Thursday, July 11, 2013

ሰበር ዜና – ደቀ መዛሙርቱ በመንበረ ፓትርያርኩ ቅጽር የተቃውሞ ትዕይንት እያካሄዱ ነው

Board members of the college
 • ፖሊስ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ አነጋግሯ
 • ‹‹ከሣሾቼን እንዳታነጋግሩ›› ያሉት አቡነ ጢሞቴዎስ ቋሚ ሲኖዶሱ በጉዳዩ ላይ እንዳይወያይ ማከላከላቸው ተሰምቷል
 • በተቃውሞው የተበሳጩት ሊቀ ጳጳሱ ራሳቸውን ስተው እንደነበር ተጠቁሟል
 • ‹‹አልፈው በመቃብራቸው ላይ መሣቅ እንፈልጋለን›› – የጥላቻው ምሬት
 • ‹‹በተራዘመው መርሐ ግብር ሳቢያ የተጨመረው በጀት ለብክነት እየተዳረገ ነው›› /ደቀ መዛሙርቱ/
ዛሬ ጠዋት ወደ መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያመሩት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት በመንበረ ፓትርያሪኩ ቅጽር ላይ የተቃውሞ ትዕይንት እያካሄዱ ነው፡፡
ጥቁር የአገልግሎት ቀሚሳቸውንና መጽሐፍ ቅዱስ በመያዝ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ በሰልፍ ያመሩት ደቀ መዛሙርቱ፣ ወደ ቅጽሩ እንዳይዘልቁ በጥበቃ ሓላፊው በታገዱበት ነው የተቃውሞ ትዕይንታቸውን በማካሄድ ላይ ያሉት፡፡
ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ለመግባት የተፈቀደላቸው የደቀ መዛሙርቱ መማክርት መሪዎች/ተወካዮች ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ጋራ እየተነጋገሩ እንዳሉ የተመለከተ ሲኾን ቋሚ ሲኖዶሱም በጉዳዩ ላይ እየመከረበት ስለመኾኑ፣ ‹‹በግቢው ጥበቃ ሓላፊ አቶ ብርሃኔ ኀይሉ ተነግሮናል፤›› ብለዋል፡፡


ሌሎች የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች በበኩላቸው፣ የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ድረስ በአካል በመሄድ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስን ‹‹ከሣሾቼን እንዳታነጋግሩ›› ብለው በማከላከላቸው ውዝግቡን ያጣራው ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ቋሚ ሲኖዶሱ ያደረገውም ይኹን እያደረገ ያለው ውይይት አለመኖሩን በማረጋገጥ በጥበቃ ሓላፊው የተሰጠውን መረጃና በቀደመው የሐራ ዘተዋሕዶ ዜና የቀረበውን ዘገባ አስተባብለዋል፡፡
ይህም ኾኖ ደቀ መዛሙርቱ የአቡነ ጢሞቴዎስ ፈቃድ ፈጻሚና የችግሩ አካል አድርገው የሚጠቅሱት የኮሌጁ ቦርድ፣ በፓትርያሪኩ ተመርቶለታል በተባለው የአጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት ላይ ሰኞ ዕለት እንደመከረበትና ከሦስትና አራት የቦርዱ አባላት በቀር የሚበዙቱ የአጣሪ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳቦች በቀረቡበት አኳኋን ተፈጻሚ እንዲኾን መስማማታቸውን አስታውሰዋል፤ ምንጮቹ አያይዘውም ቦርዱ እስከአሁን ጉዳዩን ከማየት የዘገየውም የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ባላቸው ሓላፊነት መሠረት የሚሰጡትን ውሳኔ መነሻ ለማድረግ ነው ብለው እንደሚገምቱ ገልጸዋል፡፡
‹‹ቅ/ሲኖዶስ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በመግለጫ ብቻ ሳይኾን በተግባርም መቃወም ይገባዋል፤ ኮሌጁ የትምህርት ተቋም እንጂ የንግድ ማእከል አይደለም፤ ኮሌጁ የግለሰቦች ሳይኾን የሕዝብ ነው፤ የምእመናንን ገንዘብ የት አደረሳችኹት? ሕገ መንግሥቱንና ፍትሐ ነገሥቱን ባታከብሩ ለመጽሐፍ ቅዱሱ ተገ!›› በሚሉ ኀይለ ቃሎች ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ የሚገኙት ደቀ መዛሙርቱ፣ ለመንፈቅ ዓመት ያህል ሲያቀርቡ የቆዩዋቸው የትምህርት አመራሩንና አስተዳደሩን የተመለከቱ ጥያቄዎቻቸው በአጣሪ ኮሚቴው የቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳቦች ተፈጻሚ በማድረግ እልባት እንዲሰጠው የማስገደጃ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን ብፁዕ አቡነ ማቴዎስን፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የኮሌጁን ውዝግብ ለመፍታት በሚከተለው አካሄድ ላይ እንዳነጋገራቸው ታውቋል፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ አሳሳቢነትና ከቋሚ ሲኖዶስ በተሰጠ መመሪያ÷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከፖሊስ ተውጣጥቶ የተቋቋመውና አምስት አባላት የሚገኙበት አጣሪ ኮሚቴ ያቀረበው ባለሦስት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ አለመተግበሩን የጠቀሱት የፖሊስ አዛዡ፣ የደቀ መዛሙርቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን በማሳሰብ ውዝግቡ አስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው ብፁዕነታቸውን መጠየቃቸው ተነግሯል፡፡
ከሐምሌ ፩ ‐ ፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ለመስጠት የታቀደው የመንፈቅ ዓመቱ የማጠቃለያ የፈተና መርሐ ግብር የማስገደጃ ርምጃዎችን መውሰድ የቀጠሉት ደቀ መዛሙርቱ ለፈተናው ላለመቀመጥ በመወሰናቸው እስከ አሁን አልተካሄደም፡፡
ከሐምሌ ፩ ቀን ጀምሮ በደቀ መዛሙርቱ ተከቦ በተያዘው የአስተዳደሩ ሕንጻ፣ የበላይ ሓላፊውን ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ ሠራተኞችና መምህራን ለመግባት እንደተከለከሉ መኾናቸው ተገልጧል፡፡ ከበባውና ቁጥጥሩ ደቀ መዛሙርቱ በመንበረ ፓትርያሪክ ቅጽር በተሰለፉበት በዛሬ ዕለትም በኮሌጁ ግቢ እንዲቆዩ በተደረጉ ደቀ መዛሙርት መቀጠሉ ተዘግቧል፡፡
ደቀ መዛሙርቱ የአስተዳደር ሕንጻውን መተላለፊያና መግቢያ በሮች በመክበብና በመዝጋት ሓላፊዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች ወደ ቢሮ እንዳይገቡ በማገድ የማስገደጃ ርምጃዎቻቸውን ማጠናከራቸው የወትሮ እልካቸውን ያናረባቸው ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ በብስጭት ራሳቸውን ስተው ወደ ቤተ ዛታ ሆስፒታል ተወስደው እንደነበር የኮሌጁ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እርሳቸው አልፈው በመቃብራቸው ላይ መሣቅ እንፈልጋለን፤›› እስከማለት የተደረሰበት ከፍተኛ ምሬትም ከደቀ መዛሙርቱ መሰማቱ ተገልጧል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ፊት ለፊት ለማነጋገር እንደሚሹ የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ፣ በተቃውሞው እንቅስቃሴ ሳቢያ ለአንድ ወር ለተራዘመው የትምህርት መርሐ ግብር ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የፈቀደው የሦስት መቶ ሺሕ ብር ተጨማሪ በጀት፣ ከታቀደለት ዓላማ ውጭ አስተዳደሩ ለውድ የቢሮ የምቾት ዕቃዎች ግዥ እያዋለው በመኾኑ ለብክነት እየተዳረገ እንዳለ አጋልጠዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቀን መደበኛ እና በማታ ተከታታይ መርሐ ግብሮች ያሠለጠናቸውን 202 ደቀ መዛሙርት ባስመረቀበት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ለምሩቃኑ ሲናገሩ፡-
‹‹ቤተ ክርስቲያን እናንተ ተከብራችኹ፣ ተሻሽላችኹ እንድትኖሩ አቅም በፈቀደ የምታደርገው ይኖራታል፡፡ እናንተም የምትሰጠውን ሥልጠና አቅም በፈቀደ ልታመሰግኑ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ኮሌጆቹን ማበረታታት፣ ማስፋፋት ይገባታል፡፡ ለእናንተ ያልኾነ፣ ከስብከተ ወንጌል የበለጠ ምን ሥራ አላት?››
ብለዋል፡፡
ቅዱስነትዎ÷ ሐምሌ ፳፪ ቀን እንደሚመረቁ የሚጠበቁት 54 ያህል የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የዓመቱ መደበኛ ዕጩ ተመራቂዎችና ሌሎች የቅድመ ምረቃ ደቀ መዛሙርትም የጠየቁትኮ ‹‹አቅም በፈቀደ›› መጠን ሊደረግ የሚችለውንና የሚገባውን ነው፡፡
 • በሌላቸው የትምህርት ማስረጃ ሳይገባቸው የአስተዳደር ሓላፊነት የያዙ ግለሰቦችን አንሥቶ የሚገባቸው ቦታ መስጠት ከአቅም በላይ አይደለም፡
 • ቤተ ክርስቲያናችን የሌላን ሳይኾን የራስዋን አስተምህሮ ለማስፋፋትና ለማጠናከር ካቋቋመችው የትምህርት ተቋም መናፍቁንና ነገረ ሠሪውን ዘላለም ረድኤትን አስወግዶ ለጥያቄ ማቅረብ ለአንጋፋው ኮሌጅ እቆረቆራለኹ ከሚል አባት የሚጠበቅ አነስተኛው ተግባር ነው፡
 • መምህራኑና ደቀ መዛሙርቱ ስለ ትምህርት አመራሩ ያቀረቧቸው ማስረጃዎችኮ ኮሌጁን የሚያስወቅሱ እንጂ የሚያስመሰግኑ አይደሉም፡፡
 • የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ለግንባታቸው ብር 350,000  እንዳወጡባቸው የገለጹትን ሁለት የመማርያ ክፍሎችኮ እየተማሩባቸው ያሉት ይዞታቸው በተዳከሙ የመማርያ ክፍሎች ያሉት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ሳይኾኑ ለአዲሶቹ ክፍሎች ኪራይ የሚከፍሉ ሌሎች ኮሌጆች የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ናቸው፡
 • ደቀ መዛሙርቱም ይላሉ÷ ‹‹የሚመዘበረው ገንዘብስ ቢኾን የሚመጣው እኛ በሰበክነው /በእኛው ጉሮሮ/፣ ካህኑ በቀደሰው አይደለምን?›› ምሩቃኑ በዲግሪ ደረጃ የሚያገኙት ደመወዝ ግን ከ900 በላይ አልጨመረም፡፡ በየዓመቱ ለ10 የኮሌጁ ምሩቃን ይመጣል ሚባለው የውጭ ትምህርት ዕድልም በጎጠኝነትና አድልዎ መጠቃቀሚያ መኾኑ ደቀ መዛሙርቱ የሚያማርሩበት ጉዳይ ነው
 • ቅዱስነትዎ በበዓለ ትንሣኤ በኮሌጁ ተገኝተው ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ቢቸግራችኹ እንዳልተቸገራችኹ፣ ቢጠማችኹ እንዳልተጠማችኹ ኹኑ›› ብለው የጥያቄያቸውን ምላሽ በትዕግሥት እንዲጠባበቁ ካሳሰቧቸው ወዲህ እንኳ እነኾ ሁለት ድፍን ወራት ተቆጠሩ፡፡ ነገር ግን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በበላይነት ለመከታተልና ለመቆጣጠር ሥልጣን ላላቸው ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅና ለጽ/ቤታቸው አልታዘዝ ከማለት አልፈው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በተግባር የሻሩትን አቡነ ጢሞቴዎስን ከሚገባው በላይ ማስታመሙን፣ መከባከቡን መርጠዋል፤ ለምን?
ቅዱስነትዎ÷ በዘመነ ፕትርክናዎ ማለዳ የተባባሰው ውዝግብ አያያዝዎ፣ ከአቡነ ጢሞቴዎስ ጋራ ካለዎት የቆየ ወዳጅነትና በፓትርያሪክ ምርጫው ወቅት ከተጫወቱት ሚና ጋራ በተገናኘ ለብዙ ሐሜት እያጋለጥዎት ነውና ከዚህ በላይ ሳያዘገዩ በአጣሪ ኮሚቴው በቀረቡትና ቅዱስነትዎም በተስማማበት የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት እልባት እንዲሰጡት ተጠይቀዋል፡፡
Source: Hara Zetewahedo
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤