Sunday, October 6, 2013

ዘመነ ጽጌ

ዘመነ ጽጌ አትም ኢሜይል
መስከረም 24 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ
ክረምቱ አልፎ  በጋ ሲተካ ተራውንም ለዘመነ መፀው ሲያስረክብ የመጀመሪያው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ያለው ወቅት ዘመነ ጽጌ sidet2ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠራር በዘመነ ጽጌ ማለትም ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚደርሰው ስብሐተ እግዚአብሔር የሚቆመው ማኅሌቱ ደግሞ ማኅሌተ ጽጌ ተብሎ ይጠራል፡፡ በአባ ጽጌ ድንግል የተደረሰው ማኅሌተ ጸጌ እየተባለ የሚጠራው መልክ መሰል ድርሰትም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዜማ እየተቃኘ አገልግሎት የሚሰጥበት ጊዜም ይኸው ዘመነ ጽጌ ነው፡፡ ባሉት ሰንበታትና እንዲሁ ወርኀ በማለት ይደርሳል፡፡

ማኅሌተ ጽጌ የተባለው የድርሰት ክፍል እመቤታችንን በጽጌ ማለት በአበባ ልጇን መድኀኔዓለምን በፍሬ እንደገናም እሷንም ልጇንም በአበባና በፍሬ እየመሰለ ልብን በሚመስጥ ምሥጢራት ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያምና ስለ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር ድርሰት ሲሆን፤ በውስጡ ስለ ሥላሴ፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ ቅዱሳን ነቢያት፣ ስለ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ስለ ቅዱሳን ሰማዕታትና ስለ ቅዱሳን ጻድቃን የሚናገርና ገድላቸውን ትሩፋታቸውን መከራቸውን ከብሉይ ከሐዲስ አስማምቶ የሚገልጽ መጽሐፍ ነው፡፡


ነገረ ማርያምን ስደቷን፣ መራቧን፣ መጠማቷን፣ ማደሪያ አጥታ በምድረ በዳ መንከራተቷን፣ መቸገሯን፣ በድንግልና ከወለደችው ውድ ልጇ ጋራ የደረሰባትን ጭንቅና መከራ በሚያሳዝንና ልብን በሚሰብር ጣዕም የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህም ከመሆኑ የተነሣ ሊቃውንትም ሆኑ ምእመናን ዘመነ ጽጌ እስከሚመጣ ይጓጓሉ፣ ይናፍቃሉ፣ ዘመነ ጽጌ መጥቶ እስኪያልፍ ድረስ ከሌሎች ሰንበታት በተለየ መልኩ ማታ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መላ ሌሊቱን የእመቤታችንን ስደቷን በማሰብ፡-
“ብክዩ ሕዙናነ ሀልየክሙ ስደታ ወላህው ፍሱሐን ተዘኪረክሙ ብዝኀ ሰናይታ፣ ማርያም ተአይል ውስተ ምድረ ግብጽ ባህቲታ፣ ተአወዩ በኀጢኦታ ሀገረ አቡሐ ኤፍራታ፣ ወደመ ሕፃናት ይውህዝ በኩሉ ፍኖታ፡፡” ማኅሌተ ጽጌ

“እናንተ ሃዘንተኞች የእመቤታችንን ስደቷን አስባችሁ አልቅሱ እናንተም ደስተኞች የደም ግባቷን ብዛት አስባችሁ አልቅሱ ማርያም በግብጽ ተራራዎች ብቻዋን ትዞራለች የአባቷን ሀገር ኤፍራታን በማጣቷ ታለቅሳለች /ትጮሃለች በመንገዷም ሁሉ የሕፃናት ደም ይፈሳል፡፡
የሚለውን ሃዘንና ደስታ የተቀላቀለበትን ምስጋና በእግረ ምስጋና በእግረ ልቡና ከእርሷ ጋር በግብጽ በረሃዎች እየተሰደዱ ያድራሉ፡፡

በቀድሞ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ዘንድ የጽጌ መጀመሪያ መስከረም 26 ነገሥታቱ ልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት የአበባ ቅርፅ ያለው የክብር ልብሳቸውን ለብሰው ዘውዳቸውን ደፍተው ለሕዝቡ የሚታዩበት በዓል የሚያከብሩበት ሕዝቡን እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ የሚሉበት፣ የክረምቱ ዘመን ማለፍን የሚያበስሩበት፣ አሁን መስከረም አስር ቀን የሚከበረውን ተቀፀል ጽጌ እየተባለ የሚጠራውን በዓል የሚያከብሩበት ነበር፡፡ ይኸ በዓል ግን አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ወደ ሀገራችን ወደ አስገቡበት መስከረም አስር ዞሯል ቀድሞ ግን የሚከበረው ተቀፀል ጽጌ ተብሎ በወርኀ ጽጌ መጀመሪያ ነበር ጠቅላላውን ዘመነ ጽጌ የሚባለው በቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ነው፡፡ ይህንም ኢትዮጵያን አባቶችና እናቶች የስደቷ መታሰቢያ የተራበችበትና የተጠማችበት በመሆኑ በረከት እናገኝበታለን ብለው በፈቃዳቸው ይጾሙታል፡፡ አንድ አንዶቹ ደግሞ ማኅሌት በመቆም ለደከሙ የሚባለውን የሚጠጣውን አዘጋጅተው ከቅዳሴ ውጭ ከሊቃውንቱና እንዲሁም ይበሉት ይጠጡት ካጡት ከድሆች ጋር በመሆን በአንድ ላይ ይመገባሉ፤ ይዘክራሉ፤ ይመጸውታሉ፤ ካላቸው ያካፍላሉ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ በከተማ ከሚታየው በተለየ መልኩ የጽጌ ማኅበር በሚል ስያሜ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃውንቱ ጋር ከሚደረገው በተጨማሪ በየቤቱ ደግሰው በአንድነት ይመገባሉ፡፡ የተራቡ የተጠሙትንም ይመግባሉ፡፡ በዚያውም ለዓመቱ እመቤታችን እንድታደርሳቸው ይማጸናሉ በአንድ አንድ አካባቢ የዝክሩ ሁኔታ እስከ ጥር የሚቆይ ሲሆን በአንድ አንድ አካባቢዎች ግን ከመስከረም 26 - ኅዳር ስድስት እመቤታችን ከስደት የተመለሰችበት በደብረ ቊስቋም ያረፈችበት ቀን ድረስ ብቻ ይደረጋል፡፡ ያም ይሁን ይህ ዘመነ ጽጌ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የእመቤታችንና የልጇ የወዳጇ የኢየሱስ ክርስቶስ ስደት መታሰቢያ መሆኑን ነው፡፡

የዘመነ ጽጌ መከበር ምክንያቱ
ዘመነ ጽጌን በመጠኑ ይህን ያህል ካየነው ምክንያቱስ ምንድን ነበር የሚለው በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

ምክንያቱም ቅዱስ ወንጌል እንደነገረን በጌታችን ዓለምን ለማዳን ሰው መሆን /መወለድ/ የደከመው ዲያብሎስ ሊቃውንት አባቶች እንደነገሩን ጌታ ሊወለድ 25 ቀን ሲቀረው መካነ ልደቱን በመላእክት አስጠብቆት ነበር በዚህ ጊዜ ጣዖታቱ እየወደቁ ማንም ሳይነካቸው ይሰበሩ ነበር፡፡ አጋንንት ሄደው አለቃቸው ዲያብሎስን ጣዖታቱ እየወደቁ ተሰበሩ እኛም በጣዖታት ማደር ተሳነን ችግሩ ምንድን ነው? ብለው ጠየቁ፡፡ ዲያብሎስ ያ ኢሳይያስ “ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ኢሳ.7፥14 እያለ ሲያስተምር ሰምቼ በምናሴ አድሬ በኩላብ አሰቅዬ አስገድየው ነበር፡፡ ያም ሚክያስ “ወአንቲኒ ቤተልሄም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ” አንቺ ቤተልሄም የይሁዳ ነገሥታት ከሚነግሡባቸው አታንሽም ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና” ሚክ.5፥2

ብሎ ሲያስተምር ሰምቸው ነበር ያ ነገር ተደርጎ ይሆን ያ ነገር ተደርጎ ከሆነ ወዮ ለእኔ ወዮ ለእናንተ ብሎ እርሱም ጌታን ለመምሰል አራት ፀወርተ መንበር አበጅቶ ነበርና “እስኩ ንዑ ጹሩኒ” እስኪ ኑ ተሸከሙኝ ብሎ አንድ ጊዜ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ቢወረወር አጣው ግን በቤተ ልሄም የብርሃን ድንኳን ተተክሎ አየ ዕቀርባለሁ ቢል መላእክት በሐፀ እሳት በኲናተ እሳት እየነደፉ አላስቀርበው አሉ እርሱም ከሄሮድስ ዘንድ ሄዶ ዛሬ ገና መንግሥትህ የሚቀማ ልጅ ተወለደልህ ብሎ በሄሮድስ አድሮ ጌታን ለማስገደል ተነሣ፡፡

በቤተልሄም ለተወለደው የዓለም መድኀኒት ሰበአ ሰገል ሰግደው በሄሮድስ በኩል ሳይሆን በሌላ መንገድ እንደተመለሱ በሰማ ጊዜ ሕፃኑን ሊገለው ፈለገ “ወሰሚኦ ሄሮድስ ከመ ተሳለቁ ላዕሌሁ ሰበአሰገል ተምአ ጥቀ ወፈነወ ሀራሁ ይቅትሉ ኩሎ ሕፃናተ ዘውስተ ቤተልሔም ወዘውስተ ኩሉ አዲያሚሃ ዘ፪ኤ ዓመት ወዘይንዕስሂ” ማቴ.2፥16

“ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደዘበቱበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ጭፍራ ላከ ከሰብአ ሰገል እንደተረዳው ዘመን ልክ ሁለት ዓመት የሞላቸውን ከዚያም የሚያንሱትን በቤተልሄምና በአውራጃዎች ሁሉ የነበሩት ሕፃናት አስገደለ” ማቴ.2፥16-18

ዲያብሎስ በሄሮድስ አድሮ ጌታን ያገኘሁ መስሎት አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናት አስፈጀ፡፡

ጌታችን ግን ከእናቱ ጋር ወደ ግብጽ ተሰዶ ነበር “እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በህልም ታይቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ ሕፃኑና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ግብጽ ሽሽ አለው እንዲል፡፡ ማቴ.2፥13 በዚህም ጌታችን እንዳልሞተ ያወቀው ዲያብሎስ እየተከተለ በእመቤታችን ላይ የሰዎችን ልቡና እያጠነከረ ፈትኗታል፡፡ “ዘንዶውም /ዲያብሎስ/ በወለደች ጊዜ ልጇን ይበላ ዘንድ /ያስገድለው ዘንድ/ በዚያች ሴት ፊት /በእመቤታችን/ ቆመ” ራዕ. 12፥4፡፡ ቆመ የሚለው አንቀጽ በክፋት ምን ያህል እንደታገላት ያሳያል፡፡

“ሴቲቱም /እመቤታችንም/ በዘመኑ ሁሉ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ ቀን በዚያ ትጠበቅ ዘንድ እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላት ቦታ ወደ በርሃ ሸሸች” ራዕ.12፥5፡፡ 
ብሎ እመቤታችን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ገዳማት በጣና በአክሱም ጽዮን በዋልድባ በሌሎችም ገዳማት እንደተመላለሰች መጻሕፍት ይመሰክራሉ ሊቃውንትም ያስረዳሉ፡፡ ባለራዕዩ ቅዱስ ዮሐንስ “ሴቲቱም ከዘንዶው ፊት ርቃ አንድ ዘመን /አንድ ዓመት/ ዘመናትም /ሁለት ዓመት/ የዘመንም እኩሌታ /ስድስት ወር/ ወደምትጠበቅበት ወደ በርሃ እንድትበር የታላቁን ንስር ክንሮች ተሰጣት፡፡ /የመንፈስ ቅዱስ ኀይል/ ዘንዶውም በርሮ ተከተላት፤ ዘንዶውም ጎርፍ ይወስዳት ዘንድ ከአፉ እንደታላቅ ወንዝ ያለ በዚያች ሴት በስተኋላዋ አፈሰሰ” ራዕ. 12፥14፡፡ በማለት እመቤታችን ድንግል ማርያም በስደቷ ጊዜ የደረሰባትን ፀዋትወ መከራ እጅግ ብዙ መሆኑን ያስተምረናል፡፡ አባ ሕርያቆስም ከዚህ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡፡ “ድንግል ሆይ ከአንቺ የፈሰሰውን በልጅስ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፡፡ የደረሰብሽን ረሃብና ጽምዕ ችግርና መከራ ከልጅሽ ጋር ከአንድ አገር ወደ አንዱ አገር ስትሰደጂ ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን የደረሰብሽን አሳስቢ፡፡” ቅዳሴ ማርያም፡፡ ታዲያ ዘመነ ጽጌ እንዲከበር ምክንያቱ ይህ ነው፡፡

ይልቁንም በኢትዮጵያ ጎልቶ የሚታየውም ጥንቱን ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር እንደሆነች በነቢያት “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች መዝ.66፥ ተብሎ ትንቢት የተነገረላት እንግዳ ተቀባይ በመሆኗ የአምላክ እናት ድንግል ማርያምን ከልጇ ጋር በእንግድነት ያስተናገደች የእመቤታችን የአስራት አገር ስለሆነች ነው፡፡

አገሪቱ አገረ እግዚአብሔር እንደሆነች ሁሉ ሕዝቦቿ ሕዝበ እግዚአብሔር መሆናቸው የሚረጋገጠው በዚህ ነው፡፡
  1. ጌታችን ለምን ተሰደደ፡- ስደትን ለሰማእታት ለባሕታውያን፣ ለመናንያን መነኮሳት ከአገር ምድረ በዳ ከዘመድ ባዳ ይሻላል ብለው ለሚኖሩ ጻድቃን ቅዱሳን ሰማእትነትን ባርኮ ለመስጠት ነው፡፡ ምክንያቱ ሰማእትነት ማለት በሰይፍ መቆረጥ ብቻ አለመሆኑን አገር ጥሎ እግዚአብሔር ተከትሎ ድምጸ አራዊት ግርማ ሌሊትን ታግሶ ረሀቡን ጥሙን እርዛቱን ችሎ መኖር ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር እያሉ በምናኔ በመማር በማስተማር መኖር ሰማዕትነት መሆኑን ለጻድቃን ለሰማእታት ለመናንያን ለማስተማር ነው፡፡ የሁሉም አብነት ነውና፡፡ “ኮነነ በኩረ ወጥንተ ለኩሉ ምግባረ ትሩፋት” እንዲል “ለትሩፋት ሥራ አብነት ሆነን”
  2. ለምን ወደ ግብጽ ተሰደደ፡- ግብጽ እንደሚታወቀው ሁሉ አምልኮተ ጣዖት የፀናበት ላም ጥጃ የሚመለክባት እንጨት ጠርቦ አለዝበው የሚያመልኩ ሰዎች የበዙባት በጠቅላላው አምልኮተ ጣዖት የፀናበት አገር ናት፡፡ ችግር ወደ ጸናበት መሄድ ለጌታ ልማዱ ነው፡፡ በመዋእለ ስብከቱ ደዌ ወደ ጸናባቸው ሕመም ወደሚያሰቃያቸው ይሄድ እንደነበር ቅዱስ ወንጌል ምስክር ነው ማቴ.4፥26፡፡ ስለዚህ አምልኮተ ጣዖትን ለማጥፋት ወደ ግብጽ ተሰዷል፡፡ በሌላ መልኩ በኋላ ዘመን የሚነሡ ግብጻውያን ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉባቸው ገዳማትን ለመባረክ እነገዳመ አስቄጥስ፣ ደብረ ቊስቋም “ወትከውን አሀቲ አገር ምስዋዖ ለእግዚብሔር” አንዲት አገር የእግዚአብሔር መሰዊያ ትሆናለች፡፡ የተባለች እስክንድርያ እነዚህን ሁሉ ለመባረክ ነው፡፡
  3. ኪዳነ መልከ ጼዴቅን ለመፈጸም፡- መልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊው ከካም ዘር የተወለደው ዘመዶቼን ማርልኝ ብሎት ነበርና በኋላ ዘመን ልጄን በሥጋ ሰድጄ እምርልሃለሁ ብሎት ነበርና ያን ለመፈጸም ወደአፍሪካ ተሰዶ ምድረ አፍሪካን በኪደተ እግሩ ቀድሷታል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡ ጌታችን ወደግብጽ ወደአፍሪካ የተሰደደው፡፡ በትንቢትም ነቢያት ተናግረው ስለነበር ያንን ለመፈጸም “ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብጽ ተጽእኖ ዲበ ደመና ቀሊል” ያን ጊዜ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ወደግብጽ ይወርዳል የግብጽ ጣዖታትም በፊቱ ይወድቃሉ” ኢሳ.19፥1-5፡፡

የእመቤታችን አማላጅነት ፀጋዋ በረከትዋ ይደርብን አማላጅነት እናትነቷ አይለየን፡፡
ይቆየን 

ምንጭ ፥      http://www.eotc-mkidusan.org

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤