Saturday, January 25, 2014

የዋልድባ ዳልሻሐ ኪዳነምሕረት የእናቶች አንድነት ገዳም ለተደረገላቸው እርዳታ የምስጋና ደብዳቤ


ቀን 7 - 4 - 2006 ..
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን
በደላችንን በሞቱ፣ ሃጢያታችንን በቸርነቱ ያጠፋልን እስከ ሞት ድረስ የወደደን የአበው አምላክ እግዚአብሔር ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የከበረ የተመሰገነ ይሁን አሜን።

ገዳማውያን እናቶች ከተገዛው አቡጀዲ ጋር
ምንጊዜም ሠላምን ጠንነትን ለምንመኝላችሁ የቤተክርስቲያን እና የገዳማትእረዳት ለሆናችሁት የክርስቶስ ቤተሰቦች ለዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት ማኅበር በሙሉ ለተከበረው ውድ ጤንነታችሁ እንደምን ከርማችኃል እንደምን አላችሁልን እኛ ገዳማውያን መነኮሳይት ለጤናችን አምላከ አበው ይክበር ይመስገን ደህና ነን።

አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መራባችንን እና መታረዛችንን በመስማታችሁ $4000.00 ዶላር  72,500.00 (ሰባ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ልካችሁልን
ገዳማውያን እናቶች ከተገዛው የአቡጀዲ ጋር 

1/ 60 ጣቃ አቡጀዲ (ለአንዱ ጣቃ 550 ብር በመግዛት በአጠቃላይ 60 x 550 = 33,000 (ሠላሳ ሦስት ሺህ ብር) ተገዝቶ መጥቶልን ገዳመ መነኮሳይቱ አንድ ጣቃ አቡጀዲ ለአራት መነኮሳይት ደርሶናል በድምሩ 240 መነኮሳይት አልባሳት አገኝተዋል።

2/ እህሉም ዛሬማ ገበያ ተገዝቶልን 40 ኩንታል ማሽላ እና ዳጉሳ ለአንድ ኩንታል እህል 900 ብር (ዘጠኝ መቶ ብር) በመግዛት 40 x 900 = 36, 000 (ሠላሳ ስድስት ሺህ ብር) በአጠቃላይ እህሉ ሲገዛ በቀሪው ብር በግመል እስከ ገዳሙ ተጭኖ ተረክበናል።
እኛን በተቸገርን ጊዜ እንደረዳችሁን አምላከ አበው ይርዳችሁ፣ በረደኤት በፀጋ አይለያችሁ፣ የወለዳችሁት ምሩቅ፣ የጨበጣችሁት ለምለም፣ የረገጣችሁት እርጥብ ይሁን እድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ ያድላችሁ፣ ማኅበራችሁን ማኅበረ ፃድቃን መኅበረ ቅዱሳን ያድርግላችሁ፣ በአንድነት በፍቅር በሐይማኖት ያፅናችሁ፣ የደማማ ምርኩዝ ኪዳነ ምሕረት ተስፋ ሥጋ ተስፋ ነፍስ ታድላችሁ፣ እናንተ ለእኛ እንደሰጣችሁን የዘባውን አቅንቶ የጎደለውን ሞልቶ ለኃጢያት መደምሰሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ያድርግላችሁ፣ ለሥጋው ለደሙ ለደጀ ሠላሙ ያብቃችሁ የእናንተን ምፅዋት የእኛን ፀሎት አንድ አድርጎ አገናኝቶ ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃን፣ የገዳሙ ጸሎት አይለያችሁ፣ ገዳማችን እስከለተ ምፅዓት አይፍታብን እግዚአብሔር አሜን።

የገዳሙ መነኮሳይት ኑሮአችን የምንመራው ያለን መሬት በመጠኑ ሲሆን ያንንም እራሳችን ቆፍረን ዘርተን በመሰብሰብ ሲሆን ሴቶች በመሆናችን የዓመት አዝመራን ማግኘት ባለመቻላችን እና ቋሚ መተዳደሪያ ልማት ስለሌለን ገዳሙ የዓመት ልብስ የእለት ምግብ የሚያገኘው በእናንተ በሕዝበ ክርስቲያኑ እርዳታ ጥምር ስለሆነ አሁንም ገዳሙ ከልመና ነፃ የሚወጣበትን ዘላቂ የልማት ሥራን በማሰብ የከርሰ ምድር ውሃን ብታወጡልን እኛም ደካሞች በየአቅማችን ወጥተን ወርደን በመሥራት በገዳሙ ውስጥ ውሃው ቢወጣልን እንደምናለማ እና ፈቃደኛ መሆናችንን እየገለጽናልችሁ ይህንንም በጎ ሃሳባችሁን ተፈጽሞ የገዳሙ ችግር የምታስወግዱልን እና በዓመት በዓመት እናንተን ማስቸገር የምንድንበትን እግዚአብሔር አምላክ ያሳካልን እያልን እንደምትረዱን ተስፋ በማድረግ በኪዳነ ምሕረት ስም ከጫማ እግራችሁ ስር ወድቀን እንለምናችኃለን።

እኛ የዋልድባ ዳልሻሐ ኪዳነ ምሕረት የእናቶች አንድነት ማኅበረ ደናግል ገዳም።

ደብዳቤውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ 

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤