Monday, April 22, 2013

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ችግር በVOA ራዴዮ ዘገባ


በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለዘመናት እየተንከባለለ የመጣው ችግር ዛሬም ለመመረቅ ጥቂት ወራት የቀራቸውን ደቀ መዛሙርት ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ ከቅዱስ ፓትሪያርኩ ጀምሮ እስከ ኮሌጁ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስን ጨምሮ ሁለት መምህራን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ትምህርት አያስተምሩም፣ ችግር አለባቸው ቢባሉም እኛ ያልነው ብቻ ልክ ነው በሚል፣ ይልቁንም ሌላ ተልዕኮ አላችሁ፣ የቀደመ የቤተክርስቲያን ትምህርት የላቸውም እና የመሳሰለውን ምክንያት በመስጠት ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ምክንያት መደርደር የሚወዱት የኮሌጁ የቦርድ አባላት እና የበላይ ጠባቂው ኮሌጅን ያህል የቤተክርስቲያኒቱን ትልቅ ተቋም እንደግል ቢሮአቸው በሰረገላ ቁልፍ ክርችም ካደረጉት ወራት ተቆጥረዋል። የደቀ መዛሙርቱን ችግር ለማዳመጥ ጆሮውን የሰጠ የኮሌጁ ዲን የለም፣ የበላይ ጠባቂውም በችግሩ ላይ ችግርን ጨምረው፣ የሚመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስም ዝም ብሏል፣ ምዕመናንም ዝም ብለዋል፣ ሁሉም ዝም ብለዋል በመካከሉ ግን ስውር ዓላማ ያላቸው ቤተክርስቲያኒቱን ወደ ሌላ ተቋም ለመቀየር የሚጣጣሩት አካላት ተሳክቶላቸዋል፡፡ ነገ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ተመርቀው ወጥተው ወልድ ዋሕድ ብለው የሚያጠምቁ፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ይዘው ዓለምን በወንጌል ሊያዳርሱ የሚችሉ በሁለት ሰዎች ምክንያት ከ5000 በላይ የሚሆኑ ደቀመዛሙርት ለረሃብ፣ ለጥም፣ እና ለዕርዛት ተዳርገዋል። ኸረ የቤተክርስቲያን አምላክ በማለት ጩኸታቸውን እያሰሙ ባሉበት ወቅት የVOAው ዘጋቢ አቶ አዲሱ አበበ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቀደምት ተማሪ እና መምህራን ከነበሩ እንዲሁም በአሁን ሰዓት ችግር አለብን ብለው የሚጠይቁትን የደቀመዛሙርቱን ተወካይ እንግዶችን አነጋግሯል ከነዚህም መካከል ፩/ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ወልደ አማኑኤል የቀድሞ ተማሪ በኃላም መምህር
፪/ መምህር ተመስገን ዮሐንስ የቀድሞ ተማሪ እና የአሁኑ ተመላላሽ መምህር 
፫/ ዲ/ን ተዓምር አየሁ አጥናፌ የተማሪዎች መማክርት ጉባኤ ሰብሳቢ 

ሦስቱንም በቃለመጠየቁ አነጋግረዋቸዋል እስቲ እንከታተለው 
ለቤተክርስቲያናችን አስተዋይ ቅን መሪ እና አባት ያምጣልን፣ አለበለዚያ ቀስ እያልን የቤተክርስቲያኒቱ ተቋማት እየተዳከሙ፣ ካህናት ተስፋ እየቆረጡ፣ ምዕመናንም ተስፋ እያጡ ወደ መጥፋት መቃረባችን እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል . . .


  • ትላንት በዋልድባ አካባቢ በወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ስም 18 አብያተ ክርስቲያናት ሊፈርሱ ነው ተባለ 
  • በጎጃም በጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ስም 17 አብያተ ክርስቲያናት እንደሚፈርሱ ተነገረን
  • የኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት በልማት ስም እንደሚነሳ ተገለጸልን
  • በሲዳሞ ፍሰሐገነት አካባቢ ቦታውን ለባለሃብት ልንሰጠው ነው ቤተክርስቲያኖቹ ይፍረሱ ተባልን
  • በደብረ ዘይት፣ በአዲስ አባባ፣ በጎንደር፣ በጅማ እና የተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የቤተክርስቲያን ይዞታዎች እየተቀነሱ ሙሉ ለሙሉ አለያም በከፊል "ለባለሃብት" በሚል ይዞታዎቿ ሲወሰዱ 
እስከ ዛሬ ድረስ ይሄ ሁሉ ለምን በቤተክርስቲያን ላይ ይደርሳል፣ ቤተክርስቲያን እራሷን የቻለች የእምነት ተቋም ስትሆን ማንም መጥቶ ይዞታዋን ሲወስድ፣ ቅርሶቿን ሲያፈርስ፣ የጌታችን የመድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ የሚፈተትባቸው አብያተ ክርስቲያናት የመፍረስ ፍርድ ሲሰጣቸው ማንም ዝም ጭጭ ብቻ . . . ታዲያ በዚህ አይነት ከቀጠልን በአንድ ዓመት ውስጥ 39 አብያተ ክርስቲያናት ለማስፈረስ ከፈቀድን በሁለት ዓመት 80 በሦስት ዓመት 120 በአራት ዓመት 160 በአምስት ዓመት 200 በስድስት ዓመት 240 በሰባት ዓመት 280 በስምንት ዓመት 320 . . . አብያተ ክርስቲያናት መፍረስ ይችላሉ
ማለት ነው ይሄ ማለት ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ በተወሰነ ዓመታት ውስጥ መንበረ ፓትርያሪኩን ብቻ ይዛ ልትቀር ነው ማለት ይቻላል 
ታዲያ ዝምታችን እስከ መቼ ይቀጥል፣ መፍረሱ ቀጥሎ እኛ ያለንበት አጥቢያ ላይ ሲደርሱ ለምን እንበል ወይስ ዛሬ በገጠሪቱ ሃገራችን
ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ሲፈርሱ ተዉ አይሆንም እንዴት ቤተክርስቲያን ትፈርሳለች ብለን እንጠይቅ?? 
መልሱ ለሁላችንም ልንመልሰው ስለሆነ በልቡናችን ያኑርልን እያልን እንሰናበታለን
ቸር ይግጠመን አሜንLet's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤