Monday, May 5, 2014

ለግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የተጠራው ስብሰባ ለግንቦት ፭ ተቀጥሯል


የዋልድባ ገዳም በሳተላይት እይታ
  •        የማይፀብሪ የመንግሥት ባለሥልጣናት የመነኮሳቱን ውሳኔ በግንቦት ፯ እንዲያሳውቁ ጥብቅ ውሳኔ አስተላልፈዋል 
  •       ለስኳር ፋብሪካው ግንባታ መኅር ገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደለሳ ቆቃ አቡነ አረጋዊ፣ እጣኖ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያናት መነሳታቸው ተወስኗል
  •       አባ ገ/ሕይወት መስፍን በመንግሥት ባለሥልጣናት እና በገዳሙ መካከል በመሆን ሥራቸውን እየሰሩ ነው
  •       አባ ነፃ ላይ በቅርቡ ካምፖች ተሰርተዋል

ባለፈው ወር አካባቢ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከአዲስ አበባ እንዲሁም ከማይፀብሪ የመን ሥት ተወካዮች ጋር በመሆን ጥቂት የመንግሥት ሰዎችን በማይፀብሪ ላይ አነጋርረዋቸው እንደነበር ይ ታወሳል። በዚህም ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ የስኳር ፋብሪካ ኮርፖሬችን የበላይ ሃላፊዎች የስኳር ፋብሪካው ግንባታ ለመጓተት ምክንያት የሆኑትን መነኮሳት በማንኛውም መንገድ አሳምኖ ወይንም አስፈላጊውን ነገር ተጠቅሞ ስራው እንዲሰራ እና የማይፀብሪ አውራጃ አስተዳደርም ስራውን ለማስፈጸም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግ ቀጭን ትእዛዝ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል።


በእነዚሁ ባለሥልጣናት ለግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ማኅበረ መነኮሳቱ ውሳኔያቸውን ለዚሁ ቀን እንዲያሳውቁ ተነግሮ ነበር፥ አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት ይኽው ስብሰባ ለግንቦት ፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. እንዲጠራ እና ውሳኔያቸውን በቅርቡ ለሚነሱት ቦታዎች ካሳውን እንዲቀበሉ እና በምትኩም መንግሥት ግምት እንዲሁም የሚለማ ቦታ እንደሚሰጣቸው አምነው መቀበል እንዳለባቸው ተነግሯል። ይሄንንም ውሳኔ በግንቦት ፯ ቀን ፳፻፮ ዓም በማይጸብሪ አስተዳደር ጽ/ቤት ድረስ በእነ አባ ገ/ሕይወት መስፍን አማካኝነት እንዲቀርብ ቁርጥ ውሳኔ ተደርጎ ውሳኔ ተላልፏል።
የኢትዮጵያ ስኳር ፋብሪካ ኮርፖሬሽን በአምስቱ ዓመት ትራንስፎርሜሽን ዓመታት ሊገነባቸው ካሰባቸው የስኳር ፋብሪካዎች አንደኛው በዋልድባ ገዳም ዙሪያ የሚሰራው አንደኛው ነው። በዚህ የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ደግሞ የስኳር ፋብሪካ ኮርፖሬሽን በአስቸኳይ አንስቶ ግምቱን ለመስጠት እያጣደፈ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ግንባር ቀደም የሆኑት የሚከተሉት ናቸው
፩/ ማኅር ገፅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን
፪/ ደለሳ ቆቃ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን
፫/ እጣኖ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን
፬/ አባ ነፃ የብዙ ቅዱሳን አባቶች እና ቅዱሳን አበው አረፈ አጽማቸው ያለበት ቦታ ሲሆን፥ ከዚህ በፊት መንግሥት መንገድ እሰራለሁ በሚል የበርካታ አበው አጽም ሲያፈልሱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። በተለይ በአሁን ሰዓት የማይፀብሪ አስተዳደር ጽ/ቤት እና የስኳር ፋብሪካ ኮርፖሬሽን ከላይ የተጠቀሱትን ቤተክርስቲያናትን እና ቅዱሱን ቦታ ለማፍረስ በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል። ለዚህ ቦታ ሃላፊው ወይም ተጠሪው እራሱ የቦታው መሥራች እና ባለቤት መድኅኒዓለም እንደሆነ በተለያየ ጊዜ የተናገሩት አበው መነኮሳት ምስክሮች ናቸው፥ ነገር ግን በማን አለብኝነት የቅዱሳንን ዓጽም ቢያፈልሱ እና እነዚህን አቢያተ ክርስቲያናት ቢያፈርሱ ሊመጣባቸው የሚችለውን ሊቀበሉ የሚችሉት እራሳቸው እንደሚሆኑ ሊታመን ይገባል።
በግንቦት ፭ ቀን ማይለባጣ ላይ ሊደረግ ያታሰበው ስብሰባ አስቀድሞ የአበረንታንት መድኅኒዓለም የቀድሞ አበ መኔት የሆኑት በአሁኑ ሰዓት በጡረታ ሆነው እያገለገሉ ያሉት አባት መምህር ወልደ ልዑል ዳንዶሮቃ ላይ ሲጠየቁ የሰጡት መልስ እስከ ዛሬ ድረስ ማኅበረ መነኮሳቱ ሲናገሩት የነበሩት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት አልዋጥ ያላቸው እውነታ ነው ይህውም የቦታው መሥራች እና ባለቤት እራሱ የሰማይ እና የምድር ገዢ መድኅኒዓለም ነው እኔ አንድ ጡረተኛ፣ ደካማ አባት ነኝ የእኔን ሃሳብ ከሆነ የምትፈልጉት አልቀበልም አልስማማም እኛ አፈር ጠባቂዎች እንጂ የቦታው ፈቃጅ እኛ አይደለንም እባካችሁ ተውን ማድረግ የምትፈልጉትን ማድረግ ትችላላችሁ ውጊያችሁ ወይም ተግዳሮታችሁ ከእኛ ሳይሆን ከቦታው ባለቤት ስለሆነ የምትፈልጉት አድርጉ በማለት ነበር የመለሱላቸው። እኛስ በአርባ እና በሰማኒያ ቀናችን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የተወለድን ክርስቲያኖች? ዝም ብለን እነዚህ አረማውያን ቤተክርስቲያንን ይልቁንም ዋልድባን ያህል ታላቅ ገዳም እንደዋዛ ሲፈርስ እና ሲዋረድ ዝም ብለን መመክከት ወይስ ቢያንስ በጸሎት ማገዝ . . .
ባለፈው ዓመት ጥር አካባቢ በማይፀብሪ አውራጃ አስተዳዳሪዎች ከተሾሙት የእቃ ቤት ሹም አባ ገብረ ሕይወት መስፍን (ታጋይ የነበሩ) ዛሬ በትክክል የመንግሥት አጋርነታቸውን እያስመሰከሩ ያሉበት ጊዜ ነው። የዜሬ ሁለት ሳምንት አካባቢ በማይፀብሪ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ስብሰባ ተቀምጠው የተሰጣቸውን መመሪያ በገዳሙ ላይ የሚያስፈጽሙ እኚሁ አባት ተብዬ እንደሆኑ ለመረዳት ችለናል። አባ (ታጋይ) ገብረ ሕይወት መስፍን ውሳኔውን ይዘው ከመንግሥት በመምጣት ከላይ የተጠቀሱት አብያተ ክርስቲያናት ሊፈርሱ እንደሆነ እና እቃ ማውጣት እንዳለባቸው አስቀድመው ለማኅበረ መነኮሳቱ ሲገልጹ ተሰምተዋል ከዚህ በተጨማሪ በአባ ነፃ አካባቢ እየተሰራ ባለው ካምፕ ውስጥም በርካታ ወታደሮች እና ለመንግሥት ወሬ የሚያመላልሱ መነኮሳት ጭምር በቦታው እንደታዩ ተነግሯል፥ በዚህ ቦታ አካባቢ ስራቸውን እንደነሱ ግምት ለመሥራት ቅድመ ዝግጅቶችን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፣ ከነዚህም ዝግጅቶች መካከል የዛሬማን ወንዝ መንገዱን ቀይረው ለግድቡ ሥራ አስቀድሞ ቦታውን ማድረቅ እና ቁፋሮን መጀመር የሚሉትን ዝግጅቶች ተጀምረዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ የግል ገልባጭ እና ትራክተሮች ያላቸው ባለሃብቶች ቁሳቁሶቻቸውን ለሥራው ወደቦታው በማስገባት ላይ እንደሚገኙ እና ሥራቸውንም እንደጀመሩ የዓይን ምስክሮች ገልጸውልናል። አንድ የግል ባለ ሃብት 12 የሚጠቁ ቀላልና ከባድ የጭነት መኪናዎችን ይዘው ወደ ወልድባ የገቡ የአዲስ አበባ ባለሃብት ሲሆኑ፥ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ የባለሃብቱ ገልባጭ መኪናዎች ውስጥ 4 ያህሉ ተገልብጠው ከጥቅም ውጪ በመሆናቸው ባለሃብቱ ሥራቸውን አቋርጠው የቀሯቸውን 8 ቀልላል እና ከባድ ገልባጭ መኪናዎች ይዘው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን እነዚሁ የዓይን ምስክሮች ገልጸውልናል። እግዚአብሔር አምላክ አሁንም በቅዱሱ ዋልድባ ላይ የሚነሱትን ሁሉ በቀላሉ ምልክት እያሳየ የማፍረስ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ደጋግሞ ምልክት ቢያሳያቸውም ልባቸውን እንደ ፈርዖን ያደነደኑት የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ባለጊዜዎች ጽዋው የሞላ ቀን ወዴት ይገቡ ይሆን? ለሁሉም ልቦናቸውን መልሶላቸው ይሄንን ቅዱስ እና ታሪካዊ ገዳማችንን ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ የቅዱሳን መናኽሪያ፣ የደካሞች መጽናኛ የሚሆንበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን በረሃ ለበረሃ፣ ፍርክታ ለፍርክታ በመንገላታት ጽድቁን የሚሹት ቅዱሳንም ጸሎታቸው እና ልመናቸው ይኽው ስለሆነ በቀነ ቀጠሮ ከሚያስፈራሩን አረማውያን እለት ተዕለት ከእግዚአብሔር የሚገናኙት ቅዱሳን ተስፋ አለውና ያንን ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ያቅርብልን።

ወስብሃት ለእግዚአብሔር

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

3 comments:

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤