Sunday, June 9, 2013

የገዳማውያኑን አቤቱታ ለመስማት አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ዛሬ ወደ ዋልድባ ይገባል  • በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
  •      አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን የዋልድባ አባቶችን ለማነጋገር ወደ ወልድባ ከትላን በስቲያ ወደዚያው በማምራት ላይ ናቸው
  • ·        አቶ ሸዊት የማይጸብሪ የፖለቲካ መምሪያ ሃላፊ ለአባ ገብረሕይወት መስፍን ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተዋል
  • ·        ነገ የሚገባው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግሩፕ የሚያነጋግረው እነ አቶ ሸዊት እና አባ ገብረሕይወት ያዘጋጇቸውን የሐሰት መነኮስት ቡድን ነው
  • ·        እስከ አሁን ድረስ ከስድሳ በላይ መነኮሳት ከዋልድባ ገዳም በግፍ ተግዘው በተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማት ተሰደው ይገኛሉ
  • ·        እነ አባ ገብረሕይወት ሶስት የጎጠኛው ቡድኖችን ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግሩፑ መልስ እንዲሰጡ አዘጋጅተው እየጠበቁ ነው

ሰሞኑን አንድ የዋልድባ መነኮሳትን ችግር እና ብሶት ሊመለከት እና ሊመረምር የተነሳ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሽሬ እንደሥላሴ ትግራይ አድርጎ መድረሻው የዋልድባ መነኮሳት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር እና እንግልት በደረሰው ጥቆማ መሰረት ሊመረምር እና በቦታው ተገኝቶ አስስመንቱን ሊሰራ ከትላት በስቲያ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ የሃገራችን ክፍል በመጓዝ ላይ እንዳለ ለመረዳት ችለናል። እንደሚታወቀው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ከተጀመረ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ጀምሮ በርካታ መነኮሳት በግፍ ታስረዋል፣ ተደብድበዋል፣ ያለፍርድ ለግዞት ተዳርገዋል፥ ይሄንን ያለውን ችግር ከወረዳ ቤተክህነት እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ከወረዳ የመንግሥት አካላት ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቢሮ ድረስ አቤቱታቸውን ሲሰሙ መቆየታቸውን እና በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ያለፍርድ በርካቶች ታስረዋል፣ ተግዘዋል እንዲሁም የሰውን አዕምሮ በሚነካው መልኩ የመነኮሳቱን እና የመነኮሳይቱን መብት በሚጋፋ አኳኃን በርካታ እንግልት እና ችግሮች ሲያደርሱባቸው (እየደረሰባቸው) ይገኛል። ከዚህም የተነሳ ከጠቅላይ ቤተክህነቱ ጀምሮ እስከ ምዕመናን ድረስ ለምን ያለ አካል እስከ አሁን የለም ወይንም ሊከላከል የሞከረም እስከ አሁን አለመታየቱ ብዙዎችን ኦርቶዶክሳውያን እያሳዘነ ያለ ጉዳይ መሆኑን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚዘነጋው ጉዳይ አይደለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቶ ሸዊት የማይጸብሪ አውራጃ የፖለቲካ መምሪያ ሃላፊ የሚመራው ክፍል አባ ገብረሕይወት መስፍን በቅርቡ በአቶ ሲሳይ መሪሳ አማካኝነት ለዋልድባ አበረንታት የእቃ ቤት ሆነው በመንግሥት ባለሥልጣን የተሾሙ እና እጅግ ጎጠኛ የሆኑ አባትን ጨምሮ ስብሰባ በማድረግ ቀጭን ትዕዛት ከአቶ ሸዊት የተላለፈውን ይዞ ወደ ገዳሙ በመግባት አርባ የሚሆኑ መነኮሳት እና መነኮሳይት ለስብሰባ እንደሚፈለጉ ትዕዛዝ ተላልፎላቸው ነበር፥ ነገር ግን ከመነኮሳት ወገን ማንም ፈቃደኛ እንዳልሆነ እና ምክንያቱን ሳናውቅ ምንም ስብሰባ የሚባል እንደማይሄዱ እና ፍቃዳቸውን እንዳልሆነ ስለተረዱ አባ ገብረሕይወት መስፍን ማስፈራሪያን በመጨመር ገዳማውያኑ ለስብሰባ እንዲመጡ ቢነገራቸውም፥ ከዚህ በተጨማሪ በማይሳተፉት መነኮሳት ላይ “መቅኑን እንዳታደርስ ተብያለሁ” (የሰርክ ጉርስ) በማለት አባው ለመነኮሳቱ ቢያስፈራሩም ገዳማውያኑ እንኳን በዋልድባ ጌታችንበቅዱስ ወንጌል ራሳቸውን ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲሉ ጃንደረባ ያደረጉ አሉ (ማቴ. 19 ፥ 10) እንዳለው የዚህን ዓለም ጣዕም ንቀው፣ ድምፀ አራዊቱ፣ ግርማ ሌሊቱ ሳያቅቃቸው፣ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ የቀኑን ሐሩር፣ የሌሊቱን ቁር ታግሰው ራሳቸውን ጃንደረባ አድርገው በድንግልና ሕይወት በምናኔ የሚኖሩ አባቶች አሉ። የተባለላቸው አባቶቻችን የመጣው ሁሉ ቢመጣ ምንም ዓይነት ስብሰባ እንደማይሄዱ ቁርጥ ያለ ሃሳባቸውን ሲያሳዩአቸው፣ መንገዳቸውን ቀይረው  ከዶንዶሮቃ አካባቢ፣ እንዲሁም ከማይጋባ አካባቢ ጥቁር እራሶችን ሰብስበው እንደ መነኮሳት አልብሰው እና አስተካክለው ከአቶ ሸዊት ጋር ማይጸብሪ በሚገኘው የገዳሙ ወፍጮ ቤት አካባቢ ወደ 31 የሚጠጉ ጥቁር እራሶችን ሰብስበው የገዳሙ መነኮሳት ነን በማለት ከአቶ ሸዊት ጋር በአባ ገብረሕይወት አስተባባሪነት ሲዶልቱ ውለው ለዛሬ ተጨማሪ ከ10 – 20 የሚጠጉ ተጨማሪ አስመሳዮችን እንዲፈልጉ ተነጋግረው ለነገው ስብሰባ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ከአካባቢው በደረሰን መረጃ ለመረዳት ችለናል በዚሁ ስብሰባም ላይ ሦስት መነኮሳትን መርጠው እንዚህ ሰዎች ብቻ እንዲናገሩ እና በገዳሙ ውስጥ ችግር እንደሌለ፣ የተሰደዱ መነኮሳት ወይም መነኮሳይት እንደሌሉ ጭምር እንዲያስረዱ እና ከዚህ በፊት የሚናገሩትም መነኮሳትም የፖለቲካ ሰዎች እንደሆኑ እንዲያስረዱ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እና ማስፈራሪያ ጭምር በማይጸብሪ የፖለቲካ መምሪያ ሃላፊው ሲታላለፍ ቆይቶ ስብሰባቸውን በዚሁ በአቶ ሸዊት ዲስኩር ጨርሰዋል።
በነገው እለት በማይጸብሪ ላይ ችግር የደረሰባቸውን፣ ያለፍርድ ሲበደሉ፣ ያለ ከልካይ ሲደበደቡ እና ከልጅነት እስከ እውቀት ከኖሩበት ገዳማቸው በግፍ እና በዘነኝነት የተባረሩትን ገዳማውያን ሊያነጋግሩ የሚመጡትን የልዑካን ቡድን በወኪል በእነ አቶ ሸዊት እና አባ ገብረሕይወት የተወከሉት ሦስቱ የዘረኛው እና የጎጠኛው ቡድኖች የሚከተሉት ናቸው
፩ኛ/ አባ ገብረማርያም አብረሃ
፪ኛ/ አባ ገብረትንሣኤ መስፍን
፫ኛ/ አባ ገብረየሱስ ነጋ የተባሉ ሦስት ሰዎች ተወክለው ለሚመጡት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ብድኖች በገዳሙ አካባቢ ችግር እንደሌለ እንዲሁም በወልቃይት ስኳር ፋብሪካ አማካኝነት በገዳሙ ላይ ምንም አይነት ችግር እንዳልደረሰባቸው፣ ገዳማቸውንም እንደማይነካ እና በገዳሙ አካባቢ የሚደረገውን የልማት ሥራ ሁሉ እንደሚደግፉ፣ እና በአጠቃላይ መንግሥት ያወጣውን የልማት እቅድ በሙሉ ደግፈው አብረውም እንደሚሰሩ በሃሰት እንደሚመሰክሩ በእነ አቶ ሸዊት እና አባ ገብረሕይወት ዛሬ ቀኑን ሙሉ ሲያስጠኗቸው እና ሲመክሯቸው መዋላቸውን ተያይዞ የመጣልን መረጃ ያሳያል።
ላለፉት ዓመታት በዋልድባ ፍርድ ሲጓደል፣ ደሃ ሲበደል፣ በለጊዜ ያሻውን ሲፈርድ በተለያየ መልኩ አቤቱታ ለማሰማት ቢሞከርም ነገር ግን ሰሚ ሊገኝ ባለመቻሉ ገዳማውያን አባቶች በዚህ ገዳም ተወስነው መኖር ካለመቻላቸው የተነሳ ተሰደው በተያዩ ገዳማት ገብተው በእዛ ጊዜ እስቲያልፍ ተጠልለው ይገኛሉ፣ ጥቂቶችም ሃገር ጥለው በባዕድ ምድር በመንከራተት ላይ ይገኛሉ። ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ከምንታወቅባቸው ጥቂት ነገሮች አንደኛው እና መለያችን እንግዳ ተቀባይነታችን እንደነበር ማንም የሚዘነጋው አይደለም፥ ነገር ግን ዛሬ ዛሬ እንኳንስ እንግዳ ልንቀበል የራሳችንን ዘወትር ወደ ፈጣሪያቸው የሚለምኑልንን ለሃገር፣ ለወገን፣ ብሎም ለዓለም ሁሉ ዘወትር ከፈጣሪያቻው የሚገናኙትን መናኒያን መነኮሳት እንደ አውሬ ሲያሳድዷቸው ማየት በእውነት በእጅጉ የዘገንናል ያሳዝናልም። ለዚህም ይመስለናል በሃገራችን ሰላም የጠፋው፣ ፍቅር የራቀው፣ ጎጠኝነት የነገሰው፣ ሰው ያለማመን የነገሰው ታዲያ እስከመቼ እርስ በእርሳችን ተገፋፍተን? አንዱ ያንዳችንን መቃብር ጉድጓድ ስንቆፍር እንኖራለን ለዚህች ቅድስት ሃገራችን በጋራ በመቆም ለቅድስት ቤተክርስቲያናችን አለኝታ እና ጠበቃ መሆን ሲገባን ነገር ግን ለጠላት አሳልፈን ስንሰጣት፣ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን መናፍቃን እና አክራሪዎች እንዲሁም ተረፈ አርዮሳውያን በሁኑ ባለጊዜዎች በርካታ ጥፋት እና በደል በቤተክርስቲያን ላይ ሲደርስባት እግዚአብሔርም እንደክፋታቸው ሳያጠፋቸው እድሜ ለንሰሃ ሰጥቷቸው እስከ አሁን ድረስ ሁሉም በያለበት አለ ነገር ግን ያ ምህረቱ ያለቀ እለት በቅድናው ቦታ ላይ የተቃጡ እጆች በሙሉ መቆረጣቸው እንደማይቀር እሙን ነው።
ይቆየን
ወስብሃት ለእግዚአብሔር


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

4 comments:

  1. የገዳሙ አምላክ ፍርዱን አይርሳ።እች ምድር ከሆነ ለፈጠራትም አልተመቸች፤ አባቶችን ሐይሉን ፤ብርታቱን እንዲሰጣቸው እንጸልይ።

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤