Monday, March 25, 2013

መናኝ ገ/ኪዳን የተባሉ $25000.00 ብር ይዘው ከማይጋባ እቃቤት ተሰወሩ


“ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።” የያዕቆብ መልዕክት ፩ ፥ ፲፪

በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ ካርታ (ወልቃይት ክኳር ፋብሪካ)
·         በማይጋባ እቃቤት ሹም ሆነው የተቀመጡ መናኝ ገ/ኪዳን የተባሉ $25000.00 ብር ይዘው ተሰውረዋል
·         ባለፈው ለአቤቱታ በጎንደር እና በባሕር ዳር የሄዱትን አባቶች እና እናቶች በሙሉ በተለያየ ተጽዕኖ ከገዳሙ ወጥተው ወደ ሌላ ገዳም እንዲሰደዱ ተደርገዋል
·         በማይጋባ፣ በአዲርቃይ፣ በማይጸብር፣ የሚገኙት እቃ ቤቶች በአባ ገ/ሕይወት ሹሞች እየመዘበሩት ይገኛሉ


በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
ባለፍት ጥቂት ሳምንታት በዋልድባ ገዳም አካባቢ እየደረሰ ያለውን ፈተና እና ተያይዞም የክልሉ ባለሥልጣናት እያደረሱ ያለውን ኢ-ቀኖናዊ የሆነ ሥራ ለአንባቢያን ማድረሳችን ይታወሳል። ገዳማውያኑም ተባረው ገዳሙን ጥለው ለእርዳታ ጥየቃ ብሎም ለሚመለተው አካል አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ጎንደር ብሎም ባሕር ዳር በመሄድ ለአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ችግራቸውን፣ መገፋታቸውን፣ ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ የሚደርስባቸውን ሰቆቃ በሰው ሰውኛ ለማስረዳት ሞክረዋል፥ በምላሹም ችግሮቹ ይስተካከላሉ፣ ከክልሉ አቻቸው አቶ አባይ ወልዱ የትግራይ ክልል ፕሬዘደንት ጋር ተነጋግረው መፍትሄ እንደሚሰጧቸው ተነግሯቸው ነበር፥ ሁኔታቹንም በቅርቡ እንደሚያሳውቋቸው ነግረዋቸው በጎንደር እንዲጠብቁ ነበር የተሰጣቸው መልስ፣ በጎንደርም በተመሳሳይ መልኩ ለሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ለሰሜን ጎንደር የጸጥታ ክፍል ሃላፊዎች ስለጉዳዩ ያለማሰለስ ለማስረዳት ሞክረዋል፣ አቤቱታቸውንም የአካባቢው ወጣቶች እና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በየአካባቢያቸው የተቻላቸውን እያደረጉ እነኝህን በስደት ከባዕታቸው በግፍ የተባረሩትን አባቶች በረከታችሁ ይደርብን በማለት ሲንከባከቧቸው ቆይተው ነበር።

ከጥቂት ወራት በፊት በአቶ ሲሳይ መሪሳ አማካኝነት ከተቀመጡት የገዳሙ አበሜኔት እና እቃቤት ሹሞች የራሳቸውን ሰዎች በመሾም እና በመተካት ለዓመታት ተከብረው የነበሩት የገዳሙ ትብረት የሆኑት እቃቤቶች ባለቤት እንደሌለው ንብረት አግባብነት በሌለው መልኩ መመዝበር ከጀመረ ውሎ አድሯል። አባ ገብረሕይወት ተብለው የተሾሙት የእቃቤት ሃላፊው ባለፈው ከበላያቸው በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት በገዳሙ ውስጥ ችግር የለም፣ ወጥተው የሄዱትም አባቶች የፖለቲካ ሰዎች ናቸው እና የመሳሰሉትን በማለት ሲናገሩ እና ደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለአካባቢው ሃገረ ስብከት ተወካዮች ሲጽፉ የቆዩት እነዚህ ሰዎች፣ በተለያየ ቦታ ያለውን የገዳሙን እቃ ቤቶች ለዘመናት እራሳቸውን ዝቅ አድርገው በብትውና የሚኖሩትን አባቶች ከቦታቸው አንስተው በምትካቸው ወንበዴ አስገብተውበት ዛሬ የመጀመሪያው በማይጋባ የሚገኘው እቃቤት ሹም መነኝ ገብረ ኪዳን የተባለ መናኝ የአባ ገብረ ሕይወት የቅርብ ዘመድ እንደሆነ የሚነገርለት ትውልዱ አክሱም አካባቢ የሆነ መናኝ በሃላፊነት እጁ ላይ የነበረውን $25000.00 የኢትዮጵያ ብር ይዞ ከአካባቢው መሰወሩን ስንሰማ ገና ሁለት ወር ሳይሞላው እንዲህ አይነት ሥራ መስራት ከጀመሩ ሲጀመር ጀምሮ የራሳቸውን ሰዎች ያስቀመጡት ለዚህ ተመሳሳይ ስራ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

እንደሚታወቀው የዋልድባ አበረንታት ገዳም በተለየዩ ቦታዎች ላይ ምእመናን ገዳሙ እራሱን ሊጠቀምበት እንዲችል የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ሰርተው ለገዳሙ ያበረከቷቸው ወፍጮ ቤቶች እና እቃቤቶች ነበሯቸው እነዚህ እቃቤቶች የገዳሙ ውስጥ ከአቀማመጥ እና ምቾት እጥረት ሊበላሹ እና ይዘታቸውን እንዳይለውጡ በማሰብ በእነዚህ ቦታዎች የሚቀመጡ እቃቤቶች ሲኖሩ በተመሳሳይ መልኩ ለገዳሙ ፍጆታ የሚሆኑ እንደ ኑግ እና ዳጉሳ የመሳሰሉት ጥራጥሬዎች የሚፈጩበት ወፍጮቤቶችም በተለያዩ ከገዳሙ በረከት ለመቀበል ከሚመጡ ምዕመናን የተበረከት ገጸበረት ሲሆን እነዚህን ንብረቶች ነው የእቃቤቱ ሹም  በበላይነት የሚጠብቀው፣ በመሆኑም እቃቤት ሹም ሆነው በአቶ ሲሳይ የተቀመጡት አባ ገብረሕይወት የራሳቸውን ሶዎች የተኩባቸው ቦታዎች ውስጥ በጥቂቱ
፩/ ማይጋባ ላይ ወለት የሞተር ወፍጮዎች ሲኖሩ በሃላፊነት መናኝ ገብረኪዳን (ገንዘብ ይዘው የተሰወረው)
፪/ አዲርቃይ ላይ አራት የሞተር ወፍጮዎች ሲኖሩ በሃላፊነት አባ ገብረተንሣይ (በአባ ገብረሕይወት የተሾሙ)
፫/ ማይጸብሪ ላይ ሦስት የሞተር ወፍጮዎች ሲኖሩ በሃላፊነት አባ ሰላማ (በአባ ገብረሕይወት የተሾሙ)

እነዚህ ቦታዎች ላይ ለብዙ ዘመናት በሃላፊነት ላይ የነበሩትን አባቶች አንስተው የራሳቸውን ሶዎች በማስቀመት የገዳሙን መተዳደሪያ የሆኑትን ወፍጮዎች እና እቃቤቶች ያለአግባብ እያስመዘበሩት ይገኛሉ፤ እነዚህ የገዳሙ ንብረቶች አሁን ያሉት ገዳማውያን ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት ገዳሙ ህልውናው ተጠብቆ እስከቆየ ድረስ፣ ገዳማውያኑ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለምሳሌ ጨው፣ ኑግ፣ የአቡጀዱ ጨርቅ የመሳሰሉትን ነገሮች የሚገዙት እነዚህ ወፍጮዎች በሚያስገቡት ገንዘብ ሲሆን ለዕለት ጉርሳቸው የሚሆነውን አግኝተው ከዛ በተረፈ ለቋርፍ የሚሆነውን የሙዝ ተክል ለማልማት እና አንዳንድ ለቤተክርስቲያን የሚሆኑ ንዋየ ቅድሳንን እና ዘቡብ እና እጣን የመሳሰሉትን ሁሉ ሊገዛባቸው የሚችለው በእነዚሁ ቦታዎች ከሚገኘው ጥቂት ገቢዎች ሲሆን ነገር ግን በአሁን ሰዓት በሃላፊነት ላይ የተቀመጡት አለአግባብ ገዳሙን እያስመዘበሩት እንደሆነ ማናችንም ልብ ልንለው የሚገባ እንደሆነ ለማሳወቅ እንወዳለን።

በተያያዘ ዜና ባለፈው አቤቱታቸውን ለመንግሥት አካላት እንዲሁም ለቤተክህነት ተወካዮች ለማቅረብ ወደ አርባ የሚጠጉ የመነኮሳት እና የመነኮሳይት ቡድን ወደ ጎንደር ከዛም ወደ ባሕርዳር ሄደው እንደነበር እና ከዚያም የአማራው ክልል የጸጥታ ክፍል ሃላፊዎች እና የቤተክህነቱ ተወካዮች እናስማማችኋለን በማለት ሳይፈልጉ ተገደው ወደ አዲርቃይ ከዚያም ማይጸብሪ እንደሄዱ እና ለማስማማት የተሰየሙትም፣ ዳኞቹም፣ ፈራጆቹም፣ እርቅ ፈላጊዎቹም እራሳቸው የዚህ ችግር ፈጣሪዎች እነ አቶ ሲሳይ መሪሳ እና የአካባቢው ዘረኛ ሹሞች ሆነው ሳለ ነበገር ግን እራሳቸው በፍርድ ወንበር ተቀምጠው እነዚህን መነኮሳት እና መከኮሳይት ሰድበው፣ አዋርደው፣ አበሻቅጠው ወደገዳማችሁ እንድትመለሱ በማለት ከማስፈራሪያ ጋር ቢመለሱም ከገዳሙ ለአቤቱታ የወጡበት ጉዳይ ተመልሶ በመምጣቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተሰደው ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማት እንደገቡ ተሰምቷል። የመሰዳዳቸው ጉዳይ የቆየ ቢሆንም ነገር ግን አብዛኞቹ በመንገድ ላይ ስለነበሩ የሚደርስባቸውንም በትክክል ስለማይታወቅ፣ የተሰደዱት በሙሉ ተጠቃለው ወደ ተለያዩ ቦታዎች እስከሚገቡ ድረስ ተጠብቆ ለምዕመናን ማሳወቅ ስለሚገባ እነዚህ ገዳማውያን በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ ገዳማት መድረሳቸውን በማረጋገጣችን ለጊዜው እፎይታ ቢሰማንም፥ ነገር ግን አንድ ሰው በገዛ ሃገሩ ይልቁንም በማንም ላይ ሳይነሳ ሃይማኖቱን ማመን አለመቻሉ እና እምነቱን መፈጸም ባለመቻሉ በይበልጥ ያሳዝናል። እነዚህ ገዳማውያን እንደመጀመሪያቸው የጠየቁት ነገር ቢኖር ቤተክርስቲያናችንን አንሸጥም፣ ገዳማችንን አትንኩብን፣ የጸሎት ቦታችንን አታደፍርሱብን በማለት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ቆይተው ነበር አሁን አሁን ይባስ ብሎ እናንተ የዚያኛው ተወላጆች ናችሁ፣ ይሄ ምድር የናንተ አይደለም በመባላቸው ይበልጡኑ አሳዝንኖናል። በዚህ ዓይነትም እስከ መቼ መቀጠል እንዳለብን በእጅጉ ልብልንለው የሚገባ ነው እንላለን።

እውን ለሃይማኖታችን መቆም እና መጠየቅ ሌላ ሊያስብል ይችላል? ሁላችንም ልንመልሰው የሚገባ የወቅቱ ጥያቄ ነው ትላንት መንግሥት በዋልድባ ላይ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካን አቋቁማለው በሚል ሰበብ፣ ከዚያም የፖርክ ይዞታዎችን እናስፋፋለን፣ የወርቅ ማውጫ ማዕድን እንከፍታለን፣ የእምነ በረድ ፋብሪካ እንገነባለን፣ የእጣን ፍብሪካ እንገነባለን በሚል
ከዚያም በአዲስ አበባ አካባቢ የሰማዕቱን አቡነ ጴጥሮስን ሃውልት ለመንገድ በሚል ሰበብ ለማንሳት ማሰባቸው በመቀጠል ደግሞ በቅርቡ በጎጃም ባሕርዳር ዳንግላ አካባቢ የጣና በለስ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀት ቢሚል ለበርካታ አብያተ ክርስቲያናት መፍረስ እና መነሳት ምክንያቶቹን በዝርዝር ስንመለከተው የዚህችን ጥንታዊት፣ ሐዋሪያዊት እና ብሔራዊት የሆነውችውን ሃይማኖታችንን ህልውና በእጅጉ የሚፈታተን ሆኖ እናገኘዋልን እስቲ ዝርዝሮቹን እንመልከት
፩/ በዋልድባ ወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ምክንያት 18 አብያተ ክርስቲያናት መፍረሳቸው አይቀሬ ነው
፪/ የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ለመንገድ በሚል ሽፋን መነሳቱ አይቀሬ ነው መመለሱ ግን ጥያቄ ውስጥ ነው ያለው
፫/ በምዕራብ ጎዳም ዳንግላ አካባቢ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ 17 አብያተ ክርስቲያናት መፍረሳቸውም እንዲሁ

ተመልከቱ አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 35 ቤተክርስቲያናት ከፈረሱ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ የሚፈተትባቸው አብያተ ክርስቲያናት ከፈረሱ በመጪው 4 ዓመት ውስጥ 140 ቤተክርስቲያናት ከዚያም በ8 ዓመት ውስጥ ሌሎች 280 አብያተ ክርስቲያናት ሊፈርሱ ነው ማለት ነው። እውን በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛው ቤተ እምነት ነው የእምነት ቦታዎቹ የፈረሱበት ይልቁንም በሥልጣን ባለው መንግሥት? ልብ ያለው ልብይበል ዛሬ በተለያዩ የሃገራችን ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሲፈርሱ እያየን ዝም ካልን ነገ እራሳችን የምንገለገልበት አጥቢያ ሲፈርስ ምን ልንል እንደምንችል ከወዲሁ ልናጤነው ይገባል፥ ዛሬ ጥቂት አረማውያን በሃይማኖታችን ላይ መነሳታቸው ማንም ሊገነዘበው የሚገባ እውነታ ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን ሁላችንም እኔን አይመለከተኝም በሚል ሰምተን እንዳልሰማን፣ ዓይተን እንዳላየን ጆሮ ዳባ ልበስ በሚል መልኩ በዝምታ ተሸብበን ዝምታን መርጠናል። ያዲያ ዛሬ በሃይማኖታችን ላይ  የተቃጣውን ውጊያ ጦርነት ዝም ብለን መመልከት መፍትሄ ያመጣ ይሆን? የኛስ ዝምታ ከታሪክ ተጠያቂነት ያድነን ይሆን?
ለማንኛውም ስለሃይማኖታችን ዝምታ መምረት መፍትሄ እንደማይሆን በተደጋጋሚ በዚህ ዝግጅት ክፍል ሲነገር ቆይቷል፣ ድምጻችንን በአንድም በሌላ ከማሰማት ወደ ኃላ የምንል መሆን የለብንም ለዚህም ለደጋጎቹ አባቶቻችን ለቅዱሳን ለሐዋሪያት የተለመነ አምላከ ቅዱሳን መልሱንም ሳይውል ሳያድር የሰጠ ልዑል እግዚአብሔር አሁንም ከእኛ ጋር እንደሆነ እናምናለን ይዘገያል እንጂ መልስ እንደሚሰጠን እምነታችን የጸና ነው።

የሲዖል ደጆች አችሏትም የተባለላት ቅድስት፣ ንፅህይት፣ ርትዕይት የነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን በቸርነቱ ይጠብቅልን አሜን
  

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

3 comments:

 1. ደሮስ ከሌባ ወያኔ ምን ይጠበቃል !!!

  ReplyDelete
 2. May Lord pay the price of this mad man...i have no word to say....kezih belay min eyetebekin endehone ligebagn alchalem.
  Amlak yifireden.
  Weletekidan.

  ReplyDelete
 3. እጅግ በጣም ያሳዘናል እግዚአብሔር መፍትሄ ይስጠን

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤