Thursday, April 30, 2015

የወንድሞቻችን ደም ምክንያት ኾኖ አንድነታችን ቢጸና… አንድ መኾን በቀል ነው

ethiopian and coptic christians
ግብጻውያን እና ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት (ሥዕል: ዘሪሁን ገብረ ወልድ)
‹‹የኢራቅ እና የሶርያ እስላማዊ መንግሥት›› (Islamic State in Iraq and Syria) የሚል መጠሪያ ለራሱ የሰጠው ታጣቂ ቡድን፣ ጸጥታቸው የደፈረሰ አገሮችን የወታደራዊ ኃይሉ እንዲኹም እስከ ኹለት ቢልዮን ዶላር የሚገመተው የገንዘብ እና የንብረት ሀብቱ ማጠናከርያ በማድረግ ወደ ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
‹‹የጥንቱን ገናና የእስልምና ሥርዐት›› በ፳፩ኛው ምእት ዳግም ለማስፈን የአምስት ዓመታት ግብ ያስቀመጠው ቡድኑ÷ መካከለኛው ምሥራቅን፣ እስያን እና አፍሪቃን በማካተት እገነባዋለኹ ያለውን ሙሉ በሙሉ በሱኒ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ እስላማዊ ከሊፋየሚያሳይ ካርታም ይፋ አድርጓል፡፡ በአፍሪቃ ከምድር ወገብ በላይ ሦስት ንኡሳን ከሊፋዎችን የሠየመው ቡድኑ÷ ‹‹የሐበሻ ምድር››በሚል ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማልያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማእከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክንና ካሜሩንን ያካተተ ሲኾን ግብጽ፣ ሰሜን ሱዳን፣ ቻድ እና ከፊል ሊቢያ ደግሞ ‹‹የአልካና ምድር›› በሚል አካትቷቸዋል፡፡
እስላማዊ ከሊፋውን የመገንባት የተስፋፊነት ሕልሙን እውን እናደርጋለን በሚል ለቡድኑ ርእዮት እና አስተዳደር ማደራቸውን ያወጁበየሀገሩ የሸመቁ ጽንፈኞች እየበረከቱ ናቸው፤ ባለፉት ዐሥር ወራት ብቻ ከቡድኑ ጋራ ማበራቸውን ያወጁ እንደ ቦኮ ሃራም ያሉ ዐበይት ሸማቂዎች ከ30 በላይ ተቆጥረዋል፤ ዋነኞቹ የቡድኑ ታጣቂዎች ኢራቃውያን እና ሶርያውያን ሱኒዎች ቢኾኑም በድረ ገጽ በሚያካሒደው ቅስቀሳና ምልመላው ተነሣሥተው፣ ለመዋጋት እና ለመሞት ፈቅደው የተቀላቀሉት ኮብላይ ተሰላፊዎች(ጂሐዲስቶች) ከ80 በላይ አገሮች እንደተውጣጡና ከ12 ሺሕ በላይ መድረሳቸው ተነግሯል፡፡


በመንግሥት አልባዋ ሊቢያ የሚንቀሳቀሱትና ከቡድኑ ቀጥተኛ ትእዛዝ የሚደርሳቸው ታጣቂ ኃይሎች፣ ከሜዲትራኒያን ባሕር እና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ ባሻገር የተዘረጉ የጥፋት እጆቹ ኾነዋል፡፡ ይኸው የጥፋት ጥምረትም ታጣቂዎቹ፣ የቡድኑን ስም በመጠቀምና የሽብር ተግባሮቹን በመቅዳት በግብጽ – ኮፕት እና በኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ በፈጸሙት አረመኔያዊ ግድያተረጋግጧል፡፡
ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ መዋቅር በዘረጋባቸው ይዞታዎቹ እስልምናን መቀበልን የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ ያደረገው ቡድኑ፣ በአንድ በኩል የሺዓ እስልምና ተከታዮችን ያለርኅራኄ ሲፈጅ፣ ክርስቲያኖችን ጨምሮ የሌላ እምነት ተከታይ ወገኖች ደግሞ ለሌሎች አመለካከት ቦታ በማይሰጠው መሥመሩ እንዲሰልሙ አልያም የተገዥነት ግብር እንዲከፍሉ ያስገድዳል፡፡ ይህን ባልፈጸሙት ላይ ግን የሽብር በትሩን ይሰነዝራል፡፡ ሃይማኖታችንን አንክድም ያሉትን ግብጻውያንና ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን በተመሳሳይ ቦታና አኳኋን በግፍ የገደሉት ባለጭምብል የከሊፋው ታጣቂዎች የተናገሩትም፡- ‹‹የመስቀሉ ተከታይ አገሮች መጣንባችኹ! የእኛን እምነት ካልተቀበላችኹ በሕልማችኹ እንኳ ዕረፍት አይኖራችኹም!›› የሚል ፉከራ ነበር፡፡
ከፌስ ቡክ ገጻቸው የተገኘው ተከታዩ የዲያቆን ዓባይነህ ጽሑፍ በአንጻሩ፣ የንጹሐንን ደም በማፍሰሳቸው የአእምሮ ዕረፍት አጥተው የሚቅበዘበዙት ገዳዮቹ ራሳቸው በመኾናቸው በዚኽ ረገድ ፍርድን እና በቀልን በእግዚአብሔር መንገድ መረዳት እንደሚገባ ያብራራል፡፡ ‹‹የወጣቶቹ ወንድሞቻችን ደም ለክርስቲያኖች የጽናት ማኅተም ነው፤›› ያሉት ጸሐፊው፣ ሰማዕትነትን በጥብዐት እና በጸጋ መቀበል ለገዳዮች የእግር እሳት እንደሚኾንባቸው ገልጸዋል፡፡
ይልቁንም የጥፋት ቡድኑ በሙስሊሞች ዘንድ ሳይቀር በተወገዘበት የተስፋፊነት ንቅናቄው ፊትና አገራችን ኢትዮጵያን በትልቁ ከሊፋው ማህቀፍ ዒላማ ውስጥ በከተተበት ኹኔታ፡- አንድነትን አጽንቶ፣ አንድ ኾኖ መገኘት እንደሚገባ ይመክራሉ፤ ሲኖዶሳዊ አንድነትን በመመለስ በኩልም ‹‹የድርሻችንን እንወጣ፤ ከእንባ ወዳለፈ ተግባርም እንሒድ›› ሲሉም ይማጠናሉ – ‹‹አንድነታችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚፈለግበት የጥሪ ደወል የተሰማበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ … የወንድሞቻችን ደም ምክንያት ኾኖ አንድነታችን ቢጸና፣ ከኹለት ሲኖዶስ ወደ አንድ ጠንካራ ሲኖዶስ ብንመጣ ይኽም ሌላ በቀል ይኾናል፡፡ ሞታቸው ምክንያት ይኹነንና እንስማማ፡፡››
*       *       *
Dn. Abayneh Kasse
ዲያቆን ዓባይነህ ካሴ
በተደጋጋሚ በማኅበረሰብ ብዙኀን መገናኛ /social media/ እየጎመዘዘን የተጎነጨነው እየወጋን የለቀምነው የዜጎቻችን ግፍ አኹንም ከኅጽነ ኅሊናችን አልጠፋም፡፡ በነጋ በጠባ እየተጉላላብን ይገኛል፡፡ ከበሻሻ እስከ ሊቢያ የደረሰ የንጹሐን ደም እየጮኸ ዕረፍት ነስቶናል፡፡ ሰማዕታቱ በቅድመ እግዚአብሔር፣ ‹‹በታላቅ ድምፅ እየጮኹ፤ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ÷ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?›› እያሉ ለመጮኻቸው ጥርጥር አይገባንም፡፡ ራእ. ፮፥፲።
በዚኽ ቃል ውስጥ ፍርድ እና በቀል የሚለው የብዙዎቻችንን ትኩረት እንደሚስብ አምናለኹ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንገድ እንደ እኛ አይደለምና ፍርድ እና በቀልን በእርሱ መንገድ ልንረዳው ይገባናል፡፡ እንደ ሰብአ ትካት ምድርን በንፍር ውኃ ሊያጠፋት ይችላል፡፡ እንደ ሰዶም እና ገሞራም ደግሞም ነቢዩ ኤልያስ እንዳደረገው የቁጣውን እሳት ሊያዘንብ ይችላል፡፡ እንደ ግብጽ ስደት ደግሞ በዓይነት በዓይነት እያፈራረቀ መዓቱን ሊያወርድ ይችላል፡፡ እንደ ሐናንያ እና ሰጲራ ‹‹ገንዘባችኹ ከእናንተ ጋር ይጥፋ›› ሊልም ይችላል፤ ደግሞም ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና›› ሊልም ሥልጣኑ የእርሱ ነው፡፡
ነገር ግን እነዚያ በራእየ ዮሐንስ ላይ ልመና ያቀረቡት ሰማዕታት አንድ መልስ ተመልሶላቸዋል፡፡ ‹‹ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።” የሚል፡፡ ራእ. ፮፥፲፩።
የመጀመሪያው በቀል ነጭ ማልበስ ነው፡፡ ይኽም ክብረ ሰማዕታትን፣ አክሊለ ሰማዕታትን ማቀዳጀት ነው፡፡ እነዚኽ አንድ መቶ አርባ አራት ሺሕ ሕፃናት ስለ ክርስቶስ ፈንታ የተገደሉ ናቸውና ክብረ ሰማዕታትን ተቀዳጅተዋል፡፡ በአፍ ባይመሰክሩም ሞታቸው ስለ ክርስቶስ ስለኾነ አክሊለ ሰማዕታትን አግኝተዋል፡፡ ሰሞኑን ወንድሞቻችን ደግሞ‹‹ሃይማኖት ካዱ ወይም ታረዱ›› ሲባሉ እንታረዳለን እንጂ እምነታችንን አንለውጥም፤ ክርስቶስን አምላክ ነው ብለን እንዳመንን እንሠዋለን በማለት ገድለ ሰማዕታትን ፈጽመዋል፡፡ የመከራዋን ጽዋ ያለማመንታት ፉት ብለዋታል፡፡ እንዲህ ነው ጥብዐት በሃይማኖት!
እነዚያ አቋማቸውን ለመግለጽ አቅም ያነሳቸው ሕፃናት ስለ ክርስቶስ ፈንታ በመሞታቸው አክሊለ ሰማዕታትን ከተቀዳጁ በአፋቸው የመሰከሩት እነዚኽማ እንዴት ክብረ ሰማዕታትን አያገኙ? ይኽን ሰማያዊ ክብር መቀዳጀታቸው የመጀመሪያው በቀል ነው፡፡ አጥፊውን እርር ኩምትር የሚያደርግ እሳት ነው፤ ምክንያቱም በመግደል እንደማያጠፋን አንገት በመቅላት እንደማይደመስሰን ያይበታልና፡፡
ኹለተኛው መቅበዝበዝ ነው፡፡ የአቤል ደም እየጮኸበት፣ በሚሔድበት ኹሉ እየተከተለው፣ ምድር አልቀበለው ያለችው ቃየን እንደተቅበዘበዘ ሞተ፡፡ እነዚኽም ከእንግዲኽ ዕረፍት አይሰማቸውም፡፡ በቀን ይቃዣሉ፡፡ በሌሊት በሕልም ይመጣባቸዋል፡፡ የንጹሐን ደም ይጮኽባቸዋል፡፡ ወንጀል ሲሠሩ አልተገኙም፡፡ ይኽ ሌላው በቀል ነው፡፡ ሀገርን አይወክሉምና በሀገር ላይ መዐት አንጠብቅም፡፡ ሽፍቶች ናቸውና በያሉበት ቅጣታቸውን ያገኛሉ፡፡ የሚጠጡት ደም ባጡ ጊዜ እንደ እብድ ያደርጋቸዋል፡፡ ለአእምሯቸው ዕረፍት ይነሳቸዋል፡፡ በሕልማቸው ያስደነግጣቸዋል፡፡ እንደተሠቃዩ ይሞታሉ፡፡
ሦስተኛው በቀል የደረሰባቸው ውግዘት ነው፡፡ ሕዝብ እና አሕዛብ አውግዟቸዋል፡፡ ዓለም ጠልቷቸዋል፡፡ ምድር ድርጊታቸውን ተጸይፋለች፡፡ ሙስሊሞች ‹‹ኢትዮጵያን አትንኩ ያለውን ትእዛዛችንን ጥሰዋል›› በሚል አንቅረው ተፍተዋቸዋል፡፡ ‹‹ክርስቲያንን በመግደል የሚገኝ ጽድቅ የለም›› በማለት በየመድረኩ ዐውጀዋል፡፡ መተርጒማኑ የጠቀሱት ገዳዮቹ የሚጠቅሱትን ያንኑ ቁርዓን ነው፡፡ በዚኽም የተነሣ ገዳዮቹ እና ሙስሊሞች ተለያይተዋል ማለት ነው፡፡ ስለኾነም ሙስሊሞችም አውግዘዋቸዋል፡፡
አራተኛው በቀል የሰማዕታቱ ደም ለክርስቲያኖች የጽናት ማኅተም መኾኑ ነው፤ ክርስቲያን እና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል ይኾናልና፡፡ ለእኛ አይምሰለን እንጂ የእኛ ሰማዕትነትን በጸጋ መቀበል ለገዳዮቻችን እንደ እግር እሳት የሚፋጅ መልስ ነው፡፡ ይፈራሉ ብለው ሲጠብቁ እኛ ግን ግፍአ ሰማዕታትን በጸጋ የምንቀበል ኾንባቸው፡፡ አንድ ሲገድሉ እልፎች ይነሣሉ፡፡ ያረፉት በሰማይ፣ የተረፉት በምድር አንድ ይኾኑባቸዋል፡፡ ያጠፏቸው ሲመስላቸው ይበዙባቸዋል፡፡ በሰይፋቸው ስለት ያመነመኑን ሲመስላቸው እንበረክትባቸዋለን፡፡
አምስተኛው በቀል አንድ መኾን ነው፡፡ በጥቃቅን ጉዳዮች የተለያየን አንድ ብንኾን ይህ ሌላው በቀል ነው፡፡ አሁን አንድነታችን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የሚፈለግበት የጥሪ ደወል የተሰማበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ አልሰማንም ለማለትም የማንችልበት ወቅት ነው፡፡ ክርስትና ተሸንፎ የማሸነፍ ሕይወት የበለጸገበት ጎዳና ነው፡፡ ክርስቶስ ተሸንፎ አሸነፈን፡፡ በወርቀ ደሙ ገዛን፡፡ ለፍቅር በተከፈለ መሥዋዕትነት ረታን፡፡
ክርስትና አይደለም የወንድምን በደል ሞትን እንኳ እንዲኽ ያሥታግሳል፡፡ ታዲያ አባቶቻችን ወደ አንድነት ቢመጡልን እንዴት ያማረ በኾነ፡፡የወንድሞቻችን ደም ምክንያት ኾኖ አንድነታችን ቢጸና ከኹለት ሲኖዶስ ወደ አንድ ጠንካራ ሲኖዶስ ብንመጣ ይኽም ሌላ በቀል ይኾናል፡፡ሞታቸው ምክንያት ይኹነንና እንስማማ፡፡
ስድስተኛው በቀል በራእየ ዮሐንስ ላይ ለእነዚያ ሰማዕታት የተነገረው ነው፡፡ እርሱም ‹‹ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ›› የሚለው ነው፡፡ እርሱ አይቀርም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት የራሱ የጊዜ ሰሌዳ አለው፡፡ እርሱ ሲደርስ ያደርገዋል፡፡ ምን እንደሚኾን ለጊዜው አናውቀው ይኾናል እንጂ እርሱ ዝም አይልም፡፡ ‹‹ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም›› እንዲል፡፡ ት.ኢሳ. ፷፪፥፩።
እግዚአብሔር ዝም አይልም፡፡ እኛም ዝም አንልም፡፡ እናም ድርሻችንን እንወጣ፡፡ ከእንባ ወዳለፈ ተግባር እንሒድ፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤