Saturday, August 2, 2014

እንደሚታረዱ በጎች ሆንን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“. . . ወኮነ ከመ አባግፅ ዘይጠብሁ. . .”
“. . .እንደሚታረዱ በጎች ሆንን . . .” መዝሙር ፵፫

የክርስትና ሃይማኖት በጌታችን በመድኅኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በዕለተ ዐርብ የተመሠረተች፣ በበዓለ ሃምሳ በርዕደተ መንፈስ ቅዱስ ያሸበረቀች እንከን የሌለባት ንጽህት ሃይማኖት ናት። ያለ ክርስትና የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይደለም ወርሶ ሊኖርባት ቀርቶ በዓይኑ እንኳን ሊያያት አይችልም።ዘአተጠምቀ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ አይከል ርዕዮታ ለመንግሥተ እግዚአብሔርዮሐ. በመሆኑም ይህች ሃይማኖት በነፍስ ዘላለማዊ ሕይወት የምናገኝባት፣ ዘላለማዊ ደስታ የምንጎናፀፍባት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንደርስባት በሥጋ ምድራዊ በረከት የምናገኝባት መንገድ ናት።


ጥንት ነቢያቶችን የበላች ምድር ደግሞ ሐዋርያትን በልታለች፤ ሰማዕቱ እስጢፋኖስን በድንጋይ በመውገር የጀመረችው ክርስቲያኖችን የማሳደድ በዚህ ክፋቷ እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቃለች፥ ቅዱስ ጴጥሮስን ሰቅላለች፣ ቅዱስ ጳውሎስን አንገቱን ቆርጣለች፣ የቶማስን ቆዳ ሸልታለች፣ ቅዱስ ያዕቆብን አርዳለች፣ እረ ምኑ ተነግሮ አባቶቻችን እንደ ሽንኩርት ተልጠው፣ እንደ ጎመን ተቀርድደው፣ ለአራዊት ተሰጥተው፣ በመጋዝ ተሰንጥቀው፣ ለእግዚአብሔር መንግሥት በእንተ ፍቅረ ክርስቶስ መራራ ሞትን ተጎንጭተው አልፈዋል።

ለደገኛይቱ ሕግ በወንጌል ላይ ዓለም ትጠላችኃለች፣ እኔን እንደሰቀለች ትሰቅላችኋለች ብሎ ጌታችን የተናገረው ሁሉ ደርሷል። ይህንንም መራራ ዘመን ቤተክርስቲያንዘመነ ሰማዕታት ብላትዘክረዋለች። ይሁን እንጂ አባቶቻችንን በመግደል የክርስትና ሃይማኖትን አጠፋለሁ ብላ በሰይጣን አቀነባባሪነት በዓረማውያን ነገሥታት ጋሻ ጃግሬነት የተቀነባበረው የጥፋት ዘመቻ ብዙም አልተሳካም፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ አንድ ዛፍ ሲቆረጥ በርካታ ዛፎች ከስር እንደሚበቅሉ ሁሉ፥ አንድ ቅዱስ አባት ሲሞት በርካታ ክርስቲያኖችን እያፈሩ በተቃራኒው ክርስትና ሰፍታለች። ምክንያቱም የመሠረታት እውነተኛና ፃድቅ ፈራጅ እውነትና እውነት ብቻ ነው፤ እውነት ደግሞ ከእግዚአብሔር ነው። ከእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ደግሞ አይጠፋም ይልቁንም ይሰፋል ይበዛል እንጂ።

በዚህ መሃል ነው እንግዲህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት 318 ሊቃውንት መራራ ትግል የጸናችው መጽሐፍትን ገልጸው፣ ጥቅስ ጠቅሰው፣ መናፍቃንን አሳፍረው ያለፉትን ሁለት ሺህ ዓመታት ዘልቃ እኛ ጋር የደረሰችው ይህንን እና ይህንን የመሳሰሉ መከራና ፈተና አልፋ ነው

በዓለም ላይ ካሉት ታላላቅ ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነችው የእኛዋ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት። ይህች ጥንታዊት፣ ሐዋሪያዊት ቤተክርስቲያን ሁለት ሺህ ዘመናትን ያሳለፈችው በመራራ ትግልና መከራ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት በማይጠፋ ብዕራቸው ዘግበውታል። የዮዲት ጉዲት 40 ዘመን ስደት፣ የግራኝ አህመድ እልቂት እና ጥፋት፣ የዘመነ መሳፍንት ፍጅት ከህሊናችን የማይጠፋ ጥቁር ጠባሳዎች ናቸው። አባቶቻችን በዚህ ሁሉ ግፍና መከራ ውስጥ ግን ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ምግባራቸውን አጽንተው፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ታድገው ለትውልድ አስረክበዋል። የእኛ አባቶች  ለቅድስት ቤተክርስቲያናቸውና ለሀገራቸው ተሰውተዋል። የቅርቦቹ አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው ቅድስት ቤተክርስቲያንም ታሪካቸው ለመዘገር ትውልድን ለማስተማር ጽላት ቀርጻ ስማቸውን ስትዘክር ትኖራለች።   

አባቶቻችን ለቤተክርስቲያን ሲሉ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለሌላው በመኖር እንደጧፍ ነደው ለሌላው እያበሩ  የሞቀ የደመቀ ቤታቸውን ጥለው ከሀገር ምድረ በዳ፣ ከዘመድ ባዳ፣ ከሕገ ሰብዕ ሕገ መላዕክት ይሻላል ብለው በዱር በገደሉ በመቅበዝበዝ በምድረ በዳ ውስጥ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምጸ አራዊቱን፣ የሌሊት ቁሩን፣ የቀን ሐሩሩን፣ ግርማ ሌሊቱን ታግሰው በመኖር ቤተክርስቲያናችንን ታድገዋል። የአላውያን ነገሥታትን በትር፣ የመናፍቃንን ሴራ በጽናት መክተዋል፥ በዚህ ሁሉ ትግል ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የፈረሰውን አድሰው ያልተመሠረተውን መሥርተው ዛሬ የምናያቸውን እጹብ ድንቅ የሆኑትን ዓለም እንደ ብርቅ የምታያቸውን አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል፣ የሚማርኩ ገዳማትን አስፋፍተዋል።

በአማሌቃውያንና በአህዛብ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ ገዳማት ሲፈርሱ፣ ምዕመናን ሲሰደዱ፣ ካህናት ሲታረዱ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ መቀመጡ ሲገርመን፤ በክፉ ድርጊታቸው ተይዘው በፍርድ አደባባይ ሲገኙ በነፃ ሲለቀቁ እናያለንእንዳያማህ ጥራው፥ እንዳይበላ ግፋውዓይነት በፍርድ አደባባይ ፍትህ መዛባቱ ሲደንቁን ዛሬ ደግሞ በልማት ሰበብ አብያተ ክርስቲያናቱን ማፍረስ ገዳማቱን ማረስ ተያይዘዋታል።
ቤተ ክርስቲያንን አናስነካም ሃይማኖታችንን አናስደፍርም ያሉ ገዳማችንን አናሳርስም ብለው የአባቶቻቸውን አሠረ ፍኖት ተከትለው የተነሱትን አባቶች ለወኅኒ እና ለእንግልት ተዳርገዋል። የዚህን ዓለም ምኞት ጣዕምና ለዛ ንቀው ከዓይነ ሰብዕ ርቀው፣ ዕራፊ ጨርቅ ታጥቀው፣ መኖራቸው ሳያንሳቸው ለሰውነታቸው ምቾትና ድሎት ነፍገውት ጥሬ ቆርጥመው፣ ቋርፍ (ሥራሥር) ተመግበው ውሃ ተጎንጭተው ከሚኖሩበት ገዳማቸው ለስደት እና ለእንግልት ተዳርገዋል። ጮማ እየበሉ ወስኪ እየጨለጡ፣ የሰባውን አርደው፣ የጸራውን አውረደው በልተው ጠጥተው የፈረጠሙ ክንዶች በቋርፍና በጥሬ የከሱ ገላዎችን ሲያሰቃዩ፣ ሲደበድቡና ሲያንገላቱ እንኳን ለተመለከተው ለሚያስበው ኅሊና እንኳን እንዴት ይከብዳል።

እነዚህ ከዚህ ዓለም ራሳቸውን ያዋረዱ፣ በሥጋ ሲያዩአቸው ደካሞች፣ በመንፈሳቸውና በወኔያቸው ግን ኃያላን የሆኑ አባቶች የደረሰውን ፈተና ታግሰውኧረ የሰው ያለህ፥ የወገን ያለህ፥ የክርስቲያን ያለህ፥ እያሉ ሲጣሩብዙም ሰሚ ያገኙ አይመስሉም መንግሥትንም ቢሆንኧረ ተው፣ ከገዳማችን ላይ፣ ከዋልድባ ላይ እጃችሁን አንሱ!” በገዳማት ላይ፣ በቤተክርስቲያን ላይ፣ የተሰነዘሩ እጆች ይቆረጣሉ፣ የፈረጠሙ ክንዶች ይደቃሉ፣ ቢሉም የሚያዳምጣቸው አላገኙም። የልብሳቸውን አዳፋነት፣ የሰውነታቸውን ክሳት፣ ተመልክተው ናቋቸው። የአሁኑ ይባስ እንደሚባለው በክብር ወንበር ላይ ያስቀመጠቻቸው ካሕናት እና ጳጳሳት ሳይቀሩ ተሳለቁባትለገዳማቱ እኛ መነኩሳቱ እንቀርባለን ወይስ በርገር ፍለጋ የመጣውበማለት ሕዝብን ለማሞኘት የእለት ፍርፋሪያቸውን ለማግኘት ሰማያዊቱን ቤተክርስቲያን መዘበሯት።

እንግዲህ ምን ይደረጋል ሰሚ ሲጠፋ፣ ለማን አቤት ይባላል? ለማን ይግባኝ ይጠየቃል? መልሱ ለእግዚአብሔር ነዋ ! አባቶቻችንይግባኝ ለመድኅኒዓለምአሉ በቤተክርስቲያን ላይ፣ በዋልድባ ላይ የሚደረገው ግፍ ካልቆመ ዳዊቱን አንደግምም መቋሚያችንን አናነሳም ብለው፥ ዋይታቸውንና ለቅሷቸውን ለባለቤቱ አሰሙ፤ የራሔልን እንባ ያበሰ አምላክ የአባቶቻችንን ጩኽት ሰማ፣ እንባቸው በራማ ተሰማ፣ ጩኽታቸውም በጽርሐ ዓርያም ተስተጋባ፥ እንዳሉትም የተሰነዘሩ እጆች መቆረጥ ጀምረዋል። ለሚያስተውለው ሰው የእግዚአብሔር ኃያልነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በገሃድ የታየበት፣ እጹብ ድንቅ የሚያሰኘው ተዓምራቱ የተገለጠበት ወቅት ነው። ዛሬ ዛሬ ደግሞ ካሳ ከፍልን ቤተክርስቲያንን አፍርሰናል በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡የኛ ገዳማውያን አባቶች ቤተክርስቲያንን አስፈርሰው ካሳ የሚቀበሉ ሳይሆን አለምን የተፀየፉ በደሙ ለገዛን ለኢየሱስ ክርስቶስ የደሩ ናቸው፡፡እንደፈርኦንና ሰራዊቱ መቅሰፍት እንዳይበላቸው የሚበጀው ከዋልድባና ከሌሎችም ገዳማት ላይ እጃችሁን ማንሳቱ ነው፡፡ሰው ሆኖ የማየበድል እንጨት ሆኖ የማይጨስ የለምና በንስሃ ተመልሳችሁ በገዳማት በመገኘት የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን መማጠኑ ለናንተና ለትውልዳችሁ የተሻለ እድል ነው፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያንከሁሉ ጋር በፍቅር ኑሩበሚለው አምላካዊ ቃል እንመራለን፤ በዚህም የማንንም ድንበር አልነካንም፣ የማንንም ቤት አላንኳኳንም፣ ተሰደው የመጡትን ተቀብለናል፣ የተራቡትን አብልተናል፣ የተጠሙትን አጠጥተናል፥ ነገር ግን ድንበራችንን ለሚያፈርሱ፣ ቤታችንን በድፍረት የሚያንኩዋኩትን ግን ልንታገሳቸው አይገባምበቃ!’ ልንላቸው ይገባል ከአባቶቻችን የተማርነውም ይህንኑ ነው እኛ በቃ ካላልን፥ ይበቃቸዋል የሚለን የለም።
ጉዟችን ክርስትና የመስቀል ጉዞ ነው፣ መስቀል ደግሞ መራራ ነው።

ስለዚህ ከታሪክ ወቀሳ፣ ከኅሊና ፍርድ፣ ለመዳን ከእግዚአብሔር ፍርድ እንድናመልጥ የበኩላችንን እንወጣ፣ ባለንበት ድምጻችንን ይሰማ፣ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደ ጧፍ ነደው ብርሃን ያየንባቸውን ቅዱሳን መካናት እና ገዳማት ለእኛ እንዳስረከቡን እኛም ቢያንስ ከነ ሙሉ ክብራቸው ለመጪው ትውልድ እንድናስተላልፍ የአባቶቻችን አምላክ እንዲረዳን ሁላችንም የበኩላችንን እናድርግ።

ያለኃጢያታቸው ስለተደበደቡት፣ ስለታሰሩት፣ ስለተሰደዱት አባቶቻችን ብለን ታሪካችንን ጠብቀን ለማስጠበቅ አብያተ ክርስቲያናቱን እንድንጠብቅ፣ ገዳማውያኑን እንድንታደግ፣ ዋልድባን እንድንታደግ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን።
እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ሀገራችንን፣ ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን በረደኤት ይጠብቅልን::


ወስብሐት ለእግዘአብሔር ወለመስቀሉ ክቡር ወለወላዲቱ ድንግል


ባለፈው በሰሜን አሜሪካ የስፖርትና የባሕል ፌዴሬሽን ላይ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  እምነት ተከታዮች አንድነት ካቀረበቻው በርካታ ትራክቶች መካከል ሦስቱ ለአንባቢ ቢቀርቡ የሚል አስተያየቶች በርከት ብለው በመምጣታቸው እነሆ እነዚህን 
ለዛሬ አቅርበናል መልካም ምንባብ።


፩/ እንደሚታረዱ በጎች ሆንን
፪/ ኢትዮጵያዊነት እና ኦርቶዶክሳዊነት
፫/ የዋልድባ አጠቃላይ ገጽታ

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤