Tuesday, April 23, 2013

መናኝ ኃይለመለኮት ከእስር ተፈቱ


·         መናኝ ኃይለመለኮት ከእስር ተፈቱ፥ ነገር ግን በአስቸኳይ ገዳሙን ለቀው እንዲወጡ ተነገራቸው 
የጸሎታቸው በረከት ይደርብን
·         ከትንሳኤ በኃላ ከገዳሙ የሚባረሩ እንደሚኖሩም ተጠቁሟል
·         ማቄን ጨርቄን ሳትሉ ቦታውን ጥላችሁ ውጡልን
 በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ  
ባለፈው አርብ እለት ማታ በተከሰተው በታጣቂዎች በማይለበጣ እናበዳንዶሮቃ ዘረፋ ከተፈጸመ በኃላ በቀጣዩ እለት ማለትም ቅዳሜ መናኝ ኃይለመለኮት የተባሉትን አባት ያለ ጥፋታቸው ወደ ማይጸብሪ በመውሰድ በእስር ላይ እንደነበሩ ይታወሳል። በእለቱ አሉ ተብለው ለእስር የዳረጋቸውም “ታጣቂዎች ይዘርፉናል፥ ታጣቂዎች የዳኙናል” በሚል ሰበብ እንደነበረ ዘግበን እንደነበረ ይታወሳል። በዚሁ እለትም በታጣቂዎች ተደብድበው የሕክምና እድል እንኳን ማግኘት ያልቻሉትንም አባ ፍቅረማርያምን እስከ አሁን ድረስ ደማቸውን ከሚጠራርጉላቸው ወንድሞቻቸው በቀር የረባ ሕክምና ወደ ማይጋባ ወስደን እናሳክም ብለው የጠየቁትን “አይመለከታችሁም አርፋችሁ ተቀመጡ” በማለት ማስፈራራት ደርሶባቸዋል፥ እኝህ አባትም እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ምንም አይነት ህክምና ሳያገኙ መቆየታቸውን ስጋታቸው አባቶች ገለጸውልናል፥ ነገር ግን ከሰዎቹ ፈቃድ ውጪ ምንም ለማድረግ አለመቻላቸውም በእጅጉ አሳዝኗቸዋል።


ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ቅዳሜ የታሰሩት መናኝ ኃይለመለኮት ከታሰሩበት እስር ቤት ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ወጥተዋል። በትዕዛዙ መሰረትም መናኝ ኃይለመለኮት ወደ ገዳሙ የመግባት ፈቃድ እንደሌላቸው እና በቀጥታ ወደሚሄዱበት እንዲሄዱ አሳሪዎቻቸው አስፈራርተው ነግረዋቸዋል። ከጥቂት ወራት በፊት ወደ አርባ የሚጠጉ አባቶች እና እናቶች የሚደርስባቸውን በደል በባሕርዳር ለአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ቢሮ፣ ለክልሉ የጸጥታ ክፍል፣ ለክልሉ የፓሊስ ኮሚሽነር ቢሮ፣ በጎንደር ከተማ ለሚገኙት ለሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ለሰሜን ጎንደር የጸጥታ ቢሮ አቤቱታቸውን እንዳሰሙ ይታወሳል፥ በመጨረሻም የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ጸሐፊ፣ የሰሜን ጎንደር የጸጥታ ክፍል ሃላፊዎች ከማይጸብሪ አስተዳዳሪ ጋር በመነጋገር ችግራችሁን እዛው ሄደን ተነጋግረን እንፈታዋለን ተብለው ሳይፈልጉ በግድ ከጎንደር ተግዘው (ተገደው) ማይጸብሪ ተወስደው የስድብ እና ማንጓጠጥ መዓት ወርዶባቸው ወደ ገዳማቸው እንደገቡ ይታወሳል። ከገቡም በኃላ በየእለቱ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ደርሶባቸው የበረቱት በውድቅት ሌሊት ሕይወታቸውን ለማቆየት ከገዳሙ ተሰደው በተለያዩ የክልሉ ገዳማት ገብተው እንዳሉ ለመረዳት ችለናል። ቅዳሜ እለት ለእስር የተዳረጉት መናይ ኃይለመለኮትም በወቅቱ ማስፈራራት ከደረሳቸው አባቶች መካከል አንደኛው ሲሆኑ፣ የሚመጣውን እንደጌታዬ እየሱስ ክርስቶስ በጸጋ እቀበለዋለሁ ብለው በገዳሙ ቆይተው እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በዚህም ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር አንዳንድ አባቶች ይገምታሉ መናኝ ኃይለመለኮትን ለእስር ያበቃቸው እንጂ ከሳሾቻቸው (ታጣቂዎቹ) እንደሚሉት “ታጣቂዎች ዘረፉን፥ ታጣቂዎች ይዳኙናል” የሚለውን ቃል እሳቸው እንዳልተናገሩ ለመረዳት ችለናል።

የደረሰን መረጃ እንደሚያስረዳን በመጪው ትንሳኤ በኃላ ተጨማሪ አባቶች በተለይም አማርኛ ተናጋሪ የሆኑትን ተከታትለው ከገዳሙ እንደሚባረሩ እና እንደሚያስወጧቸው እየተነገረ ነው። ሲያስወጧቸውም ማቄን ጨርቄን ማለት እንደማይችሉ እና
 ልክ ትላንት በቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢ የተደረገውን አይነት ማፈናቀር እንደሚሆን እነዚሁ ምንጮቻችን ስገታቸውን ገልጸዋል፣ እስከ ዛሬም ድረስ ለስደት የተዳረጉት፣ ያለበደላቸው እንደሌባ ተደብድበው ደማቸውን እንኳን ለማስቆም ህክምና ለማግኘት ነጸነት የተነፈጉት አባትን ጨምሮ፣ ሌሎችም ያለ በደላቸው በእስር እየተዳረጉ ያሉትን አባቶችን፣ ማስፈራራት ደርሶባቸው ጥለው በውድቅት ወጥተው እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ የማይታወቅላቸው መነኮሳት አባቶች እና መነኮሳይት እናኖታችን በሙሉ ቋንቋን እና ጎጥን ምክንያት ተደርጎ እየተባረሩ እና እየተሳደዱ እንዳሉ ለመረዳት ችለናል። ላለፉት 1600 ዓመታት በዋልድባ ገዳም አንተ ወንዝህ የትነው፣ ጎጥህ ወየዴት ነው፣ ከየትስ መጣህ፣ ጎሳህ ማን ይባላል ተባብለው በፍጹም እምነታቸው እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ የኖሩ አባቶች እና እናቶች ዛሬ ቋንቋችሁ የተለየ ነው፣ ወንዛችሁ ከወዲያ ማዶ ነው አለያም ትውልዳችሁ ከወዲያኛው ተራራ ነው በሚል ሰበብ አባቶች እና እናቶች በሰላም እግዚአብሔርን እያገለገሉ ከኖሩበት ፍጹም የገዳማዊ ሕህወታቸው እየተሰደዱ እና እየተንከራተቱ ይገኛሉ።

በሰለጠው ዓለም አንድነት ይበልጥ እያመዘነ ያለው አንድነትን የማምጣት ሁኔታ በይበልጥ እየተሰራበት ባለበት ዓለም ለምሳሌ የጀርመን ከሁለትነት ወደ አንድነት መምጣት፣ አውሮጳውያን ተነጣጥለን ከምንኖር ሃይል እንዲኖረን እንድ እንሁን ብለው የጋራ መገበያያ እና ድንበራቸውን ከፍተው የየትኛውም የአንድነቱ አባል ሃገር ተወላጅ ወደ ሚፈልገው ቦታ ሄዶ የመኖር፣ የመሥራት፣ የማደግ እና ንብረት የማፍራት ፈቃድ ባለበት በዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እኛ ጋር ከሃገርም አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ከሃይማኖትም አንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሆነን ሳለ ጎጣችሁ፣ ወንዛችሁ፣ ተራራችሁ እንዲሁም ቋንቋችሁ የተለየ ነው በሚል ሰበብ ዛሬ በርካቶች ሃገር እያላቸው ሃገር እንደሌላቸው፣ ወገን እያላቸው እንደ ስደተኛ የተቆጠሩበት ጊዜ ስለሆነ ልብ ብለት ወደ እግዚአብሔር ልናመለክት ይገባናል፣ በዚህ ልክፍት የተለከፉትንም እግዚአብሔር አምላክ ልቦናውን ሰጥቷቸው አዕምሮውን አድሏቸው በገዛ ወገናቸው ላይ የሚያደርሱትን ስቃይ፣ ግፍ እና በደል እንዲያቆሙ ማስተዋሉን ይስጣቸው ወደ ልቦናቸው ይመልሳቸው እንላለን።
እግዚአብሔር አምላክ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን በረደኤት ይጠብቅልን አሜን
ይቆየን

ቸር ይግጠመን
IUEOTCFF

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤