Tuesday, September 17, 2013

በሐሮ ወንጪ ቅ/ገብርኤል አንድነት ገዳም ላይ የቦምብ ጥቃት ተፈጸመ

  • መነኰሳቱ ገዳሙን ለቀው እንዲወጡ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው ነው
  • አስተዳደሩ ለመነኰሳቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አልፈቀደም
  • ‹‹ከዚህ ቦታ ባትመጡ ይሻል ነበር፤ ብትውሉ አታድሩም!›› /ጥቃት ፈጻሚዎቹ/
Haro Wonchi Monasteryበደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ወንጪ ወረዳ ሐሮ ወንጪ ቀበሌ በሚገኘው የሐሮ ወንጪ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው ጳጉሜ ፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ምሽት 5፡00 ላይ ወደ ገዳሙ ቅጽር በተወረወረው ቦምብ ነው፡፡
በገዳሙ የኪዳነ ምሕረት፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ዑራኤልና ቅድስት አርሴማ ታቦታት መኖራቸውን የገለጹት የገዳሙ አበምኔት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ኣብርሃ፣ የተወረወረው ቦምብ በገዳሙ ቅጽር ውስጥ ቢፈነዳም በመነኰሳቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ለዜና ሰዎች ተናግረዋል – ‹‹ቢፈነዳም እርሱ ከልሎናልና ጉዳት አላደረሰብንም፡፡››


የአንድነት ገዳሙ አስተዳደር በቁጥር 17/2005 በቀን ፭/፲፫/፳፻፭ ለሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ ለወንጪ ወረዳ መስተዳደርና ፖሊስ ጽ/ቤት በጻፈው የድረሱልን ጥሪ÷ ከዚህ ቀደም የገዳሙን ይዞታ በመጋፋት፣ መነኰሳቱና መናንያኑ ገዳሙን ለቀው እንዲሄዱ ተደጋጋሚ ዛቻና ስድብ በማሰማት የሚታወቁ 18 ግለሰቦችን በስም ለይቶ በመዘርዘር በጥቃቱ አድራሽነት እንደሚጠረጥራቸውና በቁጥጥር ሥር ውለው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቋል፡፡ በስም ከተዘረዘሩት 18 ግለሰቦች መካከል ጌቱ ታደሰ እና መኰንን ካሳ የተባሉ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የኾኑ የቀበሌው ነዋሪዎች በዋና አስተባባሪነት ተጠቅሰዋል፡፡Haro Gedam Appeal
ደብዳቤው ‹‹ፀረ ሃይማኖት የኾኑ ግለሰቦች›› ሲል የገለጻቸውና በቡድን የሚንቀሳቀሱት እኒህ አካላት፣ በገዳሙ ላይ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ የተለያዩ ጥቃቶችን በገዳሙና በገዳማውያኑ ላይ በማድረስ ንብረት ማውደማቸውንና መነኰሳቱን ማሳደዳቸውን ጠቅሷል፡፡ ‹‹ለቀበሌው ብዙ ጊዜ አመልክተናል፤ ከአቅሜ በላይ ነው በማለቱ መፍትሔ ሳናገኝ እስከ አሁን አለን›› በማለት ከግለሰቦቹ ጥቃት ባሻገር አስተዳደራዊ በደልም እየተፈጸመ እንደሚገኝ ደብዳቤው አጋልጧል፡፡
የወረዳውና ቀበሌው ባለሥልጣናት በተገኙበት ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ከነዋሪው ጋራ በተደረገ ውይይት ሕዝቡ በቡድን እየተንቀሳቀሱ በገዳሙ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ግለሰቦችን የጠቆመ ቢኾንም ተገቢው ርምጃ ባለመወሰዱ÷ ግለሰቦቹ ገዳሙ በሚገለገልበት የውኃ ታንከርና የሶላር ቴክኖሎጂ ላይ ባደረሱት ጉዳት ሲስተሙ ለብልሽት ተደርጓል፤ መነኰሳቱ በሱባኤ ላይ ባሉበት ቀን ለቀን ወደ ገዳሙ ክልል ገብተው በይዞታው ላይ ችግኝ ከመትከል፣ የገዳሙ መውጫና መግቢያ በኾነ ቦታ ላይ አጥር ከማጠር አልተከለከሉም፤ ገዳማውያኑንም ‹‹ከዚህ ቦታ ባትመጡ ይሻል ነበር፤ ለዛሬ ብቻ ነው የምትኖሩት፤ ብትውሉ አታድሩም›› እያሉ በስልክና በአካል በተደጋጋሚ ዛቻና ስድብ ከማስፈራራት አልታቀቡም፡፡
‹‹በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዕለቱ ጨለማን ተገን በማድረግ የሚሰነዘርብን ጥቃት በዘመናዊ የጦር መሣርያ ጭምር የታገዘና በቀጣይም እየተጠናከረ እንደሚሄድ ያሳያል›› ያለው የገዳሙ አስተዳደር÷ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ከሌሊቱ 7፡40 ዘመናዊ የጦር መሣርያ ታጥቀው ወደ መናንያኑ መኖርያ የመጡት ግለሰቦቹ በመናንያኑ መኖርያዎች ላይ የድንጋይ ውርጅበኝ ማዝነባቸውን፣ ጥይት መተኰሳቸውን፣ ገዳሙን በጥበቃ እንዲያገለግሉ የተቀጠሩ የአካባቢው ተወላጆች ሥራቸውን እንዲተዉ ያልተሳካ ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውሷል፡፡
ገዳሙ ይዞታውን በሕግ ያረጋገጠበት ደብተር እንዳለው የጠቀሰው አስተዳደሩ የሹራብ ሽመና፣ የዶርና እንስሳት ርባታን ጨምሮ ራሱን የሚያግዝበት የልማት ጅምሮችና ዕቅዶች ቢኖሩትም ፍትሕ እያጡ በሚሰደዱት መነኰሳት ምክንያት ጥረቱ እየተሰናከለ ነው፤ በገዳሙ ምሥረታ ከነበሩት 15 መነኰሳት መካከልም ጸንተው የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
ወረዳው በተለይ ከ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ ከገዳሙ ለሚቀርቡለት አቤቱታዎች ሁልጊዜ ተስፋ ይሰጠናል እንጂ የተጨበጠ ነገር አላስገኘልንም፤ ትኩረትም አይሰጡትም ያለው አስተዳደሩ÷ ‹‹መንግሥት ለሃይማኖታችንና ለገዳማችን ልማት የማይተኙልንን ፀረ ሃይማኖት የኾኑ ግለሰቦች››በአስቸኳይ በቁጥጥር ሥር እንዲያውልና ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድባቸው ጠይቋል፡፡
የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ መረጃው እንዲደርሰው ሲደረግ የቆየ በመኾኑ ‹‹ማመልከቻ አስገቡ›› ከሚለው ቸልተኝነቱ ተላቆ ገዳማውያኑ አስፈላጊውን ሕጋዊና አስተዳደራዊ እገዛ እንዲያገኙ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡
የሐሮ ወንጪ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም መቋቋም በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም መልአከ ሰላም አባ ገብረ ማርያም ኣብርሃ በተባሉ መነኮስ የተጀመረ ሲኾን የተገደመው ደግሞ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ሀ/ስብከቱን (ደቡብ ምዕራብ ሸዋን) ከምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ጋራ ደርበው በሚያስተዳድሩበት በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. እንደኾነ የገዳሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
*                        *                      *
መንሥኤው አክራሪነት ይኹን ጥቅመኝነት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በበርካታ መንገዶች እየተፈጸመ ለሚገኘው ግልጽ ጥቃትና አስተዳደራዊበደል የወንጪ ሐሮ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም ልዩ አይደለም፡፡ ለመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ፴እና ፴፩ መደበኛ ስብሰባ ላይ በቀረቡ የ፳፻፬ ዓ.ም. እና ፳፻፭ ዓ.ም. የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች እንደሚያስረዱት÷ እምነታችኹን ለውጡ እያሉ ማወክ፤ የማንነት/ባህል ወረራ፣ የጠብ አጫሪነት፣ የቅርስ ዝርፊያና የታቀደ ቃጠሎ አለመገታት፣ ማስረጃ በሌለው የይገባናል ጥያቄ ይዞታን መንጠቅ፣ ለሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ሥራና ለልማት የቦታ ጥያቄ ምላሽ አለመስጠት፣ በፍትሕ አካል የተሰጠን ውሳኔ ፖሊስ አለማስፈጸም በየጊዜው እየገጠሙን ያሉ ችግሮቻችን ናቸው፡፡
‹‹የልዩ እምነት ተከታይ የኾኑ ባለሥልጣናት በመንግሥት ስም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርጉት ተጽዕኖና አድልዎ›› በዓመቱ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል በዋናነት ያስቀመጠው የ፳፻፭ ዓ.ም. የአጠቃላይ ጉባኤው ሪፖርት፣ በሲዳማ ሀ/ስብከት ሥር የወንዶ ገነት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር ፕሮቴስታንቶች በግድ እየተቀበሩበት መቸገሩን ይጠቅሳል፡፡ ይኹንና ቤተ ክርስቲያን ከሥር ፍ/ቤት እስከ ሰበር ድረስ ተከራክራ መብቷን ብታስከብርም የፍርድ ውሳኔ የሚያስፈጽም አካል በመጥፋቱ ጉዳዩ ወደ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዲሄድ ወይም የክልሉ ፖሊስ ባለመፈጸሙ በሕግ እንዲጠየቅ አለመደረጉን ሪፖርቱ ገልጧል፡፡ በደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ ሲጠየቅ በጎ ምላሽ አልተገኘም፤ የልማት ቦታም ያለሊዝ ሊፈቀድ አልቻለም፡፡ በምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት አራት አብያተ ክርስቲያን በመናፍቃን ተዘርፈው እስከ አሁን የፍርድ ቤት አላገኙም፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ የተጠቃለለው የ፳፻፬ ዓ.ም. የአህጉረ ስብከቱ ሪፖርት በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በሀዲያና ሥልጢ አህጉረ ስብከትየቤተ ክርስቲያን ይዞታ በሌሎች እንደተነጠቀና የመንግሥት ሓላፊዎች ለቤተ ክርስቲያን ፍትሕ እንደነፈጉ፣ ለልማት ሥራ፣ ለግንባታ ፈቃድ መስተዳድሮቹ በቂ ትብብር እንደማያደርጉ ይገልጻል፡፡ በደቡብ ኦሞ ሀ/ስብከት የሦስት አብያተ ክርስቲያን ምእመናን ሰፈር በኢአማንያን በመቃጠሉ ምእመናን አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡
በደቡብ ምሥራቅ መቐለ ሀ/ስብከት ከካህናት ይኹን ከምእመናን የቅ/ሲኖዶስ መመሪያ ተላልፈውና የቃለ ዐዋዲ ድንጋጌ ጥሰው ሲገኙ ለሚሰጣቸው የቅጣት ውሳኔ አፈጻጸም ፖሊስ ከፍ/ቤት ትእዛዝ ካልተሰጠኝ አላስፈጽምም ብሏል፡፡ በጅማ ሀ/ስብከት እምነታችሁን ለውጡ እያሉ ምእመናንን ማወክ፣ በሰሜን ወሎ እና በመተከል አህጉረ ስብከት የፕሮቴስታንቶች ትንኮሳና የባህል ወረራ፣ የተሐድሶ መናፍቃን በጥቅም ያስከዷቸው ‹ካህናት› ተመልሰው የአገልግሎት ዕንቅፋት መፍጠራቸው በሪፖርቱ ዝርዝር ተጠቅሷል፡፡
በየአህጉረ ስብከቱ በገዳም፣ ደብርና ገጠር ሥሪት የሚገኙ አብያተ ክርስቲያን ይዞታቸውን በባለቤትነት መታወቂያ ካርታ ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረትና ያስገኙት ውጤት የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ይዞታን በባለቤትነት መታወቂያ ካርታ ማረጋገጡ አብያተ ክርስቲያኑ ከሰበካ ጉባኤ ዓመታዊ አስተዋፅኦ፣ ከሙዳይ ምጽዋትና ስእለት ገቢዎች ባሻገር ማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸውና መንፈሳዊ አገልግሎቱን የሚያጠናክሩ የራስ አገዝ ልማት እንቅስቃሴዎችንም ለማድረግ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ ይኹንና በአንዳንድ አጋጣሚ በጉልሕ እንደሚስተዋለው በመንግሥት መዋቅር ባሉና የእነርሱን ብልሹ አሠራር ተገን ባደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች በየጊዜው የሚፈጸመውን ግልጽ ጥቃትና አስተዳደራዊ አድልዎ ለመግታትና በብቃት ለመመከት ቅ/ሲኖዶስ በጥብቅ ሊመክርበትና የሚመለከተውን የመንግሥት አካልም በማትጋት የአገልጋዮችንና ምእመናንን መብት ሊያስከብር ይገባል፡፡
በሰላምና ልማት ጉዳዮች ላይ አብሮ መሥራት፣ የዜጎችን ሰላም፣ ደኅንነት፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዋስትና ማረጋገጥ የመንግሥት ግዴታ እንደኾነ የሚገልጹ መንግሥታዊ ሰነዶች÷ መንግሥታዊ አገልግሎትን የሚሰጥ ማንኛውም ሓላፊ ይኹን ሠራተኛ ተግባሩን ከራሱም እምነት ጭምር ገለልተኛ በኾነና በእኩልነት መንገድ መካሄዱን ማረጋገጥ እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡ ሓላፊዎቹና ሠራተኞቹ ገለልተኝነትን ለድርድር ከሚያቀርቡ ስሕተቶችን መጽዳታቸውን፣ የአንዱ ወይም የሌላው እምነት ውግንና እንዳላቸውና አድልዎ ለመፈጸም የተዘጋጁ ከሚያስመስሏቸው አቀራረቦች ራሳቸውን መጠበቃቸውን፣ የሕዝቡን ከፍተኛ አመኔታ ባተረፈ አኳኋን ሥራቸውን ማከናወናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡
በተጨባጭ ሃይማኖታዊ ውግንና የሚያሳዩ አመራሮች እንዲሁም ከጥንቃቄ ጉድለት የሃይማኖት አድልዎ እንዳለ አስመስለው የሚያሳዩ ድርጊቶች/ዝንባሌዎች በአፋጣኝ መስተካከል እንደሚኖርባቸው የሚያሳስቡት ጽሑፎቹ፣ ‹‹ካልተስተካከሉም ከመንግሥት ሓላፊነት ተነሥተው የሃይማኖት መምህርነትን ወደሚቀጥሉበት አቅጣጫ ማመላከት ይገባል› በማለት የመንግሥትን አቋ ያስቀምጣሉ፡፡YeDebre Tabor Metmeke Melkot Debir
በቀበሌ ይኹን በወረዳ የመስተዳድሩ አንዳንድ ባለሥልጣናት አይዞህ ባይነትና ሽፋን ያላቸው የሚመስሉትና የሐሮ ወንጪ ቅ/ገብርኤል አንድነት ገዳም ንብረትን በተደጋጋሚ ከማውደምና መነኰሳቱን ከማሳደድ አልፈው የቦምብ ጥቃት ለማድረስ የተደፋፈሩት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የኾኑ ግለሰቦች፣ መንግሥት በጽሑፉ ያተተውን የፀረ አክራሪነት አቋምና እንቅስቃሴ በግልጽ የሚፃረሩ ናቸው፤ በድብቅም በገሃድም የሚደግፏቸው ባለሥልጣናትም ከጥቃት አድራሾቹ ጋራ ‹‹ዘይትና ሞተር ኾነው የሚሠሩ››፣ ዋጋ የሚያስከፍሉ እንጂ በአስተዳደር ሓላፊነታቸው የሰላምና መረጋጋት ምንጭ ሊኾኑ አይችሉም፡፡
ስለዚህም አፋጣኝ የማስተካከያ ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ችግሩ በየደረጃውና በወቅቱ እልባት እንዲሰጠው ከማድረግ ባሻገር ተቋማዊ ህልውናዋንና ነጻነቷን በሚያስከብር አኳኋን መሠረታዊ መፍትሔ እንዲያገኝ በከፍተኛ አመራሯ አማካይነት መንቀሳቀስ ይገባታል፡፡ ሳይዘገይ ዛሬውኑ!
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

  1. አባቶች እባካችሁ ተንቀሳቀሱ። ልጃች ይጮሐሉ !

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤