Tuesday, July 9, 2013

በዋልድባ ገዳም ግፉ እና እንግልቱ እንደቀጠለ ነው፥ አረማውያን የግፍ በትራቸውን በገዳማውያን አባቶች ላይ እየሰነዘሩ ነው!

ገዳማውያኑ ያለበደላቸው ለምን ይንገላቱ?

ከትናንት በስቲያ በደረሰን ሪፖርት እንደሚያመለክተው ላለፉት ጥቂት ወራቶች ሲደረግ እንደነበረው ታጣቂዎች በመነኮሳቱ ላይ ድብደባ፣ እንግልት፣ ስድብ እና እስራት እየፈጸሙባቸው ይገኛሉ። መንግሥት በዋልድባ ገዳም ላይ የሥኳር ፋብሪካ፣ የወርቅ ማዕድን ማውጫ፣ የፖርክ ይዞታን እከልላለው ብሎ በመነሳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሏት በርካታ ገዳማት በጥንታዊነቱ እና በታሪካዊነቱ የሚታወቀውን የዋልድባ (ዋሊ) ገዳም ለማፍረስ እና ገዳማውያኑን ለማሰደድ አረማውያን ደፋ ቀና ማለት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህ ሁሉ ግፍ እና በደል በገዳማውያኑ ላይ ሲደርስ በሰዎች ዘንድ ምንም ጥያቄ እና የመከላከል እርምጃ ባይደረግም ነገር ግን የቤተክርስቲያኒቱ መስራች መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ተዓምራትን እያሳየ በርካታ እንቅፋቶችን ቢፈጥርባቸውም፥ ነገርግን በእምቢተኛነት ተግዳሮቱን እንደቀጠለ ነው፥ ነገር ግን የልብሳቸውን አዳፋነት፣ የሰውነታቸውን ክሳት አይቶ ሳይፈራ ስቃይንና መከራን ያበዛባቸውን አረማዊ እንዳይፈሩ በትንቢተ ኢሳያስ ፶፩ ፥ ፯ ላይ የሰፈረውን ቃል መመልከት በቂ ነው፤ እንዲህ ይላል “ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፥ በስድባቸውም አትደንግጡ።” ኢሳ. ፶፩ ፥ ፯


በላፉት ጥቂት ወራቶች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መነኮሳት እና መነኮሳይት በግፍ ከገዳማቸው ተባረዋል፣ ተብድበዋል፣ ተግዘዋል ታዲያ ይሄ ሁሉ በደል እና የልብ መደንደን ለምን በገዛ ሃገራቸው እንዲህ አይነት በደል ይፈጸምባቸዋል ብለን ብንጠይቅ፥ መልስ እንኳን መስጠት የማይችሉ ሰዎች እነኝህ ለሃገር እና ለወገን ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ቀን ከሌሊት ሥብሃተ እግዚአብሔርን ሳያጓድሉ የሚያደርሱትን አባቶች እና እናቶች እንደ ጠላት በየጊዜው አንድና ሁለት እያሉ ይልቁንም የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑትን መነኮሳይት እና መነኮሳት በመደብደብ ማስወጣታቸውን ተያይዘውታል፥ ለዚህም ነው በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ አምስት መነኮሳት በአውራጃው ፖሊስ ታጣቂዎች (አንጋቾች) ክፉኛ ተደብድበው ከፊሉ ለእስር ሲዳረጉ ከፊሎቹ ደግሞ ለሆስፒታል መዳረጋቸውን በሰማን ጊዜ ልባችን በሃዘን ቆስሏል። እነዚህ መነኮሳት ተወልደው እትብታቸው በተቀበረበት ምድር ለመኖር የአንድ  ወረዳ ጎጠኛ አስተዳዳሪ ውሳኔ ሲጠየቅ ተመልከቱ፣ ከልጅነት እስከ እውቀታቸው በዚህ ገዳም ኖረው ነገር ግን በወንዛቸው እና በተራራቸው በሚያምኑ ጎጠኞች መከራው እየጸና፣ እንግልቱም እንደቀጠለ ነው። አባቶቻችንም ወደ እግዚአብሔር ያመለክታሉ፣ ታጣቂዎችም ለጊዜውም ቢሆን ድል የቀናቸው ይመስላል ነገር ግን ጠቢቡ እንዳለው “ወ ጊዜ ለኩሉ” ነውና ዛሬ ድል አድራጊ መስለው የታዩት፥ ነገ እጆቻቸውን ወደ አምላክ ዘርግተው እንደሚለምኑ ምንም ጥርጥር የለንም አዎ እርሱም መሃሪ የባሕሪይ ገንዘቡ ነው እና ምሕረቱን አይነፍጋቸውም።

ከጥቂት ቀናት በፊት በታጣቂዎች ድብደባ የደረሰባቸው መነኮሳት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል
፩/ አባ ገብረማርያም [ክፉኛ ቆስለው እጃቸው ተሰብሮ በህክምና ላይ ይገኛሉ]
፪/ አባ ገብረ ዮሐንስ [ክፉኛ ተደብድበው ወደ ክልልችሁ ሂዱ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ]
፫/ አባ ገብረ ሥላሴ [ክፉኛ ተደብድበው ወደ ክልልችሁ ሂዱ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ]
፬/ አባ ገብረ ሚካኤል [ክፉኛ ተደብድበው ወደ ክልልችሁ ሂዱ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ]
፭/ መናኝ ሠይፈ ገብርኤል [ክፉኛ ተደብድበው ወደ ክልልችሁ ሂዱ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ]

በጣም የሚያሳዝነው እነኝህ ደቂቀ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ የእግዚአብሔር ፍጡራን ሃገር እንደሌላቸው “ይሄ ክልላችሁ አይደለም” እየተባሉ ይህን ያህል ዱላ እና ስደት የሚደርስባቸው በእውነት ምን ስላደረጉ ነው? በሰው ላይ አልደረሱ፣ ቀለብ ስፈሩልን፣ ገንዘብ ቁጠሩልን ሳይሉ በበረሃ ተወስነው ለፍቅረ ክርስቶስ እራሳቸውን መስዋዕት አድረገው ለዓለም በጸለዩ እንዲህ አይነት በደል ሲደርስባቸው ማየት እጅጉን ይከብዳል። ንጹህ ህሊና ላለው ሰው፣ ለሚያገናዝብ ሰው በእውነቱ የበደል በደል ነው በገዳማውያኑ ላይ የሚደርሰው፣ ነገር ግን ሳይውል ሳያድር ብድራቱን ያገኙታል፥ እነዚህ አባቶቻችን የሚያመልኩት አምላክ ተዋጊ ነው ስሙም ቅዱስ ነው “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው” ዘፍጥረት ፲፭ ፥ ፫ ላይ እንደተገለጸው ዛሬ ባለጊዜዎች የመከራ ቀንበር ቢያበዙብንም፣ እጅግ ለመሸከም ቢከብድም ነገር ግን የነገሥታት ንጉሥ ሁልጊዜ የድሆችን ይልቁንም ለክብሩ ዱር ለዱር፣ ፍርክታ ለፍርክታ የተንከራተቱትን ዘወትር ከጽሕረ አርያም ይመለከታል ፍርዱም አይጓደልም፥ ነገር ግን ለሰዎች የዘገየ፣ የማያይ፣ የማይሰማ ሊመስላቸው ይችላል፤ እርሱ ግን እድሜ ለንሰሐ እየሰጣቸው መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል መጽሐፈ ነሕምያም እንዲህ ይላል “አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነቢያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ።” ነሕምያ ፱ ፥ ፴፪

በአጠቃላይ ባለጊዜዎች የሚያደርሱት መከራ እጅግ መራራ ቢሆንም፣ የጣሉብን ቀንበር ከባድ ቢሆንም የእሥራኤል አምላክ ዝም አይልም፣  ዘወትር በድካማችን ይጎበኘናል ጠላቶቻችንም ያፍራሉ፣ በእግራችን ሥርም ይወድቃሉ። የአባቶቻችንን ግፍ እና በደል ቆጥሮ ይዘገያል እንጂ ብድራቱን ሁሉ እንደማይነሳቸው እናውቃለን በእምነት መነጽር ለምንመለከተው ሁልጊዜም እግዚአብሔር ሃያል አምላክ ነው፥ ለማያምኑት ለአረማውያኑ ፌዝና ቧልት ሊመስላቸው ይችላል ፣ በመጨረሻ ግን በግንባራቸው ተደፍተው ወደ ፈጣሪ እንደሚለምኑ እናምናለን።
የደጋጎቹ ቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ በረደኤት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ያስባት
ያለሃጢያታቸው እና በደላቸው የሚንገላቱትን አባቶቻችንን ድካማቸውን ድካመ ቅዱሳን አድርጎ ይቀበልልን

ወስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤