Tuesday, November 12, 2013

ዜግነት ዋጋ ሲያጣ

Friday, November 8, 2013
(PDF):- ዜጋህ እንደ ወንጀለኛ በየመንገዱ እየታፈሰ ሲታሰር፣ ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ሁኔታ ደግሞ አንዱ የአገርህ ልጅ በአረብ ፖሊስ ጥይት ተመትቶ ዋዕዩ በሚነድደው አስፓልት ላይ ደሙ ረግቶ ስትመለከት ምን ይሰማኻል? ይህ ሁሉ በሳዑዲ ምድር ላይ በየቀኑ እተፈጸመ መሆኑን ስትረዳ ውስጥህ ምን ይልኻል? ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከሌላ ዜግነት በቅጡ አን ይሆን?ትናንት ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችባቸው 5 ዓመታት ብዙ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን አድርሳለች። ከነዚህ መካከል  በግራዚያኒ ላይ የተደረገውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ የደረሰው የየካቲት 12 ጭፍጨፋ አንዱ ነው። በአዲስ አበባ በግፍ የተጨፈጨፉት የየካቲት 12 ሰማዕታት በሚዘከሩባቸው ቀናት አንድም ፈረንጅ በአዲስ አበባ መንገድ ዝር አይልም ነበር አሉ። ኢትዮጵያውያን በቁጭት ስለሚወጡ። እንኳን ጣሊያን እና የጣሊያን ዝርያ ያለው ቀርቶ ሌላ ፈረንጅም ቢሆን ይፈራ ነበር። ኢትዮጵያውያን በወገኖቻቸው ጥቃት ይኼን ያህል ቁጭት ነበራቸው።ዛሬ ኢትዮጵያን ወገኖቻችን በአረቦች እንደ ውሻ በየመንገዱ የሚደበድቧቸው በዚያን ዘመን ቢሆን ኖሮ አንድም አረብ በአዲስ አበባ ጎዳና በሰላም ይኼድ ነበር? ኢትዮጵያዊነት እንዲህ የረከሰውና የተዋረደው ድሆች ስለሆንን ብቻ ነው? ስንት ድሃ አገር ሞልቶ የለምን? ምነው እንደዚህ አልተንቋሸሹ?
ኢትዮጵያዊውን “አለኹልህ” የሚለው ማነው? ውስጤ ሐዘን ሳይሆን ንዴት፣ ቁጭት፣ እልህ ነው ያለው።  ካልተንገበገብን ታዲያ ምን ዋጋ አለን?
አንድ ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ አስታወሰኝ። ታሪኩ የብርሃነ ዓለም የቅዱስ ጳውሎስ ታሪክ ነው። ይህ በእግዚአብሔር ተዓምር፣ በመባርቀት የተጠራ ሐዋርያ ታሪክ ነው። ቅ/ጳውሎስ በኢየሩሳሌም በሚያስተምርበት ጊዜ ትምህርቱን የተቃወሙ አይሁድ በብርቱ፡ያስቸግሩት ነበር። ከማስቸገርም አልፈው ሊያስሩትና ለገ ዎቻቸው አሳልፈው ሊሰጡት ይፈልጉ ነበር። ይህንንም ራሱ ቅ/ጳውሎስ ቀድሞ ተረድቶ ነበር። በዘመኑ የነበረ አጋቦስ የተባለ ነቢይ ተንብዮ ነበር። ይህንን ያወቁ ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ቢለምኑትም በጀ አላላቸውም። ለምን “ልቤን እንዲህ አድርጋችሁ ትሰብሩታላችሁ? እኔ እኮ ተስፋ የማደርገው እግር ብረትና ሰንሰለትን ብቻ አይደለም። … በኢየሩሳሌም ለመሞት ደግሞ ቆረትኩ ነኝ” በማለቱ ልመናቸውን ተዉ። (የሐዋ. 20፡24)
ወደ ኢየሩሳሌምም ሄዶ ማስተማሩን ቀጠለ። እስያ በነበረበት ወቅት ስብከቱን የሰሙ አይሁድ ባዩት ጊዜ በጣሙ ተናደዱ። ሰዎችን አስተባብረው አስያዙት። “ሊደግሉት ሽተው ብዙ ደበደቡት” (የሐዋ. 21፡31። የሮማ ወታደሮች ባይደርሱ ኖሮ ደግሉት ነበር። በወታደሮች ከተያዘ በኋላም ቢሆን የተያዘበት ምክንያቱና አይሁድ ለምን እንደጠሉት ያልተረዳው ሻለቃው ለወታደሮቹ ትዕዛዝ ሰጠ፦ ጳውሎስን “ወደ ቅጣት መቀበያው ቦታ እንዲያገቡትና እየገረፉ የሠራውን እንዲመረምሩት አዘዘ።”
ይህንን የተረዳው ቅ/ጳውሎስም ትውልዱ አይሁዳዊ ቢሆንም በዜግነቱ ሮማዊ መሆኑን ተናገረ። ሊገርፉት የተዘጋጁት ወታደሮች ደነገጡ። “የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ። ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ ብሎ ነገረው። የሻለቃውም ቀርቦ። አንተ ሮማዊ ነህን? ንገረኝ አለው፤ እርሱም፦ አዎን አለ። ስለዚህም ሊመረምሩት ያሰቡት ከእርሱ ወዲያው ተለዩ፤ የሻለቃውም ደግሞ ሮማዊ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፥ አሳስሮት ነበርና።” ይለናል ታሪኩ (የሐዋርያት ሥራ 2226 -29/2327)። ከዚያም ፈትቶታል።
በዚያን ዘመን ሮማዊ መሆን ወይም ሮማዊ ዜግነት ከመገረፍ ያተርፍ ኖሯል። ሮማዊ ዜጋ የትም ይኑር የት ስለ ሮማነቱ ብቻ ይከበር ነበር። በዚህ ሮማዊ ዜግነት ባለው ሰው ላይ አንድ ዓይነት አደጋ ማድረስ ብዙ መዘዝ እንዳለው ይታወቃል።
በዘመናችንም ብዙ ታላላቅ አገሮች ዜጎቻቸው በየትም ይኑሩ በየት ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ማንኛውንም ነገር ያደርጋሉ። ከሰሞኑ ለዕይታ የበቃ አንድ አዲስ ፊልም (“Captain Phillips”) የመመልከት ዕድል ገጥሞኝ ነበር። ታሪኩ በሶማሌ የባሕር ላይ ዘራፊዎች መርከቡ ስለተጠለፈችና እርሱም በጠላፊዎቹ ስለተያዘ አንድ አሜሪካዊ ካፒቴን እውነተኛ ታሪክ የሚያትት ነው። ታሪኩ በ2009 የተከሰተ ሲሆን የአሜሪካ ወታደሮች ካፒቴኑን ያስጣሉበትን የአጋች-ታጋች ታሪክ የሚያስረዳ ነው። ጭብጡ፦ ዜጋህን እንዴት ትታደገዋለህ ነው።
ንጉሰ ነገሥት አጼ ካሌብ የመን እና ዐረቢ ድረስ ዘልቅ የወረሩትና ሹሞቻቸውን ሰይመው የተመለሱበትን የታሪክ ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለን እንመልከት። ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች ተደርገው የሚቆጠሩባቸውና የሚንገላቱባቸው የዐረብ አገሮች የአጼ ካሌብ ፈረሶች የሮጡባቸው፤ እንደ ገል ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው የገዙባቸው አገሮች ናቸው።
ልቤ በታሪክ መዘውር ወደ ኋላ የሚወረወረውን ያህል ወደ ዘመናችንም ተመልሶ ከክብር ዙፋን የወደቅንበትን እና በአረቦች ጫማ ሥር የተደፋንበትን የውርደት ምክንያት ሊመረምር ይፈልጋል? ከሌላው አገር ሁሉ ተርታ ተለይተን ወደ ኋላ መቅረታችን ብቻ ሳይሆን እጅግ አምርረው በሚጠሉን በአረቦች ጓዳ ባርነት የገባንበትን ምክንያት ለማወቅ ኅሊናዬ ይጨነቃል።
እጅግ የማከብራቸው ፕ/ር መስፍን እንዲህ አሉ፦ “በሀገረ-መንግስትነት (state) ኢትዮጵያ ብዙዎቹን የአውሮፓ አገሮች ትቀድማቸዋለች። ታላቋ ብሪታንያ ሀገር የተባለችው በ1707 አካባቢ ነው። ጀርመን ከ1815 እስከ 94 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ሀገር የተባለችው። ኢጣሊያ በ1870 አካባቢ ነው ሀገረ-መንግስት የሆነችው። ፈረንሳይም በ18 መቶ ግድም ነው፤ ኢትዮጵያ በ525 ዓ.ም ሀገረ-መንግስት ከመሆን አልፋ ንጉስ ካሌብ የመንን የወረረበት ዘመን ነበር። እና ኢትዮጵያ ገና እንግሊዞች ሀገረ-መንግስት ለመሆን በሚፍጨረጨሩበት ጊዜ እኛ ግን ሀገረ-መንግስት ነበርን። እነሱ ‘‘ማግና ካርታ’’ የሚሉት በምዕራባውያን ለመጀመሪያው ጊዜ የመብት ጥያቄ ያነሱት እ.ኤ.አ በ1215 ዓ.ም ነበር። … 1215 ዓ.ም የዛጉዌ ስርወ መንግስት ወደ ሰሎሞን ስርወ-መንግስት የተለወጠበት ጊዜ ነበር። እኛ በዚያን ጊዜ የተደራጀን ሀገረ-መንግስት (state) ነበር” (‘‘የኢትዮጵያ ወጣትና የወደፊት ኃላፊነት’’ ከሚለው ንግግር የተወሰደ)
 ዛሬ ግን ይህንን ሁሉ ጸጋ አጥተናል። በየአረብ አገሩ ያሉ ኤምባሲዎቻችን እንኳን መጠጊያ አልሆኑንም። ለኢትዮጵያዊው አለኹልህ የሚለው የለውም። ከአርባ ዓመት በፊት በአረብ መንገዶች ላይ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ እና በአሜሪካ ጎዳናዎች በኩራት ይራመድ የነበረ ዘረ-ኢትዮጵያ አሁን ግን በሱዳንና በግብጽ በረሃዎች፣ በሜዴትራኒያን ባህር፣ በሞዛምቢክና በዚምባቡዌ እስር ቤቶች ይሰቃያል። በየመን የስደተኛ ካምፖች ይገረፋል። በሳዑዲ አረቢያ መንገዶች ይደበደባል። ኢትዮጵያዊ ክብር ወዴት ወደቀች? ከአጼ ካሌብ እስከ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ በባዕድ አገሮች ለማንነታቸው ክብር የቆሙ ኢትዮጵያውያን ልጆች አልነበርንም?
ኢትዮጵያዊነት ንጹህ ዕንቁ በቆሻሻ ተበላሽታለች። ለሚያዩዋት በሙሉ ዕንቁነቷ ሳይሆን ቆሻሻነቷ ብቻ ይታያል። የተደፋባት ጉድፍ የምታበራ ዕንቁ መሆኗን ሸፍኖታል። ኢትዮጵያ ዕንቁዬ፤ አብሪ!!! በድህነትና በስደት፣ በእስርና በአምባገነንት ከተቀበርሽበት ጉድጓድ ውጪ። አብሪ!!! ከሰሜን ተራሮች እስከ ደንከል ዋዕዮች፣ ከቀይ ባህር ውኃዎች እስከ ጋንቤላ ደኖች ደወልሽን አሰሚ። በዓለም የተበተነውን ልጅሽን አይዞህ በዪ!! ኢትዮጵያ አብሪ!!!

አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን!!! 
Picture: Courtesy of Abenezer Marvel.
source: http://www.adebabay.com
--------------------------------------------
ማስተካከያ - አፄ ካሌብ የመንን አልወረሩም። ምክንያቱም የመን በኢትዮጵያ አስተዳደር ውስጥ ነበረችና። በጽሑፍ የቆየው ማስረጃ እንደሚያሳየው የየመን ነዋሪዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነበሩ። አፄ ካሌብ ወደ ናግራን የዘመቱት በሳቸው የተሾመው ክርስቲያኑ ንጉሥ በህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም ሲለይ ወራቱ ክረምት በመሆኑ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ክርስትናን ለማጥፋት አንድ አይሁድ ተነስቶ እራሱን ንጉሥ ብሎ ሰይሞ ሃያ ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን (ካህናቶችን ጨምሮ) በመግደሉ ነበር።  ይህም በጽሁፍ ሰፍሮ በቅርስ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤