Friday, May 3, 2013

ዋልድባ በታጣቂዎች እየታመሰ ነው፥ ለምን የሚል የቤተክሕነት ተወካይ ግን የለምገዳመ ዋልድባ ላለፉት 1600 ዓመታት ተከብሮ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ እኛ ላይ ደርሶ ነበር። በአሁን ሰዓት መንግሥት በልማት ሰበብ ሸንኮራ አለማለሁ፣ እምነበረድ ፋብሪካ አቋቁማለሁ፣ የወርቅ ማዕድን ማውጫ እሰራለሁ፣ ወዘተ በማለት ልማት እያለ ታላቁን፣ ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ሃብት ለማጥፋት ብሎም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሕናት፣ ዲያቆናት፣ መነኮሳት፣ ቆሞሳት እና ጳጳሳት ምንጭ የሆነውን ገዳም ለማድረቅ እና ለማጥፋት ወገቡን ታጥቆ ከተነሳ ሰንበት ብሏል። ኢትዮጵያውያንም ለሃይማኖት የማይቆረቆር ግዴለሽ ትውልድ ሆኗል እና ዛሬ የመፍረስ እና የመበተን ፍርድ የተፈረደበት ገዳም ገዳማውያን ያለጥፋታቸው እየታሰሩ፣ እየተደበደቡ፣ እንደወንጀለኛ ያለፍርድ በየእስር ቤቱ እየታጎሩ ይገኛሉ፣ ታዲያ ማነው ለምን ብሎ ሊጠይቅ የሚገባው እኛ አይደለንም እንዴ አንዱ በሬዲዮ "ገዳሙን አንነካም ብለዋል" ይለናል እነሱማ ሁሉንም ይላሉ አረማውያን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታን ሲሰቅሉት እኮ ምክንያት አበጅተው ነው ሕይወት የሚሆናቸውን ሰቀሉት ዛሬም የኛ ሰው ለመጪው ትውልድ ታሪክ ማጣቀሻ የሚሆነውን ብርቅ እና ድንቅ ገዳም ለማፍረስ ደፋ ቀና ይላሉ እውን እነዚህ ለኢትዮጵያ አሳቢዎች ናቸው?? ትልቅ ጥያቄ ነው ዛሬ ታሪኮቻችንን ቅርሶቻችንን እና ብርቅና ድንቅ የሃገራችንን ሃብቶች ቀስ በቀስ እያጣናቸው ነው ማን ይጠይቅ?
ትላንት የአቡነ ጴጥሮስን ሃውልት አፈረሱ እውን እቦታው ይመለስ ይሆን? ሁላችንም የምንመለከው እውነታ ነው
የሉሲ ቅሪት በጉብኝት ሰበብ በብዙ ሚሊዮን ብሮች ወጥታለች ትመለስ ይሆን?
እድሜ ጠገብ የሆኑት የብራና መጻሕፍት የወርቅና የብር መስቀሎች ከየገዳማቱ እየተዘረፉ ለገባያ ውለዋል ማን ይጠይቅ
ልብ ያለው ልብ ይበል

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

3 comments:

 1. የዋልድባው አባት፦

  “…ሕዝቡ ግን ምንም ስለማይሰማና ስለማይገባው፤ ብትነግረው ብትነግረው ስለማይገባው፤ እንግዲህ ያው ቅርሱንም ያስዘርፈው፤ ገዳሙንም ይፍታው። ራሱ ሕዝቡ እንደፈታው ነው እኛ እምናውቀው!!”

  “…ማኅበረሰቡ ይኸን ነገር ማስቆም አለበት!! እኛ ብቻ አደለንም!! ይኸ ንብረት የእኛ አይደለም!! ይኸ ንብረት የሕዝብ ሀብት ነው!! የሕዝብ ንብረት ነው!! የሕዝብ ገዳም ነው!! የኢትዮጵያ ንብረት ነው!! የኢትዮጵያ ቅርስ ነው!! ዝም ብሎ ቅርሱና ሀብቱ ሲጠፋ ማየት ማለት ምንድን ነው? ክርስትናው ምኑ ላይ ነው? ሃይማኖቱስ ምኑ ላይ ነው? ሃይማኖት ማለት መቋሚያ ይዞ ቤተ ክርስቲያን መኼድ ነው? ሃይማኖት ማለት ነጠላ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን መኼድ ነው? ሃይማኖት ማለት ከበሮ ይዞ ሲደበድቡ መዋል ነው? ይኸ አይደለም ሃይማኖት! ሃይማኖት ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ችግርና መከራ ሲደርስባት ፊትለፊት መጋፈጥ ነው፤ ይኸ ነው ይመስለኛል።”

  የኔ አስተያየት፦

  ሕዝቡ እንዳይሰማ፤ ሕዝቡ እንዳይገባው፤ በተለይ “ኮሌጅ የበጠሰው” ክፍል እንዲህ እንዲደነዝዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉት አለባበስና አለጫጨታቸውን እያሳመሩ ከበሮ መደብደብን እንደሃይማኖት እየቆጠሩት የመጡ የሚመስሉት፤ ብለው ብለው ጽድቅ ያለምንም መሸራረፍ ለሚመሰከርበት የነቢያት የካህናት ጉባኤ የተነገረውን የዳዊት ቃል (“…ወጽድቀከኒ በማኅበረ ቅዱንሳን” የሚለውን) በጠራራ ፀሐይ ቀምተው ለራሳቸው ታርጋ ኾኖ በምእመናን ልብ ላይ ይለጠፍላቸው ዘንድ ባማረ ዜማ የሚያንቆረቁሩት ማኅበረ ቅዱሳን ተብየዎች ናቸው። [ምናልባት “ከነሱ ምን አለኽ? ይኸንንስ ጕዳይ ከነሱ ጋራ ምን ያገናኘዋል?” የሚለኝ ቢኖር፤ ጕዳዩ’ኮ ከዅላችንም ጋራ እንደሚገናኝ ገዳማዊው አባት ነገሩን። ይኽም ብቻ አይደለም። ማኅበሩ ከገዛ ራሱ ዝምታ ዐልፎ፤ ስንኳን ባገር ውስጥ በውጭ አገር እንኳ ስለዋልድባ ውይይት እሚባል ነገር እንዳይኖር በግልጥ ዕንቅፋት ሲያኖር ስላየኹት ነው። ዝርዝሩ ይቆየኝ።]

  እናም ማኅበሩ ሰሞኑን የጀመረውን “ቴሌቫንጄሊዝም” ለጊዜው የነሊቀ ሊቃውንት እዝራን ትክሻ ሲታከክበት ብናይም፤ ስንኳን የዋልድባን ጕዳይ፤ ባጠቃላይም በቤተ ክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ሊያወያይበት ጭራሽ ኼዶ ኼዶ የኢቲቪ ታናሽ ወንድም እንደሚያደርገው የሚያሰጋ ነገር ይታይበታል። ይኸውም በትንሣኤው ምድር ባለጊዜዎች እንዲህ በጉልበት እያፈረሷት ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ በምናይ ገንዘብ እናይ ዘንድ እንዳቅማችን ምን ማድረግ እንዳለብን እንዳንመካከርበት፤ መርበብቱን ሳይቀር ሊያጨናንቅ የተዘጋጀ የማደናገሪያ ድግስ ደግሰውልናል። በየግድግዳው ተለጥፎ እንዳየነው በዐቢይ ጾም ይቅርና ባዘቦት ቀን እንኳ ከበኣታቸው ውልፍት የማይሉ መነኮሳት እንዲህ በየበረሃው ሲባረሩና ሲደበደቡ የት እንደደረሱ ሊነግሩን ቀርቶ ለራሳቸውም ሊጠይቁ የማይፈልጉት አባት ተብየ፤ ‘ከአባ ጳውሎስ እሻላለኍ’ ለማለት ጥቁር እንጂ ነጭ አለመልበሳቸውን የምንኩስናቸው መታወቂያ አድርገው ከመመጻደቃቸው ባሻገር፤ በወቅቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቁንጮ ናቸው ተብለው ሳለ፤ “እኔ እንግዳ ነኝ፤ እንደወደዳችኍ አድርጉ” በማለት የቤተ ክርስቲያኗን የኹለት ሺህ ዘመን ሕጋዊ ሰብእና ሳይቀር ባንድ ጀንበር ለሾማቸው ፓርቲ መዝገብ ክፍል እያስረከቡ የሚገኙትን “ቅዱስ” ብለን እናመልክላቸው ዘንድ፤ ከሸፍጥና ከጕኅሉት እንደማያልፍ የሚጠበቀውን ቃለምልልስ ይዘውልን ብቅ ሊሉ እንደኾነ ነግረውናል። የት እንድረስላቸው? ረ የት እንግባ?

  የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ሆይ፦ ረ ቅድሚያ ሕዝብ ኹኑ! ምእመን ኹኑ! ቅድስናው ይቆያችኍ። ደግሞ ከዚህ ቀደም “እኍኒ ኢያድኅን እኅዋኁ” ያለውን ላስታውሳችኍ ሞክሬ ነበር፤ “ወንድም ወንድሙን አያድንም” ማለት ነው። አኹንም ፍርድ በጅምላ ሳይኾን እየራስ መኾኑን አስታውሱና፤ በምእመንነታችኍ፤ ካህናቱም በማዕርገ ክህነታችኍ መጠን ልትሠሩት የሚገባውን ሥሩ እንጂ። እኛም በቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ወንድም/እቶቻችኍ ነንና እንመካከር፤ ባካችኍ የማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ብቻ አትጠብቁ!!! ከምር በምር እንመካከርና ቤተ ክርስቲያናችንን ከማጥ እናውጣት። የእውነተኞቹ ቅዱሳን አምላክ ትንሣኤዋን ያሳየን። አሜን።

  ReplyDelete
 2. የኢህአዴግ ዋናው ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ እየታገለ ነው፡፡ ለዚህ ጥፋት የቤተክርስቲያን አባቶች ደግሞ ምቹ ናቸው፡፡ መንፈሳዊነት የሌላቸው፣ ሃይማት የጎደላቸው፣ የሞኖሩት ለሆዳቸውና ለዘመዶቻቸው ብቻ በምንኩስና ስምና ማስመሰል ብቻ በመሆናቸው ነው፡፡ በተጨማሪ ለጳጳሳቱ መንፈሳዊነት መውደቅ ማኅበረ ቅዱሳን ተጠያቂ ነው፡፡ ምክንያቱም የሌላቸውን ብጽእናና ቅድስና እየሠጠ፣ በጣም እዚህ ግባ በማይባል የእጅ መንሻ መደለያ እንደ ህጻን ልጅ እያታለለ፣ የማይገባቸውን ውዳሴና ቅኔ እሰጠ፣ የተደበቀ ሚስጥራቸውን አወጣባችኋለሁ በማት፣ የማይሠራውን እሠራለሁ በማለት በቁማቸው እየገደላቸው ይገኛል፡፡
  ለዚህ ትልቅ መፍትሔ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ብቻ ነው መንግሥት፣ የሃይማኖት አባት ካህን ሰባኪ የሚባል የለም፡፡

  ReplyDelete
 3. Who cares about Lucy since we believe that the world exists only for 7500 years. Lucy is just the imagination of scientists.

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤