Sunday, September 8, 2013

የአክራሪነት ውንጀላ የተሰነዘረበት ማኅበረ ቅዱሳን ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተቃውሞ ሪፖርት/ክሥ ማቅረቡ ተጠቆመ

 • አክራሪነት ውንጀላው በ‹‹አገር አቀፍ የሰላም ዕሴት ማጎልበቻ ጉባኤ›› ወቅት ማኅበሩንና አገልግሎቱን ከተቀበረ ፈንጂ ጋራ ያመሳሰለውና በአቶ ስብሓት ነጋ አጽንዖት የተሰጠው የአባ ዮናስ ጥቆማ ነው፤ ጥቆማው የተሰማው ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ‹‹የአክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርእስ ያቀረቡትን ጽሑፍ ተከትሎ አቶ በረከት ስምዖን በመሩት የውይይት መድረክ ነው፡፡ 
ማኅበረ ቅዱሳን
ማኅበረ ቅዱሳን
 • ከሃላባ ወረዳ ቤተ ክህነት ተወክለው የመጡት አባ ዮናስ÷ ማኅበሩን በስም ለይተው ባይጠቅሱም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ለቤተ ክርስቲያን ልጆች የሚሰጠው ሥልጠና ትውልዱን ‹አክራሪነትን ያደርጋል› በማለት፣ በእነርሱም በኩል የመንግሥትንና የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር ይካሄዳል ያሉት እንቅስቃሴ ‹‹በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተቀበረ ትልቁ የአክራሪነት ፈንጂ›› እንደኾነ ጠቅሰው ማኅበሩን ቅ/ሲኖዶስ አጽድቆ በሰጠው የአገልግሎት ድርሻው በመጠቆም በከፍተኛ ደረጃ ወንጅለዋል፡፡
 • ለአባ ዮናስ በቂምና ጥላቻ የተሞላ ውንጀላ ምላሽ ለመስጠት ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው ያላገኙ የውይይቱ ተሳታፊ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከስብሰባው በኋላ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፍተኛ ሓላፊዎች በተለይ ከሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ጋራ ከፍተኛ ሙግት ገጥመው ታይተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና የሰጠችውና በመዋቅሯ የምትቆጣጠረው ማኅበርና አገልግሎቱ ከአክራሪነት ጋራ መያያዙና ትርጉሙ በቀላሉ እንደማይታይ ያመለከቱት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ሚኒስቴሩ ማኅበሩን ጠርቶ ለማነጋገርና ለመመካከር ሞክሮ እንደኾነ ጠይቀዋል፤ ጉዳዩንም መንበረ ፓትርያርኩ በጥብቅ ይዞ እንደሚነጋገርበት አሳስበዋቸዋል ተብሏል፡፡

 • የአባ ዮናስን ውንጀላና አቶ ስብሃት በውንጀላው ላይ ተመሥርተው ለሚኒስትሩ የሰጡትን አስተያየት ያጸደቀ የሚመስሉት ዶ/ር ሽፈራው ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ አቤቱታ በሰጡት ምላሽ ‹‹ማስረጃ›› እንዳላቸው መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ የዜና ምንጩ እንዳመለከተው ዶ/ር ሽፈራው በማስረጃነት የጠቀሱት ማኅበረ ቅዱሳን እንደተቋም ሳይኾን የማኅበሩ አባላትና አገልጋዮች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች በግል ፕሬሶች፣ በኢሳት ቴሊቪዥንና በቪ.ኦ.ኤ ሬዲዮ ከዋልድባ ገዳም፣ ከዕርቀ ሰላም እና ከ፮ው ፓትርያርክ ምርጫ ጋራ በተያያዘ ያሰፈሯቸውን ጽሑፎችና የሰጧቸውን ቃለ ምልልሶች ነው፡፡
 • በዚህ ሳምንት ከወጣው ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ጋራ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ሽፈራው ‹‹በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሽፋን›› ይታያል ያሉት አክራሪነትና ጽንፈኝነት ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰጡትን ምላሽ ያጠናከረ ነው – ‹‹አክራሪነትና ሽብርተኝነት በፍልስፍና መንገድ ተፈልጎ የሚታይ ሳይኾን በየዐደባባዩ በግላጭ የሚታይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚሄዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ይህን ድርጊታቸውን በአካል ይፈጽማሉ፤ በመጽሔታቸው፣ በጋዜጣቸው፣ በድረ ገጾቻቸው ያስነብባሉ፡፡ አንዳንድ ጋዜጦች በየቀኑ ከሚተላለፉ የአሸባሪ ጣቢያዎች ናቸው ተብለው ከሚታወቁ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋራ መግለጫ ሲሰጡ ነው የሚውሉት፡፡ ብዙ የተደበቀ ነገር አይደለም፡፡ ከኢሳት ቴሌቪዥን፣ ከመጽሔቶችና ሬዲዮኖች ጋራ አብረው ነው የሚሠሩት፡፡ በዚህ ዙሪያ ወጣቶች እና ሴቶችንም አደራጅተው የሚንቀሳቀሱበት ኹኔታ አለ፡፡ ስለዚህ የተደበቀ ነገር የለም፡፡››
 • ማኅበረ ቅዱሳን መንበረ ፓትርያሪኩን በመወከል በስብሰባው ከተካፈሉ ኀምሳ ያህል ልኡካን መካከል እንደ ጽ/ቤት አልተጋበዘም፡፡ ይኹንና በስብሰባው ከተሳተፉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ከተነጋገረ በኋላ የማኅበሩ ጽ/ቤት ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተቃውሞ ክሥ/ሪፖርት ማቅረቡ ተጠቁሟል፡፡ ጽ/ቤቱ ጉዳዩን ለቋሚ ሲኖዶስ በአጀንዳነት አቅርቦ የበኩሉን አቋምና ርምጃ እንደሚወስድ ተመልክቷል፡፡
 • በሌላ በኩል ‹‹የፀረ አክራሪነት ትግል የወቅቱ ኹኔታ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች›› በሚል ርእስ በግንቦት ወር ፳፻፭ ዓ.ም በመንግሥት አካል መዘጋጀቱ የተገለጸ አንድ ሰነድ በማኅበረ ቅዱሳን መሽገዋል ያላቸው የትምክህት ኀይሎች፣ ‹‹ጽንፈኛ የፖሊቲካ ኀይሎች አካል በመኾን በጋዜጣና በመጽሔት ሕዝቡን ለዐመፅና ሁከት ለማነሣሣት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ በስደተኛው ሲኖዶስ በመሸፈንም እያንዳንዱ ሌላ ቀን ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሌለች አስመስለው የግንቦት ሰባትን ከበሮ ሲመቱ ከርመዋል›› በማለት መተቸቱ ተገልጧል፡፡ 
 • ይኸው ሰነድ ‹‹በ፮ው የኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ምርጫ ወቅት የታዩ አንዳንድ ዝንባሌዎች ከውስጥም ይኹን ከአገር ውጭ ያሉትን የአክራሪነት አሰላለፎች በግልጽ ያመለከተ ነበር›› በማለት በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ሽፋን ይንቀሳቀሳሉ ያላቸው ማኅበራት ‹‹የአክራሪነትና የከሰሩ ፖሊቲከኞች ምሽግ ኾነው ማገልገል ከጀመሩ ውለው አድረዋል›› በማለት ይከሣቸዋል፡፡
 • በፓትርያርክ ምርጫው ‹‹የየራሳቸውን ፍላጎት የሚያሳኩ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍና አሜሪካ ከሚገኘው ስደተኛው ሲኖዶስ ከሚባለው ቡድን ጋራ የዕርቅ ኹኔታ በሚል እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርጉ›› ሰነዱ ጠቅሷል፡፡ አያይዞም ‹‹ራሳቸው በፈጠሩት ትርምስ መንግሥት እጁን አስገብቷል ወዘተ እያሉ ኦርቶዶክስ አማኞችን ለማወናበድ ይሞክራሉ፡፡ በራሳችንም እንደሌላቸው ኃይል ሰልፍ ልንወጣ ይገባል በሚል የመፅና የሁከት ቅስቀሳ ለማድረግ ይፈልጋሉ፤›› ሲል ገልጧል፡፡
 • በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው የአሜሪካ ሲኖዶስ የ፮ውን ፓትርያርክ ምርጫ በማውገዝ መግለጫ መስጠቱን ያስታወሰው ሰነዱ፣ ‹‹[ሕዝቡ] ይህ ኀይል ሰላም እንዳልኾነ፣ የሰላም ጥረቶችን በሙሉ ሲያሰናክል የሰነበተ፣ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ሳይኾን የከሰሩ ፖሊቲከኞች እንቅስቃሴ መኾኑን ግንዛቤ ይዟል፤›› ብሏል፡፡ የ፮ው ፓትርያርክ ምርጫ ‹‹ሰላማዊ፣ አሳታፊና ግልጽ›› ኾኖ መካሄዱን የሚገልጸው ጽሑፉ ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሕዝብ ራሱን ስደተኛው ሲኖዶስ ብሎ ለሚጠራው አካል ተከታታይ የውግዘት መግለጫ ጆሮ ሳይሰጥ አልፏል›› ሲል ውግዘቱን አጣጥሏል፡፡ 
 • በማኅበሩ ውስጥ መሽገዋል የተባሉ የትምክህት ኀይሎችን ለማጋለጥና በሕግ ለመፋረድ ይካሄዳል የተባለው የ‹ፀረ አክራሪነት› እንቅስቃሴ የማኅበሩን ሕዝባዊ ተቀባይነት ለማሳጣትና የድጋፍ መሠረቱን ለማሸሽ የተወጠነ ሊኾን እንደሚችል ተጠርጥሯል፡፡
 • መንግሥት፡- የመንፈሳውያን ማኅበራትን የፋይናንስ ዝውውርና አጠቃቀም በምዝገባ ሕግ ከመቆጣጠር ጀምሮ ‹‹በማኅበራት ውስጥ ያሉኝን አባሎቼን [ኢሕአዴግ] በማንቀሳቀስ ቅኝታቸውን አስተካክላለኹ›› የሚል ዕቅድ መያዙ ተሰምቷል፡፡
 • በመንፈሳውያን ማኅበራቱ ውስጥ ያሉ የኢሕአዴግ አባሎችን በማንቀሳቀስ ‹‹የማኅበራቱን ቅኝት የማስተካከል››እንቅስቃሴ በሁሉም ክልሎች የሚፈጸም ሲኾን በትግራይና በአማራ ክልሎች የግንባሩ አመራሮችና አባላት ላይ ልዩ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል፡፡ በተለይ በክልል ትግራይ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከላት የመንግሥት ሠራተኞች የኾኑ የማኅበሩ አባላት ከሥራቸው ወይ ከአገልግሎታቸው እንዲመርጡ እንደሚገደዱ ተጠቁሟል፡፡
 • ማኅበረ ቅዱሳን ከሰሞኑ ‹‹የሰላም ዕሴት ማጎልበቻ ጉባኤ›› ሁለት ሳምንት በፊት ‹‹የአክራሪዎችና ትምክህተኞች ምሽግ›› በሚል ስለተፈረጀበት ኹኔታ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ጋራ ለመወያየት በተለያዩ መንገዶች ያቀረበው ጥያቄ በሚኒስቴሩ ሓላፊዎች ፈቃደኝነት ማጣት ተቀባይነት አለማግኘቱ ተገልጧል፡፡ ከዚህ ቀደም የማኅበሩ አመራር በተመሳሳይ ጉዳዮች ከሚኒስቴሩ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች ጋራ ለአራት ጊዜ ያህል መወያየቱ ታውቋል፡፡Mahibere Kidusan Statement 
 • መንግሥት አካሂደዋለኹ የሚለው የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ አሁን በሚታየው ስፋት ከመጀመሩ በፊት ማኅበሩ በኅትመት ውጤቶቹ የአክራሪነትንና አሸባሪነትን አደጋ የሚተነትኑ፣ ተከባብሮ የመኖር ባህላችን ጎልብቶ እንዲቀጥል የሚመክሩና የሚያሳስቡ ጽሑፎችን በተደጋጋሚና በጥልቀት ማቅረቡን የሚያስታውሱ አስተያየት ሰጭዎች÷ በፀረ – አክራሪነት/ጽንፈኝነት ሰበብ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከአገራዊ ሰላም አንጻር ብቻ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያናችንን ኦርቶዶክሳዊ ማንነት፣ ተቋማዊ ህልውናና ነጻነት ከማስጠበቅ አንጻር በጥንቃቄ እንዲታይ በጥብቅ ያሳስባሉ፡፡
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤