Saturday, September 28, 2013

ነገረ ወልድ

ነገረ፡ ወልድ።
በቅዱስ ኤፍሬም። ፫፻፶ ዓ. ም.  


ቸሩ እግዚአብሔር “አብራም” ብሎ ጠራው።
ከዘመዶችህ ተለይና
እኔ ወደማሳይህ ምድር ተሰደድ አለው።

አብራም ከካራን ወጣ
በ፸፭ አመቱ ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደከነዓን ወረደ።
ከዘመዶቹም ካገሩም ይልቅ
ልቡ እግዚአብሔርን ወደደ።

ከካራን ሲወጣ
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሊጠብቅ
“ሀ” ብሎ ጀመረ።
እግዚአብሔርም አየ፡ ትእዛዝ ጨመረ።
አረጋዊው አብራም
በብርቱ ፈተናወች ታጠረ።


ወደአዜብም አለፈ።
በረሃብ ፈተና ተነደፈ።
በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ
ወደ ግብፅም ወረደ።
ፈርኦን ውድዋን ሦራ ወደቤቱ ወሰደ።
እግዚአብሔርም አየ።
በፈርኦን ቤት መቅሰፍትን አወረደ።
አብራም ሦራንና ከብቶቹን ይዞ
ከግብጽ ወጣ።
የእግዚአብሔርም በረከት ወደሱ መጣ።
በከብት። በብርና በወርቅ እጅግ በለጸገ።
የአምላኩን ስም ለመጥራት ተጋ።
በመንፈስም አደገ።

ዘመን ወጥቶ ዘመን ደረሰ።
እርጅናም ወደአብራም ቤት ገሰገሰ።
በዚህም ምክንያት
ልጅ ወልዶ የማቀፍ ልጅነት
ባለቤቱ ሦራ አለፈባት።
እርጅና ሲገባ።
ልጅነት በርግጥ አለቀ።
ነገር ግን ለእግዚአብሔር ያላቸው ፍቅር
እንደ እንቡጥ አበባ ፈነደቀ።
የውርጭ የሀሩርና የጊዜ ብዛት
ሰውነታቸውን ቢጎዳውም።
በእግዚአብሔር ያላቸውን ተስፋ

እርጅናም ሆነ ክሳት አልዳሰሰውም።
እግዚአብሔርም ስም ሰጣቸው።
እሱን አብርሃም እሷን ሣራ አላቸው።

የእግዚአብሔር መልዕክት
ካዛፏ ሥር ከድንኳኑ አጠገብ መጣ።
ለአብርሃምም የምሥራች አበሰረ።
የዛሬ አመት
ሣራ ልጅ ታገኛለች ብሎ ተናገረ።

ሣራም በድንኳኑ ጀርባ ሳለች።
መልዕክቱን ሰምታ ሳቀች።
እኔም አርጅቻለሁ። ጌታየም ሸምግሏል።
በውኑ ልጅ
በዚህ እድሜያችን እንዴት ይቻላል?
ብላ በልቧ አሰበች።

እግዚአብሔርም
“ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን” ስትል
ሣራ ለምን ሳቀች ብሎ
አብርሃምን ጠየቀው።
መልሶም
“በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው አለን? አለው።

በእምነታቸው ፅናትም
በእርጅና ታይቶ የማይታወቅ ፀጋ።
ወደ ሣራ ተጠጋ።
በእርጅናቸው ተአምር ከፈጣሪ ወረደ።
የጌታው አምሳል ይስሃቅ ተወለደ።

በርጅና የተኛ ማህፀን አጎልብቶ።
በእድሜ ብዛት የደረቀ ጡት ወተት አቁቶ።
እንዴት ህፃን ወልዶ ሊመግብ ይችላል?
እግዚአብሔር በውን ተአምሩን ሠራ።
ከድንኳኑ ጀርባ በሳቀችው ሣራ።

በአምሳሉም
ድንግል ያለወንድ ወልዳ።
የሰውን ልጅ መገበችው ምግብ፡ መድኃኒት
የሚያነፃ የሚፈውስ
ነፃ የሚያወጣ ከአዳም እዳ።

ኤልሳቤጥ
በእርጅና በፀነሰች በስድስት ወር።
መልአኩ ገብርኤል
ወደናዝሬት መጥቶ ዜና ሊያበስር።
ድንግል ማርያምን እንዲህ አላት፦
ደስ ይበልሽ።
አንቹ ፀጋ የሞላብሽ።
ከሴቶች መካከል ተለይተሽ።
አንቺ የተባረክሽ ነሽ።
በእግዚአብሔር ፊት
አግኝተሻልና ፀጋ።
ወንድ ልጅ ትፀንሻለሽ።
የዳዊትን ዙፋን የሚቀበል
በአዳም ዘር ላይ
የወደቀውን ጨለማ የሚያነጋ።  

ማርያምም ደነገጠች።
ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው አለች።
ወንድ ካጠገቤ የማይደርስ ድንግል እያለሁ።
እንዴት ልጅ መውለድ እችላለሁ?
ብትል
መልአኩም መልሶ
“በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?” ቢላት
“እንደቃልህ ይሁንልኝ” ብላ ደስ ተሰኘች።
በዘጠነኛ ወሩ
መድኃኒታችን ኢየሱስን ወለደች።

ተስፋ በሌለበት ተስፋን ያወረደ።
ይስሃቅን ለሣራ የሰጠው ጌታ
እሱ እራሱ ከድንግል ተወለደ።

የአሮጊትዋ የሣራ ጡት።
እንደጅረት አፍልቆ ወተት
ይስሃቅን እንደመገበ።
እነሆ ከድንግልዋ ጡት፡
የፈለቀው ወተት
ከዳር እስከዳር የፍጥረታትን መጋቢ መገበ።

ማን ይመስክር ለምድር ሰዎች።
ሣራ በእርጅና
ማርያም በድንግልና እንዳጠባች?

ለካስ ሣራ የሳቀችው አልሳኩም ስትል።
ለይስሃቅ መወለድ ሳይሆን
ከማርያም ለሚወለደው ኖሯል።

ዮኃንስ በኤልሳቤጥ ማህፀን ውስጥ ሆኖ
በደስታ እንደዘለለው።
የሣራ ሳቅ
የደስታ መግለጫ
የየምሥራች እልልታ ነው።

ትንሹ ልጅ ይስሃቅ ጉልምስናን አነሳ።
ሰውነቱ ለግላጋ። አመሉ ሸጋ።
ሆኖ ወላጆቹን አሳሳ።
ይስሃቅ ሲጫወት እያየ።
አብርሃም ደስታን ገበየ።
ከእለት እለት ስለልጁ ሲያስብ
በልጁም ሲደሰት።
ድንገት ትልቅ ፈተና መጣበት።

እግዚአብሔር “አብርሃም” ብሎ ጠራው።
ትእዛዝም አዘዘው።
የምትወደውን አንድ ልጅህን
ይስሃቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ውረድ።
በማሳይህም ተራራ
መስዋእት አድርገህ ሰዋው አለው።

በልጁ ፍቅር የተያዘው የአብርሃም ሥጋ።
እንደጦር በሰላው
በእግዚአብሔር ትእዛዝ ተወጋ።
ሥጋና ነፍስ ተፋጠጡ።
ትግል ገጥመው ተናኮሩ።
ማን ይበልጣል?
የሚወደው ልጁ ይስሃቅ
ወይስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማክበሩ?

እናንተስ ተመልካቾች።
ምን ትላላችሁ?
የትኛውን ታስበልጣላችሁ
ከአብራካችሁ የወጣውን ልጅ መኖር
ወይስ የእግዚአብሔርን ፍቅር?

በመጀመሪያ “አብርሃም” ብሎ ሲጠራው።
ዘርህን አበዛዋለሁ ያለው ትዝ ብሎት፡
ጠበቀ መልካሙን ነገር በጉጉት።
ይመጣል ብሎ የደስታ ድግስ።
የእርጅና በረከት ተድላና ሞገስ።
ነገር ግን የመጣው ድግስ።
ሳይሆን ተድላና ሞገስ።
ልብን የሚበሳ ጦር።
የሚያንቀጠቅጥ ትእዛዝ ነበር።

አባት የሆናችሁ እስኪ አስቡት።
“የምትወደውን ልጅህን” የሚል ድግስ።
አባት ለልጁ ያለውን ፍቅር
እንዴት እንደሚቀሰቅስ።
አንዱን ልጅህን በሚለው ቃል።
አብርሃም ለልጁ ያለው ፍቅር
ሆነበት ሥጋውን የሚያቃጥል።
አባት የልጁን መታረድ መልእክት ሲሰማ።
ምን ይጨብጥ ምን ይዋጠው።
ያውም እሱ እራሱ አራጅ ሆኖ ሊፈጽመው።

እስኪ እንመስክር ከአዳም ልጆች ውስጥ ልጁን ወደመስዋእትነት ተራራ ከማድረስ።
የማይመርጥ ማን ነው ትእዛዙን ማፍረስ?

ወይስ አምላኩን
መልሶ የማይጠይቅ ማን ነው እንዲህ ብሎ፦
“ለምን ፈጣሪ?
ለምን አስቸጋሪ ትእዛዝ አዘዝክ?
እንደዚህስ ካደረግህ።
መጀመሪያ ለምን እኔን ባረክህ?
አባት ሆኘ ያቀፍኩት በእርጅና ክንዴ።
ልጅ ሰጥተህ፤ ልጅ ገዳይ ልታረገኝ ነበር እንዴ?
የሚጣፍጠውን ፀጋ የሰጠኸኝ።
ኖሯል እንዴ አግኝቶ ያጣ እያሉ
አህዛብ እንዲሳለቁብኝ?
ልጅ ታገኛለህ ያልከኝ ከደጄ።
እንድቆርጠው ኖሯል እንዴ እጄን በእጄ?
ዘርህን እንደከዋከብት አበዛዋለሁ እያልክ።
ምነው አንዱን ይስሃቅ ልትነሳኝ አሰብክ?”

ነገር ግን ብፁኡ አብርሃም።
እንዲህ ያለ አዳችም አቤቱታ አላሰማም።
ይልቁንም
ትእዛዙን እንዲያከናውን ፈቀደ።
ስለዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር
በውስጡ እንደ እሳት ነደደ።
የታዘዘውን ሳያቅማማ ይፈጽም ዘንድ።
አህያውን ጭኖ ጀመረ የተራራውን መንገድ።
ትእዛዙን ለመፈፀም።
አማካሪም አልፈለገም።
ሄዋን አዳምን ያማከረችው ትዝ አለውና
የታዘዘውን ለሣራ ሊያማክራት አልፈቀደም።
ትእዛዙን ከፈፀምኩት በኋላ።
በልጇም በኔም ትዘን ብሎ አሰበና።
ሳያማክራት ወደቀጠሮው ቦታ አቀና።

የፈራው ቢያማክራት
እንዲህ ትለኛለች ብሎ ነው፦

“አብርሃም ልጅህን አድን።
የምድር መሳቂያ እንዳትሆን።
በእርጅና ያፈራነውን አንዱን ፍሬ።
በእጅህ እንዳትቆርጠው ዛሬ።
የመደገፊያ ምርኩዛችን እንዳትሰብር።
አይናችን እንዳታጠፋ።
መታሰቢያችን እንዳታስቀር።
እንደበግ እንዳታርደው ጠቦታችን።
በሃዘን እንዳይቀየር ደስታችን።
እሱ ከሌለ አብሮን ከገበታ ማን ይቀርባል።
እናቴስ ብሎ ማን ይጠራኛል።
ማንስ ይጦረናል?
እስኪ ተመልከት ውበቱን።
የልጅነት አንደበቱን።
እንክዋን አንተ አባቱ።
በጁ ቢያገኘው ይራራል ጠላቱ።
የእርጅና ምርኩዛችን እንዳትሰብር።
የዘር ሃረግ መውረጃ ገመዱን እንዳታሳጥር።
በልጄ አንገት ላይ ከምታሳርፍ ቢላዋ።
በኔ ላይ አርገዉና
የሱን ሞት ሳላይ እኔው በክብሬ ልሰዋ።
አንድ ላይ ይሁን ድግሳችን።
የመታሰቢያ ቀናችን።
ተው እንዳታደርገው።
ጌታየ አብርሃም ገዳይ።
ልጄ ይስሃቅ ተገዳይ
ሆነው እንዳላይ።”

ብታውቅ
እንዲህ ያለ ምክር ብታደርግስ ብሎ ፈርቶ።
ሚስጢሩን ለሣራ አልነገራትም ከቶ።

ወደ ተራራው ሲያቀና ማልዶ።
ይስሃቅን አሸከመው
የመስዋእትነቱን እንጨት ማገዶ።
ልክ መዳህኒታችን እንደተሸከመው።
ይስሃቅም ተሸክሞ ጀመረ ጉዞ።
ልቡን ለአባቱ ትቶ። ሸክሙን እሱ ራሱ ይዞ።
ይስሃቅ ተራራውን ወጣው ከሸክም ጋር።
እንደጠቦት በግ በመሰዊያው ሊታረድ።
ክርስቶስም ተራራውን ወጣው ከሸክም ጋር።
እንደጠቦት በግ በቀራንዮ ሊታረድ።

ልብ አድርጉ፦
ቢላዋውን ስታስቡ ጎራዴውን።
መሰዊያውን ስታስቡ ቀራንዮን።
እንጨቱን ስታስቡ መስቀሉን።
እሳቱን ስታስቡ ፍቅሩን አትዘንጉ።

በዛፉ ላይ ያለውን በግ ተመልከቱ።
እንደተሰቀለ በቀንዱ።
በመስቀሉ ላይ ያለውን
ክርስቶስን ተመልከቱ።
እጁ እነድተቸነከረ ተዘርግቶ ክንዱ።

በጉን በቀንዱ ያንጠለጠለው ዛፍ
ስሙ ይቅርታ ነው።
ለጊዜው በሱ የዳነው ይስሃቅ ነው።
ኢየሱስ በተሰቀለበት በመስቀሉ።
ይቅርታን አገኘ ኃጥእ በሙሉ።
ለዓለም የህይወት ምንጭ ከመስቀሉ ፈለቀ።
ጨለማው ሞት በብርሃን ተፋቀ።

ማረጃውን ቢላዋና እንጨቱን።
መስዋእት ማንደጃ እሳቱን።
ተሸክሞ በጀርባው።
ይስሃቅ አባቱን እንዲህ አለው፦

“አባባ
እንጨቱን ይዣለሁ። በእጄ አለ።
ቢላዋም ይዣለሁ። በእጄ አለ።
እሳቱን ይዣለሁ። በእጄ አለ።
የሚሰዋ በግ የታለ?”

የልጁ የዋህ አንደበት።
ለአባት እንደጦር ሆነበት።
አብርሃም እንደገና በልጅ አንደበት ተፈተነ።
ልቡ
የልጅና የፈጣሪ ፍቅር ጦርነት አውድማ ሆነ።

አብርሃም እንዴት አያንባ።
ሊሰዋው የሚወስደው ልጁ
አይኖቹን እያንከባለለ ሲል “አባባ”
እንደማር የሚጣፍጠውን
የልጁን ድምጽ እየሰማ።
ፈተናውን ተቋቋመው ሳያቅማማ።

ለልጁም መለሰለት እንዲህ ሲል፦
“ልጄ ሆይ!
በጉን እግዚአብሔር ያቀርባል።”

የአብርሃም መልስ ትንቢት ሆነ።
እግዚአብሔር በሚያቀርበው በግ አለም ዳነ።

ከቀጠሮው ቦታም እንደደረሰ።
በፍጥነት መሰዊያውን ቀለሰ።
ካራው ተዘጋጀ እሳቱም ቀረበ።
በእንጨቱ ላይ ተጋድሞ
ይስሃቅ በገመድ ተሸበበ።
እንዳሻው እንዲያደርገው
ልጅ ላባቱ ራሱን ሰጠ።
አባት ካራዉን በጁ ይዞ
ወደሰማይ አንጋጠጠ።
ማን ይደነቅ የማን ይበልጣል?
ለፈጣሪ ፍቅር ሲል
በሚወደው ልጁ ላይ ካራ ያሳረፈ።
ወይስ ያባቱን ትእዛዝ ሊፈጽም
ህይወቱን ላባቱ ያሳለፈ?

አብርሃም ካራውን በልጁ ላይ አነጣጠረ።
አንገቱን ሊያርድ ጀመረ።
በድንገት የመጣ ድምጽ
ከሰማየ ሰማያት አስተጋባ።
“አብርሃም፡ አብርሃም ይስሃቅን እንዳትነካ”
በማለት
የእግዚአብሐር መልአክ
ቀጥሎም እንዲህ አለ፦
“እግዚአብሐርን እንደምትፈራ
አውቄያለሁ በእውነት።
ለኔ ስትል የምትወደውን ልጅ
አቀረብከው ልታደርገው መስዋእት።
በይቅርታ ዛፍ ላይ ሙክት ይሄውና።
እሱን ወስደህ ሰዋው ይስሃቅን ፍታና።
ያቀረብከው መስዋእት።
ቀርቦ በእግዚአብሔር ፊት
ስላገኘ ተቀባይነት።
ዝማሬ ቀልጧል በመላእክት።
እባርክሃለሁ በበረከት።
አበዛሃለሁ እንደከዋክብት።
ዘርህ በምድር ይቅና።
ትእዛዜን ፈጽመሃልና።”
ብሎ ባረከ አብርሃምን።
ትውልድ ሃረግ ዘራ ዘሩን።

እግዚአብሔር በውን የሚወደው።
ተቃጥሎ የሞተ መስዋእት ሳይሆን
የሚታዘዝ ቅን ልብን ነው።
አብርሃም በፈተና መቸገሩ።
አይደለም የዚህ ፈተና ሚስጢሩ።
መልእክቱ የዚህ ፈተና።
አንድ ሁለት ተብሎ መች ይቆጠርና።
በዚህ ምድር ያለ ምንም ቢሆን ምንም።
የልጅም ፍቅር ቢሆን።
ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚበልጥ
አንድም ነገር የለም።

አብርሃም አገኘ በረከትን።
በመስዋእቱ ክህነትን፡
በምሳሌው ነቢይነትን።
እግዚአብሔርም በበኩሉ
ልጁን ሰጥቶ የአዳምን ልጅ ለማዳን።
ምሳሌ በይስሃቅ ሠራ
ለአብርሃም ገባ ቃልኪዳን።
ድንግል አትወልድም ብለው ለማያምኑት።
ይሆን ዘንድ ምልክት።
የበግ ዘር ከሌለበት ባዶ ተራራ
ድቅን አለ ሙክት።
በጉ በዛፉ እንደታሰረ።
አንድየ ልጅ ክርስቶስ
በመስቀል ተቸነከረ።
ክርስቶስም እንዳለው፦
“አብርሃም ቀኔን ሊያይ ልቡ ጠየቀ።
አየም ፈነደቀ።”

ትንቢቱን በምሳሌ የወጠነው።
በመጽሐፍ ያሰፈረው።
መጥቶም የፈፀመው።
ፈፅሞም በግርማ ያረገው።
ይመስገን ፈጣሪ እሱ ነው።
በማናቸውም ቦታ።
ጧትም ሆነ ማታ።
አብ። ወልድ። መንፈስቅዱስ ብለን
እናቅርብ ምስጋና።
ምሳሌም። አዳኝም። ፈራጅም እሱ ነውና።
አሜን።

2 comments:

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤