Thursday, February 13, 2014

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ባለፈው ቅዳሜ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን በመኖሪያ ቤታቸው አነጋገሩ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት ከተቋቋመ ማግሥት ጀምሮ ለብዙ ጊዜ ሲመኘው እና ሲሰራበት የነበረው እውን ሆኖ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን በመኖሪያ ቤታቸው ለማግኘት በመቻሉ የፈጣሪያችን የመድኅኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን አሜን።

ቀኑ ቅዳሜ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. (February 8, 2014) ከእኩለ ቀን በኃላ ነበር ስድት የሚሆኑ የማኅበሩ ተወካዮች በሜሪላንድ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ አባታችን መኖሪያ የደረሰው። በወቅቱም ከብፁዕ አቡነ መርቆርዮስ ጋር አቡነ ሳሙኤል እና አቡነ ያዕቆብ አብረዋቸው ነበር የልዑካን ቡድኑን መምጣት እየተጠባበቁ የነበረው፥ የልዑካን ቡድኑ በቦታው እንደደረሱ በመልካም አባታዊ አቀባበል እና ቡራኬ ተቀብለው በመልካም ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ተቀብለው ነበር የተስተናገዱት። ክብር ለመድኅኒዓለም ይሁንና ብፁዓን አባቶች በተገኙበት የልዑካን ቡድኑ የመጣበትን እና ለብፁዓን አባቶች መኅበሩ ከየት ተነሥቶ የት እንደደረስ የተነሳበትን ዓላማ እና ግብ ካስረዳ በኃላ በተለይ በአሁኑ ወቅት በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ ያጠላውን የመከራ ድባብ ለማስረዳት ተሞክሯል።

በስደት የሚገኙት ብፁዓን አባቶች


የልዑካን ቡድኑ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት (ዋልድባን እንታደግ) ብሎ ከተነሳበት ከመጋቢት ፳፻፫ ዓ. ም. ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያደረገውን እንቅስቃሴ፣ ያጋጠሙትን ችግሮች እንዲሁም ያከናወናቸውን መልካም ተግባሮች ጨምሮ ለብፁዓን አባቶች ያስረዳ ሲሆን፥ ቅዱስ አባታችንን በጸሎታቸው እንዲራዱን እና ሥራችንንም እስከመጨረሻው ድረስ በመልካም እንድንፈጽም በአደራ ጭምር ብፁዓን አባቶችን አሳስቧል። የልዑካን ቡድኑ በተለይ በወቅቱ የቤተክርስቲያኒቱ ችግሮች ዙሪያ ያነሳቸው ነጥቦችን በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል የወቅቱ የቤተክርስቲያን ችግሮች እና ፈተናዎች:

፩/   ቤተክርስቲያን በውጪ እና በውስጥ ሲኖዶስ በሚል አስተዳደራዊ መዋቅሯ መበታተኑ
፪/   በቤተክርስቲያን በጉያዋ ተሰግስግው ፈተና የሆኑባት አጽራረ ቤተክርስቲያናት
፫/   በተለያየ የሃገራችን ክፍሎች የሚቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት፥ ያለተጠያቂነት መታለፋቸው
፬/   በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ
፭/   በተለያየ የሃገራችን ክፍሎች የገዳማት መፈታት፣ የአብነት ተማሪዎች መበትን እና የቤተክርስቲያን  
     አገልጋቾች መጥፋት።
ከተነሱት ችግሮች ዋነቹ ሲሆኑ፥ ብፁዓን አባቶች ሊያደጓቸው የሚችሉት ትልቅ ሚና እንዳለ የልዑካን ቡድኑ ለማስረዳት ችሏል።
በመጨራሻም በብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እና አቡነ ሳሙኤል በኩል ረዘም ያለ ምክር እና ዓላማን ሳይስቱ ለተነሱለት ዓላማ እስከ ሞት ድረስ እንደሚያስፈልግ እና አላማን ከግብ ማድረስ ሰማያዊ ክብር እንደሚያሰጥ ብፁዓን አባቶች ሰፋ ባለ ሁኔታ አስረድተዋል። በተለይ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በሃገራችን ኢትዮጵያ ያለውን የአክራሪዎች በብዛትን እና በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ እያደረሱት ያሉትን ብዙ ችግሮች በምሳሌ በመጥቀስ ለማስረዳት ሞክረዋል በመጨረሻም ብፁዓን አባቶች ጀማሪዎች ብቻ ሳትሆኑ ጨራሾች እንዲያደርጋችሁ እኛም ወደ ፈጣሪ በጸሎት እንረዳለን የምንችለውን እናደርጋለን በማለት ተስፋ ሰጪ ንግግሮችን ከደረጉ በኃላ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት እና ቡራኬ ስብሰባው እና ውይይቱ ተጠናቋል። በመጨራሻም የልዑካን ቡድኑ ለቅዱስ ፓትርያሪኩ ይዘውይ የሄዱትን ደብዳቤ በእጃቸው ሰጥተዋል፣ ከውይይቱ መጨረሻ ላይም ቅዱስ ፓትርያሪኩ ደብዳቤውን ቁጭ ብለው አንብበው ጸሎተ ማርያም አድርሰው ደብዳቤውን በመስቀላቸው በመባረክ ውይይቱ ተጠናቋል።

በመጨረሻም ይህንን እድል እንድናገኝ ለረዱን እህቶች እና አባቶች እግዚአብሔር አምላክ የልባቸውን መሻት እና ተምኔታቸውን ሁሉ ይፈጽምልን እንላለን፥ ለአባቶቻችንም አክብረው መልካም አባትነታቸውን ላሳዩን በሙሉ አምላከ አበው እረጅም የአገልግሎት ዘመን እና መልካም ፍጻሜን እንዲያደርግላቸው ከልብ እንመኛለን።
ወስብሃት ለእግዚአብሔር
ወለመስቀሉ ክቡር

ወለ ወላዲቱ ድንግል አሜን

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

2 comments:

  1. what is patriarch's comment on two synod? HE knows about politics and problem .he showed any direction to become one before his death like aba pawulos.

    ReplyDelete
    Replies
    1. ብጹዕነታቸው በእነት የእግዚአብሔር ሰው ናቸው፣ እኔ እንደምገምተው እንደውም ተገደው የተቀመጡ ነው የሚመስለኝ ምክንያቱም እውን አንድ ነገር ሳይናገሩ ሰው እንዴት 20 ዘመን ሙሉ ይቀመጣሉ እንደው አንድ ነገር ደግ ይሁን ክፉ . . . እጅግ የሚያስገርም ነው ተናግሬ ሰውን እና እግዚአብሔርን አላሳዝንም ብለው ይመስለኛል ሳስበው ነገር ግን በዙሪያቸው ቤተክርስቲያንን እና ሕዝቦቿን እንደዋሻ አድርገው የሚያደቡ ብዙ ተኩላዎች እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባል፣ ለመፍረድም አንቸኩል በእውነት እግዚአብሔር እንዲረዳቸው እና ቤተክርስቲያንን ከባሰ መለያየት እና መከፋፈል እንዲታደጉልን እኛ ምዕመናን ልንጸልይላቸው ይገባል ባይ ነኝ አለበለዚያ በዙሪያቸው የሚያደቡት ሰዎች ምን ፍላጎት እንዳላቸው የምናውቀው ነገር የለም ከባሰ መለያየት መከፋፈል እና መበላላት እግዚኧብሔር አምላክ ያድነን ይጠብቀን እያልኩኝ እናም ከመፍረድ ያድነት ይጠብቀን ይፈረድብናልና

      Delete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤