Tuesday, April 21, 2015

ሰበር ዜና – ቅ/ሲኖዶስ ከነገ ሚያዝያ ፲፬ ቀን ጀምሮ የሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ ዐወጀ፤ ቤተሰቦች የተሠው ክርስቲያኖችን ፎቶ፣ ስመ ክርስትና እና ሙሉ አድራሻ እንዲያቀርቡ አዘዘ – ‹‹ልጆቻችን የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን ናቸው››

  • ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹ግፉዓን ይትመሰጥዋ ለመንግሥተ ሰማያት፤ በሃይማኖታቸው ምክንያት ግፍ የሚደርስባቸው መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል››(ማቴ.11÷12) በሚል ርእስ በሰሜን አፍሪቃ ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀልን በተመለከተ ዛሬ፣ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀትር ላይ በድጋሚ ባወጣው ባለዘጠኝ ነጥብ ወቅታዊ የአቋም መግለጫ፡- በግፍ የተሠውት ክርስቲያኖች፣ ሃይማኖታችንን አንክድም በማለት የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉየሃይማኖት መስተጋድላን መኾናቸውን አረጋገጠ፤ ቤተሰቦቻቸውንም አጽናና፡፡
Qirqos parents and relatives mourns‹‹የመዋች ቤተሰቦች የኾናችሁ ወገኖቻችን ኹሉ፡- 
በዚኽ ግፍ የተሞላበት ጭካኔ የገደሉት ልጆቻችን በዚኽ ዓለም የመኖር መብታቸው በአጭሩ ቢቀጭም ጌታችን፣ ‹‹የተገፉ መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል ማለትም ይወርሷታል›› ባለው አምላካዊ ቃለ እግዚአብሔር፣ ዕንባቸውን አብሶ በመንግሥቱ የሚቀበላቸው መኾናቸውን ዐውቃችኹ፤
እንደዚኹም ልጆቻችን ‹‹ወኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት፤ እስከ ሞት ድረስ የታመንኽ ኹን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለኹ፤››(ራእይ 2÷10) ያለውን የጌታችንን ቃል ጠብቀው ሃይማኖታችንን አንክድም በማለት በሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን ስለኾኑ የጀግና እናት አታለቅስም እንደተባለው የልጆቻችኹ ሰማዕትነት በእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅ ዋጋ ስላላቸው በዚኽ ከሐዘናችኹ እንድትጽናኑ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች፡፡››


  • ከነገ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለ7 ቀናት ያኽል በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በግፍ ለተገደሉት ወገኖች ጸሎተ ፍትሐት፤ ለሀገራችን እና በአጠቃላይ ለዓለሙ ኹሉ ሰላም መጠበቅ፣ ለሰው ልጆች በሕይወት የመኖር መብት መከበር ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡
Holy Synod on the excution of Eth Ortho christians in Libyaነገ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 14 ቀን ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ÷ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መላው የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ ካህናት እና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች እንዲኹም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ሓላፊዎች እና ልዩ ልዩ ሠራተኞች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ወንጌል ይከናወናል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ ዛሬ፣ ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ የሊቢያ የሃይማኖት መስተጋድላን ቤተ ሰዎችን እና ወዳጆችን በየአጥቢያው በአካል እየተገኙ የሚያጽናኑበት መርሐ ግብር ይካሔዳል፡፡

  • በየትኛውም አካባቢ የሚገኙትን ወገኖቻችንን እና የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ከመሰል ጥቃት ለመታደግ እንዲቻል ከመንግሥት ጋራ በቅርበት የሚሠራ ዐቢይ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ ይቋቋማል፡፡
  • ነገ ሚያዝያ 14 ቀን ከጠዋቱ 3፡00 – 4፡30 በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የካህናት አስተዳደር መምሪያአስፈጻሚነት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት የሚከናወነው የጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ወንጌል ሥነ ሥርዐት፣ በደቡብ አፍሪቃ በግፍ የተገደሉ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንንም ይጨምራል፡፡
  • በሃይማኖታቸው ምክንያት ለተሠዉ ክርስቲያኖች ሊሰጥ የሚገባውን የሰማዕትነት ክብር በቀኖናው መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ መፈጸም ይቻል ዘንድ፣ በአይ ኤስ አሸባሪ ቡድን በግፍ የተገደሉት ልጆቻችን ቤተሰብ የኾናችኁ ሁሉ የመዋቾቹን ስመ ክርስትና፣ ፎቶ እና ሙሉ አድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተቻለ መጠን በፍጥነት እንድታቀርቡ ቤተ ክርስቲያን አሳስባለች፡፡
  • የተፈጸመው የግድያ ወንጀል፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይኾን በኹሉም የዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተቃጣ የወንጀል ተግባር መኾኑን በማመን መላው የሀገራችን ሕዝቦች እና የሃይማኖት ተቋማት እንደዚኹም የዓለም መንግሥታት እና ማኅበረሰብ ድርጊቱን በጽኑ ከመቃወም እና ከማውገዝ በተጨማሪ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያፈላልግ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ጠይቋል፡፡

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤