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ገዳሙ ሰላም እንደሆነ፣ ችግር እንደሌለባቸው፣ መንግሥትም እየረዳቸው እንዳሉ እና ልማቱንም ተቃውሞ እንደሌላቸው የሚገልጽ ደብዳቤዎችን ጽፈው እንዲልኩ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
፪/ ከገዳሙ ለአቤቱታ የወጡትን አባቶች እና እናቶች ጸረ ልማት እና ጸረ ሰላም ሃይሎች እንደሆኑ እና እንደማያውቋቸው የሚገልጽ ደብዳቤ በአስቸኳይ እንዲጽፉ ትዕዛዝ ተቀብለዋል፥
፫/ የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት እያደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ ደብዳቤ እንዲጽፉም ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል
፬/ ለቅዱስ ሲኖዶስም አስቸኳይ ደብዳቤ እንዲጽፉ እና ለፖትርያሪክ ምርጫውም የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ትዕዛዝ ተቀብለዋል

እነዚህን ውሳኔዎች በቀጥታ ከወረዳው አስተዳዳሪው ተቀብለው ለመተግበር ትዕዛዙን የተቀበሉት በዋናነት የገዳሙ እቃ ቤት ተብለው የተሾሙት አባው ገብረ ሕወት መስፍን መሆናቸውን ጭምር ከአካባቢው በደረሰን መረጃ ለመረዳት ችለናል።

በተያያዘ ዜና የሰሜን ጎንደር የጸጥታ ክፍል ሃላፊዎች በጎንደር ከተማ እየተንገላቱ ለሚገኙት መነኮሳት እና መነኮሳይት ትላንት ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት እና መልስ ለማግኘት አጠቃላይ የመነኮሳቱ ቡድን በሙሉ፣ የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ተወካዮች፣ የሽሬ እንደሥላሴ ሃገረ ስብከት ተወካዮች እና የጸለምት ወረዳ አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ክፍል ሃላፊዎች አዲርቃይ ላይ በመጪው ስብሰባ እናደርጋለን በማለት ተነገራቸው። አያይዘውም ለእናንተ አውቶብስ እናቀርባለን እኛ ግን በሌላ መኪና እንመጣለን በማለት ለመነኮሳቱ በተነገራቸው ሰዓት ስለ ጉዳዩ የሀገረ ስብከቱን ሃላፊዎች እና የክልሉን ባለሥልጣናት በሚጠይቁበት ወቅት ስለተባለው ስብሰባ ማንም እንደማያውቅ እና ምናልባትም ከጸለምት ወረዳ አስተዳደር ጋር ተማክረው ወስደው በእስር ለማስገባት ያደረጉት ሙከራ እንደሆነ ይገመታል። የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ሃላፊዎች፣ የአማራ ክልል መስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ የገዳሙ ጥቂት መነኮሳት ወይንም በአዲርቃይ አካባቢ ያሉ በስደት የሚንገላቱትን አባቶች የሚያጽናኑ አባቶች እንዳሉት ከሆነ በየአካባቢያቸው ስለ ስብሰባው ምንም እውቀት እንደሌላቸው እና በፍጹም የሰሙት ነገር እንደሌለ ለመረዳት ችለናል። የመነኮሳቱ ቡድንም አራት አባቶችን ወክሎ ወደ ባሕር ዳር በመሄድ ከክልሉ በለሥልጣናት ጋር ስለስብሰባው ለመጠየቅ እና እየተደረገባቸው ያለውንም ለማሳወቅ፣ በሕይወታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ለማስረዳት በደቦታው ማምራታቸውንም በተያየዘ ዜና ለመረዳት ችለናል።

ለቤተክርስቲያናችን ፍጹም ሰላምን፣
በዱር በገደሉ ለሚቅበዘበዙት ፍጹማውያን አባቶቻችን ጽናቱን
ለእኛም የቤተክርስቲያን ጥፋቷን አያሳየን እያልን መልካሙን እንዲያመጣልን እንመኛልን
ቸር ወሬ ያሰማን እንላለን


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

3 comments:

  1. እንደዚህ በቃ ወያኔ ወርሶን ሊቀር ነው ማለት ነው? እንዴት ለቤተክርስቲያን እንኳን መተንፈስ ተሳነን? በእውነት የሃይማኖታችንን ነገር እኛ አያገባንም ብለን መቀመጥ አለብን ማለት ነው? ኸረ እንዴት አይነት ጊዜ ላይ ደረስን ጎበዝ አባቶቻችን እኮ ናቸው በወያኔ ሰራዊት እየተደበደቡ ያሉት የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑት እውን ይህንን እያየን እና እየሰማን ዝም ብንል ፈጣሪስ አይታዘበንም እንዴ? ትውልድስ አይወቅሰንም እንዴ እባካችሁ ኦርቶዶክሳዊያን ስለ ቅዱሳን አባቶቻችን እና እናቶቻችን ብላችሁ ሌላው ቢቀር በያለንበት አጥቢያ ዝም አንበል፣ በየበረሃው ወድቀው ስለእኛ ለሚጸልዩት እንኳን አብረን ለፈጣሪ እናመልክት ጩኸታችንን እናሰማ ያኔ የሰማይ እና የምድር ፈጣሪ መድኅኒዓለም ከአርያም ሆኖ ጩኸታችንን የራሔልን ጩኸት የሰማው ጌታ የኛንም ሰምቶ ምላሽ ይሰጠናል። ስለዚህ . . .እባካችሁ ካህናቱ አድርባዮች ግብረ በላዎች ሆነዋል እነሱ ስለ ቅድስቲቱ ቤተክርስቲያን ሳይሆን የሚያስቡት ስለ አጥቢያቸው ብቻ ነው የሚናገሩት በአጥቢያቸው ገቢ ሲጎድል ወይንም ምዕመኑ መምጣት ሲያቆም ምነው ይላሉ አለበለዚያ ወያኔ ሃይማኖታችንን ሲያጠፋ ዝም ነው ለዚህ ነው እና እባካችሁ ዝም አንበል የማርያም ልጅ ይርዳን

    ReplyDelete
  2. እባክህ ጌታ የአባቶቸን መከፋት እምሰማበትን ቀን አርቅልኝ። እንደሙስሌም ወገናችን መሆን ቤያቅተን የኬሳችን ካዝና ብንቆልፍ ምን አለ። ለማን ነው የምንሰጠው ያለ? በጣም ብዙ የወንጌል አስተማሪወች አሉን ምነው መተግበር ተሳናቸው?የሀሐይማኖት ሐዋርያት የምንላቸው ማሕበሮቾስ እንዲት ነው? እባክህ ዓምላኬ ለሐይማኖቱ ቀናኤ የሆነ ተሰሜነት ያለው እራሰን ለንዋይ ፣ ለሹመት ያላስቀደመ ፈልገህ አስነሳልን።አሜን

    ReplyDelete
  3. ኧረ እባካችሁ የሰማዩ ንጉስ እንዲታደገን እንጸልይ

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤